የጥናት ርዕስ 18
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ ተበረታቱ
“አንዳችን ለሌላው እናስብ፤ . . . እርስ በርስ እንበረታታ።”—ዕብ. 10:24, 25 ግርጌ
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ
ማስተዋወቂያ a
1. በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የምንሰጠው ለምንድን ነው?
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው? በዋነኝነት ይሖዋን ለማወደስ ነው። (መዝ. 26:12፤ 111:1) በስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ሌላው ምክንያት ደግሞ በዚህ አስቸጋሪ ዘመን እርስ በርስ እንድንበረታታ ነው። (1 ተሰ. 5:11) እጃችንን አውጥተን ሐሳብ ስንሰጥ ሁለቱንም ዓላማዎች እናሳካለን።
2. በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በየትኞቹ ክፍሎች ላይ ሐሳብ መስጠት እንችላለን?
2 በየሳምንቱ በስብሰባዎቻችን ላይ ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ እናገኛለን። ለምሳሌ በሳምንቱ መጨረሻ ስብሰባ ላይ ስንገኝ በጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ መሳተፍ እንችላለን። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ደግሞ በመንፈሳዊ ዕንቁዎች፣ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና በውይይት በሚቀርቡ ሌሎች ክፍሎች ላይ ሐሳብ መስጠት እንችላለን።
3. የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? ዕብራውያን 10:24, 25 የሚረዳንስ እንዴት ነው?
3 ሁላችንም ይሖዋን ማወደስና የእምነት አጋሮቻችንን ማበረታታት እንፈልጋለን። ይሁንና ሐሳብ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሐሳብ መስጠት ሊያስፈራን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ተሳትፎ ለማድረግ ብንጓጓም የምንፈልገውን ያህል ዕድል ላይሰጠን ይችላል። እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እናገኛለን። ጳውሎስ አንድ ላይ መሰብሰብ ስላለው ጥቅም ሲናገር ‘እርስ በርስ በመበረታታት’ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ገልጿል። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) አጭር መልስ እንኳ በመመለስ እምነታችንን ስንገልጽ ሌሎቹ ተሰብሳቢዎች እንደሚበረታቱ ከተገነዘብን መልስ ለመመለስ የሚሰማን ፍርሃት ይቀንሳል። የምንፈልገውን ያህል ብዙ ዕድል የማይሰጠን ከሆነ ደግሞ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶችም ሐሳብ የሚሰጡበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ደስተኞች መሆን እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:8
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ሦስት ነጥቦች እንመረምራለን?
4 በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ነጥቦችን እንመረምራለን። በመጀመሪያ፣ ሐሳብ የሚሰጡ ብዙ ሰዎች በሌሉበት ትንሽ ጉባኤ ውስጥ እርስ በርስ መበረታታት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ቀጥሎም፣ እጃቸውን የሚያወጡ ብዙ ሰዎች ባሉበት ትልቅ ጉባኤ ውስጥ እርስ በርስ መበረታታት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በመጨረሻም፣ የመልሳችን ይዘት ሌሎችን የሚያበረታታ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
በትንሽ ጉባኤ ውስጥ እርስ በርስ መበረታታት
5. ተሰብሳቢዎቹ ትንሽ ከሆኑ እርስ በርስ መበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?
5 በትንሽ ጉባኤ ወይም ቡድን ውስጥ መሪው ሐሳብ እንዲሰጡ ሊጠይቃቸው የሚችላቸው ብዙ ሰዎች ላያገኝ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ እጅ የሚያወጣ ሰው እስኪያገኝ ድረስ ብዙ መጠበቅ ሊያስፈልገው ይችላል። በዚህ የተነሳ ስብሰባው አሰልቺ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ አያበረታታም። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? እጃችሁን በተደጋጋሚ ለማውጣት ፈቃደኛ ሁኑ። ይህም ሌሎች ይበልጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
6-7. ሐሳብ ለመስጠት ስናስብ የሚሰማንን ፍርሃት መቀነስ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ይሁንና ሐሳብ ስለመስጠት ስታስቡ እንኳ በጣም የሚያስፈራችሁ ከሆነስ? ብዙዎች እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። ያም ቢሆን ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ይበልጥ ማበረታታት እንድትችሉ ፍርሃታችሁን ለመቀነስ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላላችሁ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
7 ከዚህ በፊት በወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የተሰጡትን ምክሮች መከለሳችሁ ሊረዳችሁ ይችላል። b ማድረግ የምትችሉት አንዱ ነገር በደንብ መዘጋጀት ነው። (ምሳሌ 21:5) ትምህርቱን ከራሳችሁ ጋር ይበልጥ ባዋሃዳችሁት መጠን ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ይቀላችኋል። በተጨማሪም አጭር መልስ ለመመለስ ሞክሩ። (ምሳሌ 15:23፤ 17:27) መልሳችሁ አጭር ከሆነ ያን ያህል አያስፈራችሁም። ደግሞም ብዙ ነጥቦች ከታጨቁበት ረጅም ሐሳብ ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር ብቻ የያዘ አጭር ሐሳብ ለመረዳት ይበልጥ ቀላል ነው። በራሳችሁ አባባል አጭር መልስ መመለሳችሁ በደንብ እንደተዘጋጃችሁና ትምህርቱን በሚገባ እንደተረዳችሁት ያሳያል።
8. አቅማችን የፈቀደውን ስናደርግ ይሖዋ ምን ይሰማዋል?
