በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 18

መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣትና ግቦቻችን ላይ መድረስ የምንችለው እንዴት ነው?

መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣትና ግቦቻችን ላይ መድረስ የምንችለው እንዴት ነው?

“እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።”—1 ጢሞ. 4:15

መዝሙር 84 እገዛ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት

ማስተዋወቂያ a

1. የትኞቹን መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት እንችላለን?

 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን በጣም እንወደዋለን። ለእሱ በምናቀርበው አገልግሎት ምርጣችንን መስጠት እንፈልጋለን። ይሁንና ለይሖዋ ምርጣችንን ለመስጠት መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ያስፈልገናል። ከእነዚህም መካከል ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን መማር እንዲሁም ሌሎችን ማገልገል የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ይገኙበታል። b

2. መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣትና ግቦቻችን ላይ ለመድረስ መጣጣር ያለብን ለምንድን ነው?

2 መንፈሳዊ እድገት የማድረግ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው? በዋነኝነት፣ አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው። ይሖዋ ተሰጥኦዎቻችንን እና ክህሎቶቻችንን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመን እሱን ስናገለግለው ይደሰታል። በተጨማሪም መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይበልጥ ለመርዳት ያስችለናል። (1 ተሰ. 4:9, 10) እውነት ቤት ውስጥ የኖርነው ለምንም ያህል ጊዜ ቢሆን ሁላችንም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

3. በ1 ጢሞቴዎስ 4:12-16 ላይ እንደተገለጸው ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ምን እንዲያደርግ አበረታቶታል?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የመጀመሪያውን ደብዳቤ በጻፈለት ወቅት ጢሞቴዎስ ወጣት ቢሆንም ተሞክሮ ያለው ሽማግሌ ነበር። ያም ቢሆን መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል ጳውሎስ አበረታቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:12-16ን አንብብ።) የጳውሎስን ምክር በጥንቃቄ ከመረመርነው፣ በሁለት አቅጣጫዎች እድገት እንዲያደርግ ጢሞቴዎስን እንዳበረታታው እናስተውላለን። አንደኛ እንደ ፍቅር፣ እምነትና ንጽሕና ያሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብር፣ ሁለተኛ ደግሞ ለሰዎች እንደ ማንበብ፣ አጥብቆ እንደ መምከርና እንደ ማስተማር ያሉ ክህሎቶችን እንዲያዳብር መክሮታል። የጢሞቴዎስን ምሳሌ በአእምሯችን ይዘን፣ ምክንያታዊ ግቦችን ማውጣት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። አገልግሎታችንን ማስፋት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶችም እንመለከታለን።

ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አዳብር

4. በፊልጵስዩስ 2:19-22 መሠረት ጢሞቴዎስ በይሖዋ አገልግሎት የተዋጣለት እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?

4 ጢሞቴዎስ በይሖዋ አገልግሎት የተዋጣለት እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? ግሩም የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበሩ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:19-22ን አንብብ።) ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ሲናገር ከተጠቀመበት መግለጫ ጢሞቴዎስ ትሑት፣ ታማኝ፣ ትጉና እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን። ጢሞቴዎስ ወንድሞቹን የሚወድና ለእነሱ ከልቡ የሚጨነቅ ሰው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ይወደው ነበር፤ እንዲሁም ከባድ የሆኑ ኃላፊነቶችን በአደራ ሰጥቶታል። (1 ቆሮ. 4:17) እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ የሚወዳቸውን ባሕርያት የምናዳብር ከሆነ በእሱ ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍና ጉባኤያችንን ይበልጥ መርዳት እንችላለን።—መዝ. 25:9፤ 138:6

ይበልጥ ማዳበር የምትፈልገውን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ምረጥ (ከአንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት)

5. (ሀ) አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ለማዳበር ግብ ማውጣት የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) በፎቶግራፉ ላይ የምትታየው ወጣት እህት የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ያወጣችው ግብ ላይ ለመድረስ እየተጣጣረች ያለችው እንዴት ነው?

