የጥናት ርዕስ 15
ከኢየሱስ ተአምራት ምን እንማራለን?
“መልካም ነገር እያደረገና . . . እየፈወሰ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ።”—ሥራ 10:38
መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ
ማስተዋወቂያ a
1. ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተአምር በፈጸመበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ግለጽ።
ጊዜው 29 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ነው። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ ብዙም አልቆየም። ኢየሱስ፣ እናቱ ማርያምና አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያደገባት ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት በስተ ሰሜን በምትገኘው በቃና በተካሄደ ሠርግ ላይ ተገኝተዋል። ማርያም የጋባዦቹ ወዳጅ ስለሆነች እንግዶቹን በማስተናገዱ ሥራ ተጠምዳለች። ሆኖም በድግሱ ወቅት ሙሽሮቹንና ቤተሰቦቻቸውን ሊያሸማቅቅ የሚችል አንድ ችግር ተፈጠረ፤ የወይን ጠጅ አለቀባቸው። b ምናልባት ይህ የሆነው በሠርጉ ላይ የተገኙት እንግዶች ቁጥር ከተጠበቀው ስለበለጠ ሊሆን ይችላል። ማርያም ቶሎ ብላ ወደ ልጇ በመሄድ “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው። (ዮሐ. 2:1-3) ታዲያ ኢየሱስ ምን ያደርግ ይሆን? ውኃውን ወደ ‘ጥሩ የወይን ጠጅ’ በመቀየር አስደናቂ ተአምር ፈጸመ።—ዮሐ. 2:9, 10
2-3. (ሀ) ኢየሱስ ተአምራት የመፈጸም ችሎታውን የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
2 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎች በርካታ ተአምራትንም ፈጽሟል። c ተአምር የመፈጸም ችሎታውን ተጠቅሞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ረድቷል። ሁለቱን ተአምራት ብቻ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ 5,000 ወንዶችን፣ በኋላ ላይ ደግሞ 4,000 ወንዶችን በመገበበት ወቅት በቦታው የነበሩትን ሴቶችና ልጆችም ከቆጠርን የተመገቡት ሰዎች ቁጥር ከ27,000 በላይ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 14:15-21፤ 15:32-38) በሁለቱም ጊዜያት ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችንም ፈውሷል። (ማቴ. 14:14፤ 15:30, 31) ኢየሱስ የፈወሳቸውና የመገባቸው ሰዎች ምን ያህል ተደንቀው እንደሚሆን እስቲ ለማሰብ ሞክሩ!
3 ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት ብዙ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን። ከእነዚህ ተአምራት የምናገኛቸውን እምነት የሚያጠናክሩ ትምህርቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ከዚያም ኢየሱስ ተአምራት ሲፈጽም ያሳየውን ትሕትናና ርኅራኄ መኮረጅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
ይሖዋንና ኢየሱስን በተመለከተ የምናገኛቸው ትምህርቶች
4. የኢየሱስ ተአምራት ስለ ማን ያስተምሩናል?
4 የኢየሱስ ተአምራት ስለ እሱ ብቻ ሳይሆን ስለ አባቱም እምነት የሚያጠናክሩ ትምህርቶች ይሰጡናል። ደግሞም የእነዚህ ተአምራት ምንጭ ይሖዋ ነው። የሐዋርያት ሥራ 10:38 እንዲህ ይላል፦ “አምላክ [ኢየሱስን] በመንፈስ ቅዱስ ቀባው፤ ደግሞም ኃይል ሰጠው፤ ኢየሱስም አምላክ ከእሱ ጋር ስለነበር መልካም ነገር እያደረገና በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የወደቁትን እየፈወሰ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ።” በተጨማሪም ኢየሱስ፣ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የአባቱን አስተሳሰብና ስሜት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ ይህም የፈጸማቸውን ተአምራት ይጨምራል። (ዮሐ. 14:9) ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት የምናገኛቸውን ሦስት ትምህርቶች እስቲ እንመልከት።
5. ኢየሱስ ተአምራትን እንዲፈጽም ያነሳሳው ምንድን ነው? (ማቴዎስ 20:30-34)
5 አንደኛ፣ ኢየሱስና አባቱ በጣም ይወዱናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተአምር የመፈጸም ችሎታውን ተጠቅሞ ሥቃያቸውን በማቅለል ለሰዎች ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል። በአንድ ወቅት ሁለት ዓይነ ስውሮች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲረዳቸው ለመኑት። (ማቴዎስ 20:30-34ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “በጣም አዘነላቸውና” ፈወሳቸው። እዚህ ጥቅስ ላይ “በጣም አዘነላቸው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ከአንጀት የመነጨ ጥልቅ የአዘኔታ ስሜትን ያመለክታል። ኢየሱስ የተራቡትን እንዲመግብና አንድን የሥጋ ደዌ በሽተኛ እንዲፈውስ ያነሳሳውም እንዲህ ያለው ከፍቅር የሚመነጭ ጥልቅ ርኅራኄ ነው። (ማቴ. 15:32፤ ማር. 1:41) ‘ከአንጀት የሚራራ’ አምላክ የሆነው ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ በጣም እንደሚወዱንና መከራ ሲደርስብን እጅግ እንደሚያዝኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሉቃስ 1:78፤ 1 ጴጥ. 5:7) በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ወዮታ በሙሉ ለማስወገድ ከልባቸው ይጓጓሉ!
