የጥናት ርዕስ 18
‘ሩጫውን ጨርሱ’
“ሩጫውን ጨርሻለሁ።”—2 ጢሞ. 4:7
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
ማስተዋወቂያ *
1. ሁላችንም ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
ከባድ እንደሆነ በምታውቁት የሩጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ትሆናላችሁ? በተለይ ደግሞ አሟችሁ ወይም ደክሟችሁ ከሆነ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ እንደማትሆኑ የታወቀ ነው። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች በሩጫ ላይ እንዳሉ ተናግሯል። (ዕብ. 12:1) ደግሞም ወጣትም ሆንን አረጋዊ፣ ጠንካራም ሆንን ደካማ ሁላችንም ይሖዋ ያዘጋጀልንን ሽልማት ለማግኘት እስከ መጨረሻው መጽናት ይጠበቅብናል።—ማቴ. 24:13
2. በ2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ የመናገር ነፃነት የኖረው ለምንድን ነው?
2 ጳውሎስ በተሳካ ሁኔታ ‘ሩጫውን ስለጨረሰ’ የመናገር ነፃነት ነበረው። (2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8ን አንብብ።) ይሁንና ጳውሎስ የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ውድድር ነው?
ውድድሩ ምን ዓይነት ነው?
3. ጳውሎስ የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ውድድር ነው?
3 ጳውሎስ አንዳንድ አስፈላጊ ትምህርቶችን ለማስተላለፍ በጥንቷ ግሪክ የሚካሄዱ ስፖርቶችን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (1 ቆሮ. 9:25-27፤ 2 ጢሞ. 2:5) በአንዳንድ ቦታዎች ላይ፣ የክርስትና ሕይወትን ከሩጫ ውድድር ጋር አመሳስሎታል። (1 ቆሮ. 9:24፤ ገላ. 2:2፤ ፊልጵ. 2:16) አንድ ሰው በዚህ “ውድድር” ላይ መሳተፍ የሚጀምረው ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ሲጠመቅ ነው። (1 ጴጥ. 3:21) ሩጫውን የሚያጠናቅቀው ደግሞ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ሲሰጠው ነው።—ማቴ. 25:31-34, 46፤ 2 ጢሞ. 4:8
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 የረጅም ርቀት የሩጫ ውድድርንና የክርስትና ሕይወትን የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ? አዎ። እስቲ ሦስቱን ብቻ እንመልከት። አንደኛ፣ በትክክለኛው ጎዳና ላይ መሮጥ አለብን፤ ሁለተኛ፣ በመጨረሻው መስመር ላይ ትኩረት
ማድረግ ያስፈልገናል፤ ሦስተኛ፣ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመን ሩጫችንን መቀጠል ይኖርብናል።በትክክለኛው ጎዳና ላይ ሩጡ
5. የትኛውን ጎዳና መከተል አለብን? ለምንስ?
5 በሩጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሰዎች፣ ሽልማቱን ማግኘት የሚችሉት የሩጫው አዘጋጆች የመረጡላቸውን ጎዳና ተከትለው ከሮጡ ብቻ ነው። በተመሳሳይ እኛም የዘላለም ሕይወት ሽልማት ማግኘት ከፈለግን የክርስትናን ጎዳና ወይም አኗኗር መከተል አለብን። (1 ጴጥ. 2:21) ይሁን እንጂ ሰይጣንና የእሱን ጎዳና የሚከተሉ ሰዎች በዚህ ውሳኔያችን አይደሰቱም፤ ‘ከእነሱ ጋር መሮጣችንን እንድንቀጥል’ ይፈልጋሉ። (1 ጴጥ. 4:4) እኛ የምንከተለውን የሕይወት ጎዳና የሚያጣጥሉ ሲሆን የእነሱ መንገድ የተሻለ እንደሆነና ወደ ነፃነት እንደሚመራ ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ውሸት ነው።—2 ጴጥ. 2:19
6. ከብራያን ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
6 በሰይጣን ዓለም ተጽዕኖ ሥር ካሉ ሰዎች ጋር የሚሮጡ ሁሉ የመረጡት መንገድ ወደ ነፃነት ከመምራት ይልቅ ለባርነት እንደሚዳርግ ብዙም ሳይቆይ ይገነዘባሉ። (ሮም 6:16) እስቲ ብራያንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወላጆቹ የክርስትናን ጎዳና እንዲከተል ያበረታቱት ነበር። እሱ ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ ይህ ጎዳና ደስታ ያስገኝለት እንደሆነ መጠራጠር ጀመረ። በመሆኑም የሰይጣንን መሥፈርቶች ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ለመሮጥ ወሰነ። እንዲህ ብሏል፦ “ነፃነት ያስገኛል ብዬ የተከተልሁት ጎዳና በሱስ ተተብትቤ እንድያዝ እንደሚያደርገኝ አልተገነዘብኩም ነበር።” አክሎም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ቀስ በቀስ ዕፅ መውሰድና ከመጠን በላይ መጠጣት እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር መከተል ጀመርኩ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይበልጥ ኃይለኛ የሆኑ ዕፆችን መውሰድ የጀመርኩ ሲሆን ውሎ አድሮም የብዙዎቹ ዕፆች ባሪያ ሆንኩ። . . . ሱሴን ለማርካት የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ለማግኘት ስል ዕፅ መሸጥ ጀመርኩ።” ከጊዜ በኋላ ብራያን የይሖዋን መሥፈርቶች ለመከተል ወሰነ። ይከተለው የነበረውን ጎዳና በመተው በ2001 ተጠመቀ። በአሁኑ ወቅት፣ የክርስትናን የሕይወት ጎዳና እየተከተለ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነው። *
7. በማቴዎስ 7:13, 14 ላይ የትኞቹ ሁለት መንገዶች ተጠቅሰዋል?
