የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ
“በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ብሏል”
ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት የምንችለው ኢየሱስ በደሙ በከፈለው ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው። (ኤፌ. 1:7) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ቻይ በመሆን በቀደሙት ዘመናት [ማለትም ኢየሱስ ቤዛውን ከመክፈሉ በፊት] የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ብሏል” ይላል። (ሮም 3:25) ይሖዋ ፍጹም የሆነውን የፍትሕ መሥፈርቱን ሳይጥስ ይህን ማድረግ የቻለው እንዴት ነው?
ይሖዋ እምነት ያላቸውን የሰው ልጆች የሚያድን “ዘር” እንደሚያዘጋጅ ከወሰነበት ቅጽበት አንስቶ በእሱ ዓይን ቤዛው እንደተከፈለ ሊቆጠር ይችላል። (ዘፍ. 3:15፤ 22:18) አምላክ፣ ጊዜው ሲደርስ አንድያ ልጁ ቤዛውን በፈቃደኝነት እንደሚከፍል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። (ገላ. 4:4፤ ዕብ. 10:7-10) ኢየሱስ የአምላክ ወኪል ሆኖ በምድር ላይ በኖረበት ወቅት ገና ቤዛው ባይከፈልም እንኳ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር የማለት ሥልጣን ነበረው። ይህን ያደረገው፣ ወደፊት የሚከፈለው ቤዛ እምነት ያላቸውን ሰዎች ኃጢአት እንደሚሸፍን ስላወቀ ነው።—ማቴ. 9:2-6