የጥናት ርዕስ 12
መዝሙር 77 በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን ማብራት
ከጨለማ ራቁ—በብርሃን ኑሩ
“በአንድ ወቅት ጨለማ ውስጥ ነበራችሁና፤ አሁን ግን . . . ብርሃን ውስጥ ናችሁ።”—ኤፌ. 5:8
ዓላማ
ኤፌሶን ምዕራፍ 5 ላይ ከሚገኙት ጨለማ እና ብርሃን ከሚሉት ዘይቤያዊ አገላለጾች የምናገኘው ትምህርት
1-2. (ሀ) ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ምን ዓይነት ሁኔታ ነበር? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ሐዋርያው ጳውሎስ ሮም ውስጥ የቁም እስር ላይ ነው፤ የእምነት አጋሮቹን ማበረታታት ፈልጓል። በአካል ሄዶ ሊጠይቃቸው ስለማይችል ደብዳቤዎች ጻፈላቸው። ለምሳሌ በ60 ወይም በ61 ዓ.ም. ገደማ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎላቸዋል።—ኤፌ. 1:1፤ 4:1
2 ከአሥር ዓመት ገደማ በፊት ጳውሎስ ኤፌሶን ነበር፤ ምሥራቹን እየሰበከና እያስተማረ በዚያ ረዘም ያለ ጊዜ ቆይቷል። (ሥራ 19:1, 8-10፤ 20:20, 21) ለወንድሞቹ ጥልቅ ፍቅር ስላለው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ፈልጓል። ሆኖም ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ጨለማና ስለ ብርሃን የጻፈላቸው ለምንድን ነው? ሁሉም ክርስቲያኖች ከዚህ ምክር ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እያየን እንሂድ።
ከጨለማ ወደ ብርሃን
3. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የትኛውን ዘይቤያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል?
3 ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች “እናንተ በአንድ ወቅት ጨለማ ውስጥ ነበራችሁና፤ አሁን ግን . . . ብርሃን ውስጥ ናችሁ” ሲል ጽፎላቸዋል። (ኤፌ. 5:8) እዚህ ላይ ጳውሎስ ጨለማንና ብርሃንን ዘይቤያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመው ሁለት ተጻራሪ ወይም ተቃራኒ ሁኔታዎችን ለማስረዳት ነው። እስቲ በመጀመሪያ የኤፌሶን ክርስቲያኖች “በአንድ ወቅት ጨለማ ውስጥ” እንደነበሩ የተናገረው ለምን እንደሆነ እንመልከት።
4. የኤፌሶን ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ጨለማ ውስጥ ነበሩ ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?
4 ሃይማኖታዊ ጨለማ። ጳውሎስ የጻፈላቸው የኤፌሶን ሰዎች እውነትን ተምረው ክርስቲያኖች ከመሆናቸው በፊት የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና የመናፍስታዊ ድርጊቶች ባሪያ ነበሩ። ኤፌሶን ዝነኛው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ የሚገኝባት ከተማ ነች። ይህ ቤተ መቅደስ በጥንት ዘመን ከዓለም ሰባት ድንቅ ነገሮች አንዱ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በዚህ ቤተ መቅደስ አምልኮ የሚያካሂዱት ሰዎች ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ። የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ምስሎችን መሥራትና መሸጥ አትራፊ ንግድ ነበር። (ሥራ 19:23-27) ከዚህም ሌላ ከተማዋ በአስማት ሥራዎች የታወቀች ነበረች።—ሥራ 19:19
5. የኤፌሶን ሰዎች ሥነ ምግባራዊ ጨለማ ውስጥ እንደነበሩ የተገለጸው ለምንድን ነው?
5 ሥነ ምግባራዊ ጨለማ። ኤፌሶን መረን በለቀቀ ብልግናና በነውረኛ ምግባር የታወቀች ከተማ ነበረች። በከተማዋ ቲያትር ማሳያ ስፍራዎች ሌላው ቀርቶ በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ እንኳ ጸያፍ ንግግር መስማት የተለመደ ነበር። (ኤፌ. 5:3) ብዙዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች “የሥነ ምግባር ስሜታቸው [ደንዝዟል]”፤ ይህ አገላለጽ ቀጥተኛ ትርጉሙ “ምንም ዓይነት ሕመም የማይሰማው” ማለት ነው። (ኤፌ. 4:17-19) የኤፌሶን ክርስቲያኖች ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር እውነቱን ከመማራቸው በፊት የሕሊና ጸጸት የሚሰማቸው ሰዎች አልነበሩም፤ በይሖዋ ፊት ተጠያቂነት እንዳለባቸውም አያስቡም ነበር። ጳውሎስ ስለ ኤፌሶን ሰዎች ሲናገር “አእምሯቸው ጨልሟል፤ እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል” ያለው ለዚህ ነው።
6. ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን “አሁን . . . ብርሃን ውስጥ ናችሁ” ያላቸው ለምንድን ነው?