7 በእርግጥም ትክክለኛውን ጎዳና ለመከተል መምረጣችን በጣም አስፈላጊ ነው! ሰይጣን ሁላችንም ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው’ ቀጭን መንገድ ላይ መሮጣችንን አቁመን አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ወደሚሄድበት ሰፊ መንገድ እንድንገባ ይፈልጋል። ሰፊው መንገድ በብዙዎች ዘንድ የሚመረጥና ምቹ ነው። ሆኖም ‘የሚወስደው ወደ ጥፋት’ ነው። (ማቴዎስ 7:13, 14ን አንብብ።) በትክክለኛው ጎዳና ላይ መሮጣችንን መቀጠልና ወደ ሌላኛው ጎዳና እንዳንሳብ ከፈለግን በይሖዋ መታመንና እሱን ማዳመጥ ይኖርብናል።
ትኩረታችሁ እንዳይከፋፈልና መሰናክል እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ
8. አንድ ሯጭ ቢደናቀፍ ምን ያደርጋል?
8 በረጅም ርቀት ውድድር የሚሳተፉ ሯጮች ትኩረት የሚያደርጉት ከፊት ለፊታቸው ባለው መንገድ ላይ ነው፤ ይህን የሚያደርጉት እንዳይደናቀፉ ነው። እንደዚያም ሆኖ አብሯቸው የሚሮጥ ሰው ሊያደናቅፋቸው ወይም መንገዱ ላይ ያለ የተቦረቦረ ጉድጓድ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። እነዚህ ሯጮች ቢወድቁም ተነስተው ሩጫቸውን ይቀጥላሉ። ትኩረት የሚያደርጉት ባደናቀፋቸው ነገር ላይ ሳይሆን በመጨረሻው መስመርና ሲያሸንፉ በሚያገኙት ሽልማት ላይ ነው።
9. ከተደናቀፍን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
9 እኛም በሩጫችን ላይ ብዙ ጊዜ ልንደናቀፍ ይኸውም በምንናገረውና በምናደርገው ነገር ስህተት ልንሠራ እንችላለን። ወይም ደግሞ አብረውን የሚሮጡ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት እንጎዳ ይሆናል። ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። ምክንያቱም ሁላችንም ፍጹም አይደለንም፤ እንዲሁም ሁላችንም የምንሮጠው ቀጭን በሆነው የሕይወት መንገድ ላይ ነው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ልንጋጭ እንችላለን። ጳውሎስ፣ አንዳችን ሌላውን ‘ቅር የምናሰኝበት’ ጊዜ እንዳለ ተናግሯል። (ቆላ. 3:13) ሆኖም ባደናቀፈን ነገር ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ከፊታችን በሚጠብቀን ሽልማት ላይ እናተኩር። ከተደናቀፍን፣ ተነስተን መሮጣችንን እንቀጥል። ባጋጠመን ነገር ተበሳጭተን ወይም ተመርረን ከወደቅንበት ለመነሳት ፈቃደኞች ካልሆንን የመጨረሻውን መስመር አልፈን ሽልማቱን ማግኘት አንችልም። ከዚህም ሌላ ቀጭን በሆነው የሕይወት ጎዳና ላይ ለመሮጥ ጥረት ለሚያደርጉ ሌሎች ሰዎች መሰናክል ልንሆን እንችላለን።
10. ሌሎችን ‘እንዳናደናቅፍ’ መጠንቀቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
10 አብረውን የሚሮጡትን ሰዎች ‘እንዳናደናቅፍ’ መጠንቀቅ የምንችልበት ሌላው መንገድ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለን ሌሎችን ከመጫን ይልቅ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ የእነሱን ምርጫ ማክበር ነው። (ሮም 14:13, 19-21፤ 1 ቆሮ. 8:9, 13) በዚህ ረገድ ቃል በቃል በውድድር ላይ ከሚሳተፉ ሯጮች እንለያለን። እነዚህ ሯጮች እርስ በርስ የሚፎካከሩ ሲሆን እያንዳንዱ ሯጭ ከሌሎቹ ቀድሞ ሽልማቱን የግሉ ለማድረግ ይጥራል። ሯጮቹ በዋነኝነት የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ነው። ስለዚህ ሌሎቹን ተወዳዳሪዎች ገፍተውም ቢሆን ከፊት ለመገኘት ጥረት ያደርጋሉ። እኛ ግን እርስ በርስ አንፎካከርም። (ገላ. 5:26፤ 6:4) ግባችን በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች አብረውን የመጨረሻውን መስመር አልፈው የሕይወትን ሽልማት እንዲያገኙ መርዳት ነው። በመሆኑም ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን።—ፊልጵ. 2:4
11. ሯጮች ትኩረት የሚያደርጉት በምን ላይ ነው? ለምንስ?
