በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ልክ ከመሞቱ በፊት፣ ዳዊት በመዝሙር 22:1 ላይ የተናገራቸውን ቃላት የጠቀሰው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ልክ ከመሞቱ በፊት ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት መካከል በማቴዎስ 27:46 ላይ ያለው ሐሳብ ይገኝበታል፤ ኢየሱስ “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ብሏል። ኢየሱስ ይህን በመናገር፣ መዝሙራዊው ዳዊት በመዝሙር 22:1 የመዘገባቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርጓል። (ማር. 15:34) ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በይሖዋ ስላዘነ ወይም ለጊዜውም ቢሆን እምነቱ ስለተዳከመ እንደሆነ መደምደም ስህተት ነው። ኢየሱስ፣ መሞት ያስፈለገው ለምን እንደሆነ በሚገባ ያውቅ ነበር፤ ለመሞትም ፈቃደኛ ነበር። (ማቴ. 16:21፤ 20:28) በተጨማሪም በሚሞትበት ወቅት ይሖዋ እሱን ‘በአጥር መከለሉን’ ማቆም እንደሚኖርበት ያውቅ ነበር። (ኢዮብ 1:10) ይሖዋ ይህን ማድረጉ፣ ኢየሱስ የሚሞትበት ሁኔታ በጣም ከባድ ቢሆንም ታማኝ ሆኖ እንደሚገኝ በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጥበት አጋጣሚ እንዲያገኝ አድርጓል።—ማር. 14:35, 36

ታዲያ ኢየሱስ በዚህ መዝሙር ውስጥ ያለውን ሐሳብ የተናገረው ለምንድን ነው? ስለዚህ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ይህን እንዲል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት። *

ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ከሞት እንደማያስጥለው ለመጠቆም ይሆን? ኢየሱስ ያለይሖዋ እርዳታ ቤዛውን መክፈል ነበረበት። ኢየሱስ ሰው የነበረ ሲሆን “ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን [ለመቅመስ]” ሕይወቱን መስጠት ነበረበት።—ዕብ. 2:9

ኢየሱስ ከዚህ መዝሙር ላይ ጥቂት ቃላት የጠቀሰው ሰዎች ሙሉውን መዝሙር እንዲያስታውሱ ስለፈለገ ይሆን? በዘመኑ የነበሩ አይሁዳውያን በርካታ መዝሙሮችን በቃላቸው መያዛቸው የተለመደ ነገር ነበር። ከመዝሙሩ ላይ አንድ ስንኝ ሲጠቀስላቸው ሙሉውን መዝሙር ማስታወሳቸው አይቀርም። ኢየሱስ ከመዝሙሩ የጠቀሰው ይህን አስቦ ከሆነ አይሁዳውያን ተከታዮቹ በዚህ መዝሙር ውስጥ የሚገኙ ከእሱ ሞት ጋር የተያያዙ በርካታ ትንቢቶችን እንዲያስታውሱ ረድቷቸው መሆን አለበት። (መዝ. 22:7, 8, 15, 16, 18, 24) በተጨማሪም የመዝሙሩ የመጨረሻ ስንኞች ይሖዋን የሚያወድሱት ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ በምድር ሁሉ ላይ ንጉሥ እንደሆነ ይገልጻሉ።—መዝ. 22:27-31

