በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 9

መዝሙር 75 “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!”

ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጁ ነህ?

ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጁ ነህ?

“ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ?”መዝ. 116:12

ዓላማ

ይህ ርዕስ፣ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርት ይረዳሃል፤ ይህም ራስህን ለእሱ ለመወሰንና ለመጠመቅ ፍላጎት እንዲኖርህ ያደርጋል።

1-2. አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት ምን ማድረግ አለበት?

 ባለፉት አምስት ዓመታት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው እንደ ጢሞቴዎስ እውነትን የተማሩት ‘ከጨቅላነታቸው ጀምሮ’ ነው። (2 ጢሞ. 3:14, 15) ሌሎች ደግሞ ስለ ይሖዋ የተማሩት አዋቂ ከሆኑ በኋላ ነው፤ በዕድሜ ከገፉ በኋላ እውነትን የተማሩም አሉ። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ አንዲት ሴት በ97 ዓመታቸው ተጠምቀዋል።

2 መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ከሆነ ወይም ወላጆችህ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ለመጠመቅ እያሰብክ ነው? ይህ በጣም ጥሩ ግብ ነው! ይሁንና ከመጠመቅህ በፊት ራስህን ለይሖዋ መወሰን ይኖርብሃል። ይህ ርዕስ ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም ዝግጁ እስከሆንክ ድረስ ራስህን ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ እንድትል የሚያደርግህ ምንም ምክንያት እንደሌለ እንድታስተውል ይረዳሃል።

ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው?

3. ለይሖዋ የተወሰኑ አንዳንድ ሰዎችን ምሳሌ ጥቀስ።

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ራስን መወሰን የሚለው አገላለጽ ቅዱስ ለሆነ ዓላማ መለየትን ያመለክታል። የእስራኤል ብሔር ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር ነበር። ሆኖም በእስራኤል ብሔር ውስጥ ለየት ባለ መንገድ ለይሖዋ የተወሰኑ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ አሮን በጥምጥሙ ከፊት በኩል “ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት” ማለትም የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ያደርግ ነበር። ይህ ጠፍጣፋ ወርቅ፣ አሮን ልዩ አገልግሎት ለማከናወን ማለትም የእስራኤል ሊቀ ካህናት ለመሆን የተመረጠ እንደሆነ ያመለክታል። (ዘሌ. 8:9) ናዝራውያንም ለየት ባለ መንገድ ለይሖዋ የተወሰኑ ነበሩ። “ናዝራዊ” የሚለው ቃል ናዚር ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ሲሆን “ለአንድ ዓላማ የተለየ” ወይም “ለአንድ ነገር የተወሰነ” የሚል ትርጉም አለው። ናዝራውያን በሙሴ ሕግ ውስጥ ለእነሱ የተሰጡትን ገደቦች ማክበር ነበረባቸው።—ዘኁ. 6:2-8

4. (ሀ) ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ሰው ምን ያደርጋል? (ለ) ‘ራስን መካድ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 ራስህን ለይሖዋ ስትወስን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆንና በሕይወትህ ውስጥ ምንጊዜም የአምላክን ፈቃድ ለማስቀደም ትመርጣለህ። ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ምን ማድረግ ይጠበቅብሃል? ኢየሱስ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ” ብሏል። (ማቴ. 16:24) “ራሱን ይካድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐረግ “ራሱን እንቢ ይበል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ራስህን የወሰንክ የይሖዋ አገልጋይ ስትሆን ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚጋጭን ማንኛውንም ነገር እንቢ ማለት ይኖርብሃል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) ይህም እንደ ፆታ ብልግና ካሉት “የሥጋ ሥራዎች” ጋር በተያያዘ እንቢ ማለትን ይጨምራል። (ገላ. 5:19-21፤ 1 ቆሮ. 6:18) እንዲህ ያሉት ገደቦች ሕይወትህን ያከብዱብሃል? ይሖዋን የምትወድና የእሱን ሕጎች መከተል እንደሚጠቅምህ የምታምን ከሆነ እነዚህን ሕጎች መከተል ከባድ አይሆንብህም። (መዝ. 119:97፤ ኢሳ. 48:17, 18) ኒኮላስ የተባለ ወንድም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋን መሥፈርቶች፣ ማድረግ የምትፈልጉትን ነገር ከማድረግ እንደሚያግዳችሁ የእስር ቤት አጥር ወይም ደግሞ ከአደጋ እንደሚጠብቃችሁ የአንበሶች ዋሻ አጥር አድርጋችሁ ልትመለከቷቸው ትችላላችሁ።”

