በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 16

አዳምጧቸው፣ እወቋቸው እንዲሁም ርኅራኄ አሳዩአቸው

አዳምጧቸው፣ እወቋቸው እንዲሁም ርኅራኄ አሳዩአቸው

“የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።”—ዮሐ. 7:24

መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት

ማስተዋወቂያ *

1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን የሚያጽናና እውነታ ይዟል?

ሰዎች የቆዳህን ቀለም፣ መልክህን ወይም ቁመናህን በማየት ብቻ ስለ አንተ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ቢደርሱ ደስ ይልሃል? ደስ እንደማይልህ የታወቀ ነው። ይሖዋ እንደ ሰዎች ከውጭ በሚታይ ነገር ላይ ተመሥርቶ የማይፈርድ መሆኑ ምንኛ ያጽናናል! ለምሳሌ ያህል፣ ሳሙኤል የእሴይን ልጆች የተመለከተው ይሖዋ በሚያይበት መንገድ አልነበረም። ይሖዋ ከእሴይ ልጆች አንዱ የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆን ለሳሙኤል ነግሮት ነበር። ይሁንና ይሖዋ የመረጠው የትኛውን የእሴይ ልጅ ነው? ሳሙኤል፣ የእሴይ የበኩር ልጅ የሆነውን ኤልያብን ሲመለከት “መቼም ይሖዋ የሚቀባው ሰው ይህ መሆን አለበት” አለ። ኤልያብ የንጉሥ ዓይነት አቋም ነበረው። “ሆኖም ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘እኔ ስላልተቀበልኩት መልኩንና የቁመቱን ርዝማኔ አትይ።’” ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ አክሎ ሲናገር “ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው” ብሏል።—1 ሳሙ. 16:1, 6, 7

2. በዮሐንስ 7:24 ላይ የተገለጸውን መመሪያ በመከተል የሰውን ውጫዊ ገጽታ ተመልክተን መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

2 ፍጹማን ባለመሆናችን ሁላችንም የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ ተመልክተን መፍረድ ይቀናናል። (ዮሐንስ 7:24ን አንብብ።) ሆኖም ከውጭ በሚታየው ነገር ብቻ ስለ አንድ ሰው ልናውቅ የምንችለው ነገር በጣም ውስን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ ችሎታ ያለውና ተሞክሮ ያካበተ ሐኪምም እንኳ ታካሚውን ከውጭ በመመልከት ብቻ ሊያውቅ የሚችለው ነገር ጥቂት ነው። የታካሚውን የሕክምና ታሪክ፣ ያለበት ሁኔታ ያሳደረበትን ስሜት ወይም በእሱ ላይ ስለሚታዩት የበሽታ ምልክቶች ሊያውቅ የሚችለው ታካሚውን በጥሞና ካዳመጠው ነው። እንዲያውም ሐኪሙ፣ የታካሚውን ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎች ለማየት ምርመራ ያዝለት ይሆናል። አለዚያ ግን ሐኪሙ የግለሰቡን ሕመም በተመለከተ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊደርስ ይችላል። እኛም በተመሳሳይ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ውጫዊ ገጽታ በመመልከት ብቻ ስለ እነሱ በሚገባ ማወቅ አንችልም። ከውጭ ከሚታየው ነገር አልፈን ውስጣዊ ማንነታቸውን ለማወቅ መጣር ይኖርብናል። በእርግጥ የሰዎችን ልብ ማንበብ ስለማንችል የይሖዋን ያህል ሙሉ በሙሉ ስሜታቸውን ልንረዳ አንችልም። ሆኖም ይሖዋን ለመምሰል የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዴት?

3. በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ይሖዋን ለመምሰል የሚረዱን እንዴት ነው?

3 ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው እንዴት ነው? ያዳምጣቸዋል። በማንነታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ነገሮችንና ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባል። እንዲሁም ርኅራኄ ያሳያቸዋል። ይሖዋ ዮናስን፣ ኤልያስን፣ አጋርንና ሎጥን በዚህ መንገድ የያዛቸው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት፤ በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።

በጥሞና አዳምጧቸው

4. ስለ ዮናስ አሉታዊ አመለካከት ሊያድርብን የሚችለው ለምንድን ነው?

