በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ

የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ

“የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ።”—2 ቆሮ. 3:17

መዝሙሮች፦ 49, 73

1, 2. (ሀ) በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን የነበሩ ሰዎች የባርነትና የነፃነት ጉዳይ ያሳስባቸው የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የሚቻለው ከየት እንደሆነ ተናግሯል?

በሮም ግዛት የነበሩ ሰዎች፣ ባሏቸው ሕጎች እንዲሁም ፍትሕንና ነፃነትን በማስከበራቸው ይኩራሩ ነበር። ይሁን እንጂ ኃያል የሆነው የሮም ግዛት የተገነባው በባሪያዎች ጉልበት ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በሮም ግዛት ውስጥ ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ባሪያዎች ነበሩ። ከዚህ አንጻር የባርነትና የነፃነት ጉዳይ በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ጨምሮ በብዙኃኑ አእምሮ ውስጥ የሚጉላላ ርዕስ እንደነበረ አያጠራጥርም።

2 ሐዋርያው ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ላይ ስለ ነፃነት በተደጋጋሚ ተናግሯል። ሆኖም የአገልግሎቱ ዓላማ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች እንደሚመኙት ከማኅበራዊ ወይም ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለውጥ ማምጣት አልነበረም። ጳውሎስና የእምነት ባልንጀሮቹ የትኛውም ሰብዓዊ ገዢ ወይም ድርጅት ነፃነት እንዲያስገኝላቸው አልጠበቁም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራችና የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስላለው ውድ ዋጋ ሰዎችን ለማስተማር በትጋት ሠርተዋል። ጳውሎስ፣ እውነተኛ ነፃነት የሚገኘው ከየት እንደሆነ ለእምነት ባልንጀሮቹ ነግሯቸዋል። ለምሳሌ፣ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ “ይሖዋ መንፈስ ነው፤ የይሖዋ መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ” በማለት በግልጽ ተናግሯል።—2 ቆሮ. 3:17

3, 4. (ሀ) ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 3:17 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ በፊት ስለ ምን ተናግሯል? (ለ) ይሖዋ የሚሰጠውን ነፃነት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

3 ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 3:17 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ በፊት ምን እንደተናገረ እንመልከት፤ ሐዋርያው፣ ሙሴ ከይሖዋ መልአክ ጋር ተነጋግሮ ከሲና ተራራ ሲወርድ ስለነበረው ሁኔታ ገልጿል። ሕዝቡ የሙሴን ፊት ክብር ሲያዩ ስለፈሩ ሙሴ ፊቱን በመሸፈኛ ይሸፍን ነበር። (ዘፀ. 34:29, 30, 33፤ 2 ቆሮ. 3:7, 13) ጳውሎስ “ሆኖም አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ሲመለስ መሸፈኛው ይወገዳል” በማለት ቀጥሎ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 3:16) ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር?

4 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ገደብ የለሽ ነፃነት ያለው የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። በመሆኑም “የይሖዋ መንፈስ ባለበት” ነፃነት እንዳለ መገለጹ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ነፃነት ለማግኘት ‘ወደ ይሖዋ መመለስ’ ይኸውም በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት ያስፈልገናል። በምድረ በዳ የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋ ስላደረገላቸው ነገር ሰብዓዊ አመለካከት አዳብረው ነበር። ልባቸው ደንድኖ እንዲሁም አእምሯቸው ተጋርዶ ነበር፤ በመሆኑም ትኩረታቸው ያረፈው ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣታቸው ያስገኘላቸውን ነፃነት ተጠቅመው ሥጋዊ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ነበር።—ዕብ. 3:8-10

5. (ሀ) የይሖዋ መንፈስ ምን ዓይነት ነፃነት ያስገኛል? (ለ) አንድ ሰው ቢታሰር ወይም ባሪያ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የሚሰጠውን ነፃነት ማግኘት እንደሚችል እንዴት እናውቃለን? (ሐ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል?

5 ይሁን እንጂ የይሖዋ መንፈስ የሚያስገኘው ነፃነት ቃል በቃል ከባርነት ነፃ ከመውጣት የላቀ ነው። ሰዎች ሊያስገኙ ከሚችሉት ነፃነት በተለየ የይሖዋ መንፈስ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ያወጣቸዋል፤ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖትና ልማዶቹ ከሚጭኑባቸው ቀንበር ያላቅቃቸዋል። (ሮም 6:23፤ 8:2) ይህ እንዴት ያለ ክብራማ ነፃነት ነው! አንድ ሰው እስር ቤት ውስጥ ወይም በባርነት ሥር ቢሆንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ማግኘት ይችላል። (ዘፍ. 39:20-23) በእምነታቸው ምክንያት ለዓመታት ታስረው የነበሩት የእህት ናንሲ ዩወን እና የወንድም ሃሮልድ ኪንግ ተሞክሮ ይህ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። የእነዚህን ክርስቲያኖች ተሞክሮ JW ብሮድካስቲንግ ላይ ከራሳቸው አንደበት መስማት ትችላለህ። (ቃለ መጠይቅ እና ተሞክሮ > ፈተናዎችን በጽናት መወጣት በሚለው ሥር ተመልከት።) ይሁንና ‘ነፃነታችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ይህን ነፃነታችንን በጥበብ ለመጠቀም ምን ማድረግ እንችላለን?’ የሚሉትን ጥያቄዎች መመርመር ያስፈልገናል።