6 አንዳንድ የኤፌሶን ሰዎች ግን ከጨለማ ወጥተዋል። ጳውሎስ “አሁን ግን የጌታ በመሆናችሁ ብርሃን ውስጥ ናችሁ” ሲል ጽፎላቸዋል። (ኤፌ. 5:8) ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት የሚፈነጥቀውን ብርሃን ተቀብለዋል። (መዝ. 119:105) እነዚህ የኤፌሶን ሰዎች የሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶችንና የሥነ ምግባር ብልግናን ትተዋል። ‘አምላክን መምሰል’ ጀምረዋል፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማምለክና እሱን ለማስደሰት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነበር።—ኤፌ. 5:1
7. የእኛ ሁኔታ ከብዙዎቹ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
7 እኛም እውነትን ከመማራችን በፊት በሃይማኖታዊና በሥነ ምግባራዊ ጨለማ ውስጥ ነበርን። አንዳንዶቻችን የሐሰት ሃይማኖታዊ በዓላትን እናከብር ነበር፤ ሌሎቻችን ደግሞ ሥነ ምግባር የጎደለው የአኗኗር ዘይቤ ነበረን። ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑት ነገሮች የይሖዋን መሥፈርቶች ከተማርን በኋላ ግን ለውጥ አደረግን። በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታችንን መምራት ጀመርን። ይህም ብዙ ጥቅሞች አስገኝቶልናል። (ኢሳ. 48:17) ያም ቢሆን አሁንም ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጣችን አይቀርም። ትተነው ከመጣነው ጨለማ ለመራቅና ‘የብርሃን ልጆች ሆነን ለመመላለስ’ ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ከጨለማው ራቁ
8. በኤፌሶን 5:3-5 መሠረት የኤፌሶን ክርስቲያኖች ከየትኞቹ ድርጊቶች መራቅ ነበረባቸው?
8 ኤፌሶን 5:3-5ን አንብብ። የኤፌሶን ክርስቲያኖች ከሥነ ምግባራዊ ጨለማ ጨርሶ መራቅ ከፈለጉ ይሖዋን ከማያስደስቱ ልማዶች ለመራቅ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ይህ ደግሞ ከብልግና ድርጊቶች ብቻ ሳይሆን ከጸያፍ ንግግር መራቅንም ይጨምራል። የኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ካላስወገዱ “በክርስቶስና በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ” እንደማይኖራቸው ጳውሎስ አሳስቧቸዋል።
9. ሥነ ምግባር ከጎደለው ነገር ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?