የይሖዋን መሥፈርቶች የምትመለከታቸው የምትፈልገውን ነገር ከማድረግ እንደሚያግድህ የእስር ቤት አጥር አድርገህ ነው ወይስ ከአደጋ እንደሚጠብቅህ የአንበሶች ዋሻ አጥር? (አንቀጽ 4ን ተመልከት)


5. (ሀ) ራስህን ለይሖዋ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) ራስን በመወሰንና በጥምቀት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ራስህን ለይሖዋ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ በመጸለይ፣ እሱን ብቻ እንደምታመልክ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ የእሱን ፈቃድ እንደምታስቀድም ቃል ትገባለህ። እንዲህ ስታደርግ እሱን ምንጊዜም “በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ” እንደምትወድ ለይሖዋ ቃል መግባትህ ነው። (ማር. 12:30) ራስህን የምትወስነው በግልህ ነው፤ ይህ በአንተና በይሖዋ መካከል ያለ ጉዳይ ነው። የምትጠመቀው ግን በሕዝብ ፊት ነው። ጥምቀት፣ ራስህን መወሰንህን ለሌሎች ለማሳየት ያስችላል። ራስን መወሰን ቅዱስ ስእለት ነው፤ ይሖዋም ይህን ስእለት እንድትፈጽም ይጠብቅብሃል፤ አንተም ይህን ስእለት ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።—መክ. 5:4, 5

ራስህን ለይሖዋ ስትወስን በግልህ ጸሎት በማቅረብ እሱን ብቻ እንደምታመልከው እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ የእሱን ፈቃድ እንደምታስቀድም ቃል ትገባለህ (አንቀጽ 5ን ተመልከት)


ራስህን ለይሖዋ መወሰን ያለብህ ለምንድን ነው?

6. አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ እንዲወስን የሚያነሳሳው ምንድን ነው?

6 ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ዋነኛው ምክንያት ለእሱ ያለህ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር በስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘በትክክለኛ እውቀት’ እና ‘በመንፈሳዊ ግንዛቤ’ ማለትም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እንዲያድግ ባደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተ ነው። (ቆላ. 1:9) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ (1) ይሖዋ እውን እንደሆነ፣ (2) መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንዲሁም (3) ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ድርጅቱን እንደሚጠቀም እንድታምን አድርጎሃል።

7. ራሳችንን ለአምላክ ከመወሰናችን በፊት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 ራሳቸውን ለይሖዋ የሚወስኑ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶች ማወቅ እንዲሁም በቃሉ ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መመራት ይኖርባቸዋል። ሁኔታቸው በሚፈቅድላቸው መጠን እምነታቸውን ለሌሎች ያካፍላሉ። (ማቴ. 28:19, 20) ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር አድጓል፤ እንዲሁም እሱን ብቻ ለማምለክ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። አንተስ እነዚህን ነገሮች እያደረግክ ነው? እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካለህ ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ የምትነሳሳው የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚህን ወይም ወላጆችህን ለማስደሰት አሊያም ደግሞ ከጓደኞችህ ጋር ለመመሳሰል ብለህ ብቻ አይሆንም።

8. አመስጋኝ መሆንህ ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን የሚያነሳሳህ እንዴት ነው? (መዝሙር 116:12-14)

8 ይሖዋ ስለሰጠህ ስጦታዎች በሙሉ ስታስብ ራስህን ለእሱ ለመወሰን መነሳሳትህ አይቀርም። (መዝሙር 116:12-14ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚመጣው ከይሖዋ እንደሆነ ይናገራል፤ ደግሞም እንዲህ ማለቱ ተገቢ ነው። (ያዕ. 1:17) ከእነዚህ ስጦታዎች ሁሉ የላቀው የልጁ የኢየሱስ መሥዋዕት ነው። እስቲ አስበው! ቤዛው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንድትመሠርት መንገድ ከፍቶልሃል። በተጨማሪም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ሰጥቶሃል። (1 ዮሐ. 4:9, 10, 19) ከሁሉ ለላቀው ለዚህ የይሖዋ ፍቅር መግለጫ እንዲሁም ይሖዋ ለሰጠህ ሌሎች በረከቶች ሁሉ አድናቆትህን ማሳየት የምትችልበት አንዱ መንገድ ራስህን ለይሖዋ መወሰን ነው። (ዘዳ. 16:17፤ 2 ቆሮ. 5:15) ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 46 ነጥብ 4 እንዲሁም በውስጡ ያለው ስጦታችሁን ለአምላክ አቅርቡ የሚለው የሦስት ደቂቃ ቪዲዮ እንዲህ ስላለው የአመስጋኝነት ስሜት ይናገራል።

ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ?