አምላክ የሰጠንን ነፃነት ከፍ አድርጎ መመልከት

6. እስራኤላውያን ይሖዋ ለሰጣቸው ነፃነት አድናቆት እንደጎደላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

6 አንድ ስጦታ ምን ያህል ውድ እንደሆነ መገንዘባችን ለሰጪው አመስጋኝነታችንን ለማሳየት ይበልጥ እንደሚያነሳሳን የታወቀ ነው። እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ከግብፅ ባርነት ነፃ በማውጣት ለሰጣቸው ነፃነት አድናቆት አላሳዩም። ነፃ በወጡ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ በግብፅ የነበረውን ምግብና መጠጥ መመኘት እንዲሁም ይሖዋ የሰጣቸውን ነገር ማማረር ጀመሩ፤ ይባስ ብሎም ወደ ግብፅ መመለስ ፈለጉ። እስቲ አስበው፣ ‘ዓሣ፣ ኪያር፣ ሐብሐብ፣ ባሮ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት’ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በነፃነት ከማምለክ መብታቸው በለጠባቸው። ታዲያ ይሖዋ በሕዝቡ እጅግ መቆጣቱ ምን ያስገርማል? (ዘኁ. 11:5, 6, 10፤ 14:3, 4) ይህ ለእኛም ትልቅ ትምህርት ይዞልናል!

7. ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 6:1 ላይ ከሰጠው ምክር ጋር ተስማምቶ የኖረው እንዴት ነው? እኛስ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በደግነት የሰጣቸውን ነፃነት አቅልለው እንዳይመለከቱ ሁሉንም ክርስቲያኖች አሳስቧል። (2 ቆሮንቶስ 6:1ን አንብብ።) ጳውሎስ የኃጢአትና የሞት ምርኮኛ እንደሆነ ስለተሰማው ሕሊናው በጣም ይረብሸው ነበር። ሆኖም “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ሰዎች ሕይወት የሚያስገኘው መንፈስ ሕግ፣ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቷችኋል።” (ሮም 7:24, 25፤ 8:2) እኛም የጳውሎስን ምሳሌ መከተላችን ተገቢ ነው፤ ይሖዋ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ በማውጣት ያሳየንን ደግነት ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ቤዛው፣ በንጹሕ ሕሊና አምላካችንን እንድናገለግልና የእሱን ፈቃድ በደስታ እንድንፈጽም መንገድ ከፍቶልናል።—መዝ. 40:8

የመምረጥ ነፃነትህን የምትጠቀምበት ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን ነው? ወይስ የራስህን ፍላጎት ለማስቀደም? (ከአንቀጽ 8-10⁠ን ተመልከት)

8, 9. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ ነፃነታችንን የምንጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ተደቅኖብናል?

8 ላገኘነው ነፃነት አመስጋኝነታችንን መግለጻችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ይህን ውድ ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳንጠቀምበት መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ የመምረጥ ነፃነታችንን ሥጋዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ሰበብ እንዳናደርገው ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 2:16ን አንብብ።) ይህ ማሳሰቢያ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ያጋጠማቸውን ነገር ያስታውሰናል። ማስጠንቀቂያው በዛሬው ጊዜ ለምንኖር ክርስቲያኖችም ይሠራል፤ እንዲያውም ከእነሱ የባሰ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመናል። ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ከአለባበስና ከአጋጌጥ፣ ከምግብና ከመጠጥ፣ ከመዝናኛ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አጓጊ ምርጫዎች ያቀርቡልናል። ማስታወቂያ የሚያዘጋጁ ሰዎች መልከ መልካም የሆኑ አስተዋዋቂዎችን በመጠቀም፣ የማያስፈልጉንን ነገሮች የግድ እንደሚያስፈልጉን አድርገው ሲያቀርቡ ይታያል። በእርግጥም እንደነዚህ ያሉት ዘዴዎች በቀላሉ ሊያታልሉንና ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንድንጠቀምበት ሊያደርጉን ይችላሉ!

