በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም”

“ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም”

“በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።”—ያዕ. 1:4

መዝሙሮች፦ 135, 139

1, 2. (ሀ) ጌድዮንና አብረውት የነበሩት 300 ሰዎች ካሳዩት ጽናት ምን እንማራለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) በሉቃስ 21:19 መሠረት ጽናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ጦርነቱ ተፋፍሟል። በመስፍኑ ጌድዮን የሚመሩት የእስራኤል ወታደሮች፣ ጠላቶቻቸው የሆኑትን ምድያማውያንንና ግብረ አበሮቻቸውን ሌሊቱን ሙሉ ሲያሳድዱ አድረዋል፤ እነሱን እየተከታተሉ ወደ 32 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ስለተጓዙ እጅግ ዝለዋል! መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሆነውን ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ከዚያም ጌድዮን ወደ ዮርዳኖስ መጥቶ ወንዙን ተሻገረ። እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት 300 ሰዎች ደክሟቸው [ነበር]።” ያም ሆኖ ጌድዮንና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በጦርነቱ ገና ድል አልተቀዳጁም፤ ወደ 15,000 የሚጠጉ የጠላት ወታደሮች ይቀሯቸዋል። እስራኤላውያን በምድያማውያን የጭቆና ቀንበር ሥር በርካታ ዓመታት ስላሳለፉ ይህ፣ ውጊያውን የሚያቆሙበት ወቅት እንዳልሆነ ያውቃሉ። በመሆኑም “ጠላቶቻቸውን ከማሳደድ ወደኋላ” አላሉም፤ ከዚህ ይልቅ ምድያማውያንን በማሸነፍ እንዲገዙላቸው አደረጉ።—መሳ. 7:22፤ 8:4, 10, 28

2 እኛም ብንሆን ምንጊዜም ውጊያ ላይ ነን፤ ውጊያው ደግሞ ከባድ ነው። ጠላቶቻችን፣ ሰይጣንና እሱ የሚገዛው ዓለም እንዲሁም የራሳችን አለፍጽምና ናቸው። አንዳንዶቻችን በውጊያው ላይ በርካታ አሥርተ ዓመታት ያሳለፍን ሲሆን በይሖዋ እርዳታ ብዙ ድሎችን ተቀዳጅተናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከጠላቶቻችን ጋር መዋጋትና የዚህን ሥርዓት መጨረሻ መጠባበቅ ሊታክተን ይችላል። ሆኖም በውጊያው ሙሉ በሙሉ እንዳላሸነፍን እናስታውስ። ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት የምንኖር ክርስቲያኖች፣ ከባድ ፈተናዎች ሊያጋጥሙንና ግፍ ሊፈጸምብን እንደሚችል አስጠንቅቆናል፤ በተጨማሪም ድል መቀዳጀታችን የተመካው በመጽናታችን ላይ እንደሆነ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:19ን አንብብ።) ይሁንና ጽናት ምንድን ነው? ለመጽናት ምን ሊረዳን ይችላል? ከጸኑት ምን እንማራለን? “ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ [እንዲፈጽም]” ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?—ያዕ. 1:4

ጽናት ምንድን ነው?

3. ጽናት ምንድን ነው?

3 መጽናት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ ፈተናዎችን ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ከመቋቋም የበለጠ ነገርን ለማመልከት ነው። ጽናት ከአስተሳሰባችንና ከስሜታችን ማለትም መከራ ሲደርስብን ከምናደርገው ነገር ጋር የተያያዘ ነው። የሚጸና ሰው ድፍረትና ትዕግሥት እንዳለው እንዲሁም ከአቋሙ ፍንክች እንደማይል ያሳያል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ጽናት “አንድን ነገር ምርጫ ስለሌለን ብቻ መቀበልን ሳይሆን ብሩህ ተስፋ ይዞ የመቻልን መንፈስ ያመለክታል።” ይኸው ጽሑፍ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ጽናት፣ አንድ ሰው ወደ እሱ የሚነፍሰውን ነፋስ ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሳይንገዳገድ እንዲቆም የሚያስችለው ባሕርይ ነው። ከሥቃዩ ባሻገር ያለውን ግብ ለመመልከት ስለሚረዳ ከባዱን መከራ ወደ ክብር መለወጥ የሚያስችል ግሩም ባሕርይ ነው።”

4. ለመጽናት የሚያነሳሳን ፍቅር ነው የምንለው ለምንድን ነው?

