በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 14

‘የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ ተከተሉ’

‘የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ ተከተሉ’

“ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።”—1 ጴጥ. 2:21

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

ማስተዋወቂያ *

ኢየሱስ በጥብቅ እንድንከተለው ፈለጉን ትቶልናል (ከአንቀጽ 1-2⁠ን ተመልከት)

1-2. በ1 ጴጥሮስ 2:21 ላይ ያለውን ሐሳብ ለመረዳት የሚያስችለን የትኛው ምሳሌ ነው?

በአሸዋ በተሸፈነ አደገኛ በረሃ ውስጥ በቡድን ሆናችሁ እየተጓዛችሁ ነው እንበል። ልምድ ያለው አስጎብኚ ከፊታችሁ ሆኖ እየመራችሁ ነው። አስጎብኚው ሲራመድ በአሸዋው ላይ ኮቴውን ወይም ዱካውን እየተወ ይሄዳል። በጉዟችሁ መሃል ቀና ስትል የሚመራችሁን ሰው ማየት አቃተህ። ሆኖም በዚህ አትሸበርም። ከዚህ ይልቅ አንተም ሆንክ አብረውህ የሚጓዙት ሰዎች የአስጎብኚያችሁን ኮቴ በጥብቅ ለመከተል የተቻላችሁን ሁሉ ጥረት ታደርጋላችሁ!

2 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንደ አደገኛ በረሃ በሆነው በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እየተጓዝን ነው። ደስ የሚለው፣ ይሖዋ ፍጹም መሪ ይኸውም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጥቶናል፤ የእሱን ፈለግ በጥብቅ መከተል እንችላለን። (1 ጴጥ. 2:21) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው እዚህ ላይ ጴጥሮስ ኢየሱስን መንገድ ከሚመራ ሰው ጋር አመሳስሎታል። መንገድ የሚመራ ሰው ዱካውን እየተወ ከፊት ከፊት እንደሚሄድ ሁሉ ኢየሱስም ልንከተለው የምንችል ዱካ ወይም ፈለግ ትቶልናል። ከዚህ በመቀጠል የኢየሱስን ፈለግ መከተልን በተመለከተ የሚነሱ ሦስት ጥያቄዎችን እንመለከታለን። የኢየሱስን ፈለግ መከተል ማለት ምን ማለት ነው? የኢየሱስን ፈለግ መከተል ያለብን ለምንድን ነው? እንዲሁም የኢየሱስን ፈለግ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

የኢየሱስን ፈለግ መከተል ሲባል ምን ማለት ነው?

3. የአንድን ሰው ፈለግ መከተል ሲባል ምን ማለት ነው?

3 የአንድን ሰው ፈለግ መከተል ሲባል ምን ማለት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መሄድ’ እና ‘እግር’ የሚሉት ቃላት አንድ ሰው የሚከተለውን የሕይወት ጎዳና ለማመልከት የተሠራባቸው ጊዜ አለ። (ዘፍ. 6:9፤ ምሳሌ 4:26) አንድ ሰው የሚተወው ምሳሌ፣ ሲራመድ ከሚተወው ዱካ ወይም ፈለግ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ስለዚህ የአንድን ሰው ፈለግ መከተል ማለት አርዓያውን መከተል ወይም እሱን መምሰል ማለት ነው።

4. የኢየሱስን ፈለግ መከተል ሲባል ምን ማለት ነው?

4 ታዲያ የኢየሱስን ፈለግ መከተል ሲባል ምን ማለት ነው? በአጭር አነጋገር ምሳሌውን መከተል ማለት ነው። በጭብጡ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ እየተናገረ የነበረው ኢየሱስ መከራን በጽናት በመቋቋም ረገድ ስለተወው ምሳሌ ነው። ሆኖም ኢየሱስን መምሰል የምንችልባቸው ሌሎች ብዙ መንገዶች አሉ። (1 ጴጥ. 2:18-25) እንዲያውም ኢየሱስ በመላው ሕይወቱ ማለትም በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል።

5. ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የኢየሱስን ፍጹም ምሳሌ መከተል ይችላሉ? አብራራ።

