በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 16

መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ለሚያስተምረው እውነት ጥብቅና ቁሙ

መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ለሚያስተምረው እውነት ጥብቅና ቁሙ

“በመንፈስ የተነገረውን የእውነት ቃልና በመንፈስ የተነገረውን የስህተት ቃል ለይተን [እናውቃለን]።”—1 ዮሐ. 4:6

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

የትምህርቱ ዓላማ *

በቤተሰባችሁ ውስጥ ሐዘን ሲያጋጥም አምላክን በሚያሳዝኑ ልማዶች ሳትካፈሉ ዘመዶቻችሁን አጽናኑ (ከአንቀጽ 1-2⁠ን ተመልከት) *

1-2. (ሀ) ሰይጣን ሰዎችን ያሳሳተው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

“የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ሰዎችን ሲያሳስት ቆይቷል። (ዮሐ. 8:44) ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች መካከል ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የሚገልጹት የሐሰት ትምህርቶች ይገኙበታል። እነዚህ ትምህርቶች በብዙ አካባቢዎች በስፋት ለሚታዩት ልማዶችና አጉል እምነቶች መሠረት ሆነዋል። በመሆኑም አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የቤተሰባቸው ወይም የማኅበረሰባቸው አባል በሚሞትበት ጊዜ ለእምነታቸው ጥብቅና ለመቆም ‘ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ’ አስፈልጓቸዋል።—ይሁዳ 3

2 እናንተም እንዲህ ያለ ፈተና ቢያጋጥማችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ለሚያስተምረው እውነት ጥብቅና ለመቆም ምን ይረዳችኋል? (ኤፌ. 6:11) አምላክን በሚያሳዝኑ ልማዶች እንዲካፈል ጫና የሚደረግበትን የእምነት አጋራችሁን ማጽናናትና ማበረታታት የምትችሉትስ እንዴት ነው? ይሖዋ ይህን በተመለከተ የሰጠን መመሪያ በዚህ ርዕስ ላይ ተብራርቷል። እስቲ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል እንመልከት።

ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

3. የመጀመሪያው ውሸት ምን ውጤት አስከትሏል?

3 አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ኖረው እንዲሞቱ አስቦ አልነበረም። አዳምና ሔዋን ለዘላለም መኖር ከፈለጉ ግን ይሖዋ የሰጣቸውን ቀላል መመሪያ መታዘዝ ነበረባቸው፤ መመሪያው የሚከተለው ነበር፦ “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ . . . አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍ. 2:16, 17) ይሁንና ሰይጣን ጣልቃ ገብቶ ችግር ፈጠረ። በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” አላት። የሚያሳዝነው፣ ሔዋን የተነገራትን ውሸት በማመን ፍሬውን በላች። በኋላ ላይ ባሏም ፍሬውን በላ። (ዘፍ. 3:4, 6) በዚህ መልኩ ኃጢአትና ሞት በሰው ዘር ላይ ነገሡ።—ሮም 5:12

4-5. ሰይጣን ሰዎችን ማሳሳቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

4 አምላክ በተናገረው መሠረት አዳምና ሔዋን ሞቱ። ሰይጣን ግን ስለ ሞት ውሸት መናገሩን አላቆመም። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ውሸቶችን ማስፋፋት ጀመረ። ከእነዚህ ውሸቶች መካከል አንዱ ‘ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ አለች’ የሚለው ትምህርት ነው። በተለያየ መልኩ የሚነገረው ይህ ውሸት እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀ ሲሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች አሳስቷል።—1 ጢሞ. 4:1

5 ብዙ ሰዎች በእነዚህ ውሸቶች የተታለሉት ለምንድን ነው? ሰይጣን ሰዎች ስለ ሞት ያላቸውን ስሜት ያውቃል፤ ሞትን አስመልክቶ የሚናገራቸው ውሸቶችም ይህን ግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው። የተፈጠርነው ለዘላለም እንድንኖር ስለሆነ መሞት አንፈልግም። (መክ. 3:11) በመሆኑም ሞትን የምንመለከተው እንደ ጠላታችን አድርገን ነው።—1 ቆሮ. 15:26

6-7. (ሀ) ሰይጣን ሞትን በተመለከተ እውነቱን ለመደበቅ ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል? አብራራ። (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስፈላጊ ካልሆነ ፍርሃት የሚገላግለን እንዴት ነው?

