በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘው መንገድ

እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘው መንገድ

“ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ።”—ዮሐ. 8:36

መዝሙሮች፦ 54, 36

1, 2. (ሀ) ሰዎች ነፃነት ለማግኘት እንደሚታገሉ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) እነዚህ ትግሎች ምን ውጤት አስገኝተዋል?

በዛሬው ጊዜ ስለ እኩልነት፣ ስለ መብትና ስለ ነፃነት ብዙ ሲነገር እንሰማለን። በበርካታ የዓለም ክፍሎች ያሉ ሰዎች ከጭቆና፣ ከአድልዎና ከድህነት ነፃ መውጣት ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ የመናገርና የመምረጥ እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ነፃነት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። በእርግጥም፣ የፈለጉትን የማድረግ ወይም በፈለጉት መንገድ ሕይወታቸውን የመምራት ነፃነት በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ጉዳይ ይመስላል።

2 ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሞክሩት ግን በምን መንገድ ነው? ከማኅበራዊና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብዙዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲሉ ተቃውሞ ያሰማሉ፤ ሰልፍ ይወጣሉ፤ ዓመፅ ያነሳሳሉ ብሎም አብዮት ያካሂዳሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አካሄድ የታለመለትን ግብ ማሳካት ችሏል? በፍጹም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ለብዙ መከራና ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል። ይህም ንጉሥ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት የጻፈውን “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው።—መክ. 8:9

3. እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

3 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት የሚያስችለውን ቁልፍ ተናግሯል። ያዕቆብ “ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው [በሚያደርገው] ነገር ደስተኛ ይሆናል” ሲል ጽፏል። (ያዕ. 1:25) የዚህ ፍጹም ሕግ ምንጭ የሆነው ይሖዋ፣ የሰው ልጆች እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት ምን እንደሚያስፈልጋቸው ከማንም በተሻለ ያውቃል። ደግሞም ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ ሰጥቷቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል እውነተኛ ነፃነት ይገኝበታል።

ሰዎች እውነተኛ ነፃነት የነበራቸው መቼ ነው?

4. አዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ነፃነት ነበራቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 የዘፍጥረትን መጽሐፍ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ስናነብ፣ አዳምና ሔዋን በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የሚመኙት ዓይነት ነፃነት እንደነበራቸው ይኸውም ከድህነት፣ ከፍርሃትና ከጭቆና ነፃ እንደነበሩ እንገነዘባለን። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ስለ ምግብም ሆነ ስለ ሥራ ፈጽሞ አይጨነቁም ነበር፤ ከሕመምና ከሞት ስጋትም ቢሆን ነፃ ነበሩ። (ዘፍ. 1:27-29፤ 2:8, 9, 15) ይህ ሲባል ግን አዳምና ሔዋን ገደብ የሌለው ነፃነት ነበራቸው ማለት ነው? እስቲ ይህን ጉዳይ እንመርምር።

5. ብዙዎች ከሚያስቡት በተለየ መልኩ ሰዎች ነፃነት እንዲኖራቸው ምን ያስፈልጋል?

5 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች፣ አንድ ሰው እውነተኛ ነፃነት አለው የሚባለው ድርጊቱ ስለሚያስከትለው ውጤት ሳይጨነቅ የፈለገውን ሁሉ ማድረግ ከቻለ ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ነፃነት ማለት “የመምረጥና የመረጡትን ነገር የማድረግ ችሎታ” እንደሆነ ይገልጻል። ሆኖም የሚከተለውን ተጨማሪ ማብራሪያም ይሰጣል፦ “ከሕግ አንጻር ሲታይ ሰዎች ነፃ ናቸው የሚባለው ማኅበረሰቡ ፍትሐዊ ያልሆነ፣ አላስፈላጊ ወይም ምክንያታዊነት የጎደለው ገደብ እስካልጣለባቸው ድረስ ነው።” ይህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ነፃነት እንዲኖራቸው፣ የተወሰኑ ገደቦች እንደሚያስፈልጉ ይጠቁማል። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘ፍትሐዊ፣ አስፈላጊና ምክንያታዊ የሚባሉት ገደቦች የትኞቹ እንደሆኑ የመወሰን መብት ያለው ማን ነው?’ የሚል ነው።

6. (ሀ) ገደብ የለሽ ነፃነት ያለው ይሖዋ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የሰው ልጆች ምን ዓይነት ነፃነት አላቸው? ይህ የሆነውስ ለምንድን ነው?