5 ይሁንና ፍጹማን ካለመሆናችን አንጻር የኢየሱስን ምሳሌ በእርግጥ መከተል እንችላለን? በሚገባ! ጴጥሮስ ያበረታታን ‘የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል’ እንጂ ፍጹም በሆነ መንገድ እንድንከተል አለመሆኑን ልብ እንበል። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ አቅማችን በፈቀደ መጠን የኢየሱስን ፈለግ በጥንቃቄ ለመከተል ጥረት ካደረግን ሐዋርያው ዮሐንስ እንደተናገረው ‘ኢየሱስ በተመላለሰበት መንገድ መመላለስ’ እንችላለን።—1 ዮሐ. 2:6

የኢየሱስን ፈለግ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

6-7. የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳናል የምንለው ለምንድን ነው?

6 የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ አምላክን የሚያስደስት ሕይወት መምራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐ. 8:29) በመሆኑም የኢየሱስን ፈለግ ስንከተል ይሖዋን እናስደስታለን። የሰማዩ አባታችን ደግሞ የእሱ ወዳጆች ለመሆን ልባዊ ጥረት ወደሚያደርጉ ሰዎች እንደሚቀርብ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ያዕ. 4:8

7 በሁለተኛ ደረጃ ኢየሱስ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሏል። “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ማለት የቻለው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 14:9) እኛም የኢየሱስን ባሕርያትና ሌሎችን የያዘበትን መንገድ ስንኮርጅ ይሖዋን እየመሰልነው ነው፤ ለምሳሌ ኢየሱስ ለሥጋ ደዌ በሽተኛው በጣም አዝኖለታል፤ የሚያሠቃይ ሕመም የነበረባትን ሴት ስሜቷን ተረድቶላታል፤ የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡት ሰዎች ደግሞ ርኅራኄ አሳይቷል። (ማር. 1:40, 41፤ 5:25-34፤ ዮሐ. 11:33-35) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን ይበልጥ ስንመስለው ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን።

8. የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ‘ዓለምን ለማሸነፍ’ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ አብራራ።

8 የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን በዚህ ክፉ ዓለም ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 16:33) ኢየሱስ ይህን ሲል የዚህ ዓለም አስተሳሰብ፣ ግብና ምግባር ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት አለመፍቀዱን መግለጹ ነበር። ኢየሱስ ምንጊዜም ትኩረት ያደረገው ወደ ምድር በተላከበት ዋነኛ ዓላማ ይኸውም የይሖዋን ስም በማስቀደስ ላይ ነበር። እኛስ? በዚህ ዓለም ላይ ትኩረታችንን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ሆኖም እንደ ኢየሱስ ምንጊዜም የይሖዋን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ትኩረት ካደረግን እኛም ዓለምን ‘ማሸነፍ’ እንችላለን።—1 ዮሐ. 5:5

9. ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ሳንወጣ ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራናል። አንድ ሀብታም ወጣት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለበት ኢየሱስን ሲጠይቀው ኢየሱስ “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት መልሶለታል። (ማቴ. 19:16-21) ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ መሆኑን ላልተቀበሉ አንዳንድ አይሁዳውያን “በጎቼ . . . ይከተሉኛል። የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 10:24-29) በተጨማሪም ኢየሱስ የእሱን ትምህርቶች ለማወቅ ፍላጎት ላሳየውና የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል ለሆነው ለኒቆዲሞስ በእሱ “የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት” እንደሚኖረው ነግሮታል። (ዮሐ. 3:16) በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን የምናሳየው ትምህርቶቹን በተግባር በማዋልና የእሱን ምሳሌ በመከተል ነው። እንዲህ ካደረግን ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ሳንወጣ መኖር እንችላለን።—ማቴ. 7:14

የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

10. ኢየሱስን ይበልጥ ‘ለማወቅ’ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ዮሐ. 17:3)

10 የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል በመጀመሪያ እሱን ማወቅ አለብን። (ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።) ኢየሱስን “ማወቅ” ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው። ስለ ኢየሱስ ባሕርያት፣ ስለ አስተሳሰቡና ስለ መሥፈርቶቹ በመማር ከዕለት ወደ ዕለት እሱን ይበልጥ እያወቅነው መሄድ ይኖርብናል። እውነት ውስጥ የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋንና ልጁን ለማወቅ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠላችን አስፈላጊ ነው።

11. አራቱ ወንጌሎች ምን ይዘዋል?