8 እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ብታደርጉም ከአንዴ ወይም ከሁለቴ በላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈራችሁ ቢሆንስ? አቅማችሁ የፈቀደውን ነገር ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ ሁኑ። (ሉቃስ 21:1-4) ምርጣችንን መስጠት ማለት ከአቅማችን በላይ መጣጣር ማለት አይደለም። (ፊልጵ. 4:5) ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ፤ ግብ አውጡ፤ እንዲሁም መረጋጋት እንድትችሉ ጸልዩ። መጀመሪያ ላይ፣ አንድ አጭር መልስ ብቻ ለመመለስ ግብ ማውጣታችሁ በቂ ሊሆን ይችላል።
በትልቅ ጉባኤ ውስጥ እርስ በርስ መበረታታት
9. በትላልቅ ጉባኤዎች ውስጥ ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል?
9 ጉባኤያችሁ ብዙ አስፋፊዎች ካሉት ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። እጃቸውን የሚያወጡ ወንድሞችና እህቶች ከመብዛታቸው የተነሳ የመመለስ ዕድል ላታገኙ ትችላላችሁ። ዳንየልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። c ዳንየል በስብሰባዎች ላይ መልስ መመለስ በጣም ያስደስታታል። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት የአምልኮዋ ክፍል እንደሆነ፣ ሌሎችን ለማበረታታት እንደሚያስችላት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በልቧ ውስጥ ለመቅረጽ እንደሚረዳት ይሰማታል። ሆኖም ወደ ትልቅ ጉባኤ ከተዛወረች በኋላ ብዙ ጊዜ የመመለስ ዕድል አላገኘችም፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሙሉውን ስብሰባ አንዴም ላትመልስ ትችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታው በጣም ያስከፋኝ ነበር። ትልቅ መብት እንደቀረብኝ ተሰማኝ። ነገሩ ሲደጋገም የማይጠይቁኝ ሆን ብለው እንደሆነ ይሰማኝ ጀመር።”
10. መልስ የማግኘት ዕድላችንን ለመጨመር ምን ማድረግ እንችላለን?
10 እናንተስ የዳንየል ዓይነት ስሜት ተሰምቷችሁ ያውቃል? ከሆነ ተስፋ ልትቆርጡና ዝም ብላችሁ ስብሰባውን ለማዳመጥ ልትፈተኑ ትችላላችሁ። ሆኖም መልስ ለመመለስ መሞከራችሁን አታቁሙ። ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ለእያንዳንዱ ስብሰባ በርከት ያሉ መልሶችን መዘጋጀታችሁ ሊጠቅማችሁ ይችላል። እንዲህ ካደረጋችሁ በስብሰባው መጀመሪያ አካባቢ ሐሳብ የመስጠት ዕድል ባታገኙም እንኳ ስብሰባው ሲቀጥል አጋጣሚ ልታገኙ ትችላላችሁ። ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጁ እያንዳንዱ አንቀጽ ከዋናው ጭብጥ ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ በተለያዩ አንቀጾች ላይ የምትሰጡት ሐሳብ መኖሩ አይቀርም። በተጨማሪም ለማስረዳት የሚከብዱ ጥልቅ እውነቶችን በያዙ አንቀጾች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ልትዘጋጁ ትችላላችሁ። (1 ቆሮ. 2:10) ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ባሉ አንቀጾች ላይ እጃቸውን የሚያወጡት ሰዎች ቁጥር ያን ያህል ብዙ ላይሆን ይችላል። ይሁንና እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ብታደርጉም እንኳ ሐሳብ የመስጠት ዕድል ሳታገኙ የተወሰኑ ስብሰባዎች ቢያልፉስ? ከስብሰባው በፊት ወደ መሪው ሄዳችሁ በመረጣችሁት አንቀጽ ላይ ሐሳብ የመስጠት ዕድል እንዲሰጣችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ።
11. ፊልጵስዩስ 2:4 ምን እንድናደርግ ያበረታታናል?