9 ጴጥሮስ የሰጠው ምክር እንደ ትምህርትና ሥራ ካሉ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በምናደርገው ምርጫ ረገድም ይሠራል። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ታዋቂ ወደሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት የሚያስችል ውጤት እንዲያመጡ ቀላል የማይባል ጫና ይደረግባቸዋል። ከፍተኛ ትምህርት መከታተላቸው አንቱ የሚያስብልና ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመያዝ መንገድ እንደሚከፍት ይነገራቸዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሰዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ብቻ አጠናቅቀው ያቆሙ ሰዎች በሚያገኙት ደሞዝ መካከል ምን ያህል ሰፊ ልዩነት እንዳለ የሚገልጹ መረጃዎች ይቀርቡላቸዋል። ወጣቶች እነዚህን ነገሮች ሲሰሙ ከፍተኛ ትምህርት አጓጊ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል፤ ምክንያቱም የሚያደርጉት ምርጫ በመላ ሕይወታቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሁንና ወጣቶችም ሆኑ ወላጆቻቸው ሊዘነጉት የማይገባው ነገር ምንድን ነው?

10. የግል ምርጫ የማድረግ ነፃነታችንን ከምንጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

10 አንዳንዶች እንዲህ ያሉት ጉዳዮች የግል ውሳኔ ከመሆናቸው አንጻር ሕሊናቸው እስካልወቀሳቸው ድረስ የፈለጉትን የማድረግ ነፃነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። ይህን የሚሉት ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ የተናገረውን “ነፃነቴ በሌላው ሰው ሕሊና ለምን ይፈረድበት?” የሚለውን ሐሳብ በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:29) እንደ ትምህርትና ሥራ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ነፃነት እንዳለን የታወቀ ነው፤ ሆኖም ነፃነታችን አንጻራዊ እንደሆነና የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ የሚያስከትሉት ውጤት እንዳለ ማስታወስ ይኖርብናል። ጳውሎስ “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት አይደለም” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 10:23) ይህ ጥቅስ፣ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ነፃነታችንን ከምንጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ከግል ምርጫችን ይበልጥ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ አስፈላጊ ነገሮች መኖራቸውን እንድናስተውል ይረዳናል።

አምላክን በማገልገል ነፃነታችንን በጥበብ መጠቀም

11. ነፃ የወጣንበት ዓላማ ምንድን ነው?

11 ጴጥሮስ ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳንጠቀምበት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ነፃነታችንን በምን መልኩ ልንጠቀምበት እንደሚገባም ገልጿል። “ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች ሆናችሁ ተጠቀሙበት” በማለት አሳስቦናል። ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ እንድንወጣ ያደረገበት ዋነኛ ዓላማ ሕይወታችንን ለእሱ ወስነን “እንደ አምላክ ባሪያዎች” እንድንኖር ስለሚፈልግ ነው።

12. ኖኅና ቤተሰቡ ምን ምሳሌ ትተውልናል?

12 ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳንጠቀምበት ብሎም ለዓለማዊ ግቦችና ለሥጋዊ ምኞቶች ዳግም ባሪያ እንዳንሆን የሚረዳን ከሁሉ የተሻለው መከላከያ በመንፈሳዊ ነገሮች መጠመድ ነው። (ገላ. 5:16) ኖኅንና ቤተሰቡን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እነዚህ ሰዎች ይኖሩ የነበረው ዓመፀኛ በሆነና ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ ነበር። ይሁንና በዙሪያቸው የሚኖሩ ሰዎች በሚያሳድዷቸው ነገሮች አልተጠላለፉም። ለዚህ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ በሰጣቸው ሥራ ለመጠመድ መምረጣቸው ነው፤ ኖኅና ቤተሰቡ መርከብ ይሠሩ፣ ለራሳቸውና ለእንስሳቱ የሚሆን ምግብ ያከማቹ እንዲሁም የማስጠንቀቂያ መልእክት ያውጁ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ” ይላል። (ዘፍ. 6:22) ይህን ማድረጋቸው ምን ውጤት አስገኘ? በወቅቱ የነበረው ዓለም ሲጠፋ ኖኅና ቤተሰቡ በሕይወት መትረፍ ችለዋል።—ዕብ. 11:7

13. አምላክ ምን ተልእኮ ሰጥቶናል?