ኢየሱስ ከዳዊት መዝሙር እነዚህን ቃላት የጠቀሰው ምንም ጥፋት እንዳልሠራ ለመግለጽ ይሆን? ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ሕገ ወጥ በሆነ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን ችሎቱም ‘አምላክን ሰድበሃል’ ብሎ ፈርዶበታል። (ማቴ. 26:65, 66) ይህ ችሎት ሌሊት ላይ በጥድፊያ የተሰየመ ከመሆኑም ሌላ ችሎቱ የተካሄደው በወቅቱ ከነበረው ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ ሥርዓት ጋር በሚጋጭ መንገድ ነበር። (ማቴ. 26:59፤ ማር. 14:56-59) ኢየሱስ ይህን ጥያቄ ሲጠይቅ፣ እንዲህ ዓይነት ቅጣት የሚያስበይንበት ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልሠራ እየገለጸ ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ ይህን መዝሙር የጠቀሰው፣ የመዝሙሩ ጸሐፊ የይሖዋን ሞገስ እንዳላጣ ለማመልከትም ፈልጎ ይሆን? ይሖዋ፣ ዳዊት መከራ እንዲደርስበት ቢፈቅድም ይህ መሆኑ ዳዊት የይሖዋን ሞገስ እንዳጣ አያሳይም። ዳዊት ያነሳው ጥያቄ እምነት እንደጎደለው የሚያሳይ አይደለም። ዳዊት ይህን ጥያቄ ካቀረበ በኋላ በይሖዋ የማዳን ኃይል እንደሚተማመን ገልጿል፤ ይሖዋም እሱን መባረኩን ቀጥሏል። (መዝ. 22:23, 24, 27) በተመሳሳይም ‘የዳዊት ልጅ’ የሆነው ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ እየተሠቃየ ቢሆንም ይህ መሆኑ የይሖዋን ሞገስ እንዳጣ የሚያሳይ አይደለም።—ማቴ. 21:9

ኢየሱስ ይህን ሲል፣ ንጹሕ አቋሙን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ እንዲችል ይሖዋ ጥበቃውን ማንሳት ያስፈለገው መሆኑ በጣም እንዳሳዘነው መግለጹ ይሆን? የይሖዋ ዓላማ ልጁ ተሠቃይቶ እንዲሞት አልነበረም። ኢየሱስ መሞት ያስፈለገው አዳምና ሔዋን በማመፃቸው ነው። ኢየሱስ ምንም የሠራው ጥፋት የለም፤ ሆኖም ሰይጣን ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንዲሁም የሰው ዘር ያጣውን ነገር መልሶ እንዲያገኝ የሚያስፈልገውን ቤዛ ለመክፈል ኢየሱስ ተሠቃይቶ መሞት ነበረበት። (ማር. 8:31፤ 1 ጴጥ. 2:21-24) ይህ መሆን የሚችለው ይሖዋ ለጊዜውም ቢሆን ለኢየሱስ ጥበቃ ሳያደርግ ከቀረ ብቻ ነው፤ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የገባው በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኢየሱስ ይህን ያለው ይሖዋ በዚህ መልኩ እንዲሞት የፈቀደበትን ምክንያት ተከታዮቹ እንዲያስተውሉ መርዳት ስለፈለገ ይሆን? * ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በመከራ እንጨት ላይ መሞቱ ብዙዎችን ሊያሰናክል እንደሚችል ያውቅ ነበር። (1 ቆሮ. 1:23) ሆኖም የኢየሱስ ተከታዮች መሞቱ አስፈላጊ በሆነበት ምክንያት ላይ ትኩረት ካደረጉ እሱን እንደ አዳኝ እንጂ እንደ ወንጀለኛ አይመለከቱትም።—ገላ. 3:13, 14

ኢየሱስ ይህን መዝሙር የጠቀሰበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን እየደረሰበት ያለው ነገር የይሖዋ ፈቃድ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ይህን መዝሙር ከጠቀሰ ብዙም ሳይቆይ “ተፈጸመ!” አለ። (ዮሐ. 19:30፤ ሉቃስ 22:37) በእርግጥም ይሖዋ ጥበቃውን ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ማንሳቱ ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከበትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጽም አስችሎታል። በተጨማሪም “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት” ስለ እሱ የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ለመፈጸም አስችሎታል።—ሉቃስ 24:44

^ አን.2 በተጨማሪም በዚህ መጽሔት ውስጥ በሚገኘው “ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት ተማሩ” በሚለው ርዕስ ላይ አንቀጽ 9⁠ን እና 10⁠ን ተመልከት።

^ አን.4 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የራሱን አመለካከት የማያንጸባርቁ ጥያቄዎች ወይም ሐሳቦች ያነሳበት ጊዜ ነበር። ይህን ያደረገው ተከታዮቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ለማድረግ ሲል ነው።—ማር. 7:24-27፤ ዮሐ. 6:1-5የጥቅምት 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 4-5⁠ን ተመልከት።