6 ሰይጣን ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ሞትን በተመለከተ እውነቱን መደበቅ አልቻለም። እንዲያውም ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ በርካታ ሰዎች፣ ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ስላላቸው ተስፋ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ ይህን ለሌሎች እያወጁ ነው። (መክ. 9:5, 10፤ ሥራ 24:15) እነዚህን እውነቶች ማወቃችን ያጽናናናል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ካልሆነ ፍርሃትና ጭንቀት ይጠብቀናል። ለምሳሌ፣ ‘የሞቱ ሰዎች ምን ይደርስባቸው ይሆን?’ ብለን አንጨነቅም፤ አሊያም ጉዳት ያደርሱብናል ብለን አንሰጋም። ሙታን ከሕልውና ውጭ እንደሆኑና በማንም ላይ ጉዳት እንደማያደርሱ እናውቃለን። ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ነው። (ዮሐ. 11:11-14) በተጨማሪም የሞቱ ሰዎች ጊዜ ማለፉ እንደማይታወቃቸው ተምረናል። በመሆኑም ከሞቱ በርካታ ዘመናት የሆናቸው ሰዎችም እንኳ ከሞት ሲነሱ ለቅጽበት ዓይናቸውን ከድነው የገለጡ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል።

7 መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ የሚያስተምረው እውነት ግልጽ፣ ቀላልና አሳማኝ ነው ቢባል አትስማሙም? ይህ እውነት፣ ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ግራ የሚያጋቡ ውሸቶች ምንኛ የተለየ ነው! እነዚህ ውሸቶች ሰዎችን ከማሳሳት ባለፈ የፈጣሪያችንን ስም ያጎድፋሉ። ሰይጣን ያስከተለውን ጉዳት ይበልጥ መረዳት እንድንችል እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመርምር፦ የሰይጣን ውሸቶች በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያመጡት እንዴት ነው? ሰዎች ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ እንዳይሰጡ ያደረጉት እንዴት ነው? የሰዎችን ሐዘንና ሥቃይ ያባባሱትስ እንዴት ነው?

ሰይጣን የሚያስፋፋቸው ውሸቶች ብዙ ጉዳት አድርሰዋል

8. ከኤርምያስ 19:5 አንጻር፣ ሰይጣን ስለ ሙታን የሚያስፋፋቸው ውሸቶች በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የሚያስከትሉት እንዴት ነው?

8 ሰይጣን ሙታንን አስመልክቶ የሚያስፋፋቸው ውሸቶች በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያስከትላሉ። ከእነዚህ ውሸቶች መካከል፣ የሞቱ ሰዎች በእሳት እንደሚቃጠሉ የሚገልጸው የሐሰት ትምህርት ይገኝበታል። እንደነዚህ ያሉት ትምህርቶች የአምላክን ስም ያጎድፋሉ። እንዴት? የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ የዲያብሎስ ዓይነት ባሕርይ ያለው እንዲመስል ስለሚያደርጉ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ምን የሚሰማው ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት የጭካኔ ድርጊት እንደሚጠላ ይናገራል።ኤርምያስ 19:5ን አንብብ።

9. የሰይጣን ውሸቶች በዮሐንስ 3:16 እና 15:13 ላይ የተገለጸውን የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ የሚያሳጡት እንዴት ነው?

9 ሰይጣን ሞትን አስመልክቶ የሚናገራቸው ውሸቶች፣ ሰዎች ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ እንዳይሰጡ አድርገዋል። (ማቴ. 20:28) ሰይጣን የሚናገረው ሌላው ውሸት ደግሞ ‘ሰዎች የማይሞት ነፍስ አላቸው’ የሚለው ነው። ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ሁሉም ሰው ለዘላለም መኖር ይችላል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ እኛ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል ክርስቶስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ መስጠቱ አስፈላጊ አልነበረም ማለት ነው። የክርስቶስ መሥዋዕት ይሖዋና ኢየሱስ ለሰው ዘር ያሳዩት ከሁሉ የላቀ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አንዘንጋ። (ዮሐንስ 3:16⁠ን እና 15:13ን አንብብ።) ውድ የሆነውን የቤዛውን ስጦታ ዋጋ የሚያሳጡት ትምህርቶች፣ ይሖዋንና ልጁን ምንኛ ያሳዝኗቸው ይሆን!