6 ከነፃነት ጋር በተያያዘ ልንዘነጋው የማይገባ አንድ ወሳኝ ነጥብ አለ፦ ገደብ የለሽ ነፃነት ያለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ስለሆነ ነው። (1 ጢሞ. 1:17፤ ራእይ 4:11) ንጉሥ ዳዊት፣ ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን ልዩና የላቀ ቦታ ግሩም አድርጎ ገልጾታል። (1 ዜና መዋዕል 29:11, 12ን አንብብ።) በተቃራኒው ግን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ፍጥረታት በሙሉ ያላቸው ነፃነት አንጻራዊ ነው። እነዚህ ፍጥረታት ፍትሐዊ፣ አስፈላጊና ምክንያታዊ የሚባሉት ገደቦች የትኞቹ እንደሆኑ የመወሰን ሥልጣን ያለው ይሖዋ አምላክ ብቻ እንደሆነ አምነው መቀበል አለባቸው። ደግሞም ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ሲፈጥር እንዲህ ዓይነት ገደቦችን አስቀምጧል።

7. የተፈጥሯችን ክፍል የሆኑና ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ አንዳንድ ተግባሮች የትኞቹ ናቸው?

7 አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ነፃነት የነበራቸው ቢሆንም አንዳንድ ገደቦችም ተጥለውባቸው ነበር። በእርግጥ አንዳንዶቹ ገደቦች የተፈጥሯቸው ክፍል በመሆናቸው እነዚህን ገደቦች ማክበር የተለየ ጥረት የሚጠይቅ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በሕይወት ለመቀጠል ከፈለጉ መተንፈስ፣ መብላት፣ መተኛትና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። ይህ መሆኑ ታዲያ ነፃነታቸውን ይገድበዋል? በፍጹም፤ ምክንያቱም ይሖዋ የፈጠራቸው እነዚህን ነገሮች በማከናወን ደስታና እርካታ እንዲያገኙ አድርጎ ነው። (መዝ. 104:14, 15፤ መክ. 3:12, 13) ንጹሕ አየር ሲተነፍስ፣ የሚወደውን ምግብ ሲበላ አሊያም ጥሩ እንቅልፍ ተኝቶ ሲነሳ ደስ የማይለው ማን አለ? ለመኖር አስፈላጊ የሆኑት እነዚህ ነገሮች ነፃነታችንን እንደገደቡት ሳይሰማን ደስ እያለን እናደርጋቸዋለን። አዳምና ሔዋንም ቢሆኑ እንዲህ ይሰማቸው እንደነበረ አያጠራጥርም።

8. አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምን ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር? ለምንስ?

8 ይሖዋ፣ ምድርን እንዲሞሏትና እንዲንከባከቧት አዳምንና ሔዋንን አዟቸው ነበር። (ዘፍ. 1:28) ይህ ትእዛዝ ነፃነታቸውን የሚገድብ ነበር? በጭራሽ! ይሖዋ ይህን መመሪያ የሰጣቸው፣ ምድርን ገነት ለማድረግና ፍጹም በሆኑ የሰው ልጆች ለመሙላት ካለው ዓላማ ጋር በተያያዘ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ስለፈለገ ነው። (ኢሳ. 45:18) በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ላለማግባት፣ ካገቡ ደግሞ ልጅ ላለመውለድ ቢወስኑ ውሳኔያቸው ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ማግባትና ልጆችን ማሳደግ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያስከትል ቢሆንም አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። (1 ቆሮ. 7:36-38) ለምን? ምክንያቱም ሰዎች በተፈጥሯቸው እነዚህን ነገሮች በማድረግ ደስታና እርካታ ያገኛሉ። (መዝ. 127:3) አዳምና ሔዋንም ቢሆኑ ይሖዋ የሰጣቸውን ትእዛዝ ቢያከብሩ ኖሮ በትዳርና በቤተሰብ ሕይወታቸው እየተደሰቱ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኙ ነበር።

የሰው ልጅ እውነተኛ ነፃነት ያጣው እንዴት ነው?

9. በዘፍጥረት 2:17 ላይ የሚገኘው የአምላክ ትእዛዝ ፍትሐዊ ያልሆነ፣ አላስፈላጊ ወይም ምክንያታዊነት የጎደለው አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

9 ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ሌላም ትእዛዝ የሰጣቸው ሲሆን ይህን ትእዛዝ መተላለፍ የሚያስከትለውን ቅጣትም በግልጽ ነግሯቸዋል፤ አምላክ “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ . . . አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 2:17) ይህ ትእዛዝ ፍትሐዊ ያልሆነ፣ አላስፈላጊ ወይም ምክንያታዊነት የጎደለው ነበር? ደግሞስ አዳምና ሔዋን ነፃነት እንዲያጡ የሚያደርግ ነበር? በፍጹም። እንዲያውም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህ ትእዛዝ ጥበብ የሚንጸባረቅበትና ምክንያታዊ እንደሆነ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “አምላክ [በዘፍጥረት 2:16, 17 ላይ] የሰጠው ትእዛዝ፣ ለሰዎች መልካም . . . የሆነውን የሚያውቀው አምላክ ብቻ ነው፤ ለሰዎች መልካም . . . ያልሆነውን የሚያውቀውም አምላክ ብቻ ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ሰዎች ‘መልካም’ የሆነውን ማግኘት ከፈለጉ በአምላክ መታመንና እሱን መታዘዝ አለባቸው። አምላክን ካልታዘዙ፣ መልካም . . . የሆነውን እና መልካም . . . ያልሆነውን በራሳቸው መወሰን ይኖርባቸዋል።” ይህ ደግሞ ሰዎች በራሳቸው ሊወጡ የማይችሉት ከባድ ኃላፊነት ነው።

አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ አስከፊ ውጤት አስከትሏል! (ከአንቀጽ 9-12⁠ን ተመልከት)

10. በመምረጥ ነፃነት እና መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር በመወሰን መብት መካከል ምን ልዩነት አለ?

10 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙዎች፣ ይሖዋ ለአዳም የሰጠውን ትእዛዝ ሲያነቡ አዳም የፈለገውን የማድረግ ነፃነት እንደተነፈገ ሆኖ ይሰማቸዋል። እንዲህ የሚሰማቸው፣ በመምረጥ ነፃነት እና መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር በመወሰን መብት መካከል ልዩነት እንዳለ ስላልተገነዘቡ ሊሆን ይችላል። አዳምና ሔዋን፣ አምላክን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ የመምረጥ ነፃነት ነበራቸው። ይሁንና የትኛው መልካም፣ የትኛው ደግሞ ክፉ እንደሆነ የመወሰን መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ በኤደን ገነት ውስጥ የነበረው “የመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” የሚያመለክተውም ይህን ነበር። (ዘፍ. 2:9) እውነቱን ለመናገር እኛ የሰው ልጆች ምንጊዜም ጥሩ ውጤት የሚያስገኙ ውሳኔዎችን ማድረግ አንችልም፤ የምናደርጋቸው ምርጫዎች ምን ውጤት እንደሚያስከትሉ ማወቅ የምንችለውም ቢሆን ሁልጊዜ አይደለም። ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው ያደረጓቸው ምርጫዎች ወይም ውሳኔዎች ብዙውን ጊዜ መከራ፣ ችግር ወይም አስከፊ ውጤት ሲያስከትሉ የምናየው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 14:12) የሰው ልጆች የአቅም ገደብ ያለባቸው መሆኑ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይሖዋ ከዛፉ ፍሬ እንዳይበሉ ለአዳምና ለሔዋን ትእዛዝ የሰጣቸው፣ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት እሱን መታዘዝ እንዳለባቸው ለማስተማር ነው። እንዴት? አዳምና ሔዋንስ ምን አደረጉ?

11, 12. አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ አስከፊ ውጤት ያስከተለው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

11 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክን ላለመታዘዝ መረጡ። ሰይጣን፣ ከዛፉ ቢበሉ ‘ዓይኖቻቸው እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደሚሆኑ’ የተናገረው ሐሳብ ሔዋንን አጓጓት። (ዘፍ. 3:5) ታዲያ አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ ውሎ አድሮ የበለጠ ነፃነት አስገኘላቸው? በጭራሽ። የሚያሳዝነው፣ አምላክን አለመታዘዛቸው ሰይጣን እንዳለው ጥቅም አላስገኘላቸውም። እንዲያውም የይሖዋን ትእዛዝ መጣሳቸውና የራሳቸውን አካሄድ መከተላቸው አስከፊ ውጤት አስከትሏል። (ዘፍ. 3:16-19) ለምን? ይሖዋ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በራሳቸው የመወሰንን ነፃነት ለሰዎች ስላልሰጣቸው ነው።—ምሳሌ 20:24ንና የግርጌ ማስታወሻውን እንዲሁም ኤርምያስ 10:23ን አንብብ።

12 ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት አንድን የአውሮፕላን አብራሪ እንውሰድ። አብራሪው ወደሚሄድበት ቦታ በሰላም መድረስ እንዲችል አስቀድሞ የተሰጠውን የበረራ አቅጣጫ መከተል ይኖርበታል። አብራሪው በአውሮፕላኑ ውስጥ ያሉትን አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያዎች መጠቀሙና የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በበረራው ወቅት የሚሰጡትን መመሪያ መከተሉ የታሰበለት ቦታ ላይ ለመድረስ ያስችለዋል። ሆኖም አብራሪው፣ የሚሰጠውን መመሪያ ችላ ብሎ በፈለገው አቅጣጫ ለመብረር ቢወስን ውጤቱ አስከፊ ሊሆን ይችላል። አዳምና ሔዋንም ልክ እንደዚህ አብራሪ በራሳቸው መንገድ ለመሄድ መርጠዋል። አምላክ የሰጣቸውን መመሪያ ለመከተል አሻፈረን ብለዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? አብራሪው የራሱን መንገድ ቢከተል አውሮፕላኑ እንደሚከሰከስ ሁሉ አዳምና ሔዋን የወሰዱት እርምጃም በራሳቸውም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ ኃጢአትና ሞትን አስከትሏል። (ሮም 5:12) አዳምና ሔዋን ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ያደረጉት ጥረት የነበራቸውን እውነተኛ ነፃነት አሳጥቷቸዋል።

እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

13, 14. እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 ብዙዎች የበለጠ ነፃነት ባገኙ መጠን ሕይወታቸውም ይበልጥ እንደሚሻሻል ይሰማቸዋል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ገደብ የሌለው ነፃነት በሁለት በኩል እንደተሳለ ሰይፍ ነው። ነፃነት በርካታ ጥቅሞች እንደሚያስገኝ አይካድም፤ ሆኖም ምንም ዓይነት ገደብ በሌለበት ዓለም ላይ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰቡ እንኳ ይዘገንናል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ ‘በየትኛውም የተደራጀ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉት ሕግጋት የተወሳሰቡ ናቸው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሕግጋት የተዋቀሩት ሰዎች ከተቀመጠላቸው ገደብ ሳያልፉ ነፃነታቸውን መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ነው።’ በእርግጥም ‘ሕግጋቱ የተወሳሰቡ ናቸው’ መባሉ የሚያስገርም አይደለም። የሰው ልጆች ያወጧቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕግጋት ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ በዚያ ላይ ደግሞ እነዚህን ሕግጋት ለመተርጎምና ለማስፈጸም እጅግ ብዙ የሕግ ባለሙያዎችና ዳኞች ያስፈልጋሉ።

14 ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የሚቻልበትን ቀላል መንገድ ጠቁሞናል። እንዲህ ብሏል፦ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።” (ዮሐ. 8:31, 32) ኢየሱስ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ነገሮችን ጠቅሷል፦ የመጀመሪያው እሱ ያስተማረውን እውነት መቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ነው። እነዚህን ነገሮች ማድረግ እውነተኛ ነፃነት ያስገኛል። ይሁንና ነፃ የምንወጣው ከምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጥቶናል፦ “ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው። . . . ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ።”—ዮሐ. 8:34, 36

15. ኢየሱስ እውነተኛ ነፃነት ይሰጠናል የምንለው ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሚሰጣቸው ቃል የገባው ነፃነት፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ብዙዎች ከሚመኙት ነፃነት እጅግ የላቀ እንደሆነ አያጠያይቅም። ኢየሱስ “ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ” ሲል ከሁሉ ከከፋው ባርነትና ጭቆና ይኸውም “የኃጢአት ባሪያ” ከመሆን ነፃ ስለመውጣት መናገሩ ነበር። ኃጢአት፣ መጥፎ ነገር መፈጸም እንዲቀናን የሚያደርገን ከመሆኑም ሌላ ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር እንዳናደርግ አሊያም የአቅማችንን ያህል እንዳንሠራ ያግደናል። በመሆኑም የኃጢአት ባሪያዎች ነን ማለት ይቻላል፤ ይህ ደግሞ ብስጭት፣ ሥቃይ፣ መከራ በመጨረሻም ሞት ያስከትልብናል። (ሮም 6:23) ሐዋርያው ጳውሎስም የኃጢአት ባሪያ መሆን የሚያስከትለው ሥቃይ በጥልቅ ተሰምቶት ነበር። (ሮም 7:21-25ን አንብብ።) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የነበራቸው ዓይነት እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የምንችለው እንደ ካቴና ጠፍሮ ከያዘን ከኃጢአት ነፃ ስንወጣ ብቻ ነው።

16. እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኝልን ምንድን ነው?

16 ኢየሱስ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ” ማለቱ፣ እሱ ነፃ እንዲያወጣን ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ ብቃቶች እንዳሉ ይጠቁማል። ሕይወታችንን ለይሖዋ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን ክደናል፤ እንዲሁም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ከሚያስከትላቸው ገደቦች ሳንወጣ ለመኖር መርጠናል። (ማቴ. 16:24) ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ስንሆን እሱ ቃል በገባው መሠረት እውነተኛ ነፃነት እናገኛለን።

17. (ሀ) እርካታና ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችለን ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

17 የኢየሱስን ትእዛዞች ማክበራችንና የእሱ ደቀ መዛሙርት መሆናችን እርካታና ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት ያስችለናል። በተጨማሪም ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ሙሉ በሙሉ ነፃ ለመውጣት አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ሮም 8:1, 2, 20, 21ን አንብብ።) የሚቀጥለው ርዕስ አሁን ያለንን ነፃነት በአግባቡ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል፤ ነፃነታችንን በአግባቡ መጠቀማችን የእውነተኛ ነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለዘላለም ለማክበር ያስችለናል።