4 ዮናስ ስለነበረበት ሁኔታ ካለን ውስን እውቀት የተነሳ፣ እምነት የማይጣልበት አልፎ ተርፎም ታዛዥ ያልሆነ ሰው ነው ብለን እንፈርድበት ይሆናል። ዮናስን ወደ ነነዌ ሄዶ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ያዘዘው ይሖዋ ራሱ ነው። ዮናስ ግን ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ መርከብ ተሳፍሮ በተቃራኒ አቅጣጫ ‘ከይሖዋ ፊት ሸሸ።’ (ዮናስ 1:1-3) እናንተ ብትሆኑ ኖሮ ዮናስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሌላ አጋጣሚ ትሰጡት ነበር? አትሰጡት ይሆናል። ይሖዋ ግን ዮናስ ሌላ አጋጣሚ ቢያገኝ የተሻለ እንደሆነ ተሰምቶታል።—ዮናስ 3:1, 2

5. በዮናስ 2:1, 2, 9 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ጸሎት ስለ ዮናስ ምን ያስተምረናል?

5 ዮናስ በአንድ ወቅት ያቀረበው ጸሎት ስለ እሱ ትክክለኛ ማንነት ፍንጭ ይሰጠናል። (ዮናስ 2:1, 2, 9ን አንብብ።) ዮናስ ብዙ ጸሎቶች አቅርቦ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም በዚህ ወቅት ያቀረበው ጸሎት፣ የተሰጠውን ተልእኮ ትቶ እንደሸሸ ሰው ብቻ አድርገን እንዳንመለከተው ይረዳናል። ዮናስ የተጠቀመባቸው ቃላት ትሑት፣ አመስጋኝ እና ይሖዋን ለመታዘዝ የቆረጠ ሰው እንደነበረ ያሳያሉ። ከዚህ አንጻር ይሖዋ፣ ዮናስ በሠራቸው ስህተቶች ላይ አለማተኮሩ፣ ለጸሎቱ መልስ መስጠቱና እሱን ነቢይ አድርጎ መጠቀሙን መቀጠሉ ምንም አያስገርምም!

እውነታውን ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን ይበልጥ አዛኝ እንድንሆን ያስችለናል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት) *

6. ሌሎችን በጥሞና ለማዳመጥ ጥረት ማድረጋችን ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

6 ሌሎችን በጥሞና ለማዳመጥ ትሑትና ታጋሽ መሆን ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን ቢያንስ ሦስት ጥቅሞች ያስገኛል። አንደኛ፣ ስለ ሰዎች በችኮላ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ ይረዳናል። ሁለተኛ፣ የወንድማችንን ስሜትና አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳበትን ምክንያት ስለምንረዳ ይበልጥ እንድናዝንለት ያደርገናል። ሦስተኛ፣ ግለሰቡ ስለ ራሱ ቀደም ሲል የማያውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች እንዲገነዘብ ልንረዳው እንችላለን። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ፣ የራሳችንን ስሜት በትክክል መረዳት የምንችለው በቃላት ስንገልጸው ብቻ ነው። (ምሳሌ 20:5) በእስያ ያለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “በአንድ ወቅት፣ ከማዳመጤ በፊት በመናገር ስህተት ሠርቼ ነበር። ለአንዲት እህት በስብሰባ ላይ የምትሰጣቸውን መልሶች ጥራት እንድታሻሽል ምክር ሰጠኋት። ከጊዜ በኋላ ግን፣ ይህች እህት ማንበብ እንደምትቸገርና በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅባት አወቅኩ።” በእርግጥም ሁሉም ሽማግሌዎች ‘እውነታውን ከመስማታቸው’ በፊት ምክር አለመስጠታቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ምሳሌ 18:13

