እናንት ወጣቶች፣ ትኩረታችሁ ያረፈው በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ነው?
“የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።”—ምሳሌ 16:3
1-3. (ሀ) ሁሉም ወጣቶች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? በምሳሌ አስረዳ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ክርስቲያን ወጣቶች ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት ምን ይረዳቸዋል?
ትልቅ ቦታ በሚሰጠው አንድ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ስትል ራቅ ወዳለ ከተማ ለመጓዝ አስበሃል እንበል። ያሰብክበት ለመድረስ ለረጅም ሰዓት በአውቶቡስ መጓዝ ያስፈልግሃል። ወደ አውቶቡስ መናኸሪያው ስትደርስ ቦታው በተሳፋሪዎችና በአውቶቡሶች ተጨናንቋል። ሁኔታው ግራ ቢያጋባህም የት ለመሄድ እንደምትፈልግና በየትኛው አውቶቡስ ላይ መሳፈር እንዳለብህ አስቀድመህ ስለወሰንክ ትረጋጋለህ። ወዴት እንደሚሄድ ያላወቅከው አውቶብስ ውስጥ ዘለህ መግባት የፈለግክበት ቦታ ለመድረስ አያስችልህም።
2 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ሁኔታም በአውቶቡስ መናኸሪያ ውስጥ ካሉ ተሳፋሪዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወጣቶች ረጅም የሕይወት ጉዞ ይጠብቃቸዋል። በፊታቸው የተደቀኑት ውሳኔዎችና የሚቀርቡላቸው አጋጣሚዎች አንዳንድ ጊዜ ግራ ሊያጋቧቸው ይችላሉ። እናንት ወጣቶች፣ በሕይወታችሁ ምን ማድረግ እንደምትፈልጉ ግብ ካወጣችሁ ትክክለኛውን ምርጫ ማድረግ ቀላል ይሆንላችኋል። ታዲያ በሕይወታችሁ ውስጥ የትኛውን አቅጣጫ ብትከተሉ ይሻላል?
3 ይህ ርዕስ፣ ይሖዋን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲመሩ ወጣቶችን ምሳሌ 16:3ን አንብብ።
በማበረታታት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። እንዲህ ዓይነት ሕይወት መምራት የምትችሉት በሁሉም የሕይወታችሁ ዘርፎች ይሖዋ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ነው፤ ይህም ከትምህርት፣ ከሥራ፣ ትዳር ከመመሥረትና ልጆች ከመውለድ ጋር በተያያዘ የምታደርጉትን ውሳኔ ይጨምራል። ከዚህም ሌላ ይሖዋን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት ሲባል መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግን ያካትታል። አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመሩ ወጣቶች በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ይሖዋ እንደሚረዳቸው መተማመን ይችላሉ።—መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት የሚያስፈልጋችሁ ለምንድን ነው?
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
4 ወጣቶች ገና በልጅነታቸው መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣታቸው የጥበብ አካሄድ ነው። ለምን? ሦስት ምክንያቶችን እንመለከታለን። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምክንያቶች፣ አንድ ወጣት መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣጣሩ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማጠናከር እንደሚያስችለው ያሳያሉ፤ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ያለውን ጥቅም ያጎላል።
5. መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
5 መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት፣ ይሖዋ ላሳየን ፍቅርና ላደረገልን ነገሮች አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ያለን ፍላጎት ነው። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋ ምስጋና ማቅረብ ጥሩ ነው፤ . . . ይሖዋ ሆይ፣ ባከናወንካቸው ነገሮች እንድደሰት አድርገኸኛልና፤ ከእጅህ ሥራዎች የተነሳ እልል እላለሁ።” (መዝ. 92:1, 4) ይሖዋ ያደረገልህን ነገሮች ሁሉ እስቲ መለስ ብለህ አስብ። ሕይወትህ፣ ይሖዋን ማወቅና ስለ እሱ እውነቱን መማር መቻልህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጉባኤው እንዲሁም በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋህ ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትህ ከአምላክ ላገኘሃቸው ለእነዚህ በረከቶች አመስጋኝነትህን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጥሃል፤ ይህ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል።
6. (ሀ) መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት ከይሖዋ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? (ለ) ከልጅነት ጀምሮ የትኞቹን ግቦች ማውጣት ይቻላል?