5 ግልጽ የሆነ ግብ አውጣ። የትኛውን ባሕርይ ማሻሻል እንዳለብህ በጸሎት አስብበት። ማሻሻል የምትፈልገውን አንድ ባሕርይ ምረጥ። የሌሎችን ስሜት ይበልጥ ለመረዳት ወይም የእምነት ባልንጀሮችህን ለመደገፍ ያለህን ፍላጎት ለማሳደግ መጣጣር ትችል ይሆን? ሰላም ፈጣሪና ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን? በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ እንዲጠቁምህ የምታምነውን ጓደኛህን መጠየቅ ትችላለህ።—ምሳሌ 27:6

6. አንድን ባሕርይ ለማዳበር ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣር የምትችለው እንዴት ነው?

6 ግብህ ላይ ለመድረስ ተጣጣር። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ልታዳብረው ያሰብከውን ባሕርይ በተመለከተ ጥልቀት ያለው ምርምር ማድረግ ነው። ለምሳሌ ይበልጥ ይቅር ባይ ለመሆን ግብ አውጥተሃል እንበል። ሌሎችን በነፃ ይቅር ስላሉና ስላላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በማንበብና በማሰላሰል መጀመር ትችላለህ። የኢየሱስን ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ሌሎችን በነፃ ይቅር ብሏል። (ሉቃስ 7:47, 48) እንዲሁም በስህተታቸው ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ ለማተኮር መርጧል። በአንጻሩ ግን በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ‘ሌሎችን በንቀት ዓይን ይመለከቱ’ ነበር። (ሉቃስ 18:9) በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ካሰላሰልክ በኋላ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ስለ ሰዎች ሳስብ የሚታየኝ ምናቸው ነው? የትኛው ባሕርያቸው ላይ ለማተኮር እመርጣለሁ?’ አንድን ግለሰብ ይቅር ማለት ከባድ ከሆነብህ የግለሰቡን መልካም ባሕርያት በዝርዝር ለመጻፍ ሞክር። ከዚያም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ኢየሱስ ይህን ሰው እንዴት ነው የሚመለከተው? በእኔ ቦታ ቢሆን ይቅር ይለው ነበር?’ እንዲህ ማድረጋችን አመለካከታችንን እንድናስተካክል ይረዳናል። የበደለንን ሰው ይቅር ማለት መጀመሪያ ላይ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ለማድረግ መጣጣራችንን ከቀጠልን ግን በጊዜ ሂደት ይቅር ባይ መሆን እየቀለለን ይመጣል።

ጠቃሚ ክህሎቶችን ተማር

የስብሰባ አዳራሻችሁን ለመጠገን የሚያስፈልገውን ክህሎት ለመማር ራስህን አቅርብ (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) e

7. በምሳሌ 22:29 መሠረት ይሖዋ የተካኑ ሠራተኞችን እየተጠቀመ ያለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

7 ጠቃሚ ክህሎቶችን ለመማር ግብ ማውጣትም ትችላለህ። የቤቴል ሕንፃዎችን እንዲሁም የትላልቅ እና የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባት በርካታ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ አስታውስ። በእነዚህ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ክህሎቶቻቸውን ያዳበሩት ልምድ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር በመሥራት ነው። በፎቶግራፉ ላይ እንደሚታየው፣ ወንድሞችም ሆኑ እህቶች የትላልቅ እና የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን እየተማሩ ነው። ‘የዘላለሙ ንጉሥ’ ይሖዋ አምላክና “የነገሥታት ንጉሥ” የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ የተካኑ ሠራተኞችን በመጠቀም አስደናቂ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው። (1 ጢሞ. 1:17፤ 6:15፤ ምሳሌ 22:29ን አንብብ።) ጠንክረን የምንሠራውም ሆነ ክህሎቶቻችንን የምንጠቀመው ይሖዋን እንጂ ራሳችንን ለማስከበር አይደለም።—ዮሐ. 8:54

8. አንድን ክህሎት ለማዳበር ግብ ማውጣት የምትችለው እንዴት ነው?