11 ሯጮች ከፊት ለፊታቸው ያለውን መንገድ ከማየት በተጨማሪ በመጨረሻው መስመር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የመጨረሻው መስመር ፊት ለፊት ባይታያቸውም እንኳ መስመሩን አልፈው ሽልማቱን ሲቀበሉ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸዋል። ሁልጊዜም ስለ ሽልማቱ ማሰባቸው መሮጣቸውን እንዲቀጥሉ ያነሳሳቸዋል።
12. ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ ምን ሽልማት አዘጋጅቶልናል?
12 ይሖዋ፣ እኛ የምንካፈልበትን ሩጫ ለሚያጠናቅቁ ሕዝቦቹ በደግነት ተነሳስቶ አስተማማኝ ሽልማት አዘጋጅቶላቸዋል፤ ይህም በሰማይ ወይም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የምናገኘው የዘላለም ሕይወት ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ሽልማታችን የተወሰነ ነገር ይገልጻሉ፤ በመሆኑም በዚያ ጊዜ የሚኖረን ሕይወት ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን በዓይነ ሕሊናችን መሣል እንችላለን። ይህ ተስፋ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እውን ሆኖ እንዲታየን ባደረግን መጠን የሚያጋጥመንን ማንኛውንም እንቅፋት ለማሸነፍ ያለን ቁርጠኝነት ይጨምራል።
ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም መሮጣችሁን ቀጥሉ
13. ቃል በቃል በሩጫ ውድድር ላይ ከሚሳተፉ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን የምንለው ለምንድን ነው?
13 በግሪክ ይካሄዱ በነበሩ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ሯጮች እንደ ድካም ወይም ሕመም ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ነበረባቸው። ሩጫውን በጽናት ለመጨረስ የሚረዳቸው ያገኙት ሥልጠናና አካላዊ ጥንካሬያቸው ብቻ ነበር። እኛም እንደነዚህ ሯጮች ሁሉ እንዴት መሮጥ እንዳለብን ሥልጠና እናገኛለን። ሆኖም ከእነዚህ ሯጮች በተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። የማይነጥፍ የኃይል ምንጭ ባለቤት የሆነው አምላካችን ኃይል ይሰጠናል። ይሖዋ በእሱ የምንታመን ከሆነ ሥልጠና እንደሚሰጠን ብቻ ሳይሆን እንደሚያጠነክረንም ቃል ገብቶልናል።—1 ጴጥ. 5:10
14. በ2 ቆሮንቶስ 12:9, 10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ነበረበት። ከሚደርስበት ፌዝና ስደት በተጨማሪ ድካም የሚሰማው ጊዜ ነበር፤ እንዲሁም “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ብሎ ከጠራው ነገር ጋር መታገል ነበረበት። (2 ቆሮ. 12:7) ይሁንና እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተስፋ እንዲያስቆርጡት ከመፍቀድ ይልቅ በይሖዋ ለመታመን እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10ን አንብብ።) ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ስለነበረው ያጋጠሙትን ችግሮች ሁሉ እንዲቋቋም ይሖዋ ረድቶታል።
15. የጳውሎስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ምን አጋጣሚ እናገኛለን?