6 ሁለተኛው ምክንያት፣ መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግህ መልካም ሥራ በማከናወን ረገድ በይሖዋ ዘንድ ጥሩ ስም እያስመዘገብክ ለመሄድ የሚያስችልህ መሆኑ ነው። ይህም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም” በማለት ቃል ገብቷል። (ዕብ. 6:10) መንፈሳዊ ግቦችን ለማውጣት ዕድሜያችሁ እንዳልደረሰ አድርጋችሁ ፈጽሞ አታስቡ። ክሪስቲን የታማኝ የይሖዋ ምሥክሮችን የሕይወት ታሪክ አዘውትራ ለማንበብ ግብ ያወጣችው ገና የአሥር ዓመት ልጅ እያለች ነበር። ቶቢ ደግሞ ከመጠመቁ በፊት ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቦ ለመጨረስ ግብ ያወጣው በ12 ዓመቱ ነው። ማክሲምና እህቱ ኖኤሚ ሲጠመቁ እሱ 11 ኖኤሚ ደግሞ 10 ዓመቷ ነበር። ሁለቱም ቤቴል የመግባት ግብ ያወጡ ሲሆን ግባቸው ላይ ትኩረት ለማድረግ እንዲረዳቸው ሲሉ የቤቴል ማመልከቻ ቅጽ ግድግዳቸው ላይ ለጥፈው ነበር። አንተስ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ግቦችን ለማውጣትና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ለምን ጥረት አታደርግም?—ፊልጵስዩስ 1:10, 11ን አንብብ።
7, 8. (ሀ) ግብ ማውጣት ውሳኔ ማድረግ ቀላል እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው? (ለ) አንዲት እህት በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለች ዩኒቨርሲቲ ላለመግባት የወሰነችው ለምንድን ነው?
7 በልጅነት ግብ ማውጣት አስፈላጊ የሆነበት ሦስተኛው ምክንያት ምንድን ነው? አንድ ወጣት ግብ ካለው በሕይወቱ ውስጥ ውሳኔ ማድረግ ቀላል ይሆንለታል። ወጣቶች ከትምህርት፣ ከሥራና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ውሳኔ ማድረግ፣ መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆነህ ትክክለኛውን መንገድ ከመምረጥ ጋር ይመሳሰላል። የት መድረስ እንደምትፈልግ እስካወቅህ ድረስ ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ ምንም አያስቸግርህም። በተመሳሳይም ግልጽ የሆኑ ግቦች ካሉህ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። ምሳሌ 21:5 “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” ይላል። በልጅነትህ ጥሩ ግቦችን ማውጣትህ በሕይወትህ ይበልጥ ስኬታማ እንድትሆን ይረዳሃል። ደማሪስ የዚህን እውነተኝነት በሕይወቷ ተመልክታለች፤ ይህች እህት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለች ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ ማድረግ አስፈልጓት ነበር።
8 ደማሪስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በከፍተኛ ውጤት ነበር። በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሕግ ለማጥናት የሚያስችል ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም እሷ ግን ባንክ ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ብቻ ለመሥራት ወሰነች። ይህን ያደረገችው ለምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “አቅኚ ሆኜ ለማገልገል የወሰንኩት ገና በልጅነቴ ነበር። በሳምንት ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ብቻ መሥራቴ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ይረዳኛል። በሕግ መስክ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ብይዝ ጥሩ ክፍያ እንደማገኝ የታወቀ ነው፤ ሆኖም የተወሰነ ሰዓት ብቻ የምሠራው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንብኛል።” ደማሪስ አቅኚ ሆና ማገልገል ከጀመረች 20 ዓመት አልፏታል። ታዲያ በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለች ያወጣችው ግብና ያደረገችው ውሳኔ ትክክል እንደሆነ ይሰማታል? እንዲህ ብላለች፦ “በምሠራበት ባንክ ውስጥ ከጠበቆች ጋር ብዙ ጊዜ እገናኛለሁ። ሕግ ባጠና ኖሮ የምሠራው እነዚህ ሰዎች የሚሠሩትን ሥራ ነበር። ብዙዎቹ በሥራቸው ጨርሶ አይደሰቱም። አቅኚ ለመሆን መወሰኔ፣ ትልቅ ደረጃ ላይ በሚያደርስ የሥራ መስክ ብሰማራ ኖሮ የሚያጋጥመኝን ብስጭት ያስቀረልኝ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ አገልግሎት በርካታ አስደሳች ዓመታት ለማሳለፍ ረድቶኛል።”
9. በጉባኤያችን ያሉ ወጣቶች ልባዊ አድናቆት ሊቸራቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
