በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሾማችሁ ወንዶች—ከጢሞቴዎስ ተማሩ

የተሾማችሁ ወንዶች—ከጢሞቴዎስ ተማሩ

ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች የጉባኤ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች ሆነው ተሹመዋል። አንተም ከእነዚህ ወንድሞቻችን መካከል አንዱ ከሆንክ ይህን አዲስ የአገልግሎት መብት በማግኘትህ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም።

ይሁንና በመጠኑም ቢሆን ስጋት ሊያድርብህ ይችላል፤ ደግሞም ይህ የሚያስገርም አይደለም። የጉባኤ ሽማግሌ እንዲሆን የተሾመ ጄሰን የሚባል አንድ ወጣት “መጀመሪያ ላይ አዲሱ ኃላፊነት ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ይናገራል። ሙሴና ኤርምያስም ይሖዋ አዲስ ኃላፊነት በሰጣቸው ጊዜ ብቁ እንዳልሆኑ ተሰምቷቸው ነበር። (ዘፀ. 4:10፤ ኤር. 1:6) አንተም እንደ እነሱ የሚሰማህ ከሆነ ይህን ስሜት አሸንፈህ እድገት ማድረግህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው? ክርስቲያን ደቀ መዝሙር የሆነው ጢሞቴዎስ የተወውን ምሳሌ መመልከትህ በዚህ ረገድ ይረዳሃል።—ሥራ 16:1-3

የጢሞቴዎስን ምሳሌ ተከተል

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን ጢሞቴዎስን በጋበዘው ጊዜ ይህ ወጣት በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ጢሞቴዎስ ገና ወጣት እንደመሆኑ መጠን መጀመሪያ ላይ በራስ የመተማመን ስሜት አልነበረው ይሆናል፤ ከዚህም ሌላ አዲሱን ኃላፊነቱን ለመወጣት ፈራ ተባ ብሎ ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞ. 4:11, 12፤ 2 ጢሞ. 1:1, 2, 7) ሆኖም ከአሥር ዓመታት በኋላ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበረው ጉባኤ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ ኢየሱስ ቢፈቅድ ጢሞቴዎስን በቅርቡ ወደ እናንተ እንደምልከው ተስፋ አደርጋለሁ። . . . እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝምና።”—ፊልጵ. 2:19, 20

ጢሞቴዎስ እንዲህ ያለ ጥሩ ሽማግሌ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይህ ወጣት ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት የሚቻልባቸውን ስድስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

1. ጢሞቴዎስ ለሰዎች ከልቡ ይጨነቅ ነበር። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩት ወንድሞች፣ ጢሞቴዎስ “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ [ይጨነቃል]” ብሏቸዋል። (ፊልጵ. 2:20) በእርግጥም ጢሞቴዎስ ለሌሎች ያስብ ነበር። መንፈሳዊነታቸው ከልብ ያሳስበው የነበረ ሲሆን እነሱን ለማገልገል ሲል ራሱን ሳይቆጥብ በፈቃደኝነት ይሠራ ነበር።

አንተም፣ ተሳፋሪዎችን መጫኑ ሳይሆን እያንዳንዱ ፌርማታ ላይ በሰዓቱ መድረሱ ብቻ እንደሚያሳስበው የአውቶቡስ ሾፌር አትሁን። ዊልያም የሚባል ከ20 ዓመታት በላይ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለና ብዙዎች የሚያከብሩት አንድ ወንድም፣ አዲስ ለተሾሙ ሽማግሌዎች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ለወንድሞች ፍቅር ይኑራችሁ። ከድርጅታዊው አሠራር ይልቅ ወንድሞች በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጉ።”

2. ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ጉዳዮችን አስቀድሟል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ያደረገውን ነገር ከሌሎች ጋር ሲያነጻጽር “ሌሎቹ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵ. 2:21) ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ከሮም ሲሆን በዚያ የነበሩ ወንድሞች የግል ጉዳዮቻቸውን በማከናወን እንደተጠመዱ ታዝቦ ነበር። እነዚህ ወንድሞች መንፈሳዊ ነገሮችን በሙሉ ልባቸው አያከናውኑም ነበር። ጢሞቴዎስ ግን እንዲህ አልነበረም! ጢሞቴዎስ ምሥራቹን ለማስፋፋት አጋጣሚ በሚያገኝበት ጊዜ “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” ብሎ እንደተናገረው እንደ ኢሳይያስ ዓይነት አመለካከት እንዳለው አሳይቷል።—ኢሳ. 6:8

አንተስ፣ በግል ሕይወትህ ያሉብህን ኃላፊነቶችና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባውን ነገር ለይ። ጳውሎስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ፊልጵ. 1:10) አምላክ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ ስጥ። ሁለተኛ፣ ሕይወትህን ቀላል አድርግ። ጊዜና ጉልበት የሚሰርቁ ነገሮችን አስወግድ። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ከወጣትነት ምኞቶች ሽሽ፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ለማግኘት ተጣጣር” በማለት መክሮታል።—2 ጢሞ. 2:22