4 ክርስቲያኖች እንዲጸኑ የሚያነሳሳቸው ፍቅር ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7ን አንብብ።) ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ እሱ የሚፈቅደውን ማንኛውንም ነገር በጽናት እንድንወጣ ያነሳሳናል። (ሉቃስ 22:41, 42) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር፣ ፍጹማን ባለመሆናቸው ያለባቸውን ድክመት ችለን እንድናልፍ ይረዳናል። (1 ጴጥ. 4:8) ለትዳር ጓደኛችን ያለን ፍቅር ደግሞ ደስተኛ ባለትዳሮች እንኳ የሚያጋጥማቸውን “መከራ” በጽናት እንድናሳልፍና የትዳር ጥምረታችንን እንድናጠናክር ያደርገናል።—1 ቆሮ. 7:28

ለመጽናት ምን ይረዳሃል?

5. እንድንጸና ከማንም በተሻለ ሊረዳን የሚችለው ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው። ይሖዋ “ጽናትንና መጽናኛን [የሚሰጥ] አምላክ” ነው። (ሮም 15:5) የሚያጋጥሙንን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ያለንበት ሁኔታ፣ ስሜታችን እንዲሁም ተፈጥሯችን የሚያስከትሉብንን ጫና ሙሉ በሙሉ ሊረዳልን የሚችለው እሱ ብቻ ነው። በመሆኑም እንድንጸና ከማንም በተሻለ ሊረዳን የሚችለው ይሖዋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “የሚፈሩትን ሰዎች ፍላጎት ያረካል፤ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል” ይላል። (መዝ. 145:19) ታዲያ አምላክ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን ስንጸልይ መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው?

6. መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ይሖዋ ‘መውጫ መንገዱን የሚያዘጋጅልን’ እንዴት ነው?

6 አንደኛ ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ። ይሖዋ የደረሰብንን መከራ መወጣት እንድንችል ስንጠይቀው ‘መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል።’ ይህ ሲባል ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ መከራውን ያስወግደዋል ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ሊያደርግ ይችላል። ብዙ ጊዜ ግን መውጫ መንገዱን የሚያዘጋጅልን “ፈተናውን በጽናት መቋቋም” እንድንችል በመርዳት ነው። ይሖዋ “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [እንድንቋቋም]” የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። (ቆላ. 1:11) ደግሞም ይሖዋ ከአካላችን፣ ከአእምሯችንና ከስሜታችን ጋር በተያያዘ አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ ስለሚያውቅ ታማኝነታችንን መጠበቅ እስኪያቅተን ድረስ እንድንፈተን አይፈቅድም።

7. ለመጽናት መንፈሳዊ ምግብ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

7 መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ እምነትህን ገንባ። በዓለም ላይ በከፍታው አንደኛ የሆነውን የኤቨረስት ተራራ የሚወጣ ሰው፣ ሌላ ጊዜ ቢሆን በሦስት ወይም በአራት ቀን የሚመገበውን ያህል ምግብ በአንድ ቀን ውስጥ መብላት ያስፈልገዋል። ይህም ጉዞውን በጽናት ለማጠናቀቅና ግቡ ላይ ለመድረስ ያስችለዋል። እኛም በተመሳሳይ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን መጽናትና ግባችን ላይ መድረስ ከፈለግን ከፍተኛ መጠን ያለው መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረን መመገብ ያስፈልገናል። ለንባብ፣ ለጥናትና ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ጊዜ ለመመደብ ራሳችንን መግዛት ይኖርብናል። እነዚህ ነገሮች ‘ዘላቂ የሆነና የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ምግብ’ ስለሚሰጡን እምነታችንን ያጠናክሩታል።—ዮሐ. 6:27

8, 9. (ሀ) ኢዮብ 2:4, 5 እንደሚያሳየው መከራ ሲያጋጥመን ልናስብበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) መከራ ሲያጋጥምህ የትኛውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ መሳል ትችላለህ?

