በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታህን በጥበብ እየተጠቀምክበት ነው?

በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታህን በጥበብ እየተጠቀምክበት ነው?

ክብደቱ 1.4 ኪሎ ግራም ብቻ ቢሆንም “በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እስካሁን ከደረስንባቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ ውስብስብ” እንደሆነ ይነገርለታል። የምናወራው ስለ ሰው አንጎል ነው። የሰው አንጎል በእርግጥም እጅግ አስደናቂ ነው። ስለ አንጎላችን ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን ለይሖዋ “ድንቅ” ሥራዎች ያለን አድናቆትም እየጨመረ ይሄዳል። (መዝ. 139:14) አንጎላችን ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል አንዱን ይኸውም በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን እስቲ እንመልከት።

በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታ ምንድን ነው? አንድ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው በዓይነ ሕሊና መሳል ሲባል “አዲስና አስደሳች ስለሆኑ ወይም ከዚህ በፊት አጋጥመውህ ስለማያውቁ ነገሮች በአእምሮህ ውስጥ ምስል ወይም ሐሳብ የመፍጠር ችሎታ” ማለት ነው። ከዚህ ፍቺ አንጻር፣ በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን አዘውትረን እንጠቀምበታለን ቢባል አትስማማም? ለምሳሌ ያህል፣ ወደ አንድ ቦታ ሄደህ ባታውቅም ስለዚያ ቦታ አንብበህ ወይም ሰዎች ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ቦታውን በዓይነ ሕሊናህ እንደሳልከው የታወቀ ነው። በእርግጥም ልናየው፣ ልንሰማው፣ ልንቀምሰው፣ ልንዳስሰው ወይም ልናሸተው ስለማንችለው ነገር በምናስብበት ጊዜ በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን እንጠቀማለን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ መልክ እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍ. 1:26, 27) ይህ መሆኑ ይሖዋም በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታ እንዳለው የሚጠቁም አይደለም? ይሖዋ እኛን ሲፈጥረን ይህን ችሎታ ስለሰጠን ችሎታችንን የእሱን ፈቃድና ቃል የገባልንን ነገሮች ለመረዳት እንድንጠቀምበት ቢጠብቅብን ምክንያታዊ አይሆንም? (መክ. 3:11) ታዲያ በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን የይሖዋን ፈቃድ ለመረዳት በጥበብ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ይህን ችሎታችንን አላግባብ ከመጠቀም መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን አላግባብ መጠቀም

(1) ተገቢ ባልሆነ ጊዜ ወይም ተገቢ ስላልሆኑ ነገሮች ማውጠንጠን።

ስለ አንድ ነገር ማውጠንጠን በራሱ መጥፎ አይደለም። እንዲያውም ማውጠንጠን ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። መክብብ 3:1 እንደሚገልጸው “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው”፤ ይሁን እንጂ ተገቢ ባልሆነ ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን እናደርግ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ወይም በግላችን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና አእምሯችን ሽርሽር እንዲሄድ የምንፈቅድ ከሆነ በዓይነ ሕሊና የመጠቀም ችሎታችን እየጠቀመን ነው ወይስ እንቅፋት እየሆነብን? ኢየሱስ አእምሯችን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን፣ ለምሳሌ የብልግና ሐሳቦችን እንዲያውጠነጥን መፍቀድ አደገኛ መሆኑን የሚገልጽ ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ማቴ. 5:28) በዓይነ ሕሊናችን የምንስላቸው አንዳንዶቹ ነገሮች ይሖዋን በጣም የሚያሳዝኑ ሊሆኑ ይችላሉ። በብልግና ሐሳቦች ላይ ማውጠንጠን ብልግና ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። እንግዲያው በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታህ ከይሖዋ እንዲያርቅህ ፈጽሞ ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ!

(2) ቁሳዊ ሀብት ዘላቂ ዋስትና እንደሚሆን ማሰብ።

ቁሳዊ ነገሮች አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኙልንና ዋስትና እንደሚሆኑን ካሰብን ለሐዘን መዳረጋችን አይቀርም። ጠቢቡ ሰለሞን “የባለጸጋ ሰው ሀብት የተመሸገ ከተማው ነው፤ በሐሳቡም ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርጎ ይመለከተዋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 18:11) መስከረም 2009 በማኒላ፣ ፊሊፒንስ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የከተማዋን ክፍል በጎርፍ ባጥለቀለቀው ጊዜ የተከሰተውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ብዙ ቁሳዊ ሀብት የነበራቸው ሰዎች ከአደጋው ማምለጥ ችለው ይሆን? አብዛኛውን ሀብቱን ያጣ አንድ ባለጸጋ “ጎርፉ ሁላችንንም እኩል አድርጎናል፤ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች ልዩ ልዩ ችግሮችንና መከራዎችን ቀምሰዋል” ብሏል። ቁሳዊ ነገሮች እውነተኛ ጥበቃ እንደሚያስገኙና ዋስትና እንደሚሆኑ እናስብ ይሆናል። እውነታው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው።