10. ሰይጣን ሞትን በተመለከተ የሚያስፋፋቸው ውሸቶች የሰዎችን ሐዘንና ሥቃይ ያባባሱት እንዴት ነው?

10 የሰይጣን ውሸቶች የሰዎችን ሐዘንና ሥቃይ አባብሰዋል። ልጃቸውን በሞት ያጡ ወላጆች አምላክ ልጃቸውን እንደወሰደው ምናልባትም መልአክ እንደሚያደርገው ይነገራቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ውሸት ልጃቸው የሞተባቸውን ወላጆች ያጽናናቸዋል ወይስ ሐዘናቸውን ያባብሰዋል? በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች፣ ሰዎችን ማሠቃየታቸውና የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርት የሚቃወሙ ግለሰቦችን እንጨት ላይ አስረው ማቃጠላቸው ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት ሐሰት የሆነውን የገሃነመ እሳት ትምህርት ይጠቅሱ ነበር። ስፓኒሽ ኢንክዊዚሽን በመባል ስለሚታወቀው የሮም ካቶሊክ ችሎት የሚናገር አንድ መጽሐፍ እንደገለጸው ይህን የጭካኔ ድርጊት ከፈጸሙት ሰዎች አንዳንዶቹ “በገሃነመ እሳት ለዘላለም መሠቃየት ምን ሊመስል እንደሚችል [ለመናፍቃኑ] በተወሰነ መጠን እያሳዩአቸው እንደሆነ ይሰማቸው ነበር።” መጽሐፉ አክሎ እንደገለጸው እነዚህ ሰዎች ይህን ድርጊት የፈጸሙት፣ መናፍቃኑ ከመሞታቸው በፊት ንስሐ የሚገቡበትና ከገሃነመ እሳት የሚድኑበት አጋጣሚ ለመስጠት ብለው ሊሆን ይችላል። በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የሞቱ ዘመዶቻቸውን ማምለክ፣ ማክበር ወይም የእነሱን በረከት ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። በመሆኑም ለሙታን መሥዋዕት ያቀርባሉ፣ ተዝካር ያወጣሉ እንዲሁም ሙት ዓመት ያከብራሉ። ሌሎች ደግሞ የሞቱ ዘመዶቻቸው ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ስለሚፈሩ እነሱን ለማስደሰት ጥረት ያደርጋሉ። የሚያሳዝነው ግን በሰይጣን ውሸቶች ላይ የተመሠረቱ እምነቶች እውነተኛ መጽናኛ አያስገኙም። እንዲያውም አስፈላጊ ላልሆነ ጭንቀት አልፎ ተርፎም ፍርሃት ይዳርጋሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያስተምረው እውነት ጥብቅና መቆም የምንችለው እንዴት ነው?

11. ቤተሰቦቻችን ወይም ወዳጆቻችን ከአምላክ ቃል ጋር በሚጋጭ ድርጊት እንድንካፈል ጫና ሊያሳድሩብን የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ቤተሰቦቻችን ወይም ወዳጆቻችን ከሙታን ጋር በተያያዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች እንድንካፈል ጫና በሚያደርጉብን ጊዜም እንኳ፣ ለአምላክና ለቃሉ ያለን ፍቅር ይሖዋን ለመታዘዝ ብርታት ይሰጠናል። እነዚህ ሰዎች ለሞተው ግለሰብ ፍቅር ወይም አክብሮት እንደሌለን በመናገር ሊያሸማቅቁን ይሞክሩ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በእነዚህ ልማዶች አለመካፈላችን ሟቹ በሕይወት ባሉት ላይ በሆነ መንገድ ጉዳት እንዲያደርስ ሊያደርገው እንደሚችል ይገልጹ ይሆናል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥብቅና መቆም የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ በታች የተጠቀሱት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ ረገድ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

12. ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌላቸውን ከሞት ጋር የተያያዙ አንዳንድ እምነቶችና ልማዶች ጥቀስ።

12 ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ እምነቶችና ልማዶች ‘ራሳችሁን ለመለየት’ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። (2 ቆሮ. 6:17) በአንዲት የካሪቢያን ደሴት፣ አንድ ሰው ሲሞት “መንፈሱ” በአካባቢው ሊቆይና በደል ያደረሱበትን ሰዎች ሊቀጣ እንደሚችል በስፋት ይታመናል። እንዲያውም የሟቹ መንፈስ “በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” የሚል እምነት እንዳለ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ገልጿል። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ደግሞ ሰዎች በሟቹ ቤት ውስጥ ያሉትን መስታወቶች የሚሸፍኑ ከመሆኑም ሌላ የግለሰቡን ፎቶግራፎች ወደ ግድግዳ ያዞራሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? አንዳንዶች፣ የሞቱ ሰዎች ራሳቸውን ማየት እንደሌለባቸው ይናገራሉ! የይሖዋ አገልጋዮች ግን የሰይጣንን ውሸቶች የሚያስፋፉ አጉል እምነቶችን አይቀበሉም፤ ከዚህ ጋር በተያያዙ ድርጊቶችም ጨርሶ አይካፈሉም!—1 ቆሮ. 10:21, 22

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር ማድረግና የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ የቤተሰብ አባላት ጋር በግልጽ መወያየት ችግሮችን ለመቀነስ ይረዳል (ከአንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት) *

13. አንድ ልማድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ መሆኑን ከተጠራጠራችሁ በያዕቆብ 1:5 መሠረት ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?

13 አንድ ልማድ ወይም ድርጊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ መሆኑን ከተጠራጠራችሁ ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጣችሁ በእምነት ጠይቁት። (ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።) ከዚያም በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርጉ። አስፈላጊ ከሆነ፣ የጉባኤያችሁን ሽማግሌዎች አማክሩ። ሽማግሌዎቹ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ባይነግሯችሁም እዚህ ላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይጠቁሟችኋል። እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳችሁ ‘የማስተዋል ችሎታችሁን ለማሠልጠን’ የሚረዳችሁ ሲሆን ይህም “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር [ለመለየት]” ያስችላችኋል።—ዕብ. 5:14

14. ለሌሎች እንቅፋት ላለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ። . . . እንቅፋት አትሁኑ።” (1 ቆሮ. 10:31, 32) በአንድ ዓይነት ልማድ መካፈል ይኖርብን እንደሆነና እንዳልሆነ ስንወስን፣ ውሳኔያችን በሌሎች በተለይም በእምነት ባልንጀሮቻችን ሕሊና ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖም ልናስብ ይገባል። ማንም በእኛ ምክንያት እንዲሰናከል አንፈልግም! (ማር. 9:42) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችንም ቢሆን ሳያስፈልግ ቅር ማሰኘት አይኖርብንም። ፍቅር፣ ሰዎችን አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለማነጋገር ያነሳሳናል፤ እንዲህ ማድረጋችን ደግሞ ይሖዋን ያስከብረዋል። ከሰዎች ጋር መጣላት ወይም ባሕላቸውን ማንቋሸሽ እንደሌለብን የታወቀ ነው። ፍቅር ኃይል እንዳለው አንዘንጋ! አፍቃሪ በመሆን ለሰዎች አሳቢነትና አክብሮት ስናሳይ፣ የሚቃወሙን ሰዎች አመለካከት እንኳ እንዲቀየር ልናደርግ እንችላለን።

15-16. (ሀ) ስለምታምኑባቸው ነገሮች ለሌሎች ማሳወቃችሁ የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ። (ለ) በሮም 1:16 ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?