11 ይሖዋ ልጁን እንድናውቀው ለመርዳት ሲል በፍቅር ተነሳስቶ በቃሉ ውስጥ አራቱን ወንጌሎች አካትቶልናል። ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጽ ታሪካዊ ዘገባ ይዘዋል። እነዚህ ዘገባዎች ኢየሱስ ምን እንደተናገረ፣ ምን እንዳደረገና ምን እንደተሰማው ይነግሩናል። እነዚህ አራት መጻሕፍት የኢየሱስን ምሳሌ ‘በጥሞና እንድናስብ’ ይረዱናል። (ዕብ. 12:3) በሌላ አባባል ወንጌሎች ኢየሱስ የተወውን ፈለግ ይዘዋል ሊባል ይችላል። ስለዚህ የወንጌል ዘገባዎችን በመመርመር ኢየሱስን ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ይህም የእሱን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል ይረዳናል።

12. ከወንጌሎች የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

12 ከወንጌሎች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ዘገባዎቹን ከማንበብ ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ጊዜ ወስደን በጥንቃቄ ልናጠናቸውና በጥልቀት ልናሰላስልባቸው ይገባል። (ከኢያሱ 1:8 የግርጌ ማስታወሻ ጋር አወዳድር።) በወንጌሎች ላይ ለማሰላሰልና ያነበብነውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ሁለት ዘዴዎችን እስቲ እንመልከት።

13. የወንጌል ዘገባዎች ሕያው እንዲሆኑላችሁ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

13 አንደኛ፣ የወንጌል ዘገባዎች ሕያው እንዲሆኑላችሁ አድርጉ። ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ በመሣል፣ የተከናወነውን ነገር ለማየትና ለመስማት እንዲሁም እናንተ በቦታው ብትኖሩ ኖሮ ምን ይሰማችሁ እንደነበር ለማሰብ ሞክሩ። ይህን ለማድረግ እንዲረዳችሁ የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው ጽሑፎች በመጠቀም ምርምር አድርጉ። የዘገባውን አውድ ይኸውም ከምታጠኑት ክንውን በፊትና በኋላ የተከናወኑትን ነገሮች መርምሩ። በዘገባው ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎችና ቦታዎች የሚያብራሩ መረጃዎችን ለማግኘት ሞክሩ። የምታጠኑትን ዘገባ በሌላ ወንጌል ላይ ከተጠቀሰው ተመሳሳይ ዘገባ ጋር አወዳድሩ። አንዳንድ ጊዜ አንደኛው የወንጌል ጸሐፊ ያላካተተውን ጠቃሚ ነጥብ ሌላኛው የወንጌል ጸሐፊ ያካትተዋል።

14-15. ከወንጌል ዘገባዎች የምናገኘውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

14 ሁለተኛ፣ ከወንጌል ዘገባዎች የምታገኙትን ትምህርት በሥራ ላይ አውሉ። (ዮሐ. 13:17) አንድን የወንጌል ዘገባ በሚገባ ካጠናችሁ በኋላ እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘በዚህ ዘገባ ውስጥ በሕይወቴ ተግባራዊ ላደርገው የምችለው ትምህርት አለ? ይህን ዘገባ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’ ልትረዱት የምትችሉ አንድ ሰው ለማሰብ ሞክሩ፤ ከዚያም ተስማሚ ጊዜ መርጣችሁ፣ ያገኛችሁትን ትምህርት በፍቅርና በዘዴ አካፍሉት።

15 እነዚህን ሁለት ዘዴዎች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል የሚያሳይ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስለተመለከታት ድሃ መበለት የሚገልጸውን ዘገባ እንመረምራለን።

ድሃዋ መበለት በቤተ መቅደሱ ውስጥ

16. በማርቆስ 12:41 ላይ የተጠቀሰውን ዘገባ እንዴት ትገልጸዋለህ?