(3) ላይደርስብን ስለሚችል ነገር ሳያስፈልግ መጨነቅ።

ኢየሱስ ከልክ በላይ ‘እንዳንጨነቅ’ መክሮናል። (ማቴ 6:34) ሁልጊዜ የሚጨነቅ ሰው በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታውን ከሚገባው በላይ እየተጠቀመበት ነው። በአእምሯችን ስለፈጠርናቸው ችግሮች ይኸውም ገና ስላልደረሱብን ወይም ፈጽሞ ላይደርሱብን ስለሚችሉ ችግሮች እያሰብን መጨነቅ ኃይላችንን ይጨርሰዋል። ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት ተስፋ ወደ መቁረጥ አልፎ ተርፎም ወደ መንፈስ ጭንቀት ሊመራ እንደሚችል ይጠቁማሉ። (ምሳሌ 12:25 ግርጌ) ከመጠን በላይ ባለመጨነቅና በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን አሳሳቢ ጉዳዮች እንዳመጣጣቸው በመፍታት የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ምንኛ ጠቃሚ ነው!

በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን በጥበብ መጠቀም

(1) አደገኛ ሁኔታዎችን አስቀድሞ በማስተዋል መራቅ።

ቅዱሳን መጻሕፍት ብልሆች እንድንሆንና አርቀን እንድናስብ ያበረታቱናል። (ምሳሌ 22:3) በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን በመጠቀም፣ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሊያስከትሏቸው የሚችሉ መዘዞችን አስቀድመን ማሰብ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ግብዣ ላይ ብትጠራ ግብዣው ላይ መገኘትን አሊያም መቅረትን በተመለከተ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታህ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? በግብዣው ላይ እነማን እንደሚገኙ፣ ተጋባዦቹ ምን ያህል እንደሚሆኑ፣ ግብዣው መቼና የት እንደሚካሄድ እንዲሁም የመሳሰሉትን ነገሮች ካጣራህ በኋላ ‘በግብዣው ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል?’ ብለህ አስብ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የማይጋጭ ግብዣ እንደሚሆን ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ ማሰብህ በግብዣው ላይ የሚኖረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ያስችልሃል። በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታህን በመጠቀም ጥበብ ያለበት ውሳኔ ማድረግህ መንፈሳዊነትህን ከሚጎዱ ሁኔታዎች እንድትርቅ ይረዳሃል።

(2) ከባድ ችግሮችን እንዴት እንደምትፈታ አስቀድመህ ማሰብ።

በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታ ‘ችግርን ተጋፍጦ ለመፍታትም’ ይረዳል። በጉባኤ ውስጥ ከአንድ ሰው ጋር አለመግባባት አጋጥሞሃል እንበል። በመካከላችሁ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ወንድምህን ወይም እህትህን ቀርበህ የምታነጋግረው እንዴት ነው? ከግምት መግባት ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ግለሰቡ ሐሳቡን የሚገልጸው እንዴት ነው? ስለ ችግሩ አንስቶ ለመነጋገር ተስማሚ የሚሆነው ጊዜ መቼ ነው? ምን ብዬ ብናገር ይሻላል? የድምፄ ቃናስ ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል? በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታህን በመጠቀም፣ ችግሩን መፍታት የሚቻልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ወደ አእምሮህ እያመጣህ ማሰብ ትችላለህ፤ ከዚያም ውጤታማ እንደሚሆንና ግለሰቡ ጥሩ ምላሽ እንዲሰጥ እንደሚያደርገው የሚሰማህን መንገድ ምረጥ። (ምሳሌ 15:28 ግርጌ) አስቸጋሪ ሁኔታን ለመፍታት እንዲህ ዓይነቱን አሳቢነት የተሞላበት መንገድ መጠቀም በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ይረዳል። በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን ጥሩ አድርገን ለመጠቀም ከሚያስችሉን መንገዶች መካከል አንዱ ይህ ነው።