15 እኛም በእምነታችን ምክንያት ፌዝ ወይም ስደት ሊደርስብን ይችላል። አሊያም ደግሞ የጤና እክል ይገጥመን ወይም ድካም ይሰማን ይሆናል። የጳውሎስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ግን እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የይሖዋን ፍቅራዊ ድጋፍ የምናይባቸው አጋጣሚዎች ይሆናሉ።
16. የአቅም ገደብ ቢኖርብህም እንኳ ምን ማድረግ ትችላለህ?
16 የአልጋ ቁራኛ ሆነሃል? ወይም የምትንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ነው? ጉልበትህ ወይም ዓይንህ ደክሟል? ታዲያ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ወጣትና ጤናማ ከሆኑት ጋር አብረህ መሮጥ ትችላለህ? አዎ፣ ትችላለህ! በዕድሜ የገፉና የአቅም ገደብ ያለባቸው በርካታ ክርስቲያኖች ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እየሮጡ ነው። ይህን ማድረግ የቻሉት በራሳቸው ኃይል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሚሰጣቸውን ኃይል ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ በስልክ ወይም በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን መከታተል ነው። በተጨማሪም ለሐኪሞች፣ ለነርሶችና ለዘመዶቻቸው በመመሥከር ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይካፈላሉ።
17. ይሖዋ የአቅም ገደብ ላለባቸው ክርስቲያኖች ምን አመለካከት አለው?
መዝ. 9:10) እንዲያውም ይበልጥ ወደ አንተ ይቀርባል። ተፈታታኝ የጤና እክሎች ያሉባት አንዲት እህት የሰጠችውን ሐሳብ ልብ በል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ያሉብኝ የጤና ችግሮች እየተባባሱ በመሄዳቸው እንደ በፊቱ እውነትን ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ የለኝም። የማደርገው ጥረት አነስተኛ ቢሆንም እንኳ የይሖዋን ልብ ደስ እንደሚያሰኘው ግን አውቃለሁ፤ ይህም ደስታ ይሰጠኛል።” እንግዲያው ተስፋ ስትቆርጥ፣ ብቻህን እንዳልሆንክ አስታውስ። ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ አስብ፤ እንዲሁም “በድክመት . . . ደስ እሰኛለሁ። ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና” በማለት የተናገረውን የሚያበረታታ ሐሳብ አትርሳ።—2 ቆሮ. 12:10
17 ባለብህ የአቅም ገደብ የተነሳ በሕይወት መንገድ ላይ ለመሮጥ የሚያስችል አቅም እንደሌለህ በማሰብ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ስላለህና ቀደም ሲል እሱን ለማገልገል ስትል ብዙ ስለደከምክ ይወድሃል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የእሱ እርዳታ የሚያስፈልግህ አሁን ነው፤ እሱም ፈጽሞ አይተውህም። (18. አንዳንዶች ምን ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?
18 ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ የሚሮጡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ሌሎች ሊያዩ ከማይችሉት፣ ምናልባትም ከማይረዱት የግል ችግር ጋር እየታገሉ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመንፈስ ጭንቀት ወይም በከፍተኛ የስሜት ቀውስ ይሠቃያሉ። እነዚህ ውድ የይሖዋ አገልጋዮች እየገጠማቸው ያለው ችግር በጣም ከባድ የሆነው ለምንድን ነው? እጁ የተሰበረ ወይም በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀስ ሰው ችግሩ ለሌሎች የሚታይ ስለሆነ ሰዎች እርዳታ ሊያደርጉለት ይነሳሳሉ። ስሜታዊ ወይም አእምሯዊ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ግን መታመማቸው የሚታወቅበት ውጫዊ ምልክት ላይኖር ይችላል። የእነዚህ ሰዎች ሥቃይ፣ አካላዊ ሕመም ያጋጠማቸውን ሰዎች ያህል ከባድ ቢሆንም ተመሳሳይ እርዳታና እንክብካቤ ላያገኙ ይችላሉ።
19. ሜፊቦስቴ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?