16 ዘገባው ሕያው እንዲሆንላችሁ አድርጉ። (ማርቆስ 12:41ን አንብብ።) ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ ለመሣል ሞክሩ። ቀኑ ኒሳን 11, 33 ዓ.ም. ነው። ኢየሱስ ሊሞት የቀረው ጊዜ አንድ ሳምንት እንኳ አይሞላም። ኢየሱስ የቀኑን አብዛኛውን ክፍል ያሳለፈው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያስተምር ነው። የሃይማኖት መሪዎቹ ቀኑን ሙሉ ሲቃወሙት ነበር። ቀደም ሲል አንዳንዶቹ በሥልጣኑ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ከባባድ ጥያቄዎችን በማንሳት አጣብቂኝ ውስጥ ሊያስገቡት ሲሞክሩ ነበር። (ማር. 11:27-33፤ 12:13-34) አሁን ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ወደሚገኝ ሌላ ቦታ ሄዷል። ኢየሱስ የሄደው የሴቶች አደባባይ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ቦታ ላይ ሆኖ መደዳውን የተደረደሩትን የመዋጮ ሣጥኖች ማየት ይችላል። ኢየሱስ ቁጭ ብሎ በሣጥኖቹ ውስጥ መዋጮአቸውን የሚከቱትን ሰዎች መመልከት ጀመረ። በርካታ ሀብታም ሰዎች ብዙ ሳንቲሞችን በመዋጮ ሣጥኖች ውስጥ ሲከቱ ተመለከተ። የተቀመጠበት ቦታ ለሣጥኖቹ ቅርብ ከሆነ ሳንቲሞቹ ወደ ሣጥኑ ውስጥ ሲገቡ የሚፈጥሩትን የሚያቃጭል ድምፅ ሰምቶ ሊሆን ይችላል።

17. በማርቆስ 12:42 ላይ የተጠቀሰችው ድሃ መበለት ምን አድርጋለች?

17 ማርቆስ 12:42ን አንብብ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንዲት ሴት የኢየሱስን ትኩረት ሳበችው። ይህች ሴት “ድሃ መበለት” ነች። ለዚህች ሴት ኑሮ በጣም ከባድ እንደሚሆንባት ምንም ጥያቄ የለውም፤ ምናልባትም መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ለማግኘት ትቸገር ይሆናል። ያም ቢሆን ወደ አንዱ የመዋጮ ሣጥን ሄዳ ቀስ ብላ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች፤ እነዚህ ሳንቲሞች ሣጥኑ ውስጥ ሲገቡ ምንም ድምፅ አላሰሙ ይሆናል። ኢየሱስ ይህች ሴት ምን ያህል መዋጮ እንዳደረገች አውቋል፤ መዋጮ ያደረገችው በወቅቱ ከነበሩት ሳንቲሞች ሁሉ በጣም ትንሽ የሆኑትን ሁለት ሌፕተን ሳንቲሞች ነው። ሳንቲሞቹ አንዲት ድንቢጥ እንኳ አይገዙም ነበር፤ በወቅቱ ለምግብነት ከሚሸጡት ወፎች መካከል በጣም ርካሽ የሆኑት ድንቢጦች ነበሩ።

18. ማርቆስ 12:43, 44 እንደሚናገረው ኢየሱስ መበለቷ ያደረገችውን መዋጮ በተመለከተ ምን ብሏል?

18 ማርቆስ 12:43, 44ን አንብብ። ኢየሱስ ይህች መበለት ያደረገችው ነገር ልቡን በጥልቅ ነክቶታል። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ መበለቷን አሳያቸውና “[ከሁሉም] የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች” አላቸው። ቀጥሎም እንዲህ አላቸው፦ “ሁሉም [በተለይም ሀብታሞቹ] የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች።” ይህች ታማኝ መበለት በዚያ ቀን ያላትን ገንዘብ አሟጥጣ ስትሰጥ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከባት ሙሉ በሙሉ እንደምትተማመን አሳይታለች።—መዝ. 26:3

ለይሖዋ ምርጣቸውን የሚሰጡትን በማመስገን ኢየሱስን ምሰሉ (ከአንቀጽ 19-20⁠ን ተመልከት) *

19. ኢየሱስ ስለ ድሃዋ መበለት ከተናገረው ነገር ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