7. ይሖዋ ኤልያስን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአስተዳደጋቸው፣ በባሕላቸው ወይም በባሕርያቸው የተነሳ ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ይከብዳቸዋል። ታዲያ የልባቸውን አውጥተው መናገር እንዲቀላቸው ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ኤልያስ ከኤልዛቤል ሸሽቶ በሄደበት ወቅት ይሖዋ ምን እንዳደረገለት ለማስታወስ ሞክሩ። ኤልያስ በሰማይ ላለው አባቱ የውስጡን አውጥቶ የተናገረው ከበርካታ ቀናት በኋላ ነው። ይሖዋም በጥሞና አዳምጦታል። ከዚያም ኤልያስን ያበረታታው ሲሆን በጣም አስፈላጊ ሥራ እንዲያከናውን ኃላፊነት ሰጠው። (1 ነገ. 19:1-18) በተመሳሳይም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በነፃነት የውስጣቸውን የሚነግሩን የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና እውነተኛ ስሜታቸውን ማወቅ የምንችለው እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች ሲሆኑ ብቻ ነው። ታጋሽ በመሆን ይሖዋን የምንመስል ከሆነ የወንድሞቻችንን አመኔታ ማትረፍ እንችላለን። በኋላ ላይ ስሜታቸውን አውጥተው ለመናገር ዝግጁ እንደሆኑ ሲሰማቸው ደግሞ በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብናል።

ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በደንብ እወቋቸው

8. በዘፍጥረት 16:7-13 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ አጋርን የረዳት እንዴት ነው?

8 የሦራ አገልጋይ የሆነችው አጋር፣ የአብራም ሚስት ከሆነች በኋላ የሞኝነት ድርጊት ፈጽማለች። አጋር ከፀነሰች በኋላ መሃን የሆነችውን ሦራን መናቅ ጀመረች። ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ አጋር፣ ሦራ ባደረሰችባት ነገር የተነሳ ኮበለለች። (ዘፍ. 16:4-6) ፍጹማን ባለመሆናችን አጋር ትዕቢተኛ ሴት እንደሆነችና የእጇን እንዳገኘች ይሰማን ይሆናል። ይሖዋ ግን ስለ አጋር እንዲህ አልተሰማውም። እንዲያውም መልአኩን ላከላት። መልአኩ ወደ አጋር መጥቶ አመለካከቷን እንድታስተካክል ረዳት፤ እንዲሁም ባረካት። አጋር፣ ይሖዋ እንደሚመለከታትና ያለችበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚያውቅ ተገንዝባለች። በመሆኑም ስለ ይሖዋ “አንተ የምታይ አምላክ ነህ” ብላ ለመናገር ተገፋፍታለች።ዘፍጥረት 16:7-13ን አንብብ።

9. አምላክ ከአጋር ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ አስገብቷል?

9 ይሖዋ ስለ አጋር ያስተዋለው ነገር ምንድን ነው? አስተዳደጓንና የቀድሞ ሕይወቷን እንዲሁም ያጋጠማትን ነገር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። (ምሳሌ 15:3) አጋር ግብፃዊት ብትሆንም የምትኖረው በዕብራውያን ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ታዲያ አንዳንድ ጊዜ የባይተዋርነት ስሜት ይሰማት ይሆን? ቤተሰቧና የትውልድ አገሯ ይናፍቋት ይሆን? በዚህ ላይ ደግሞ አጋር፣ የአብራም ሁለተኛ ሚስት ነበረች። በዚያ ዘመን አንዳንድ ታማኝ ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡ ነበር። ሆኖም ይህ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የነበረ ነገር አይደለም። (ማቴ. 19:4-6) በመሆኑም እንዲህ ያለው የቤተሰብ ሕይወት ቅናትና ጥላቻ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑ አያስገርምም። ይሖዋ፣ አጋር ለሦራ ያሳየችውን ንቀት ችላ ብሎ ባያልፍም የአጋርን አስተዳደግና የቀድሞ ሕይወት እንዲሁም ሁኔታዋን ግምት ውስጥ እንዳስገባ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ (ከአንቀጽ 10-12⁠ን ተመልከት) *

10. ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ይበልጥ ለማወቅ ምን ማድረግ እንችላለን?