11 ፊልጵስዩስ 2:4ን አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጡ በመንፈስ ተመርቶ መክሯቸዋል። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎችም እንደ እኛ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልጉ በማስታወስ ነው።
12. በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ሌሎችን ማበረታታት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
12 ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከጓደኞቻችሁ ጋር ስትጨዋወቱ ሌሎቹ የማውራት አጋጣሚ እስኪያጡ ድረስ ያለማቋረጥ ታወራላችሁ? እንዲህ እንደማታደርጉ የታወቀ ነው! እነሱም በጭውውቱ እንዲካፈሉ ትፈልጋላችሁ። በተመሳሳይም በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ሐሳብ እንዲሰጡ እንፈልጋለን። እንዲያውም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማበረታታት ከምንችልባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ እምነታቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ መስጠት ነው። (1 ቆሮ. 10:24) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
13. በስብሰባዎች ላይ ብዙዎች እንዲሳተፉ አጋጣሚ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
13 በመጀመሪያ ደረጃ፣ አጭር መልስ በመመለስ ብዙ ሰዎችን ለማሳተፍ የሚያስችል ጊዜ እንዲገኝ ማድረግ እንችላለን። ሽማግሌዎችና ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላሉ። አጭር መልስ በምትመልሱበት ጊዜም ቢሆን ብዙ ነጥቦችን ከመጥቀስ ተቆጠቡ። በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ነጥቦች በሙሉ ከጠቀሳችሁ ሌሎች ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት አይችሉም። ለምሳሌ በዚህ አንቀጽ ውስጥ ሁለት ምክሮች ተሰጥተዋል፦ አጭር መልስ መመለስና ብዙ ነጥቦችን ከመጥቀስ መቆጠብ። በዚህ አንቀጽ ላይ መጀመሪያ ሐሳብ እንድትሰጡ ከተጠየቃችሁ ለምን በአንደኛው ነጥብ ላይ ብቻ ትኩረት አታደርጉም?
14. እጃችንን ምን ያህል ጊዜ እንደምናወጣ ለመወሰን ምን ሊረዳን ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 እጃችሁን ምን ያህል ጊዜ እንደምታወጡ በምትወስኑበት ወቅት አስተዋይ ሁኑ። እጃችንን አሁንም አሁንም የምናወጣ ከሆነ ሌሎች አንዴም የመመለስ አጋጣሚ ባያገኙም እንኳ መሪው በተደጋጋሚ እንዲጠይቀን ጫና ልናሳድርበት እንችላለን። ይህ ደግሞ ሌሎች እጃቸውን ለማውጣት እንዳይነሳሱ ሊያደርግ ይችላል።—መክ. 3:7
15. (ሀ) ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ ሳናገኝ ስንቀር ምን ሊሰማን አይገባም? (ለ) ውይይቱን የሚመሩት ወንድሞች ለሁሉም ሰው አሳቢነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (“ ጥናቱን ለሚመራው ወንድም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
15 በውይይቱ ወቅት ብዙ አስፋፊዎች እጃቸውን ካወጡ የምንፈልገውን ያህል ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ ላናገኝ እንችላለን። አንዳንድ ጊዜም መሪው ጨርሶ ላይጠይቀን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን እናዝን ይሆናል። ሆኖም መሪው ያልጠየቀን ሆን ብሎ እንደሆነ ልናስብ አይገባም።—መክ. 7:9
16. ሐሳብ የሚሰጡ ወንድሞችና እህቶችን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?