19 ከዘገባው የምታገኙትን ትምህርት በሥራ ላይ አውሉ። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ኢየሱስ ስለ ድሃዋ መበለት የተናገረው ነገር ምን ያስተምረኛል?’ እስቲ ስለ ድሃዋ መበለት ቆም ብላችሁ አስቡ። ይህች ሴት ለይሖዋ የበለጠ መስጠት ብትችል ደስ እንደሚላት ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን የቻለችውን ሁሉ አድርጋለች፤ ለይሖዋ ምርጧን ሰጥታዋለች። ኢየሱስም ይህች ሴት ያደረገችውን መዋጮ አባቱ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ያውቅ ነበር። ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ጠቃሚ ትምህርት ይህ ነው፦ ይሖዋ ምርጣችንን ስንሰጠው ማለትም በሙሉ ልባችንና በሙሉ ነፍሳችን ስናገለግለው በጣም ይደሰታል። (ማቴ. 22:37፤ ቆላ. 3:23) ይሖዋ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ ሲያይ ልቡ ይደሰታል! ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አገልግሎትንና ስብሰባዎችን ጨምሮ ለአምልኳችን ከምናውለው ጊዜና ጉልበት ጋር በተያያዘም ይሠራል።

20. ስለ መበለቷ ከሚገልጸው ዘገባ የምታገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

20 ስለ መበለቷ ከሚናገረው ዘገባ ያገኛችሁትን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ ጥረታቸውን እንደሚያደንቅ እንዲያስታውሱ በመርዳት ልታበረታቷቸው የምትችሉ ወንድሞችና እህቶችን ለማሰብ ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ባጋጠማት የጤና እክል ወይም አቅሟ በመድከሙ የተነሳ በአገልግሎት የቀድሞውን ያህል ማድረግ ባለመቻሏ የጥፋተኝነት ወይም የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማት አረጋዊት እህት ታውቃላችሁ? አሊያም ደግሞ ባለበት የሚያሠቃይ ሕመም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ከስብሰባ ለመቅረት በመገደዱ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረበት ወንድም ታውቁ ይሆን? “የሚያንጽ . . . መልካም ቃል” በመናገር እንዲህ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች እርዷቸው። (ኤፌ. 4:29) ስለ ድሃዋ መበለት ከሚገልጸው ዘገባ የምናገኘውን የሚያበረታታ ትምህርት አካፍሏቸው። የምትሰጧቸው ማበረታቻ ይሖዋ ምርጣችንን ስንሰጠው እንደሚደሰት እንዲተማመኑ ሊረዳቸው ይችላል። (ምሳሌ 15:23፤ 1 ተሰ. 5:11) ሌሎች የሚያደርጉት ነገር ምንም ያህል ትንሽ ቢመስል ለይሖዋ ምርጣቸውን በመስጠታቸው ስታመሰግኗቸው የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ እየተከተላችሁ ነው።

21. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

21 የወንጌል ዘገባዎች ስለ ኢየሱስ ሕይወት ብዙ ዝርዝር መረጃ የሚሰጡን በመሆኑ በጣም አመስጋኞች ነን። ምክንያቱም ይህ መሆኑ ኢየሱስን እንድንመስለው ይኸውም ፈለጉን በጥብቅ እንድንከተል ይረዳናል። በወንጌሎች ላይ ያተኮረ የግል ጥናት ወይም የቤተሰብ አምልኮ ፕሮጀክት ለመጀመር ለምን አትሞክሩም? እንዲህ ካለው ጥናት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ዘገባዎቹ ሕያው እንዲሆኑልን ማድረግና ከዘገባዎቹ የምናገኘውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል እንዳለብን አትዘንጉ። ይሁንና ኢየሱስን ያደረገውን ነገር ከመኮረጅ በተጨማሪ የተናገረውን ነገር ማዳመጥ ይኖርብናል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት ምን ትምህርት እንደምናገኝ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!

^ አን.5 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል’ ይኖርብናል። ኢየሱስ ምን ዓይነት “ፈለግ” ትቶልናል? ይህ ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። በተጨማሪም የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ኢየሱስ ስለ ድሃዋ መበለት በተናገረው ነገር ላይ ካሰላሰለች በኋላ አንዲትን አረጋዊት እህት በሙሉ ነፍስ ለምታቀርበው አገልግሎት ስታመሰግናት።