9 በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከልባችን እናደንቃቸዋለን። እነዚህ ወጣቶች የሚያደርጉትን ሁሉ ለይሖዋ አደራ በመስጠት በቲኦክራሲያዊ ግቦች ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመራሉ። ትምህርትን፣ ሥራን፣ ትዳርንና ልጆች መውለድን ጨምሮ በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ሁሉ የይሖዋን መመሪያዎች ይከተላሉ፤ በሕይወታቸውም ደስተኞች ናቸው። ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በይሖዋ ዓይን ውድ ናቸው፤ ይሖዋ በጣም የሚወዳቸው ከመሆኑም ሌላ ጥበቃው፣ አመራሩና በረከቱ አይለያቸውም።
ምሥክርነት ለመስጠት በሚገባ ተዘጋጁ
10. (ሀ) ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
10 ይሖዋን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመራ ወጣት ለአገልግሎት ቅድሚያ ይሰጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ “አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት” ብሏል። (ማር. 13:10) የስብከቱ ሥራ በጣም አጣዳፊ ከመሆኑ አንጻር በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጠው እንደሚገባ አያጠራጥርም። አንተስ በአገልግሎት ይበልጥ አዘውትረህ የመካፈል ግብ ልታወጣ ትችላለህ? በአቅኚነት ማገልገል ትችል ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ በስብከቱ ሥራ መካፈል ያን ያህል የማያስደስትህ ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ይበልጥ ውጤታማ ሰባኪ መሆን የምትችለውስ እንዴት ነው? ሁለት ነገሮች ሊረዱህ ይችላሉ፦ በሚገባ ተዘጋጅ እንዲሁም የምታውቀውን ለሌሎች ለመናገር በምታደርገው ጥረት ተስፋ አትቁረጥ። እነዚህን እርምጃዎች መውሰድህ በስብከቱ ሥራ ላይ ያልጠበቅከውን ደስታ ለማግኘት ያስችልሃል።
11, 12. (ሀ) ወጣቶች ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ወጣት በትምህርት ቤት ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችለውን አጋጣሚ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
11 ለስብከቱ ሥራ በሚገባ ለመዘጋጀት የሚረዳህ የመጀመሪያው እርምጃ፣ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ብዙ ጊዜ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ለማግኘት መሞከር ነው። “በአምላክ የምታምነው ለምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወጣቶች የዚህን ጥያቄ መልስ ለመዘጋጀት የሚረዷቸውን ርዕሶች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ ማግኘት ይችላሉ። ድረ ገጻችን ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ወጣቶች በሚለው ሥር “አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?” የሚል የመልመጃ ሣጥን ይገኛል። የመልመጃ ሣጥኑ የራስህን መልስ እንድታዘጋጅ ይረዳሃል። የምታምንበትን ነገር ለማስረዳት ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ሦስት ጥቅሶች ይኸውም ዕብራውያን 3:4ን፣ ሮም 1:20ን እና መዝሙር 139:14ን በሣጥኑ ውስጥ ታገኛለህ። እንደነዚህ ያሉትን የመልመጃ ሣጥኖች በመጠቀም ለተለያዩ ጥያቄዎች የምትሰጠውን መልስ መዘጋጀት ትችላለህ።—1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።
12 አጋጣሚውን በምታገኝበት ጊዜ፣ አብረውህ የሚማሩት ልጆች jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ራሳቸው ቡጢ ሳትሰነዝር ጉልበተኞችን ማሸነፍ የተባለውን የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን እንዲመለከቱ ለሁሉም ተማሪዎች የቤት ሥራ ሰጠቻቸው። ሉካ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት በመቻሉ በጣም ተደስቷል።
እንዲመለከቱ አበረታታቸው። ሉካ የተባለ ወጣት ያደረገው ይህንን ነበር። በአንድ ወቅት የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው ያተኮረው በተለያዩ ሃይማኖቶች ላይ ነበር፤ ሉካ የመማሪያ መጽሐፋቸው ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ ሐሳብ እንደያዘ አስተዋለ። መጀመሪያ ላይ ፍርሃት ቢሰማውም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ትክክለኛውን ሐሳብ ለመናገር ዕድል እንድትሰጠው አስተማሪዋን ጠየቃት፤ እሷም ፈቀደችለት። ሉካም የሚያምንባቸውን ነገሮች ለክፍሉ ተማሪዎች ከማስረዳት ባለፈ ድረ ገጻችንን አሳያቸው። ከዚያም መምህሯ፣13. አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?