9. አንድ ሰው ራሱን እንዲወስን ጫና ሊደረግበት የማይገባው ለምንድን ነው?

9 ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ እንዳልሆንክ ይሰማህ ይሆናል። ምናልባትም በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራት በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ እምነትህን ለማጠናከር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልግህ ይሆናል። (ቆላ. 2:6, 7) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት ይለያያል፤ በተጨማሪም ሁሉም ልጆች ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ የሚሆኑበት ዕድሜ አንድ ዓይነት አይደለም። ራስህን ከሌላ ሰው ጋር ሳታወዳድር መንፈሳዊ እድገትህን ከራስህ ሁኔታ አንጻር ገምግም።—ገላ. 6:4, 5

10. ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ እንዳልሆንክ ከደመደምክ ምን ማድረግ ትችላለህ? (“ እውነት ውስጥ ላደጉ ልጆች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

10 ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጁ እንዳልሆንክ ብትገነዘብም እንኳ ይህን ግብ ምንጊዜም በአእምሮህ ያዝ። አስፈላጊዎቹን ለውጦች ሁሉ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክልህ ጸልይ። (ፊልጵ. 2:13፤ 3:16) ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማና ምላሽ እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—1 ዮሐ. 5:14

አንዳንዶች ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?

11. ይሖዋ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

11 አንዳንዶች ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ ቢሆኑም እንኳ ይህን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ ይላሉ። ‘ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ኃጢአት ፈጽሜ ብወገድስ?’ ብለው ይሰጉ ይሆናል። አንተም እንዲህ ያለ ስጋት ካደረብህ ይሖዋ ‘ለእሱ በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለስና እሱን ሙሉ በሙሉ እንድታስደስት’ አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ። (ቆላ. 1:10) በተጨማሪም ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ ጥንካሬ ይሰጥሃል። በርካታ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንዲህ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (1 ቆሮ. 10:13) ከክርስቲያን ጉባኤ የሚወገዱት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ይሖዋ ሕዝቦቹን ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።

12. ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በሙሉ መጥፎ ነገር ለማድረግ ይፈተናሉ። (ያዕ. 1:14) ሆኖም በፈተናው መሸነፍ አለመሸነፍ የምርጫ ጉዳይ ነው፤ ይህን ምርጫ የምታደርገው አንተ ራስህ ነህ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድ የምትመርጠው አንተ ራስህ ነህ። አንዳንዶች እንዲህ ማድረግ እንደማይቻል ቢናገሩም እንኳ ምኞቶችህን መቆጣጠርን መማር ትችላለህ። ተገቢ ያልሆኑ አንዳንድ ምኞቶች ቢያድሩብህም እንኳ ምኞቶቹን ከመፈጸም መቆጠብ ትችላለህ። ይህን ማድረግ እንድትችል በየቀኑ ጸልይ። ቋሚ የግል ጥናት ፕሮግራም ይኑርህ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኝ። እምነትህን ለሌሎች አካፍል። በቀጣይነት እነዚህን እርምጃዎች መውሰድህ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር ብርታት ይሰጥሃል። ደግሞም ይሖዋ ይህን እንድታደርግ እንደሚረዳህ ፈጽሞ አትርሳ።—ገላ. 5:16

13. ዮሴፍ ምን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል?

