በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ከአምላክ የሚቀበለው “ማረጋገጫ” እና ‘ማኅተም’ ምንድን ነው?—2 ቆሮ. 1:21, 22 ግርጌ

በጥንት ዘመን የአንድን ሰነድ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ የማኅተም ቀለበትን በጭቃ ወይም በሰም ላይ በመጫን ምልክት ይደረግበት ነበር

ማረጋገጫ፦ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው በ2 ቆሮንቶስ 1:22 ላይ “ማረጋገጫ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ከሕግና ከንግድ ጋር በተያያዘ የሚሠራበት” ነው፤ ትርጉሙም “የመጀመሪያ ክፍያ፣ መያዣ፣ ቀብድ ማለት ሲሆን አንድ ነገር የተገዛበትን ዋጋ በተወሰነ መጠን በቅድሚያ በመክፈል የዕቃውን ሕጋዊ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ወይም አንድን ውል ሕጋዊ ለማድረግ ያስችላል።” ይሖዋ ለቅቡዓን ሽልማት እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል፤ በ2 ቆሮንቶስ 5:1-5 ላይ እንደተገለጸው ቅቡዓኑ፣ ሙሉውን ክፍያ ወይም ሽልማት ሲያገኙ የማይበሰብስ ሰማያዊ አካል ይለብሳሉ። ሽልማቱ ያለመሞት ባሕርይ ማግኘትንም ይጨምራል።—1 ቆሮ. 15:48-54

በዘመናዊው ግሪክኛ፣ አንድ ሰው ሲታጭ የሚያደርገውን ቀለበት ለማመልከት የሚሠራበት ቃል “ማረጋገጫ” ተብሎ ከተተረጎመው ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው። ይህ መሆኑም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ቅቡዓን፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ሚስት እንደሆኑ ተደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጸዋል።—2 ቆሮ. 11:2፤ ራእይ 21:2, 9

ማኅተም፦ በጥንት ዘመን ማኅተም የአንድን ነገር ባለቤትነትና ትክክለኛነት ለማመልከት ወይም ስምምነትን ለማረጋገጥ እንደ ፊርማ ሆኖ ያገለግል ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ የአምላክ ንብረት መሆናቸውን ለማሳየት በምሳሌያዊ ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስ ‘ታትመዋል’ ወይም ምልክት ተደርጎባቸዋል። (ኤፌ. 1:13, 14) ይሁንና ይህ የመጨረሻው ማኅተም አይደለም፤ አንድ ግለሰብ የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግበት በታማኝነት ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አሊያም ታላቁ መከራ ከመምጣቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ነው።—ኤፌ. 4:30፤ ራእይ 7:2-4