19 አቅም የሚያሳጣ ችግር ቢኖርብህም ሌሎች ችግርህን እንደማይረዱልህ ከተሰማህ የሜፊቦስቴ ምሳሌ ያበረታታሃል። (2 ሳሙ. 4:4) ሜፊቦስቴ የአካል ጉዳተኛ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ንጉሥ ዳዊት በተሳሳተ መንገድ ስለተረዳው በደል አድርሶበታል። ሜፊቦስቴ እነዚህ ነገሮች የደረሱበት በእሱ ጥፋት አይደለም። ያም ቢሆን በደረሱበት ነገሮች የተነሳ ምሬት እንዲያድርበት አልፈቀደም፤ ከዚህ ይልቅ በሕይወቱ ላጋጠሙት መልካም ነገሮች አድናቆት ነበረው። ንጉሥ ዳዊት ቀደም ሲል ላሳየው ደግነትም አመስጋኝ ነበር። (2 ሳሙ. 9:6-10) በመሆኑም ዳዊት በተሳሳተ መንገድ ተረድቶት በበደለው ወቅት ነገሩን ሰፋ አድርጎ ለመመልከት ጥረት አድርጓል። ሜፊቦስቴ፣ ዳዊት የሠራው ስህተት እንዲመረር አላደረገውም። እንዲሁም ዳዊት ባደረገበት ነገር የተነሳ ይሖዋን አልወቀሰም። ሜፊቦስቴ ትኩረት ያደረገው ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ ለመደገፍ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ነበር። (2 ሳሙ. 16:1-4፤ 19:24-30) ይሖዋ ግሩም የሆነው የሜፊቦስቴ ታሪክ በቃሉ ውስጥ እንዲመዘገብ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው።—ሮም 15:4
20. አንዳንዶች ባጋጠማቸው የስሜት ቀውስ የተነሳ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ይገጥማቸዋል? ሆኖም ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?
20 አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ባጋጠማቸው የስሜት ቀውስ የተነሳ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከሰዎች ጋር መሆን በጣም ሊያስጨንቃቸውና ሊያስፈራቸው ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች ብዙ ሰው ባለበት ቦታ መገኘት ቢከብዳቸውም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። የማያውቁትን ሰው ማነጋገር ቢጨንቃቸውም አገልግሎት ወጥተው ለሰዎች ይመሠክራሉ። አንተም እንዲህ ካለ ተፈታታኝ ሁኔታ ጋር እየታገልክ ከሆነ እንዲህ ያለ ችግር የሚገጥምህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አትርሳ። ብዙዎች ተመሳሳይ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው። ይሖዋ በሙሉ ነፍስ በምታደርገው ጥረት እንደሚደሰት አስታውስ። ችግሮች ቢኖሩም ተስፋ አለመቁረጥህ በራሱ ይሖዋ እየባረከህና የሚያስፈልግህን ጥንካሬ እየሰጠህ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። * (ፊልጵ. 4:6, 7፤ 1 ጴጥ. 5:7) አካላዊ ወይም ስሜታዊ የጤና እክሎችን ተቋቁመህ ይሖዋን የምታገለግል ክርስቲያን ከሆንክ ይሖዋ በአንተ እንደሚደሰት አትጠራጠር።
21. በይሖዋ እርዳታ ሁላችንም ምን ማድረግ እንችላለን?
21 ጳውሎስ የተናገረለት ሩጫ ቃል በቃል ከሚደረገው የሩጫ ውድድር የሚለይባቸው ነገሮች መኖራቸው ያስደስታል። በጥንት ዘመን በሚካሄዱ የሩጫ ውድድሮች ላይ ሽልማቱን የሚያገኘው አንድ ሰው ብቻ ነበር። ከዚህ በተለየ መልኩ በክርስትና ጎዳና ላይ የሚሮጡ ሁሉ እስከ መጨረሻው ከጸኑ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያገኛሉ። (ዮሐ. 3:16) ቃል በቃል በሚደረግ የሩጫ ውድድር ላይ ሁሉም ሯጮች ጥሩ አካላዊ ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፤ አለዚያ በውድድሩ የማሸነፍ አጋጣሚያቸው በጣም ጠባብ ነው። በተቃራኒው ብዙዎቻችን አቅማችንን የሚገድቡ ነገሮች እያሉም ሩጫችንን ቀጥለናል። (2 ቆሮ. 4:16) በይሖዋ እርዳታ ሁላችንም ሩጫውን መጨረስ እንችላለን!
መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!
^ አን.5 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች ወይም አቅም ከሚያሳጣ ሕመም ጋር ይታገላሉ። ደግሞም ሁላችንም አልፎ አልፎ ድካም ይሰማናል። ከዚህ አንጻር በሩጫ ውድድር መሳተፍ ለእኛ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይህ ርዕስ፣ ሁላችንም በጽናት መሮጥና ሐዋርያው ጳውሎስ በጠቀሰው የሕይወት ሩጫ አሸናፊ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
^ አን.6 በጥር 1, 2013 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.20 የስሜት ቀውስን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንዲሁም በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ክርስቲያኖችን ተሞክሮ ለማየት jw.org® ላይ የወጣውን የግንቦት 2019 ብሮድካስቲንግ ፕሮግራም ተመልከት። ቪዲዮው ላይብረሪ > JW ብሮድካስቲንግ በሚለው ሥር ይገኛል።