8 ንጹሕ አቋም ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጉዳይ አስታውስ። በአንድ የይሖዋ አገልጋይ ላይ ፈተና ሲደርስ፣ በእሱ ላይ ከሚደርሰው መከራ የበለጠ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ አለ። መከራ ሲደርስብን የምንወስደው እርምጃ፣ ‘ይሖዋን የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል። የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወመው ሰይጣን የሚከተለውን ሐሳብ በመሰንዘር ይሖዋን ተገዳድሮታል፦ “[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል። ሆኖም እጅህን ዘርግተህ [ኢዮብን] በአጥንቱና በሥጋው ላይ ጉዳት አድርስበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።” (ኢዮብ 2:4, 5) እንደ ሰይጣን አባባል ከሆነ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተነሳስቶ ይሖዋን የሚያገለግል ማንም የለም። ሰይጣን ይህን ግድድር ከሰነዘረ በኋላ ሐሳቡን ቀይሮ ይሆን? በፍጹም! ከላይ ያለውን ከተናገረ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ከሰማይ በተባረረበት ወቅት “ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 12:10) ሰይጣን ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጉዳይ አልረሳውም። በመከራ ተሸንፈን ስንወድቅና የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፋችንን ስናቆም ለማየት ይጓጓል።

9 እንግዲያው መከራ ሲያጋጥምህ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። በአንድ ወገን፣ ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ የሆኑት አጋንንት ያጋጠመህን መከራ መቋቋም እንደማትችልና እንደምትሸነፍ በመግለጽ ሲጠቋቆሙብህ ይታይህ። በሌላኛው ወገን ደግሞ ይሖዋ፣ በመግዛት ላይ ያለው ልጁ፣ ከሞት የተነሱት ቅቡዓንና እልፍ አእላፋት መላእክት አሉ። በየዕለቱ ጽናት በማሳየትህና የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍህ መደሰታቸውን በመግለጽ እያበረታቱህ ነው። ይሖዋ አንተን በግለሰብ ደረጃ “ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው” እያለህ እንደሆነ አድርገህ አስብ።—ምሳሌ 27:11

10. ጽናት በሚያስገኘው ሽልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምትችለው እንዴት ነው?

10 መጽናት በሚያስገኘው ሽልማት ላይ ትኩረት አድርግ። ወደ አንድ ሩቅ ቦታ እየተጓዝክ እንደሆነ አድርገህ አስብ፤ በጉዞህ መሃል አንድ ረጅም መተላለፊያ ዋሻ አጋጠመህ። በሁሉም አቅጣጫ የሚታይህ ጨለማ ብቻ ነው። ይሁንና ጉዞውን ከቀጠልክ በመተላለፊያው ጫፍ ላይ ብርሃን እንደሚታይህ እርግጠኛ ነህ። በተመሳሳይም የሚያጋጥሙህ ችግሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ የሚሰማህ ጊዜ ይኖር ይሆናል። ኢየሱስም እንኳ እንዲህ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ‘ኃጢአተኞች የተቃውሞ ንግግር’ የሰነዘሩበትና ውርደት የደረሰበት ከመሆኑም ሌላ “በመከራ እንጨት” ላይ ተሰቅሎ ተሠቃይቶ ሞቷል፤ ይህ ወቅት በሕይወቱ ውስጥ የጨለማ ጊዜ እንደነበር ጥያቄ የለውም! ያም ሆኖ ኢየሱስ “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል” ይህን ሁሉ በጽናት ተቋቁሟል። (ዕብ. 12:2, 3) ጽናቱ በሚያስገኝለት ሽልማት፣ በተለይ ደግሞ ለአምላክ ስም መቀደስና ለይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። ኢየሱስ በመከራ ውስጥ ሆኖ ያሳለፈው የጨለማ ወቅት ጊዜያዊ ሲሆን እንደ ብርሃን የሆነለት በሰማይ የሚያገኘው ሽልማት ግን ዘላለማዊ ነው። በዛሬው ጊዜ አንተም ሥቃይ የሚያስከትሉና የሚደቁሱ መከራዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ይሁንና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ የሚያጋጥሙህ መከራዎች ጊዜያዊ እንደሆኑ አስታውስ።

“የጸኑት”

11. “የጸኑት” የተባሉት የተዉትን ምሳሌ መመርመራችን ምን ጥቅም አለው?