15 የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችሁ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲታወቅ አድርጉ። (ኢሳ. 43:10) ቤተሰቦቻችሁና ጎረቤቶቻችሁ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች መሆናችሁን አስቀድመው ካወቁ፣ ሐዘን በሚደርስበት ወቅት በምትወስዱት አቋም ያን ያህል ላይበሳጩ ይችላሉ። በሞዛምቢክ የሚኖረው ፍራንሲስኮ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔና ባለቤቴ ካሮሊና እውነትን ስንሰማ፣ ከዚህ በኋላ በሙታን አምልኮ እንደማንካፈል ለቤተሰቦቻችን ነገርናቸው። የካሮሊና እህት ስትሞት ከዚህ ጋር በተያያዘ ፈታኝ ሁኔታ አጋጠመን። በአካባቢው ልማድ መሠረት አስከሬኑ የሚታጠብበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት አለ። አስከሬኑ የታጠበበት ውኃ በሚደፋበት ቦታ ላይ ደግሞ የሟቹ የቅርብ ዘመድ ሦስት ቀን እንዲያድር ይጠበቅበታል። ይህ ልማድ የሟቹ መንፈስ እንዳይቆጣ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። የካሮሊና ቤተሰቦችም ካሮሊና እንዲህ እንድታደርግ ፈልገው ነበር።”

16 ታዲያ ፍራንሲስኮና ባለቤቱ ምን አደረጉ? ፍራንሲስኮ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋን ስለምንወድና እሱን ማስደሰት ስለምንፈልግ በዚህ ልማድ ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆንንም። የካሮሊና ቤተሰቦች በዚህ በጣም ተበሳጩ። ለሙታን አክብሮት እንደሌለን በመግለጽ የወቀሱን ከመሆኑም ሌላ ከዚህ በኋላ ቤታችን እንደማይመጡም ሆነ እርዳታ እንደማያደርጉልን ነገሩን። የምናምንበትን ነገር አስቀድመን አሳውቀናቸው ስለነበር ተበሳጭተው ባሉበት ሰዓት ስለዚህ ጉዳይ ልናስረዳቸው አልሞከርንም። የሚገርመው አንዳንድ ዘመዶቻችን አቋማችንን ቀደም ብለን እንዳሳወቅን በመግለጽ እኛን ደገፉን። የካሮሊና ቤተሰቦች ከጊዜ በኋላ የተረጋጉ ሲሆን መልሰን ሰላም መፍጠር ችለናል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ቤታችን ድረስ መጥተው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንድንሰጣቸው ጠይቀውናል።” እኛም ብንሆን የአምላክ ቃል ሞትን በተመለከተ የሚያስተምረውን እውነት ደግፈን በምንወስደው አቋም ፈጽሞ ልናፍር አይገባም።ሮም 1:16ን አንብብ።

ሐዘን የደረሰባቸውን ማጽናናትና መደገፍ

እውነተኛ ወዳጆች ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ያጽናናሉ እንዲሁም ያበረታታሉ (ከአንቀጽ 17-19⁠ን ተመልከት) *

17. ሐዘን ለደረሰበት የእምነት ባልንጀራችን እውነተኛ ወዳጅ ለመሆን ምን ይረዳናል?

17 አንድ የእምነት ባልንጀራችን የሚወደውን ሰው በሞት በሚያጣበት ጊዜ “እውነተኛ ወዳጅ” እንዲሁም “ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም” ለመሆን ጥረት ማድረግ አለብን። (ምሳሌ 17:17) በተለይ ደግሞ ሐዘን የደረሰበት ወንድማችን ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ልማዶች እንዲካፈል ጫና ሲደረግበት “እውነተኛ ወዳጅ” መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ ረገድ ይረዱናል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እስቲ እንመልከት።

18. ኢየሱስ ያለቀሰው ለምን ነበር? በዚህ ረገድ ከእሱ ምን እንማራለን?