6. አምላክ ለኢየሱስ ምን ዓይነት ኃይል ሰጥቶታል?
6 ሁለተኛ፣ አምላክ ለኢየሱስ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ለመፍታት የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት በራሳችን ፈጽሞ ልናሸንፋቸው የማንችላቸውን ችግሮች የመቅረፍ ኃይል እንዳለው ያሳያሉ። ለምሳሌ የሰው ልጆች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የሆነውን በዘር የወረስነውን ኃጢአት እንዲሁም የኃጢአት ውጤት የሆኑትን በሽታንና ሞትን ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው። (ማቴ. 9:1-6፤ ሮም 5:12, 18, 19) “ማንኛውንም ዓይነት” በሽታ የመፈወስ፣ አልፎ ተርፎም ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው የፈጸማቸው ተአምራት ያሳያሉ። (ማቴ. 4:23፤ ዮሐ. 11:43, 44) በተጨማሪም ኃይለኛ ማዕበልን ጸጥ የማሰኘት እንዲሁም ክፉ መናፍስትን የማስወጣት ችሎታ አለው። (ማር. 4:37-39፤ ሉቃስ 8:2) ይሖዋ ለልጁ እንዲህ ያለ ኃይል እንደሰጠው ማወቅ በእርግጥም የሚያጽናና ነው።
7-8. (ሀ) የኢየሱስ ተአምራት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ያደርጉናል? (ለ) በአዲሱ ዓለም ውስጥ የትኛው ተአምር ሲፈጸም ለማየት ትጓጓለህ?
7 ሦስተኛ፣ የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች የሚናገሩት ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የፈጸማቸው ተአምራት በሰማይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በስፋት ስለሚያከናውነው ሥራ ያስተምሩናል። በቅርቡ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለምናገኛቸው በረከቶች አስቡ። የሰው ልጆችን ቀስፈው የያዙትን በሽታዎችና የአካል ጉዳቶች ጠራርጎ ስለሚያስወግድ ፍጹም ጤንነት ይኖረናል። (ኢሳ. 33:24፤ 35:5, 6፤ ራእይ 21:3, 4) የምንራብበት ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የምንሠቃይበት ጊዜ አይኖርም። (ኢሳ. 25:6፤ ማር. 4:41) “በመታሰቢያ መቃብር” ውስጥ የነበሩ ወዳጅ ዘመዶቻችንን መልሰን የመቀበል ልዩ መብት እናገኛለን። (ዮሐ. 5:28, 29) እናንተስ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሲፈጸም ለማየት የምትጓጉት የትኛውን ተአምር ነው?
8 ኢየሱስ ተአምራት በፈጸመበት ወቅት ታላቅ ትሕትናና ርኅራኄ አሳይቷል። እኛም እነዚህን ባሕርያት መኮረጅ ይኖርብናል። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት። በመጀመሪያ የምንመለከተው በቃና ስለተካሄደው ሠርግ የሚገልጸውን ዘገባ ነው።
ስለ ትሕትና የምናገኘው ትምህርት
9. ኢየሱስ በቃና በተደረገው ሠርግ ላይ ተአምር እንዲፈጽም ያነሳሳው ምንድን ነው? (ዮሐንስ 2:6-10)
9 ዮሐንስ 2:6-10ን አንብብ። በሠርጉ ላይ የወይን ጠጅ ባለቀበት ወቅት ኢየሱስ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ ነበረበት? አልነበረበትም። መሲሑ በተአምራዊ መንገድ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ እንደሚቀይር የሚገልጽ ትንቢት የለም። ይሁንና በሠርጋችሁ ላይ ምግብ ወይም መጠጥ ቢያልቅ ምን ሊሰማችሁ እንደሚችል እስቲ አስቡት። ኢየሱስ ለደጋሾቹ፣ በተለይ ደግሞ ለሙሽሮቹ አዝኖላቸው መሆን አለበት። የወይን ጠጁ ማለቅ ከሚያስከትለው ኀፍረት ሊታደጋቸው ፈልጓል። ስለዚህ በመግቢያው ላይ የተመለከትነውን ተአምር ፈጸመ። ሦስት መቶ ዘጠና ሊትር ገደማ የሚሆንን ውኃ ወደ ወይን ጠጅ ቀየረ። ይህን ያህል ብዙ ውኃ ወደ ወይን ጠጅ የቀየረው የተወሰነው ተርፎ ወደፊት እንዲጠቀሙበት፣ ምናልባትም የወይን ጠጁ ተሸጦ ለአዲሶቹ ሙሽሮች የገቢ ምንጭ እንዲሆን አስቦ ሊሆን ይችላል። ሙሽሮቹ ምንኛ እፎይ ብለው ይሆን!