13 ግብህ ላይ ለመድረስ የምትከተለው ጎዳና አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ቢሆንብህም እንኳ ተስፋ አትቁረጥ። (2 ጢሞ. 4:2) ችግሮች ቢያጋጥሙህም ግብህ ላይ ለመድረስ ምንጊዜም ጥረት አድርግ። ካታሪና የ17 ዓመት ወጣት እያለች አብረዋት ለሚሠሩት ሰዎች በሙሉ ለመመሥከር ግብ አውጥታ ነበር። ከሥራ ባልደረቦቿ አንዱ በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢሰድባትም ካታሪና በፍርሃት ተሸንፋ መስበኳን አላቆመችም። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም መልካም ምግባር ማሳየቷ ሃንስ የተባለ ሌላ የሥራ ባልደረባዋን አስገረመው። በዚህም ምክንያት ጽሑፎቻችንን ማንበብ የጀመረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቶ ተጠመቀ። ካታሪና ወደ ሌላ አካባቢ ስለሄደች ይህን ሁሉ አላወቀችም። ከ13 ዓመታት በኋላ ከቤተሰቧ ጋር በጉባኤ ስብሰባ ላይ እያለች የሕዝብ ተናጋሪው ሃንስ እንደሆነ ስታውቅ ምን ያህል እንደተደሰተች መገመት እንችላለን! ካታሪና ለሥራ ባልደረቦቿ ለመስበክ ያወጣችው ግብ ላይ ለመድረስ በጽናት መሥራቷ ምንኛ ግሩም ውጤት አስገኝቷል!
ትኩረታችሁ እንዳይከፋፈል ተጠንቀቁ
14, 15. (ሀ) ወጣቶች እኩዮቻቸው ተጽዕኖ ሲያደርጉባቸው ሊዘነጉት የማይገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ወጣቶች የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ሕይወታችሁ ይሖዋን በማስደሰትና በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ያተኮረ እንዲሆን የማድረግን አስፈላጊነት ተመልክተናል። ይሁንና እኩዮቻችሁ በመዝናናትና ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ያተኮረ ሕይወት ሲመሩ ትመለከቱ ይሆናል፤ ምናልባት እናንተም ከእነሱ ጋር ጊዜ እንድታሳልፉ ይጋብዟችሁ ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ፣ ግባችሁ ላይ ለመድረስ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆናችሁ ማሳየት ይጠበቅባችኋል። በመሆኑም የእኩዮቻችሁ ተጽዕኖ ትኩረታችሁን እንዲከፋፍለው አትፍቀዱ። በአውቶቡስ ስለመጓዝ የጠቀስነውን ምሳሌ እስቲ እንደገና እንመልከት፤ በአንድ አውቶቡስ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች አስደሳች ጊዜ እያሳለፉ
እንዳሉ ይሰማን ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ስለተሰማን ብቻ አውቶቡሱ የሚሄደው እኛ ወደምንፈልገው አቅጣጫ ባይሆንም እንኳ በዚያ አውቶቡስ ላይ እንሳፈራለን? እንደማንሳፈር የታወቀ ነው።15 ወጣቶች የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ትክክል ያልሆነውን ነገር ለማድረግ የምትፈተኑበት ሁኔታ ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ ትችላላችሁ። (ምሳሌ 22:3) ሌሎችን ተከትላችሁ መጥፎ ምግባር መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ አስቡ። (ገላ. 6:7) በተጨማሪም የሌሎችን ምክር መስማት እንደሚያስፈልጋችሁ አምናችሁ ተቀበሉ። ትሕትና፣ ወላጆቻችሁም ሆኑ በጉባኤ ውስጥ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጧችሁን ምክር መቀበል ቀላል እንዲሆንላችሁ ያደርጋል።—1 ጴጥሮስ 5:5, 6ን አንብብ።
16. ትሕትና ማሳየት ያለውን ጥቅም የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
16 ክሪስቶፍ ትሑት መሆኑ የተሰጠውን መልካም ምክር እንዲቀበል አነሳስቶታል። ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ወደ አንድ የስፖርት ማዕከል አዘውትሮ መሄድ ጀመረ። በዚያ ያገኛቸው አንዳንድ ወጣቶች የስፖርት ቡድናቸው አባል እንዲሆን ጎተጎቱት። ክሪስቶፍ ስለ ጉዳዩ አንድን የጉባኤ ሽማግሌ አማከረ፤ ሽማግሌውም ክሪስቶፍን ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የቡድኑ አባል መሆኑ ሊያስከትላቸው የሚችሉ አንዳንድ አደጋዎችን እንዲያጤን አሳሰበው፤ ለምሳሌ የፉክክር መንፈስ ሊጋባበት እንደሚችል ጠቆመው። ይሁንና ክሪስቶፍ ቡድኑን ለመቀላቀል ወሰነ። ውሎ አድሮ ግን ይህ ስፖርት ዓመፅ የሚንጸባረቅበት ብሎም አደገኛ መሆኑን ተገነዘበ። በመሆኑም በድጋሚ ሌሎች ሽማግሌዎችን ምክር ጠየቀ፤ ሁሉም ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሰጡት። ክሪስቶፍ “ይሖዋ ጥሩ መካሪዎች ሰጥቶኛል፤ ጊዜ ቢወስድብኝም እንኳ የሰጠኝን እርዳታ ተቀብያለሁ” ብሏል። አንተስ የሚሰጥህን ጥሩ ምክር በትሕትና ትቀበላለህ?