9 እኛም “ፍሬ ቢስ በሆኑ የጨለማ ሥራዎች” ላለመጠላለፍ የምናደርገውን ትግል ልናቋርጥ አይገባም። (ኤፌ. 5:11) በተሞክሮ በተደጋጋሚ እንደታየው አንድ ክርስቲያን፣ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር ባየ፣ በሰማ ወይም ባወራ ቁጥር ትክክል ያልሆነውን ነገር ላለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት እየተዳከመ ይሄዳል። (ዘፍ. 3:6፤ ያዕ. 1:14, 15) በአንድ አገር የሚገኙ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጓደኛሞች ቡድን ፈጠሩ። ብዙዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚያወሩት ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ነበር። በጊዜ ሂደት ግን የሚለዋወጡት መልእክት ንጽሕናውን እያጣ ሄዶ በፆታ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ሆነ። ከእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንዶቹ በኋላ ላይ እንደተናገሩት ንጹሕ ባልሆነ ንግግር የጀመረው ነገር ከጊዜ በኋላ የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም መርቷቸዋል።
10. ሰይጣን ሊያታልለን የሚሞክረው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 5:6)
10 የሰይጣን ዓለም ሊያታልለን ይሞክራል፤ ይሖዋ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ወይም ርኩስ እንደሆነ የሚናገረው ነገር ምንም ስህተት እንደሌለበት ሊያሳምነን ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 2:19) ይህ ምንም አያስገርምም! ሰዎችን በማምታታት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲሳናቸው ማድረግ ዲያብሎስ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት የቆየ ዘዴው ነው። (ኢሳ. 5:20፤ 2 ቆሮ. 4:4) ብዙዎቹ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ድረ ገጾች ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጩ ነገሮችን እንድናደርግ ቢያበረታቱ ምን ይገርማል! ይህ የሰይጣን ማታለያ ነው፤ ርኩስ የሆኑ ልማዶችና የአኗኗር ዘይቤዎች ምንም ስህተት እንደሌለባቸው ብቻ ሳይሆን አስደሳችና ጉዳት የሌላቸው እንደሆኑ ሊያሳምነን ይፈልጋል።—ኤፌሶን 5:6ን አንብብ።
11. አንጄላ ያጋጠማት ነገር በኤፌሶን 5:7 ላይ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያለውን አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ሰይጣን የይሖዋን መሥፈርቶች መጠበቅ ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር እንድንወዳጅ ይፈልጋል። ጳውሎስ በአምላክ ዓይን መጥፎ የሆኑ ነገሮችን የሚያደርጉ ሰዎችን በተመለከተ “ከእነዚህ ሰዎች ጋር አትተባበሩ” የሚል ማሳሰቢያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የሰጠው ለዚህ ነው። (ኤፌ. 5:7) በዚህ ረገድ እኛ ከጥንቶቹ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ይበልጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ ከሰዎች ጋር የምንገናኘው በአካል ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያም ጭምር ነው። በእስያ የምትኖረው አንጄላ a ማኅበራዊ ሚዲያ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ከራሷ ተሞክሮ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “በቀላሉ ወጥመድ ሊሆን ይችላል፤ ሳታስቡት የሥነ ምግባር ስሜታችሁን እያደነዘዘው ይሄዳል። ውሎ አድሮ የይሖዋን መሥፈርቶች የማያከብሩ ሰዎችን ኢንተርኔት ላይ ጓደኛ ማድረግ የማይረብሸኝ ደረጃ ላይ ደረስኩ። በኋላ ላይ ደግሞ ‘ይሖዋ የማይደሰትበትን የአኗኗር ዘይቤ ብከተል ስህተቱ ምን ላይ ነው?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።” ደግነቱ አንጄላ በአፍቃሪ ሽማግሌዎች እርዳታ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ ቻለች። “አሁን አእምሮዬን የሚሞላው መንፈሳዊ ነገር እንጂ ማኅበራዊ ሚዲያ አይደለም” ብላለች።
12. ይሖዋ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑት ነገሮች ያወጣውን መሥፈርት በጥብቅ ለመከተል ምን ይረዳናል?
12 ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት መፈጸም ምንም ስህተት እንደሌለው የሚገልጸው የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ አለብን። እኛ ይህ አስተሳሰብ ስህተት እንደሆነ እናውቃለን። (ኤፌ. 4:19, 20) እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፦ ‘የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ከማያከብሩ የሥራ ባልደረቦቼ፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ወይም ሌሎች ሰዎች ጋር ሳያስፈልግ ጊዜ ላለማሳለፍ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ? አንዳንዶች ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለኝ አድርገው ቢመለከቱኝም እንኳ ለይሖዋ መሥፈርቶች በድፍረት ጥብቅና እቆማለሁ?’ ከዚህም ሌላ በ2 ጢሞቴዎስ 2:20-22 ላይ እንደተመከርነው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም እንኳ የቅርብ ጓደኛ የምናደርጋቸውን ሰዎች በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። አንድ ሰው ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንጸና ያግዘናል ማለት እንዳልሆነ ልናስታውስ ይገባል።
“የብርሃን ልጆች ሆናችሁ” ተመላለሱ
13. “የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ” የሚለው ምክር ምን ትርጉም አለው? (ኤፌሶን 5:7-9)