10 እኛም አንዳችን ሌላውን ለመረዳት ጥረት በማድረግ የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችላለን። እንግዲያው ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በደንብ እወቋቸው። ከስብሰባ በፊትና በኋላ ከእነሱ ጋር ተጨዋወቱ፤ አብራችሁ አገልግሉ፤ እንዲሁም የሚቻል ከሆነ ቤታችሁ ጋብዟቸው። እንዲህ ስታደርጉ፣ የማትቀረብ የምትመስላችሁ እህት ዓይን አፋር እንደሆነች፣ ቁሳዊ ነገር እንደሚወድ የሚሰማችሁ ወንድም ለጋስ እንደሆነ ወይም ደግሞ ብዙ ጊዜ ስብሰባ ላይ አርፍዶ የሚገኝ አንድ ቤተሰብ ተቃውሞን እየተቋቋመ እንደሆነ ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። (ኢዮብ 6:29) እርግጥ ነው፣ ‘በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ መግባት’ የለብንም። (1 ጢሞ. 5:13) ያም ቢሆን ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም በባሕርያቸው ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩት ነገሮች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማወቃችን ጠቃሚ ነው።

11. ሽማግሌዎች በጎቹን በሚገባ ማወቃቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 በተለይም ሽማግሌዎች በእነሱ እንክብካቤ ሥር ያሉትን ወንድሞችና እህቶች አስተዳደግ እንዲሁም የቀድሞ ሕይወት ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል የነበረውን የአርተርን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አርተር ከአንድ ሽማግሌ ጋር ሆኖ ለአንዲት እህት የእረኝነት ጉብኝት አድርጎላት ነበር፤ ይህች እህት ዓይን አፋርና ከሌሎች ጋር መቀራረብ የማትፈልግ ትመስል ነበር። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “እህት ባሏን በሞት ያጣችው ከተጋቡ ብዙም ሳይቆይ እንደሆነ ተገነዘብን። የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟትም ሁለት ሴቶች ልጆቿን በመንፈሳዊ ጠንካራ አድርጋ አሳድጋለች። አሁን ግን ዓይኗ እየደከመ የመጣ ሲሆን በመንፈስ ጭንቀት ትሠቃያለች። ያም ቢሆን ለይሖዋ ያላት ፍቅርና በእሱ ላይ ያላት እምነት ፈጽሞ አልተዳከመም። ይህች እህት ከተወችው ጥሩ ምሳሌ ብዙ የምንማረው ነገር እንዳለ አስተዋልን።” (ፊልጵ. 2:3) ይህ የወረዳ የበላይ ተመልካች የይሖዋን ምሳሌ ተከትሏል። ይሖዋ በጎቹን እንዲሁም እየደረሰባቸው ያለውን ሥቃይ በሚገባ ያውቃል። (ዘፀ. 3:7) ሽማግሌዎችም በጎቹን በሚገባ የሚያውቁ ከሆነ እነሱን በተሻለ መንገድ መርዳት ይችላሉ።

12. አንዲት እህት በጉባኤዋ ውስጥ የምትገኝን ሌላ እህት በሚገባ ለማወቅ ጥረት ማድረጓ ምን ጥቅም አስገኝቶላታል?

12 አንድ የእምነት አጋራችሁ የሚያበሳጫችሁ ከሆነ ስለ አስተዳደጉና ስለ ቀድሞ ሕይወቱ ማወቃችሁ እንድታዝኑለት ሊረዳችሁ ይችላል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በእስያ ያለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤዬ ያለች አንዲት እህት ስታወራ በጣም ትጮኻለች። በዚህም የተነሳ ጥሩ ምግባር እንደሌላት ይሰማኝ ነበር። አብረን ስናገለግል ግን፣ ይህች እህት ገበያ ውስጥ ዓሣ በመሸጥ ወላጆቿን ትረዳ እንደነበር ተገነዘብኩ። ደንበኞችን ለመሳብ ጮክ ብላ መጣራት ያስፈልጋት ነበር።” እህት አክላ ስትናገር “ወንድሞቼንና እህቶቼን ለመረዳት አስተዳደጋቸውንና የቀድሞ ሕይወታቸውን በሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልገኝ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች። ወንድሞቻችሁን በደንብ ማወቅ የምትችሉት ጥረት ካደረጋችሁ ብቻ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን ወለል አድርገን እንድንከፍት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ የሚወደውን ይሖዋን መምሰል ትችላላችሁ።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ 2 ቆሮ. 6:11-13

ርኅራኄ አሳዩአቸው

13. በዘፍጥረት 19:15, 16 ላይ እንደተገለጸው ሎጥ በዘገየበት ወቅት መላእክቱ ምን አደረጉ? ለምንስ?