17, 18. (ሀ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ምን እንዲያገኙ ይፈልጋል? (ለ) አንዳንድ አዋቂዎች ምን አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? ወጣቶች ይህ እንዳይደርስባቸው ምን ማድረግ ይችላሉ? አንድ ተሞክሮ ጥቀስ።
17 የአምላክ ቃል “አንተ ወጣት፣ በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፤ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ይበለው” ይላል። (መክ. 11:9) በእርግጥም ይሖዋ በወጣትነት ዘመንህ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። ደስታ ለማግኘት የሚረዳህን አንዱን መንገድ በዚህ ርዕስ ውስጥ ተመልክተናል። ይኸውም በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ዕቅድ ስታወጣና ውሳኔ ስታደርግ የይሖዋን ምክር መከተል ነው። ከልጅነትህ ጀምሮ ይህን ካደረግህ የይሖዋን አመራር፣ ጥበቃና በረከት ታገኛለህ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ግሩም ምክሮች በጥሞና አስብባቸው፤ እንዲሁም “በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር በተግባር አውል።—መክ. 12:1
18 የወጣትነት ዘመን ቶሎ ያልፋል። ዛሬ ወጣት የሆኑ ሰዎች ነገ አዋቂ ይሆናሉ። የሚያሳዝነው ብዙ አዋቂዎች በወጣትነታቸው የተሳሳተ ግብ በማሳደዳቸው አሊያም ጨርሶ ግብ ሳያወጡ በመቅረታቸው በኋላ ላይ ይቆጫሉ። በሌላ በኩል ግን በወጣትነታቸው ቲኦክራሲያዊ ግቦች ላይ ያተኮሩ ሰዎች፣ ባደረጉት ምርጫ አዋቂ ሲሆኑም መደሰታቸው አይቀርም። በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለች በስፖርት የላቀ ችሎታ የነበራት የሚርያና ሕይወት ይህን የሚያረጋግጥ ነው። ሚርያና ዊንተር ኦሎምፒክ ተብሎ በሚታወቀው ውድድር ላይ እንድትካፈል ግብዣ ቢቀርብላትም እሷ ግን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሰማራት መረጠች። ይህ ከሆነ 30 ዓመታት ቢያልፉም ሚርያና አሁንም ከባለቤቷ ጋር ሆና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈለች ነው። እንዲህ ብላለች፦ “እንደ ዝና፣ ክብር፣ ሥልጣንና ሀብት ያሉት ነገሮች ዘላቂነትም ሆነ እርባና ያላቸው ግቦች አይደሉም። አምላክን ማገልገልና ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ጥረት ማድረግ ግን የላቀና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ግብ ነው።”
19. ከልጅነት ጀምሮ መንፈሳዊ ግቦች ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት ያለውን ጥቅም ግለጽ።
19 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመቋቋም ጥረት ስለሚያደርጉና ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ስለቆረጡ ከፍተኛ አድናቆት ይገባቸዋል። ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋቸውና ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ መስጠታቸው በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ያስችላቸዋል። ከዚህም ሌላ ይህ ዓለም ትኩረታቸውን እንዳይከፋፍለው ይጠነቀቃሉ። ወጣቶች ልፋታቸው ከንቱ እንደማይሆን መተማመን ይችላሉ። አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ይደግፏቸዋል፤ ሕይወታቸውን ለይሖዋ አደራ ከሰጡ ዕቅዳቸው ሁሉ ይሳካል።