(3) የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህንና ጥናትህን ማሻሻል።

መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ ወሳኝ ነገር ነው። በየዕለቱ ብዙ ገጾችን ማንበቡ ብቻ ግን በቂ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ ትምህርቶች ማስተዋልና በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ለማዋል መነሳሳት ያስፈልገናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ይሖዋ ስላከናወናቸው ነገሮች ያለንን አድናቆት ሊጨምርልን ይገባል። በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን መጠቀማችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል። እንዴት? በእምነታቸው ምሰሏቸው የተሰኘውን መጽሐፍ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ዘገባዎች ስናነብ፣ የታሪኩን መቼትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የእያንዳንዱን ባለ ታሪክ ሕይወት በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። በተጨማሪም በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ ለማየት፣ ድምፆቹን ለመስማትና መዓዛውን ለማሽተት እንዲሁም የባለ ታሪኮቹን ስሜት ለመረዳት ያስችለናል። እንዲህ ማድረጋችን በደንብ እንደምናውቃቸው ከሚሰማን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ግሩም ትምህርቶችንና የሚያበረታቱ ሐሳቦችን እንድናገኝ ያደርገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንና ጥናታችን ወቅት በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን በዚህ መንገድ መጠቀማችን ጥናታችንን ለማሻሻል ይረዳናል።

(4) የሌሎችን ችግር እንደ ራስ የማየት ችሎታን ማዳበር።

የሌሎችን ችግር እንደ ራስ መመልከት፣ የሌላው ሰው ሥቃይ በልባችን ጠልቆ እንዲሰማን የሚያደርግ ግሩም ባሕርይ እንደሆነ ይገለጻል። ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ይህን ባሕርይ ስለሚያሳዩ እኛም እነሱን መምሰላችን አስፈላጊ ነው። (ዘፀ 3:7፤ መዝ 72:13) ይህን ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የሌሎችን ችግር እንደ ራስ የመመልከት ችሎታን ለማዳበር የሚረዳን አንዱ ግሩም መንገድ በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታችንን መጠቀም ነው። አንድ የእምነት ባልንጀራችን እየደረሰበት ያለው ችግር ፈጽሞ አጋጥሞን አያውቅ ይሆናል። ሆኖም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህ ችግር በእኔ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ምን ይሰማኝ ነበር? እንዲህ ባለው ሁኔታ ምን እንዲደረግልኝ እፈልግ ነበር?’ በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታችንን በመጠቀም እነዚህን ጥያቄዎች መመለሳችን፣ የሌሎችን ችግር እንደ ራሳችን ችግር በማየት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ይረዳናል። በእርግጥም አገልግሎታችንንና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያለንን ግንኙነት ጨምሮ በተለያዩ መስኮች፣ የሌሎችን ችግር እንደ ራሳችን አድርገን መመልከታችን በመላ ሕይወታችን ይጠቅመናል።

(5) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናችን መመልከት።

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ወለል ብሎ እንዲታየን የሚያደርጉ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዘዋል። (ኢሳ 35:5-7፤ 65:21-25፤ ራእይ 21:3, 4) ጽሑፎቻችንም እነዚህን መግለጫዎች ግሩም አድርገው የሚያሳዩ የሚያማምሩ ሥዕሎችን ይዘው ይወጣሉ። ለምን? ሥዕላዊ መግለጫዎች በዓይነ ሕሊናችን የማየት ችሎታችንን ይበልጥ እንድንጠቀምበት የሚረዱን ከመሆኑም ሌላ አምላክ ቃል የገባቸው በረከቶች ፍጻሜ እውን ሆኖ እንዲታየን ያደርጋሉ። በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታችንን የሰጠን ይሖዋ፣ ይህ ችሎታችን ምን ያህል ኃይል እንዳለው ከማንም በላይ ያውቃል። ይህን ችሎታ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ለማሰላሰል የምንጠቀምበት ከሆነ ተስፋዎቹ እንደሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ የምንተማመን ከመሆኑም በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ተፈታታኝ የሕይወት ውጣ ውረዶች በመቋቋም ታማኝነታችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል።

ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ አስደናቂ የሆነውን በዓይነ ሕሊና የማየት ችሎታ ሰጥቶናል። ይህ ችሎታ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እሱን በሚገባ ለማገልገል ሊረዳን ይችላል። እንግዲያው በእያንዳንዱ ቀን በዚህ ችሎታ በጥበብ በመጠቀም፣ ይህን ድንቅ ስጦታ ለሰጠን አምላክ ያለንን አድናቆት እናሳይ!