13 ሎጥ በሕይወቱ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ የይሖዋን መመሪያ ለመታዘዝ ዘግይቶ ነበር። ሁለት መላእክት ወደ ሎጥ ሄደው ቤተሰቡን ይዞ ከሰዶም እንዲወጣ ነገሩት። ለምን? መላእክቱ “ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው” በማለት ነገሩት። (ዘፍ. 19:12, 13) ሎጥና ቤተሰቡ ግን በቀጣዩ ቀን ማለዳ ላይም ከቤታቸው አልወጡም። በመሆኑም መላእክቱ ሎጥን እንደገና አስጠነቀቁት። ሎጥ ግን “ዘገየ።” ሎጥ ለይሖዋ ትእዛዝ ግድ እንደሌለው እንዲያውም ታዛዥ እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሖዋ ግን ተስፋ አልቆረጠበትም። “ይሖዋ ስለራራለት” መላእክቱ የእሱንና የቤተሰቡን እጅ ይዘው ከከተማዋ እንዲያስወጧቸው አደረገ።ዘፍጥረት 19:15, 16ን አንብብ።

14. ይሖዋ ለሎጥ የራራለት ለምን ሊሆን ይችላል?

14 ይሖዋ ለሎጥ እንዲራራ ያነሳሱት አንዳንድ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ሎጥ ቤቱን ለቆ ለመውጣት ያመነታው ከከተማዋ ውጭ የሚኖሩ ሰዎችን ስለፈራ ሊሆን ይችላል። ሎጥን ሊያሰጉት የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም ነበሩ። ሎጥ፣ በሰዶም አቅራቢያ ባለ አንድ ሸለቆ ውስጥ በቅጥራን ጉድጓዶች ውስጥ ስለወደቁት ሁለት ነገሥታት ሳይሰማ አይቀርም። (ዘፍ. 14:8-12) ሎጥ ባልና አባት እንደመሆኑ መጠን የቤተሰቡ ሁኔታ አሳስቦት መሆን አለበት። በተጨማሪም ሎጥ ባለጸጋ ሆኖ ነበር፤ በመሆኑም ሰዶም ውስጥ ጥሩ ቤት ሠርቶ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 13:5, 6) በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በሙሉ ሎጥ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ወዲያውኑ እንዳይታዘዝ ሰበብ ሊሆኑ አይችሉም። ይሁንና ይሖዋ፣ ሎጥ በሠራው ስህተት ላይ አላተኮረም፤ ከዚህ ይልቅ ሎጥን “ጻድቅ ሰው” አድርጎ ቆጥሮታል።—2 ጴጥ. 2:7, 8

በጥሞና ማዳመጣችን፣ ለሌሎች ርኅራኄ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. አንድን ሰው በፈጸመው ድርጊት የተነሳ በእሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 አንድን ሰው በፈጸመው ድርጊት የተነሳ በእሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ ስሜቱን ለመረዳት የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ። በአውሮፓ ያለች ቬሮኒካ የተባለች እህት እንዲህ ለማድረግ ጥራለች። እንዲህ ብላለች፦ “አንዲት እህት ፊቷ የማይፈታ ነው። ከሌሎች ጋር ለመቀላቀል አትሞክርም። አንዳንድ ጊዜ እሷን ቀርቤ ማነጋገር ያስፈራኛል። ሆኖም ‘እኔ በእሷ ቦታ ብሆን ኖሮ እኮ ጓደኛ ያስፈልገኝ ነበር’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ምን እንደሚሰማት ለመጠየቅ ወሰንኩ። እሷም የውስጧን አውጥታ ትነግረኝ ጀመር። አሁን ስለ እሷ ብዙ ነገር አውቄያለሁ።”