13 ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ያበረታታቸው ከጨለማ እንዲርቁ ብቻ አይደለም፤ “የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ” በማለትም መክሯቸዋል። (ኤፌሶን 5:7-9ን አንብብ።) ይህ ምን ማለት ነው? በአጭሩ በማንኛውም ጊዜ ለእውነተኛ ክርስቲያን የሚመጥን ምግባር ማሳየት ማለት ነው። ይህን ግብ ለማሳካት የሚረዳን አንዱ ነገር መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን በትጋት ማንበብና ማጥናት ነው። በተለይ ደግሞ “የዓለም ብርሃን” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ላስተማራቸው ነገሮችና ለተወው ምሳሌ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው።—ዮሐ. 8:12፤ ምሳሌ 6:23
14. መንፈስ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ‘ከብርሃን ልጆች’ የሚጠበቀውን ምግባር እያሳየን ለመኖር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታም ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ሥነ ምግባር በጎደለው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው። (1 ተሰ. 4:3-5, 7, 8) መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ ፍልስፍናዎችንና አመለካከቶችን ጨምሮ የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን በምናደርገው ትግል ያግዘናል። “ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት [እና] ጽድቅ” እንድናፈራም ይረዳናል።—ኤፌ. 5:9
15. መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ኤፌሶን 5:19, 20)
15 መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ ነው። ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን [እንደሚሰጣቸው]” ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:13) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ስናወድስም መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን። (ኤፌሶን 5:19, 20ን አንብብ።) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ይረዳናል።
16. ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳናል? (ኤፌሶን 5:10, 17)
16 ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ስናደርግ “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ማስተዋልና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:10, 17ን አንብብ።) ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ስንፈልግ አምላክ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት እያደረግን ነው። ከዚያም የእሱን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን።
17. ጊዜን በጥበብ መጠቀም ሲባል ምን ማለት ነው? (ኤፌሶን 5:15, 16) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙበትም መክሯቸዋል። (ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።) “ክፉው” የተባለው ጠላታችን ሰይጣን በዚህ ዓለም ጉዳዮች ከመጠመዳችን የተነሳ ለአምላክ አገልግሎት ጊዜ እንድናጣ ማድረግ ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 5:19) አንድ ክርስቲያን ካልተጠነቀቀ አምላክን ለማገልገል ከሚያስችሉት አጋጣሚዎች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች፣ ለትምህርት ወይም ለሙያው ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮበታል ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት እንዳልሆኑ አይካድም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ ሊይዙ አይገባም። “የብርሃን ልጆች” ሆነን ለመመላለስ ‘ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም’ ይኸውም ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ትኩረት መስጠት አለብን።
18. ዶናልድ ጊዜውን በአግባቡ ለመጠቀም የትኞቹን እርምጃዎች ወስዷል?
18 ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት ለማስፋት የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች በንቃት ተከታተል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ዶናልድ ያደረገው ይህንን ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ያለሁበትን ሁኔታ ገመገምኩ፤ በአገልግሎት የበለጠ ማድረግ እንድችል እንዲረዳኝ ይሖዋን ተማጸንኩት። ለአገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጠኝ ሥራ ማግኘት እንድችል ጸለይኩ። በይሖዋ እርዳታ የሚስማማኝን ሥራ አገኘሁ። እኔና ባለቤቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሀ ብለን የጀመርነው በዚህ መንገድ ነው።”
19. “የብርሃን ልጆች” ሆነን መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ በክርስትና ሕይወታቸው በጣም እንደረዳቸው ጥርጥር የለውም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ምክር እኛንም ይጠቅመናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መዝናኛችንን እና ወዳጆቻችንን በጥበብ እንድንመርጥ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት ከእውነት ብርሃን ሙሉ በሙሉ መጠቀማችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። በተጨማሪም የጳውሎስ ምክር መልካም ባሕርያትን ማፍራት እንድንችል መንፈስ ቅዱስ የሚያበረክተውን ድርሻ ያጎላል። ይህን ምክር በተግባር ማዋል ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ የጥበብ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል። እንግዲያው እነዚህን ነገሮች በማድረግ ከዓለም ጨለማ ርቀን በብርሃን እንመላለስ!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
-
በኤፌሶን 5:8 ላይ የተጠቀሱት “ጨለማ” እና “ብርሃን” ምን ያመለክታሉ?
-
‘ከጨለማ’ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
-
“የብርሃን ልጆች” ሆነን መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ጥንታዊ ቅጂ።