13 ፈተና ሲያጋጥምህ ምን እንደምታደርግ አስቀድመህ ከወሰንክ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ጠብቀህ መኖር ቀላል ይሆንልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ ይህን ያደረጉ በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። ለምሳሌ የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍን ለማማለል በተደጋጋሚ ሞክራ ነበር። እሱ ግን ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዝ አስቀድሞ ወስኖ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዮሴፍ “ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ . . . ‘እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?’” እንዳለ ይናገራል። (ዘፍ. 39:8-10) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት እሱን ለመፈተን ከመሞከሯ በፊትም እንኳ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ ወስኖ ነበር። እንዲህ ማድረጉ ፈተናው ሲመጣ ትክክለኛውን እርምጃ እንዲወስድ ረድቶታል።

14. መጥፎ ነገር ለማድረግ ስንፈተን እንቢ ማለትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

14 አንተስ የዮሴፍ ዓይነት ቁርጠኝነት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን እንደምታደርግ ከአሁኑ መወሰን ትችላለህ። ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ወዲያውኑ እንቢ ማለትን ተማር፤ እነዚህን ነገሮች በአእምሮህ እንኳ ለማውጠንጠን ፈቃደኛ አትሁን። (መዝ. 97:10፤ 119:165) እንዲህ ካደረግክ ፈተና ሲያጋጥምህ አቋምህን አታላላም። ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ አስቀድመህ ታውቃለህ። የምትወስደውን እርምጃ አስቀድመህ ወስነሃል።

15. አንድ ሰው ይሖዋን ‘ከልቡ እንደሚፈልግ’ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 11:6)

15 እውነትን እንዳገኘህና ይሖዋን በሙሉ ልብህ ማገልገል እንደምትፈልግ ብታውቅም እንኳ ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ዝግጁ እንዳልሆንክ ሊሰማህ ይችላል። ከሆነ የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። ይሖዋን እንዲህ ብለህ ለምነው፦ “አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ ልቤንም እወቅ። መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ። በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።” (መዝ. 139:23, 24) ይሖዋ ‘ከልብ የሚፈልጉትን’ ይባርካቸዋል። ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግህ ይሖዋን ከልብ እንደምትፈልገው ያሳያል።—ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።

ወደ ይሖዋ መቅረብህን ቀጥል

16-17. እውነት ውስጥ ያደጉ ወጣቶችን ይሖዋ ስቧቸዋል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ዮሐንስ 6:44)

16 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን የሚስባቸው ይሖዋ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:44ን አንብብ።) ይህ እንዴት ያለ ልብ የሚነካ አገላለጽ ነው! ይህ ሐሳብ ለአንተም የሚሠራው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ይሖዋ እያንዳንዱን ሰው ወደ ራሱ የሚስበው በውስጡ መልካም ነገር ስላየ ነው። ግለሰቡን እንደ “ልዩ ንብረቱ” ወይም እንደ “ውድ ሀብቱ” አድርጎ ይመለከተዋል። (ዘዳ. 7:6 ግርጌ) አንተንም እንዲሁ አድርጎ ይመለከትሃል።

17 ይሁንና እውነት ውስጥ ያደግክ ወጣት ከሆንክ ይሖዋ የሳበው ወላጆችህን እንደሆነና አንተ እነሱን ተከትለህ እንደመጣህ ሊሰማህ ይችላል። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕ. 4:8፤ 1 ዜና 28:9) አንተ ቅድሚያውን ወስደህ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት ስታደርግ እሱም በምላሹ ወደ አንተ ይቀርባል። ይሖዋ ሰዎችን የሚመለከተው በቤተሰብ ደረጃ አይደለም። እውነት ውስጥ ያደጉ ወጣቶችን ጨምሮ እያንዳንዱን ሰው የሚስበው በግለሰብ ደረጃ ነው። እንዲህ ያለው ሰው ቅድሚያውን ወስዶ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት ሲያደርግ ይሖዋም በያዕቆብ 4:8 ላይ በተጠቀሰው መሠረት ወደ እሱ ይቀርባል።—ከ2 ተሰሎንቄ 2:13 ጋር አወዳድር።

18. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (መዝሙር 40:8)

18 ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ስትጠመቅ የኢየሱስን ዓይነት ዝንባሌ ታንጸባርቃለህ። ኢየሱስ የታዘዘውን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ራሱን በፈቃደኝነት ለአባቱ አቅርቧል። (መዝሙር 40:8ን አንብብ፤ ዕብ. 10:7) ከተጠመቅክ በኋላ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን ለመቀጠል ምን ሊረዳህ እንደሚችል በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ራስን ለይሖዋ መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው?

  • አመስጋኝ መሆንህ ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን የሚያነሳሳህ እንዴት ነው?

  • ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም እንድንቆጠብ ምን ይረዳናል?

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል