በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 16

ለቤዛው አድናቆት ማሳየታችሁን ቀጥሉ

ለቤዛው አድናቆት ማሳየታችሁን ቀጥሉ

‘የሰው ልጅ የመጣው በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ነው።’—ማር. 10:45

መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን

ማስተዋወቂያ *

1-2. ቤዛው ምንድን ነው? ቤዛው የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?

ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ኃጢአት ሲሠራ እሱም ሆነ ወደፊት የሚወለዱ ልጆቹ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲያጡ አድርጓል። አዳም ኃጢአት የሠራው ሆን ብሎ ስለሆነ ለድርጊቱ ምንም ማስተባበያ ሊያቀርብ አይችልም። ይሁንና ስለ ልጆቹስ ምን ማለት ይቻላል? አዳም በፈጸመው ኃጢአት የእነሱ እጅ የለበትም። (ሮም 5:12, 14) አዳም ለሠራው ኃጢአት ሞት ይገባዋል። ሆኖም ልጆቹ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎ፣ አለ! አዳም ኃጢአት ከፈጸመ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአዳም ዘሮችን ከኃጢአትና ከሞት እርግማን ለማዳን ምን እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጽ ነገር ተናገረ። (ዘፍ. 3:15) ይሖዋ እሱ በወሰነው ጊዜ “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ [እንዲሰጥ]” ልጁን ከሰማይ ወደ ምድር ይልከዋል።—ማር. 10:45፤ ዮሐ. 6:51

2 ቤዛው ምንድን ነው? ቤዛ የሚለው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበት አዳም ያጣውን ነገር ለማስመለስ ኢየሱስ የከፈለውን ዋጋ ለማመልከት ነው። (1 ቆሮ. 15:22) ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በሙሴ ሕግ ውስጥ በተገለጸው የይሖዋ የፍትሕ መሥፈርት መሠረት ሕይወት ስለ ሕይወት መከፈል ስላለበት ነው። (ዘፀ. 21:23, 24) አዳም ያጣው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ነው። ስለዚህ በአምላክ ሕግ መሠረት ፍትሕ እንዲፈጸም ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አደረገ። (ሮም 5:17) በመሆኑም በቤዛው ለሚያምኑ ሁሉ “የዘላለም አባት” ሆነ።—ኢሳ. 9:6፤ ሮም 3:23, 24

3. በዮሐንስ 14:31 እና 15:13 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ በሰማይ ላለው አባቱና ለእኛ ታላቅ ፍቅር ስላለው ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮሐንስ 14:31⁠ን እና 15:13ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነት ፍቅር ያለው መሆኑ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ለመሆን እንዲሁም የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም አነሳስቶታል። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ያን ያህል መከራ እንዲደርስበት አምላክ የፈቀደው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ለቤዛው ጥልቅ አድናቆት ስለነበረው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በአጭሩ እንመለከታለን። በመጨረሻም ለቤዛው ያለንን አመስጋኝነት እንዴት ማሳየት እንደምንችል እንዲሁም ይሖዋ እና ኢየሱስ ለከፈሉልን መሥዋዕት ያለንን አድናቆት ማሳደግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ኢየሱስ መሠቃየት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ለእኛ ቤዛ ለመሆን ሲል ምን ያህል እንደተሠቃየ አስብ (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. የኢየሱስ አሟሟት ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ።

4 ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ምን እንዳሳለፈ በዓይነ ሕሊናችን ለመሣል እንሞክር። ኢየሱስ፣ የመላእክት ሠራዊት ጥበቃ እንዲያደርግለት መጠየቅ ይችል የነበረ ቢሆንም የሮም ወታደሮች እንዲይዙት ፈቀደ፤ እነሱም ያለአንዳች ርኅራኄ ደበደቡት። (ማቴ. 26:52-54፤ ዮሐ. 18:3፤ 19:1) ሰውነትን በሚተለትል አለንጋ ገረፉት። ከዚያም በቆሰለው ጀርባው ከባድ እንጨት ተሸክሞ እንዲሄድ አደረጉ። ኢየሱስ ከባዱን እንጨት እየጎተተ ወደሚሰቀልበት ቦታ ማዝገም ጀመረ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን እንጨቱን መሸከም ስላቃተው ወታደሮቹ በአካባቢው የነበረን አንድ ሰው ጠርተው እንጨቱን እንዲሸከምለት አስገደዱት። (ማቴ. 27:32) ኢየሱስ ወደሚሰቀልበት ቦታ ሲደርስ ወታደሮቹ እጆቹንና እግሮቹን በሚስማር እንጨት ላይ ቸነከሯቸው። እንጨቱ ቀጥ ብሎ እንዲቆም ሲደረግ የሰውነቱ ክብደት ሚስማሮቹ በገቡባቸው ቦታዎች ላይ ስለሚያርፍ ሥቃዩ በጣም ይበረታል። ወዳጆቹ በሐዘን ተውጠዋል፤ እናቱም እያለቀሰች ነው፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ግን በኢየሱስ ላይ እያፌዙበት ነው። (ሉቃስ 23:32-38፤ ዮሐ. 19:25) ሰዓታት ባለፉ ቁጥር ሥቃዩ እየበረታበት ሄደ። በዚህ ሁኔታ ተሰቅሎ መቆየቱ በልቡና በሳንባው ላይ ከፍተኛ ጫና ስላሳደረ መተንፈስ እንኳ እየከበደው መጣ። ትንፋሹ ቀጥ ሊል ሲል በድል አድራጊነት የመጨረሻውን ጸሎት አቀረበ። ከዚያም ራሱን ዘንበል አድርጎ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ። (ማር. 15:37፤ ሉቃስ 23:46፤ ዮሐ. 10:17, 18፤ 19:30) በእርግጥም የኢየሱስ አሟሟት የሚያዋርድና በሥቃይ የተሞላ ነበር!

5. ኢየሱስ ከተገደለበት መንገድ ይበልጥ የከበደው ምን ነበር?

5 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከተገደለበት መንገድ ይበልጥ ሥቃይ ያስከተለበት ነገር ነበር። ኢየሱስን ይበልጥ ያስጨነቀው የተከሰሰበት ወንጀል ነው። ‘አምላክን ተሳድቧል’ በሌላ አባባል ‘ለአምላክም ሆነ ለስሙ አክብሮት የለውም’ የሚል የሐሰት ክስ ተሰንዝሮበታል። (ማቴ. 26:64-66) ኢየሱስ፣ ‘አምላክን ተሳድቧል’ በሚል ክስ እንደሚወነጀል ማሰቡ በራሱ በጣም ስላስጨነቀው አባቱ እንዲህ ካለው የውርደት አሟሟት እንዲያድነው ጠይቆ ነበር። (ማቴ. 26:38, 39, 42) ታዲያ ይሖዋ የሚወደው ልጁ ተሠቃይቶ እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው? እስቲ ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት።

6. ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

6 አንደኛ ነገር፣ ኢየሱስ አይሁዳውያንን ከእርግማን ነፃ ለማውጣት በእንጨት ላይ መሰቀል ነበረበት። (ገላ. 3:10, 13) አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ ቃል ቢገቡም ይህን ሳያደርጉ ቀርተዋል። በመሆኑም የኃጢአተኛው የአዳም ዘሮች መሆናቸው ካስከተለባቸው ኩነኔ በተጨማሪ ሌላ እርግማን ደረሰባቸው። (ሮም 5:12) አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት የሠራ ሰው ሊገደል እንደሚገባ ይገልጻል። ግለሰቡ ከተገደለ በኋላ አስከሬኑ እንጨት ላይ ሊሰቀል ይችላል። * (ዘዳ. 21:22, 23፤ 27:26) በመሆኑም ኢየሱስ እንጨት ላይ መሰቀሉ እሱን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው ብሔርም እንኳ ከእሱ መሥዋዕት ተጠቃሚ እንዲሆን አጋጣሚ ከፍቷል።

7. አምላክ ልጁ እንዲሠቃይ የፈቀደበት ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው?

7 አምላክ ልጁ እንዲሠቃይ የፈቀደበትን ሁለተኛ ምክንያት ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን በመሆን ወደፊት ለሚጫወተው ሚና ይሖዋ እያሠለጠነው ነበር። ኢየሱስ እጅግ ከባድ በሆነ ፈተና ውስጥ አምላክን መታዘዝ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። የደረሰበት ፈተና በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እርዳታ ለማግኘት “በከፍተኛ ጩኸትና እንባ” ጸልዮአል። ኢየሱስ ራሱ በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ስላለፈ ‘ፈተና ላይ ስንሆን’ ስሜታችንን ሊረዳልን እንዲሁም ‘ሊደርስልን’ ይችላል። ይሖዋ ‘በድካማችን ሊራራልን የሚችል መሐሪ ሊቀ ካህናት’ ስለሾመልን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ዕብ. 2:17, 18፤ 4:14-16፤ 5:7-10

8. አምላክ በኢየሱስ ላይ ይህን ያህል ከባድ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበት ሦስተኛው ምክንያት ምንድን ነው?

8 ሦስተኛ፣ ይሖዋ ልጁ ይህን ያህል እንዲሠቃይ የፈቀደው ለአንድ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ለማስገኘት ሲል ነው፤ ጥያቄው ‘እጅግ ከባድ የሆነ ፈተና ቢደርስበትም እንኳ ለአምላክ ታማኝ መሆን የሚችል ሰው አለ?’ የሚል ነው። ሰይጣን ‘ይህን ማድረግ የሚችል ሰው የለም!’ ባይ ነው። ይህ የአምላክ ጠላት የሰው ልጆች አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነ ተናግሯል። ደግሞም የሰው ልጆች ልክ እንደ አባታቸው እንደ አዳም ይሖዋን እንደማይወዱት ይሰማዋል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) ይሖዋ በልጁ ታማኝነት ስለተማመነ በሰው ልጆች ላይ ሊደርስ የሚችለው የመጨረሻው ከባድ ፈተና እንዲደርስበት ፈቀደ። ኢየሱስም ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አሳይቷል።

ለቤዛው ጥልቅ አድናቆት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ

9. ሐዋርያው ዮሐንስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

9 የቤዛው ትምህርት የብዙ ክርስቲያኖችን እምነት አጠናክሮላቸዋል። በመሆኑም ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም መስበካቸውን ቀጥለዋል፤ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች ተቋቁመው እስከ ዕድሜያቸው መጨረሻ ጸንተዋል። እስቲ የሐዋርያው ዮሐንስን ምሳሌ እንመልከት። ስለ ክርስቶስና ስለ ቤዛው የሚገልጸውን እውነት ምናልባትም ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በታማኝነት ሰብኳል። ዮሐንስ በ90ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ በነበረበት ወቅት ለሮም መንግሥት ስጋት እንደሚፈጥር ስለተጠረጠረ በጳጥሞስ ደሴት ላይ ታስሮ ነበር። ጥፋቱ ምን ነበር? ‘ስለ አምላክ መናገሩና ስለ ኢየሱስ መመሥከሩ’ ነው። (ራእይ 1:9) ዮሐንስ እምነትና ጽናት በማሳየት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

10. ዮሐንስ የጻፋቸው መጻሕፍት ለቤዛው አድናቆት እንደነበረው የሚያሳዩት እንዴት ነው?

10 ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው መጻሕፍት ላይ ለኢየሱስ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ለቤዛው ያለውን አድናቆት ገልጿል። በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ስለ ቤዛው ወይም ቤዛው ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ከ100 ጊዜ በላይ ጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል ዮሐንስ “ማንም ኃጢአት ቢሠራ . . . በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) የዮሐንስ መጻሕፍት ‘ስለ ኢየሱስ የመመሥከርን’ አስፈላጊነትም ያጎላሉ። (ራእይ 19:10) ዮሐንስ ለቤዛው ጥልቅ አድናቆት እንደነበረው በግልጽ ማየት ይቻላል። እኛስ ለቤዛው አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለቤዛው ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለቤዛው ልባዊ አድናቆት ካለን ኃጢአት ለመሥራት ስንፈተን ፈተናውን እንቋቋማለን (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) *

11. ፈተናን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

11 ኃጢአት ለመሥራት ስትፈተን ፈተናውን ተቋቋም። ለቤዛው ልባዊ አድናቆት ካለን እንደሚከተለው ያለ አመለካከት አናዳብርም፦ ‘መጥፎ ነገር ላለመሥራት ያን ያህል መታገል አይኖርብኝም። ኃጢአት ብፈጽም ችግር የለውም፤ ምክንያቱም ይቅርታ መጠየቅ እችላለሁ።’ ከዚህ ይልቅ መጥፎ ነገር ለማድረግ ስንፈተን ‘በፍጹም ይህን አላደርግም! ይሖዋ እና ኢየሱስ ይህን ሁሉ ካደረጉልኝ በኋላ እንዴት እንዲህ ያለ ድርጊት እፈጽማለሁ?’ እንላለን። ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ፣ ‘በፈተናው እንዳልሸነፍ እርዳኝ’ በማለት ይሖዋ ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን እንለምነዋለን።—ማቴ. 6:13

12. በ1 ዮሐንስ 3:16-18 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ወንድሞችህን እና እህቶችህን ውደድ። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መውደዳችን ለቤዛው አድናቆት እንዳለን ያሳያል። እንዴት? ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ የሰጠው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችንም ጭምር ነው። ኢየሱስ ለእነሱ ሲል ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ በጣም እንደሚወዳቸው ያሳያል። (1 ዮሐንስ 3:16-18ን አንብብ።) ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እነሱን በምንይዝበት መንገድ ነው። (ኤፌ. 4:29, 31 እስከ 5:2) ለምሳሌ፣ ሲታመሙ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥማቸው አሊያም ሌላ ከባድ መከራ ሲደርስባቸው እንረዳቸዋለን። ሆኖም አንድ የእምነት ባልንጀራችን በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ቅር ብንሰኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13. ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

13 አንድ የእምነት ባልንጀራህ ቢበድልህ ቂም ትይዛለህ? (ዘሌ. 19:18) ከሆነ የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ አድርግ፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላ. 3:13) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ባልን ቁጥር፣ ለቤዛው ልባዊ አድናቆት እንዳለን ለሰማያዊው አባታችን እያሳየነው ነው። ይሁንና ከአምላክ ላገኘነው ለዚህ ስጦታ ያለንን አድናቆት እያሳደግን መሄድ የምንችለው እንዴት ነው?

ለቤዛው ያለህን አድናቆት ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው?

14. ለቤዛው ያለንን አድናቆት ማሳደግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

14 ለቤዛው ይሖዋን አመስግነው። ጆአና የተባሉ በሕንድ የሚኖሩ የ83 ዓመት እህት እንዲህ ብለዋል፦ “በየቀኑ በጸሎቴ ላይ ስለ ቤዛው መጥቀስና ለዚህ ዝግጅት ይሖዋን ማመስገን አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል።” በግልህ በምታቀርበው ጸሎት ላይ በቀኑ ውስጥ የሠራሃቸውን ስህተቶች አስበህ ይሖዋ ይቅር እንዲልህ ጠይቀው። እርግጥ ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ የሽማግሌዎች እርዳታም ያስፈልግሃል፤ ሽማግሌዎች ጆሮ ሰጥተው ያዳምጡሃል። እንዲሁም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር ይሰጡሃል። ሽማግሌዎቹ አብረውህ በመጸለይ ይሖዋ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት በመንፈሳዊ ‘እንዲፈውስህ’ ልመና ያቀርባሉ።—ያዕ. 5:14-16

