በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በመዝሙር 144:12-15 ላይ ያለው ሐሳብ የሚናገረው ስለ አምላክ ሕዝቦች ነው ወይስ በቁጥር 11 ላይ ስለተጠቀሱት ክፉ የሆኑ የባዕድ አገር ሰዎች?

የዕብራይስጡ አገላለጽ በሁለቱም መንገድ ሊተረጎም ይችላል። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ከዚህ በታች የቀረቡት ነጥቦች የጥቅሱን ትክክለኛ ሐሳብ ለመረዳት ያስችሉናል፦

  1. የመዝሙሩ አውድ። ቁጥር 12 የሚጀምረው “ያን ጊዜ” ብሎ ነው፤ ይህም ከቁጥር 12 እስከ 14 ላይ የተጠቀሱትን በረከቶች የሚያገኙት፣ በቁጥር 11 ላይ ከክፉዎች ‘እንዲታደጋቸውና እንዲያድናቸው’ አምላክን የለመኑት ጻድቃን መሆናቸውን ያመለክታል። ቁጥር 15ም ይህን ሐሳብ ይደግፋል፤ በዚያ ጥቅስ ላይ “ደስተኛ” እንደሆነ ተደርጎ ሁለት ጊዜ የተገለጸው “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ” ነው።

  2. ይህ አተረጓጎም አምላክ ታማኝ ሕዝቦቹን እንደሚባርካቸው የሚገልጽ ተስፋ ከያዙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ይስማማል። መዝሙር 144 አምላክ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው ከታደጋቸው በኋላ ደስተኛና ባለጸጋ እንዲሆኑ በማድረግ እንደሚባርካቸው መዝሙራዊው ዳዊት ያለውን አስተማማኝ ተስፋ የሚገልጽ ነው። (ዘሌ. 26:9, 10፤ ዘዳ. 7:13፤ መዝ. 128:1-6) ለምሳሌ ያህል፣ ዘዳግም 28:4 “የሆድህ ፍሬ፣ የመሬትህ ፍሬ፣ የቤት እንስሳህ ግልገል፣ ጥጃህና የበግህ ግልገል የተባረከ ይሆናል” በማለት ይናገራል። በእርግጥም በዳዊት ልጅ በሰለሞን የግዛት ዘመን ብሔሩ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ ሰላምና ብልጽግና አግኝቶ ነበር። ከዚህም ሌላ፣ የሰለሞን ግዛት አንዳንድ ገጽታዎች በመሲሑ አገዛዝ ወቅት የሚኖሩ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።—1 ነገ. 4:20, 21፤ መዝ. 72:1-20

ሐሳቡን ለማጠቃለል ያህል፣ በመዝሙር 144:12-15 ላይ ያለው ሐሳብ የአምላክ ሕዝቦችን እንደሚያመለክት መረዳታችን፣ ሙሉው መዝሙር የሚያወሳው የይሖዋ አገልጋዮች ለረጅም ጊዜ በናፍቆት ሲጠባበቁት ስለኖሩት ተስፋ እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን ያደርጋል፤ ይህም ተስፋ በክፉዎች ላይ መለኮታዊ የጥፋት ፍርድ ከተፈጸመ በኋላ ጻድቃን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና አግኝተው እንደሚኖሩ የሚገልጽ ነው።—መዝ. 37:10, 11