16. ለሌሎች አዛኝ መሆን እንድንችል መጸለይ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

16 ሙሉ በሙሉ ስሜታችንን ሊረዳ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ምሳሌ 15:11) በመሆኑም ሌሎችን እሱ በሚያይበት መንገድ መመልከትና ለእነሱ ርኅራኄ ማሳየት የምትችሉበትን መንገድ ማስተዋል እንድትችሉ የእሱን እርዳታ ጠይቁ። ጸሎት፣ አንዥላ የተባለችን እህት ይበልጥ አዛኝ እንድትሆን ረድቷታል። አንዥላ በጉባኤዋ ውስጥ ካለች አንዲት እህት ጋር መግባባት ከብዷት ነበር። እንዲህ ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች፦ “እህትን ለመንቀፍና ከእሷ ለመሸሽ በጣም ተፈትኜ ነበር። በኋላ ግን የዚህችን እህት ስሜት መረዳት እንድችል ይሖዋን በጸሎት ጠየቅኩት።” ታዲያ ይሖዋ ለጸሎቷ መልስ ሰጣት? አንዥላ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን አገልግሎት አብረን ወጣንና ከጨረስን በኋላ ለረጅም ሰዓት አወራን። በርኅራኄ አዳመጥኳት። አሁን ለዚህች እህት ያለኝ ፍቅር ጨምሯል፤ እሷን ለመርዳትም ፍላጎት አለኝ።”

17. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

17 ማንንም ሳንመርጥ ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ርኅራኄ የማሳየት ግዴታ አለብን። ሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደ ዮናስ፣ ኤልያስ፣ አጋርና ሎጥ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ችግሮች የሚደርሱባቸው በራሳቸው ስህተት የተነሳ ሊሆን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምንገባበት ጊዜ አለ። በመሆኑም ይሖዋ አንዳችን የሌላውን ስሜት እንድንረዳ መጠየቁ ምክንያታዊ ነው። (1 ጴጥ. 3:8) በዚህ ረገድ ይሖዋን የምንታዘዝ ከሆነ ከተለያየ ቦታ ለተሰባሰበውና አስደናቂ ለሆነው ዓለም አቀፋዊ ቤተሰባችን አንድነት አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እንግዲያው ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት እነሱን ለማዳመጥ፣ ይበልጥ ለማወቅና ለእነሱ ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት እናድርግ።

መዝሙር 87 ኑ! እረፍት አግኙ

^ አን.5 ፍጹማን ባለመሆናችን ከሰዎችና አንድን ነገር ለማድረግ ከሚያነሳሳቸው ምክንያት ጋር በተያያዘ ቸኩለን አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቀናናል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ “የሚያየው ልብን ነው።” (1 ሳሙ. 16:7) ይህ ርዕስ፣ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ዮናስን፣ ኤልያስን፣ አጋርንና ሎጥን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት የይሖዋን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ በዕድሜ የገፋ አንድ ወንድም፣ አንድ ወጣት ወንድም ወደ ስብሰባ አርፍዶ ስለመጣ ተበሳጭቶ ነበር፤ ሆኖም ወጣቱ ወንድም ያረፈደው የመኪና አደጋ ገጥሞት እንደሆነ በኋላ ላይ ተረዳ።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ የአገልግሎት ቡድን የበላይ ተመልካች የሆነ አንድ ወንድም፣ አንደኛዋ እህት ከሌሎች ጋር የማትቀራረብና ኩሩ እንደሆነች ተሰምቶት ነበር፤ በኋላ ግን እህት ዓይን አፋር እንደሆነችና ያን ያህል ከማታውቃቸው ሰዎች ጋር ስትሆን እንደሚጨንቃት ተገነዘበ።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘቻት ሌላ እህት ነጭናጫና አሳቢነት የጎደላት እንደሆነች ተሰምቷት ነበር፤ በኋላ ግን ከእሷ ጋር ጊዜ ማሳለፏ ስለ እህት ያላትን አመለካከት ለማስተካከል ረድቷታል።