15. ስለ ቤዛው ለማንበብ እና በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 በቤዛው ላይ አሰላስል። ራጃማኒ የተባሉ አንዲት የ73 ዓመት እህት “ኢየሱስ ስለደረሰበት መከራ ሳነብ ዓይኖቼ በእንባ ይሞላሉ” ብለዋል። አንተም የአምላክ ልጅ ስለደረሰበት ከፍተኛ ሥቃይ ስታስብ በእጅጉ ታዝን ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ስለከፈለው መሥዋዕት ይበልጥ ባሰላሰልክ መጠን ለእሱም ሆነ ለአባቱ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። በቤዛው ላይ ለማሰላሰል እንዲረዳህ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ለምን ጊዜ ወስደህ አታጠናም?

ኢየሱስ የእሱን ሞት ቀለል ባለ ዝግጅት አማካኝነት ማስታወስ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቷቸዋል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. ስለ ቤዛው ሌሎችን ማስተማራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

16 ስለ ቤዛው ሌሎችን አስተምር። ስለ ቤዛው ለሌሎች በተናገርን ቁጥር ለቤዛው ያለን አድናቆት እያደገ ይሄዳል። ኢየሱስ ለእኛ ሲል መሞት ያስፈለገው ለምን እንደሆነ ለማስተማር የሚረዱ ግሩም መሣሪያዎች ተዘጋጅተውልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የሚለውን ብሮሹር ትምህርት 4 መጠቀም እንችላለን። ትምህርት 4 “ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?” የሚል ርዕስ አለው። አሊያም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? የሚለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 መጠቀም እንችላለን። የዚህ ምዕራፍ ርዕስ “ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ” የሚል ነው። በተጨማሪም በየዓመቱ በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ በመገኘት እንዲሁም ሌሎችም በዚህ በዓል ላይ እንዲገኙ በቅንዓት በመጋበዝ ለቤዛው ያለንን አድናቆት ማሳደግ እንችላለን። ይሖዋ ስለ ልጁ ሌሎችን የማስተማር መብት የሰጠን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

17. ቤዛው ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

17 በእርግጥም ለቤዛው ጥልቅ አድናቆት እንድናዳብርና አድናቆታችንን ይዘን እንድንቀጥል የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን። ቤዛው ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት እንድንችል መንገድ ከፍቶልናል። ቤዛው የዲያብሎስን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለማፈራረስ ያስችላል። (1 ዮሐ. 3:8) ቤዛው ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ለምድር የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። በምድር ላይ የሚኖሩት፣ ይሖዋን የሚወዱና እሱን የሚያገለግሉ ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። እንግዲያው ከሁሉ ለላቀው የአምላክ ስጦታ ይኸውም ለቤዛው ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች በየዕለቱ እንፈልግ!

መዝሙር 20 ውድ ልጅህን ሰጠኸን

^ አን.5 ኢየሱስ ተሠቃይቶ መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይህ ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። በተጨማሪም ለቤዛው ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ ይረዳናል።

^ አን.6 ሮማውያን ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች በእንጨት ላይ አስረው ወይም በሚስማር ቸንክረው በመስቀል የመግደል ልማድ ነበራቸው። ይሖዋም ልጁ በዚህ መንገድ እንዲገደል ፈቅዷል።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ የብልግና ምስሎች ከማየት፣ ትንባሆ ከማጨስ ወይም ጉቦ ከመቀበል ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ፈተና የተቋቋሙ ወንድሞች።