8 ግልጽ የሆነ ግብ አውጣ። የትኛውን ክህሎት መማር ትችላለህ? ‘የትኛውን ክህሎት ባዳብር ይሻላል?’ ብለህ የጉባኤህን ሽማግሌዎች፣ ምናልባትም የወረዳ የበላይ ተመልካችህን ልትጠይቅ ትችላለህ። ለምሳሌ የንግግርና የማስተማር ክህሎትህን እንድታሻሽል ከጠቆሙህ ‘የትኛውን የንግግር ባሕርይ ላዳብር?’ ብለህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። ከዚያም ማሻሻያ ለማድረግ የሚረዱህን ተግባራዊ እርምጃዎች ውሰድ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

9. አንድን ክህሎት ለማዳበር ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣር የምትችለው እንዴት ነው?

9 ግብህ ላይ ለመድረስ ተጣጣር። የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ግብ አወጣህ እንበል። ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባለውን ብሮሹር በጥንቃቄ ልታጠና ትችላለህ። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ክፍል ሲሰጥህ ብቃት ያለውን አንድ ወንድም ከስብሰባው በፊት ክፍልህን አዳምጦ ምክር እንዲሰጥህ ልትጠይቀው ትችላለህ። በችሎታህ ብቻ ሳይሆን ትጉና እምነት የሚጣልብህ በመሆን ረገድም መልካም ስም አትርፍ።—ምሳሌ 21:5፤ 2 ቆሮ. 8:22

10. አንድን ክህሎት ደረጃ በደረጃ ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

10 ያወጣኸው ግብ በጣም የሚከብድህን ነገር ማድረግ የሚጠይቅብህ ቢሆንስ? ተስፋ አትቁረጥ! ጌሪ የተባለ አንድ ወንድም ማንበብ በጣም ያስቸግረው ነበር። በጉባኤ ስብሰባ ላይ ጮክ ብሎ ማንበብ በጣም ያሳፍረው እንደነበር ተናግሯል። ሆኖም ንባቡን ለማሻሻል ጥረት ማድረጉን ቀጠለ። እንዲያውም አሁን ሥልጠና በማግኘቱ በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ንግግር ማቅረብ ችሏል!

11. እንደ ጢሞቴዎስ እኛም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ምን ሊረዳን ይችላል?

11 ጢሞቴዎስ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ ወይም ግሩም አስተማሪ መሆን ችሎ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ምክር በመከተሉ የተሰጠውን ኃላፊነት በጊዜ ሂደት ውጤታማ በሆነ መንገድ መወጣት እንደቻለ ምንም ጥያቄ የለውም። (2 ጢሞ. 3:10) እኛም ክህሎቶቻችንን የምናዳብር ከሆነ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ እንሆናለን።

ሌሎችን ማገልገል የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ

12. ሌሎች ከሚያከናውኑት አገልግሎት ምን ጥቅም አግኝተሃል?

12 ሁላችንም ሌሎች ከሚያከናውኑት አገልግሎት እንጠቀማለን። ታመን ሆስፒታል ስንገባ፣ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ እና በሕሙማን ጠያቂ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች መጥተው ሲጠይቁን እንደሰታለን። በግል ሕይወታችን ከባድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አንድ አሳቢ ሽማግሌ ጊዜ ሰጥቶ ሲያዳምጠንና ሲያጽናናን ደስ ይለናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ እርዳታ ሲያስፈልገን ተሞክሮ ያለው አንድ አቅኚ አብሮን በማስጠናት ሐሳብ ሲሰጠን አመስጋኝ እንደምንሆን ምንም ጥያቄ የለውም። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች እኛን በመርዳታቸው ደስተኞች ናቸው። ወንድሞቻችንን ለማገልገል ራሳችንን ካቀረብን እኛም የዚህ ደስታ ተካፋይ መሆን እንችላለን። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 20:35) በእነዚህ ወይም በሌሎች መንገዶች አገልግሎትህን ለማስፋት ከፈለግክ ግብህ ላይ ለመድረስ ምን ሊረዳህ ይችላል?