11 በመጽናት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን ብዙዎች አሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቲያኖች ሰይጣን የሚያመጣባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጽናት እንዲወጡ ለማበረታታት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝባችሁ በእምነት ጸንታችሁ በመቆም ተቃወሙት።” (1 ጴጥ. 5:9) “የጸኑት” የአምላክ አገልጋዮች የተዉት ምሳሌ ጽኑ አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል፤ ሊሳካልን እንደሚችል ማረጋገጫ ይሰጠናል፤ እንዲሁም ታማኞች ከሆንን ሽልማት እንደምናገኝ ያስታውሰናል። (ያዕ. 5:11) እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። [1]

12. ኤደንን እንዲጠብቁ ከተመደቡት ኪሩቤል ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ኪሩቤል። ለሰዎች ከተገለጡት መንፈሳዊ ፍጥረታት መካከል የመጀመሪያዎቹ የተዉት ምሳሌ፣ አስቸጋሪ የሆነ ምድብ ሲሰጠን መጽናትን ያስተምረናል። ይሖዋ አምላክ “ወደ ሕይወት ዛፍ [የሚወስደውን] መንገድ ለመጠበቅ በኤደን የአትክልት ስፍራ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤልና ያለማቋረጥ የሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ።” [2] (ዘፍ. 3:24) ኪሩቤል የተፈጠሩት ይህን ሥራ እንዲሠሩ እንዳልሆነ የታወቀ ነው! ደግሞም ይሖዋ ለሰው ልጆች በነበረው ዓላማ ውስጥ ኃጢአትና ዓመፅ ቦታ አልነበራቸውም። ያም ሆኖ ትልቅ ቦታ ያላቸው እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት፣ የተሰጣቸው ሥራ ለእነሱ የማይመጥን እንደሆነ በመግለጽ ቅሬታቸውን እንዳሰሙ የሚገልጽ ሐሳብ የትም ቦታ አናገኝም። ይህ ምድብ ሰልችቷቸው አልተዉትም። ከዚህ ይልቅ ታዛዥ በመሆን ምድባቸው ላይ ቆይተዋል፤ ምናልባትም ከ1,600 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ የጥፋት ውኃ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ሥራቸውን በጽናት አከናውነዋል!

13. ኢዮብ የደረሰበትን መከራ በጽናት መወጣት የቻለው እንዴት ነው?

13 ታማኙ ኢዮብ። አንድ ወዳጅህ ወይም የቤተሰብህ አባል በተናገረው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ስሜትህ ተደቁሶ አሊያም በከባድ ሕመም እየተሠቃየህ ወይም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ኢዮብ ከተወው ምሳሌ ማጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። (ኢዮብ 1:18, 19፤ 2:7, 9፤ 19:1-3) ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ያደረገው ማን መሆኑን ባያውቅም እንኳ ተስፋ አልቆረጠም። እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? አንደኛ ነገር “አምላክን የሚፈራ” ሰው ነበር። (ኢዮብ 1:1) ኢዮብ አመቺ በሆነ ወቅትም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ ይሖዋን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ፣ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ባከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች ላይ እንዲያሰላስል ኢዮብን ረድቶታል። ይህም መከራዎቹን ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚያስወግዳቸው ይበልጥ እንዲተማመን አድርጎታል። (ኢዮብ 42:1, 2) ደግሞም የሆነው ይህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ እንዲያበቃ አደረገ፤ ደግሞም ብልጽግናውን መለሰለት። ይሖዋ ለኢዮብ ቀድሞ የነበረውን እጥፍ አድርጎ ሰጠው” ይላል። ኢዮብም “ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።”—ኢዮብ 42:10, 17

14. ሁለተኛ ቆሮንቶስ 1:6 እንደሚገልጸው የጳውሎስ ጽናት ሌሎችን የረዳው እንዴት ነው?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ። ከእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች፣ መራራ ተቃውሞ ሌላው ቀርቶ ስደት እየደረሰብህ ነው? ያሉብህ ከባድ ኃላፊነቶች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ የሚሰማህ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካች ነህ? ከሆነ ጳውሎስ በተወው ምሳሌ ላይ አሰላስል። ጳውሎስ ብዙ “ውጫዊ ችግሮች” የደረሱበት ይኸውም ጨካኝ አሳዳጆች ያስጨነቁት ከመሆኑም ሌላ የጉባኤዎች ሐሳብ በየዕለቱ ጫና ይፈጥርበት ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-29) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ተስፋ አልቆረጠም፤ የተወው ምሳሌም ለሌሎች የብርታት ምንጭ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:6ን አንብብ።) አንተም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት ስትቋቋም የአንተ ምሳሌነት ሌሎችም እንዲጸኑ እንደሚያበረታታቸው አስታውስ።

ጽናት በአንተ ላይ “ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም” ይሆን?