13 ዛሬስ ይሖዋ ምን እንድናደርግ አዞናል? አምላክ ምሥራቹን እንዲሰብክ ኢየሱስን እንዳዘዘውና ኢየሱስ ደግሞ ይህን ተልእኮ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሰጣቸው እናውቃለን። (ሉቃስ 4:18, 19ን አንብብ።) በዘመናችን ያሉትን አብዛኞቹን ሰዎች የዚህ ዓለም አምላክ ስላሳወራቸው የሐሰት ሃይማኖት፣ የቁሳዊ ነገሮች ምኞትና የፖለቲካው ሥርዓት ባሪያ መሆናቸውን አያስተውሉም። (2 ቆሮ. 4:4) የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን የእሱን ምሳሌ በመከተል፣ እነዚህ ሰዎች የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲያመልኩ የመርዳት መብት ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) በእርግጥ ይህን ተልእኮ ስንወጣ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን ሥራው ቀላል አይደለም። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች ለምሥራቹ ይበልጥ ግድየለሽ እየሆኑ መጥተዋል፤ ይባስ ብሎም አንዳንዶች ለመልእክቱ ጥላቻ ያሳያሉ። ያም ቢሆን ይሖዋ ምሥራቹን እንድንሰብክ ስላዘዘን ‘ነፃነቴን በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ልጠቀምበት እችላለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።

14, 15. በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ ወስነዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

14 በርካታ ክርስቲያኖች የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በጣም እንደቀረበ በማስተዋላቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል እንደተነሳሱ ስንመለከት ታላቅ ደስታ ይሰማናል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። (1 ቆሮ. 9:19, 23) አንዳንዶቹ በክልላቸው ውስጥ በአቅኚነት የሚያገለግሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ250,000 የሚበልጡ ክርስቲያኖች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል የጀመሩ ሲሆን የዘወትር አቅኚዎች አማካይ ቁጥር ከ1,100,000 በላይ ሆኗል። ብዙዎች ነፃነታቸውን በጥበብ በመጠቀም ይሖዋን በዚህ መንገድ እያገለገሉ መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው!—መዝ. 110:3

15 እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ነፃነታቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙበት የረዳቸው ምንድን ነው? ላለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ አገራት ያገለገሉትን የጆንን እና የጁዲትን ሁኔታ እንመልከት። ጆን እና ጁዲት የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት በ1977 ሲጀመር ተማሪዎቹ፣ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው እንዲያገለግሉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ለማድረግ ወሰኑ፤ በዚህም ምክንያት ጆን በተደጋጋሚ ጊዜ ሥራውን መቀየር አስፈልጎት እንደነበር ይናገራል። ከጊዜ በኋላ ወደ ሌላ አገር ሄዱ፤ በዚያም አዲስ ቋንቋ መማርን፣ አዲስ ባሕል መልመድንና ከባድ የአየር ሁኔታን መቋቋምን የመሳሰሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ወደ ይሖዋ በመጸለይና በእሱ በመታመን እነዚህን ፈተናዎች መወጣት ችለዋል። ታዲያ በተለያዩ አገሮች በማገልገል ስላሳለፏቸው ዓመታት ሲያስቡ ምን ይሰማቸዋል? ጆን እንዲህ ይላል፦ “በሕይወቴ ውስጥ ካከናወንኳቸው ሁሉ በላቀው ሥራ እንደተካፈልኩ ይሰማኛል። ይሖዋ ልክ እንደ አፍቃሪ አባት የበለጠ እውን ሆኖልኛል። በያዕቆብ 4:8 ላይ የሚገኘው ‘ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል’ የሚለው ጥቅስ ትርጉም በደንብ የገባኝ አሁን ነው። ስፈልገው የነበረውን ነገር ማለትም ዓላማ ያለው ሕይወት አግኝቻለሁ።”

16. በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ነፃነታቸውን በጥበብ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

16 ከጆንና ከጁዲት በተለየ መልኩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል የሚችሉት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። ያም ቢሆን ብዙዎች በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ ቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ ለመካፈል ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። ለምሳሌ በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ ዋናው መሥሪያ ቤት ሲገነባ 27,000 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ በፈቃደኝነት በሥራው ተካፍለዋል። ብዙዎቹ በዚያ ለማገልገል ሲሉ የተለያዩ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማወደስና ለማክበር ነፃነታቸውን በመጠቀም ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል!

17. አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት በጥበብ የሚጠቀሙ ሰዎች ወደፊት ምን በረከት ያገኛሉ?

17 ይሖዋን ማወቅና እውነተኛው አምልኮ የሚያስገኘውን ነፃነት ማጣጣም በመቻላችን በጣም አመስጋኞች ነን። በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ምርጫዎች ስናደርግ ይሖዋ የሰጠንን ነፃነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳይ። ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ይህን ነፃነት ይሖዋን በተሟላ መንገድ ለማገልገል እንጠቀምበት። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ሲያገኝ እኛም ከዚያ በረከት ተቋዳሽ መሆን እንችላለን።—ሮም 8:21