18 “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።” (ሮም 12:15) በሐዘን የተዋጠ የእምነት ባልንጀራችንን ምን ብለን ልናጽናናው እንደምንችል ግራ ይገባን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ፣ አብረነው ማልቀሳችን ብቻ ከምንናገረው ነገር ይበልጥ ስሜታችንን ሊገልጽ ይችላል። የኢየሱስ ወዳጅ አልዓዛር ሲሞት ማርያምና ማርታ ውድ ወንድማቸውን በማጣታቸው፣ ሌሎቹ ሰዎች ደግሞ ወዳጃቸው በመሞቱ አልቅሰዋል። ኢየሱስ ወደ ስፍራው የደረሰው አልዓዛር ከሞተ ከአራት ቀን በኋላ ነበር፤ አልዓዛርን ሊያስነሳው እንደሆነ ቢያውቅም እሱም ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐ. 11:17, 33-35) ኢየሱስ እንባውን ማፍሰሱ ይሖዋ በአልዓዛር ሞት ምን እንደተሰማው ያሳያል። በተጨማሪም ኢየሱስ ለዚህ ቤተሰብ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያረጋግጣል፤ ማርያምና ማርታ ይህን በማወቃቸው በጣም እንደተጽናኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ወንድሞቻችን እንደምንወዳቸውና እንደምናስብላቸው ሲመለከቱ ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንዲሁም የሚያስቡላቸውና ከጎናቸው የማይለዩ ወዳጆች እንዳሏቸው ይሰማቸዋል።

19. ሐዘን የደረሰበትን የእምነት ባልንጀራችንን ስናጽናና መክብብ 3:7⁠ን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

19 “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።” (መክ. 3:7) ሐዘን የደረሰበትን የእምነት ባልንጀራችንን ማጽናናት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ጥሩ አድማጭ መሆን ነው። የእምነት ባልንጀራችሁ የልቡን አውጥቶ እንዲገልጽ ዕድል ስጡት፤ ‘እንዳመጣለት ቢናገር’ እንኳ ቅር አትሰኙበት። (ኢዮብ 6:2, 3) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶቹ የሚያደርሱበት ጫና ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አብራችሁት ጸልዩ። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ፣ ወንድማችሁ ተረጋግቶ ማሰብ እንዲችል እንዲረዳውና ብርታት እንዲሰጠው ጸልዩ። (መዝ. 65:2) ሁኔታው የሚፈቅድላችሁ ከሆነ አብራችሁት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ። አሊያም ደግሞ በጽሑፎቻችን ላይ የወጣ ከሁኔታው ጋር የሚስማማ ርዕስ ለምሳሌ፣ አበረታች የሆነ የሕይወት ታሪክ አንብቡለት።

20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

20 ሙታንን በተመለከተ እውነቱን ማወቃችንና በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉ ሰዎች ስላላቸው አስደሳች ተስፋ መማራችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (ዮሐ. 5:28, 29) እንግዲያው ደፋሮች በመሆን በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥብቅና እንቁም፤ እንዲሁም ተገቢ በሆነ አጋጣሚ ሁሉ ይህን እውነት ለሌሎች እንናገር። ሰይጣን፣ ሰዎች በመንፈሳዊ ጨለማ እንዲዋጡ ለማድረግ ስለሚጠቀምበት ሌላ ዘዴ ይኸውም ስለ መናፍስታዊ ድርጊት በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን። ከዚህ አጋንንታዊ ወጥመድ ጋር ከተያያዙ ድርጊቶችና መዝናኛዎች መራቅ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነም እንመረምራለን።

መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ

^ አን.5 ሰይጣንና አጋንንቱ የሞቱ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ውሸት በማስፋፋት ብዙዎችን አሳስተዋል። እነዚህ ውሸቶች ደግሞ ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ በርካታ ልማዶችን እንዲከተሉ አድርገዋል። ይህ ርዕስ እንዲህ ባሉ ልማዶች እንድትካፈሉ የሚደረግባችሁን ጫና መቋቋምና ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንድትችሉ ይረዳችኋል።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ሐዘን የደረሰባት ዘመዳቸውን ሲያጽናኑ።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቀብር ጋር ስለተያያዙ ልማዶች ምርምር ካደረገ በኋላ፣ የሚያምንበትን ነገር ለዘመዶቹ በአክብሮት ሲያስረዳቸው።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሽማግሌዎች ሐዘን የደረሰበትን አንድ ወንድም ሲያጽናኑትና ሲያበረታቱት።