3. ጢሞቴዎስ በቅዱስ አገልግሎት በትጋት ተካፍሏል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ስለ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ “ከአባቱ ጋር እንደሚሠራ ልጅ ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከእኔ ጋር እንደ ባሪያ በማገልገል ማንነቱን እንዴት እንዳስመሠከረ ታውቃላችሁ” ብሏል። (ፊልጵ. 2:22) ጢሞቴዎስ ሰነፍ አልነበረም። ከጳውሎስ ጋር ሆኖ በትጋት ያገለገለ ሲሆን ይህም በመካከላቸው ያለውን ፍቅር አጠናክሮታል።

በዛሬው ጊዜም በአምላክ ድርጅት ውስጥ ብዙ የሚሠራ ነገር አለ። ይህ ሥራ የላቀ እርካታ የሚያስገኝ ሲሆን ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ይበልጥ ያቀራርብሃል። ስለዚህ ምንጊዜም ‘የጌታ ሥራ የበዛልህ ለመሆን’ ጥረት አድርግ።—1 ቆሮ. 15:58

4. ጢሞቴዎስ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ አውሏል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ “ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን በጥብቅ ተከትለሃል” ብሎታል። (2 ጢሞ. 3:10) ጢሞቴዎስ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ስላዋለ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ ሆኗል።—1 ቆሮ. 4:17

አንተስ አርዓያ የሚሆንህ ተሞክሮ ያለው ጓደኛ አለህ? ከሌለህ እንዲህ ያለ ወዳጅ ለማግኘት ለምን ጥረት አታደርግም? ለብዙ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ ቶም የሚባል ወንድም አዲስ ሽማግሌ ስለነበረበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ተሞክሮ ያለው አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ለእኔ ትኩረት በመስጠት ግሩም አድርጎ አሠለጠነኝ። አዘውትሬ ምክር እጠይቀው እንዲሁም ምክሩን በተግባር አውል ነበር። ይህም በራስ የመተማመን ስሜቴ እያደገ እንዲሄድ ረድቶኛል።”

5. ጢሞቴዎስ ሁልጊዜ ራሱን ያሠለጥን ነበር። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለአምላክ ማደርን ግብ አድርገህ ራስህን አሠልጥን” በማለት መክሮታል። (1 ጢሞ. 4:7) አንድ ሯጭ አሠልጣኝ ቢኖረውም እንኳ ራሱን ማሠልጠን እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አሳስቦታል፦ “ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። . . . እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።”—1 ጢሞ. 4:13-15

አንተም ብትሆን ችሎታዎችህን እያሻሻልክ መሄድ ያስፈልግሃል። መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን አታቋርጥ፤ እንዲሁም ከጉባኤ አሠራር ጋር በተያያዘ ከድርጅቱ እኩል ተጓዝ። በተጨማሪም ከልክ በላይ በራስህ አትተማመን፤ ‘ተሞክሮ ስላለኝ ጥልቀት ያለው ምርምር ባላደርግም እንኳ ማንኛውንም ነገር በትክክለኛው መንገድ ማከናወን እችላለሁ’ የሚል አስተሳሰብ አይኑርህ። ልክ እንደ ጢሞቴዎስ “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።”—1 ጢሞ. 4:16

6. ጢሞቴዎስ በይሖዋ መንፈስ ተማምኗል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ስለሚያከናውነው አገልግሎት ሲጽፍ “ይህን መልካም አደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጠብቅ” ብሎታል። (2 ጢሞ. 1:14) ጢሞቴዎስ አገልግሎቱን ለመጠበቅ ወይም በአገልግሎቱ ለመጽናት እንዲችል የአምላክ መንፈስ በሚሰጠው ኃይል መተማመን ነበረበት።

ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ ዶናልድ የሚባል ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የተሾሙ ወንድሞች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ‘በብርታት ላይ ብርታት እያገኙ ይሄዳሉ።’ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት የሚጸልዩና የመንፈሱን ፍሬ ለማፍራት የሚጥሩ ከሆነ ለወንድሞቻቸው እውነተኛ በረከት ይሆናሉ።”—መዝ. 84:7፤ 1 ጴጥ. 4:11

መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከት

አዲስ የተሾሙ ብዙ ወንድሞች መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ መሆናቸውን ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ጄሰን እንዲህ ይላል፦ “ሽማግሌ ሆኜ ሳገለግል ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፤ በራስ የመተማመን ስሜቴም ጨምሯል። የተሰጠኝን ሥራ ማከናወን በጣም የሚያስደስተኝ ሲሆን ግሩም መብት እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ።”

አንተስ መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን መቀጠል ትፈልጋለህ? ከሆነ ጢሞቴዎስ ከተወው ምሳሌ ለመማር ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ አንተም ለአምላክ ሕዝቦች በረከት ትሆናለህ።