15, 16. (ሀ) ጽናት የሚፈጽመው “ሥራ” የትኛው ነው? (ለ) “ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ” እንዲፈጽም ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ስጥ።

15 ያዕቆብ “ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ጽናት የሚፈጽመው “ሥራ” ምንድን ነው? ጽናት ‘በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድለን ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድንሆን’ ይረዳናል። (ያዕ. 1:4) አብዛኛውን ጊዜ ፈተናዎች፣ ምን ድክመት እንዳለብን እንዲሁም ልናሻሽላቸው የሚገቡን ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ እንድንገነዘብ ያደርጋሉ። የሚደርሱብንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ማዳበር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ይበልጥ ታጋሾች፣ አድናቂዎችና ሩኅሩኆች እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ።

የሚደርሱብንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ማዳበር እንችላለን (አንቀጽ 15, 16ን ተመልከት)

16 ጽናት ጥሩ ክርስቲያኖች እንድንሆን በመቅረጽ ረገድ አስፈላጊ የሆነ ሥራ ይፈጽማል፤ በመሆኑም የሚደርሱብንን ፈተናዎች ለማስቆም ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከመጣስ ልንቆጠብ ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ ርኩስ የሆኑ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እየመጡ ቢያስቸግሩህ ምን ታደርጋለህ? በፈተናው ከመሸነፍ ይልቅ እነዚህን ምኞቶች ለማስወገድ እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። እንዲህ በማድረግ፣ ራስን የመግዛት ባሕርይ ታዳብራለህ። ከማያምን የቤተሰብህ አባል ተቃውሞ እየደረሰብህ ነው? በተጽዕኖው ከመሸነፍ ይልቅ በሙሉ ልብህ ይሖዋን ማምለክህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይህም በይሖዋ ላይ ይበልጥ እንድትተማመን ይረዳሃል። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት፣ መጽናት እንዳለብን አስታውስ።—ሮም 5:3-5፤ ያዕ. 1:12

17, 18. (ሀ) እስከ መጨረሻው መጽናት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር። (ለ) መጨረሻው ይበልጥ እየቀረበ ሲሄድ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 መጽናት የሚያስፈልገን ለጊዜው ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አደጋ የደረሰባትን መርከብ እንውሰድ። ተሳፋሪዎቹ በሕይወት ለመትረፍ ከፈለጉ እየዋኙ ወደ ዳርቻው መሄድ አለባቸው። ወደ ዳርቻው ለመድረስ ጥቂት ሲቀረውም ሆነ ገና መሃል ላይ እያለ ተስፋ የቆረጠ ተሳፋሪ የሚያጋጥማቸው ነገር ተመሳሳይ ነው። እኛም ብንሆን ወደ አዲሱ ዓለም እስክንገባ ድረስ ለመጽናት ቆርጠናል። ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በመጽናታችን ላይ ነው። “ተስፋ አንቆርጥም” በማለት ሁለት ጊዜ እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አመለካከት አለን።—2 ቆሮ. 4:1, 16

18 ይሖዋ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናት እንድንችል እንደሚረዳን ፈጽሞ አንጠራጠርም። በሮም 8:37-39 ላይ ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ እንጋራለን፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን። ምክንያቱም ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።” እውነት ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ልንዝል እንችላለን። ያም ቢሆን ጌድዮንና አብረውት ያሉት ሰዎች ‘ወደኋላ እንዳላሉ’ እናስታውስ፤ እኛም እስከ መጨረሻው ከጸናን እንዲህ ሊባልልን ይችላል።—መሳ. 8:4

^ [1] (አንቀጽ 11) በዘመናችን የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ስላሳዩት ጽናት የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ማንበብህም ሊያበረታታህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የ1992 እና የ1999 እንዲሁም የ2008 የዓመት መጻሕፍት (እንግሊዝኛ) በኢትዮጵያ፣ በማላዊና በሩሲያ ስለሚገኙ ወንድሞች የሚያወሱ እምነት የሚያጠናክሩ ዘገባዎችን ይዘዋል።

^ [2] (አንቀጽ 12) መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ሥራ የተመደቡት ኪሩቤል ምን ያህል እንደነበሩ የሚናገረው ነገር የለም።