16 የምትፈልጉትን ያህል ሐሳብ መስጠት ካልቻላችሁ ሌሎች ተሳትፎ ሲያደርጉ በጥሞና በማዳመጥ ከስብሰባው በኋላ እነሱን ለማመስገን ለምን ጥረት አታደርጉም? የምትሰጡት ምስጋና ልትሰጡ ያሰባችሁትን መልስ ያህል ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ሊያበረታታቸው ይችላል። (ምሳሌ 10:21) ደግሞም እርስ በርስ መበረታታት የምንችልበት ሌላው መንገድ ሌሎችን ማመስገን ነው።
እርስ በርስ መበረታታት የሚቻልባቸው ተጨማሪ መንገዶች
17. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸው ዕድሜያቸውን የሚመጥን መልስ እንዲዘጋጁ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በቪዲዮው ላይ እንደተጠቀሰው መልስ ለመዘጋጀት የትኞቹን አራት ነገሮች ማድረግ አለብን? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
17 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ እርስ በርስ መበረታታት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ወላጆች ከሆናችሁ፣ ልጆቻችሁ ዕድሜያቸውን የሚመጥን መልስ እንዲዘጋጁ እርዷቸው። (ማቴ. 21:16) አንዳንድ ጊዜ በስብሰባው ላይ የምናጠናው በትዳር ውስጥ ስለሚያጋጥሙ ችግሮች፣ ስለ ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ወይም ስለ ሌሎች ከበድ ያሉ ርዕሶች ሊሆን ይችላል። ሆኖም ልጆች ሐሳብ መስጠት የሚችሉበት አንድ ወይም ሁለት አንቀጽ መኖሩ አይቀርም። በተጨማሪም ልጆቻችሁ እጃቸውን ባወጡ ቁጥር የማይጠየቁት ለምን እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። እንዲህ ማድረጋችሁ እነሱ እጃቸውን አውጥተው ሌሎች አጋጣሚ ሲያገኙ ቅር እንዳይሰኙ ይረዳቸዋል።—1 ጢሞ. 6:18 d
18. ሐሳብ በምንሰጥበት ወቅት ወደ ራሳችን ትኩረት ከመሳብ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 27:2)
18 ሁላችንም ይሖዋን የሚያስከብሩና የእምነት ባልንጀሮቻችንን የሚያንጹ መልሶችን መዘጋጀት እንችላለን። (ምሳሌ 25:11) አልፎ አልፎ የግል ተሞክሯችንን በአጭሩ መናገር የምንችል ቢሆንም ስለ ራሳችን ከልክ በላይ ከመናገር መቆጠብ ይኖርብናል። (ምሳሌ 27:2ን አንብብ፤ 2 ቆሮ. 10:18) ከዚህ ይልቅ መልሳችን በይሖዋ፣ በቃሉና በሕዝቦቹ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን። (ራእይ 4:11) እርግጥ ጥያቄው የግል ስሜታችንን እንድንናገር የሚጋብዝ ከሆነ እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ በሚቀጥለው አንቀጽ ላይ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ መስጠት እንችላለን።
19. (ሀ) በስብሰባው ላይ ለተገኙት ሁሉ አሳቢነት ማሳየታችን ምን ውጤት ያስገኛል? (ሮም 1:11, 12) (ለ) በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስደስታችሁ ለምንድን ነው?
19 መልስ የምንሰጥበትን መንገድ በተመለከተ ዝርዝር ሕጎችን ማውጣት ባይቻልም ሁላችንም ሌሎችን በሚያበረታታ መንገድ ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት ማድረግ እንችላለን። ይህም ከበፊቱ ይበልጥ ደጋግመን መልስ መስጠትን ሊጠይቅ ይችላል። ወይም ደግሞ መልስ ለመመለስ ባገኘነው አጋጣሚ መርካትንና ሌሎችም ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ በማግኘታቸው መደሰትን ሊጠይቅ ይችላል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በሌሎች ሰዎች ፍላጎት ላይ ትኩረት ካደረግን ሁላችንም ‘እርስ በርሳችን መበረታታት’ እንችላለን።—ሮም 1:11, 12ን አንብብ።
መዝሙር 93 ለስብሰባ ስንገናኝ በረከትህ አይለየን
a በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስንሰጥ እርስ በርስ እንበረታታለን። ይሁንና አንዳንዶች መልስ መመለስ ያስፈራቸዋል። ሌሎች ደግሞ መልስ መመለስ ቢያስደስታቸውም የሚፈልጉትን ያህል ዕድል እንደማይሰጣቸው ይሰማቸዋል። ያም ሆነ ይህ፣ ሁላችንም እንድንበረታታ አንዳችን ለሌላው አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በተጨማሪም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቃ ሐሳብ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች እንመልሳለን።
b ተጨማሪ ምክሮችን ለማግኘት የጥር 2019 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-13ንና የመስከረም 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 19-22ን ተመልከት።
c ስሟ ተቀይሯል።
d በjw.org ላይ የሚገኘውን የይሖዋ ወዳጅ ሁን—መልስ ለመስጠት መዘጋጀት የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
f የሥዕሉ መግለጫ፦ በአንድ ትልቅ ጉባኤ ውስጥ ያለ ወንድም ከዚህ በፊት ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ ስላገኘ ሌሎች እንዲሳተፉ አጋጣሚ ሲሰጥ።