13. ግብ ስናወጣ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

13 ግልጽ ያልሆነ ግብ አታውጣ። ለምሳሌ ‘በጉባኤ ውስጥ የማደርገውን እንቅስቃሴ ማሳደግ እፈልጋለሁ’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ግብ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ሊከብድህ ይችላል። ግብህ ላይ መድረስህን ማወቅም ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ስለዚህ በግልጽ የተቀመጠ ግብ ይኑርህ። ምናልባትም ግብህንና እዚያ ላይ ለመድረስ ያሰብከው እንዴት እንደሆነ በጽሑፍ ልታሰፍር ትችላለህ።

14. ግብ ስናወጣ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

14 ግብ ስናወጣ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ አዲስ ጉባኤ እንዲቋቋም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቶ ነበር። በዚያ የሚገኙ አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለመርዳት እዚያው የመቆየት ግብ ሊኖረው እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ተቃዋሚዎች ጳውሎስ ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ አስገደዱት። (ሥራ 17:1-5, 10) ጳውሎስ እዚያ ቢቆይ ኖሮ የወንድሞችን ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር ነበር። ሆኖም ጳውሎስ ተስፋ አልቆረጠም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን ለማስተናገድ ተገቢውን እርምጃ ወስዷል። ከጊዜ በኋላ፣ በተሰሎንቄ የሚገኙ አዳዲስ ክርስቲያኖችን እንዲረዳ ጢሞቴዎስን ልኮታል። (1 ተሰ. 3:1-3) ጢሞቴዎስ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ለማገልገል ራሱን በማቅረቡ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ምንኛ ተደስተው ይሆን!

15. ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች በግባችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ? ምሳሌ ስጥ።

15 ጳውሎስ በተሰሎንቄ ካጋጠመው ተሞክሮ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ላይ ለመድረስ እየተጣጣርን ነው እንበል። ሆኖም ከቁጥጥራችን ውጭ በሆኑ ሁኔታዎች የተነሳ እዚህ መብት ላይ መድረስ አልቻልንም። (መክ. 9:11) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ፣ ልትደርስበት የምትችለው ሌላ ግብ አውጣ። ቴድና ሃይዲ የተባሉ ባልና ሚስትም ያደረጉት ይህንኑ ነው። በጤና እክል ምክንያት የቤቴል አገልግሎታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። ሆኖም ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸውን ሌሎች መንገዶች እንዲፈልጉ አነሳስቷቸዋል። መጀመሪያ የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙ ሲሆን ቴድ ደግሞ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ሥልጠና ተሰጠው። በኋላ ግን የወረዳ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልገው የዕድሜ ገደብ ተቀየረ። በመሆኑም ቴድና ሃይዲ ከዚህ በኋላ በዚህ የአገልግሎት መብት መካፈል እንደማይችሉ ተገነዘቡ። በወቅቱ በሁኔታው ቢያዝኑም ይሖዋን ማገልገል የሚችሉባቸው ሌሎች መንገዶች እንዳሉ አስተዋሉ። ቴድ “በአንድ የአገልግሎት ዘርፍ ራሳችንን መገደብ እንደሌለብን ተምረናል” ብሏል።

16. ከገላትያ 6:4 ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ነገሮች በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። በመሆኑም በይሖዋ ዘንድ ያለንን ዋጋ ባለን የአገልግሎት መብት መለካት አይኖርብንም፤ እንዲሁም ያለንን መብት ሌሎች ካላቸው መብት ጋር ማነጻጸር የለብንም። ሃይዲ እንዲህ ብላለች፦ “የእናንተን ሕይወት ከሌሎች ሕይወት ጋር ማነጻጸር ከጀመራችሁ ሰላማችሁን ታጣላችሁ።” (ገላትያ 6:4ን አንብብ።) ይበልጥ ማገልገል የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። c

17. የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

17 ቀላል ሕይወት በመምራትና አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ባለመግባት አዳዲስ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል ራስህን ማዘጋጀት ትችላለህ። የረጅም ጊዜ ግብህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን የአጭር ጊዜ ግቦች አውጣ። ለምሳሌ የረጅም ጊዜ ግብህ የዘወትር አቅኚ መሆን ከሆነ አሁን ላልተወሰነ ጊዜ በረዳት አቅኚነት ማገልገል ትችል ይሆን? ወይም ደግሞ ግብህ የጉባኤ አገልጋይ መሆን ከሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ ያለህን እንቅስቃሴ ማሳደግ እንዲሁም በጉባኤህ የሚገኙ የጤና እክል ያለባቸውና በዕድሜ የገፉ ወንድሞችንና እህቶችን መጠየቅ ትችል ይሆን? አሁን ላይ የምታካብተው ተሞክሮ ወደፊት ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን እንድታገኝ መንገድ ሊከፍትልህ ይችላል። የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በትጋት ለመወጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።—ሮም 12:11

ሊደረስበት የሚችል ግልጽ የሆነ ግብ አውጣ (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት) f

18. እህት ቤቨርሊ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ፎቶግራፉንም ተመልከት።)

18 ዕድሜያችን ቢገፋም መንፈሳዊ ግብ ማውጣትና ግባችን ላይ መድረስ እንችላለን። ቤቨርሊ የተባሉትን የ75 ዓመት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እህት ቤቨርሊ ከባድ የጤና እክል ስላለባቸው መራመድ ይከብዳቸዋል። ሆኖም በመታሰቢያው በዓል ዘመቻ ላይ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ፈልገው ነበር። በመሆኑም ግልጽ የሆነ ግብ አወጡ። እህት ቤቨርሊ ግባቸው ላይ ሲደርሱ በጣም ተደሰቱ። እሳቸው ያደረጉት ጥረት ሌሎችም በአገልግሎት በትጋት እንዲካፈሉ አነሳስቷቸዋል። አረጋዊ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ማድረግ የሚችሉት ነገር የተገደበ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ሥራቸውን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—መዝ. 71:17, 18

19. የትኞቹን መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት እንችላለን?

19 ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ። በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ የሚረዱህን ባሕርያት አዳብር። አምላክንም ሆነ ድርጅቱን ይበልጥ ማገልገል እንድትችል የሚረዱህን ክህሎቶች ተማር። ወንድሞችህንና እህቶችህን ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችሉህን መንገዶች ፈልግ። d አንተም እንደ ጢሞቴዎስ በይሖዋ እርዳታ “እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ” ይታያል።—1 ጢሞ. 4:15

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

a ጢሞቴዎስ ብቃት ያለው የምሥራቹ ሰባኪ ነበር። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል አበረታቶታል። ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ምክር ከተከተለ ይሖዋን እንዲሁም ወንድሞቹንና እህቶቹን ይበልጥ ማገልገል ይችላል። አንተስ እንደ ጢሞቴዎስ ይሖዋንና የእምነት ባልንጀሮችህን ይበልጥ ለማገልገል ትጓጓለህ? እንደምትጓጓ ጥያቄ የለውም። ታዲያ እንዲህ ለማድረግ የሚረዱህ የትኞቹ ግቦች ናቸው? እነዚህን ግቦች ማውጣትና ግቦችህ ላይ መድረስ የምትችለውስ እንዴት ነው?

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መንፈሳዊ ግብ የሚባለው ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገልና እሱን ለማስደሰት ስንል ልንደርስበት የምንጣጣረው ማንኛውም ዕቅድ ነው።

c የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 10 አን. 6-9 ላይ የሚገኘውን “እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ለሁለት እህቶች የጥገና ሥልጠና እየሰጠ፤ እህቶች ያዳበሩትን ክህሎት በአግባቡ ሲጠቀሙበት።

f የሥዕሉ መግለጫ፦ ከቤት መውጣት የማይችሉ እህት በስልክ ምሥክርነት በመካፈል ሰዎችን ለመታሰቢያው በዓል ሲጋብዙ።