10. በዮሐንስ ምዕራፍ 2 ላይ በሚገኘው ዘገባ ውስጥ የትኞቹ ትኩረት የሚስቡ ነጥቦች አሉ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 በዮሐንስ ምዕራፍ 2 ላይ ከሚገኘው ዘገባ አንዳንድ ትኩረት የሚስቡ ነጥቦችን እንመልከት። በድንጋይ በተሠሩት ጋኖች ውስጥ ውኃ የሞላው ኢየሱስ ራሱ እንዳልሆነ ልብ ብላችኋል? ወደ ራሱ ትኩረት ከመሳብ ይልቅ ጋኖቹን ውኃ እንዲሞሉ አገልጋዮቹን ጠየቃቸው። (ቁጥር 6, 7) ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ከቀየረ በኋላ ደግሞ የወይን ጠጁን ወደ ድግሱ አሳዳሪ የወሰደው እሱ ራሱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ እንዲያደርጉ ለአገልጋዮቹ ነግሯቸዋል። (ቁጥር 8) ኢየሱስ የወይን ጠጁን ቀድቶ በእንግዶቹ መሃል በመቆም “ኑ፣ ያዘጋጀሁትን የወይን ጠጅ ቅመሱ!” አላላቸውም።
11. ከኢየሱስ ተአምር ምን እንማራለን?
11 ኢየሱስ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ ከቀየረበት ተአምር ምን ትምህርት እናገኛለን? ስለ ትሕትና ግሩም ትምህርት እናገኛለን። ኢየሱስ ስለ ተአምሩ ጉራ አልነዛም። በመሠረቱ ኢየሱስ፣ ያከናወናቸውን ነገሮች በተመለከተ ፈጽሞ ጉራ ነዝቶ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ምስጋናውና ውዳሴው ወደ አባቱ እንዲሄድ በማድረግ ትሕትና ያሳይ ነበር። (ዮሐ. 5:19, 30፤ 8:28) እኛም ትሑት በመሆንና ስለ ራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ኢየሱስን የምንመስል ከሆነ ያከናወንናቸውን ነገሮች በተመለከተ ጉራ አንነዛም። በይሖዋ አገልግሎት ምንም ዓይነት ስኬት ብናገኝ በራሳችን ሳይሆን በምናገለግለው ታላቅና ክብራማ አምላክ እንኩራራ። (ኤር. 9:23, 24) ለእሱ የሚገባውን ምስጋና እንስጠው። ደግሞስ ይሖዋ ባይረዳን ኖሮ ምን ማከናወን እንችል ነበር?—1 ቆሮ. 1:26-31
12. የኢየሱስን ትሕትና መኮረጅ የምንችልበት ሌላ መንገድ ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
12 የኢየሱስን ትሕትና መኮረጅ የምንችልበትን ሌላም መንገድ እንመልከት። አንድ ወጣት የጉባኤ አገልጋይ የመጀመሪያ ንግግሩን ለማቅረብ በሚዘጋጅበት ወቅት አንድ ሽማግሌ ብዙ ጊዜ ወስዶ ረዳው እንበል። በመሆኑም ወጣቱ ወንድም ጉባኤውን የሚያስደስት አበረታች ንግግር አቀረበ። ከስብሰባው በኋላ አንድ ወንድም ወደ ሽማግሌው መጥቶ “ወንድም እገሌ ያቀረበው ንግግር ደስ አይልም?” ይለዋል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌው “አዎ፣ ብዙ ጊዜ ወስጄ ነው ያዘጋጀሁት” ቢል ተገቢ ይሆናል? ከዚህ ይልቅ በትሕትና “አዎ፣ ግሩም ንግግር ነው ያቀረበው። በጣም ኮርቼበታለሁ” ቢል የተሻለ አይሆንም? ትሑት ከሆንን፣ ሌሎችን ለመርዳት ስንል ላደረግናቸው መልካም ነገሮች እውቅና እንዲሰጠን አንጠብቅም። ይሖዋ የምናከናውነውን ነገር እንደሚያየውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ማወቃችን ብቻ ይበቃናል። (ከማቴዎስ 6:2-4 ጋር አወዳድር፤ ዕብ. 13:16) በእርግጥም ትሕትና በማሳየት ኢየሱስን ስንመስል ይሖዋ ይደሰትብናል።—1 ጴጥ. 5:6
ስለ ርኅራኄ የምናገኘው ትምህርት
13. ኢየሱስ በናይን ከተማ አቅራቢያ ምን ተመለከተ? ምንስ አደረገ? (ሉቃስ 7:11-15)
13 ሉቃስ 7:11-15ን አንብብ። በኢየሱስ አገልግሎት አጋማሽ አካባቢ የተከናወነውን ነገር እስቲ በዓይነ ሕሊናችን ለመሣል እንሞክር። ኢየሱስ የገሊላ ከተማ ወደሆነችው ወደ ናይን ተጓዘ፤ ናይን የምትገኘው ከ900 ዓመታት ገደማ በፊት ነቢዩ ኤልሳዕ የአንዲትን ሴትዮ ልጅ ከሞት ካስነሳበት ከሹነም እምብዛም ሳትርቅ ነው። (2 ነገ. 4:32-37) ኢየሱስ ወደ ከተማዋ መግቢያ ሲቃረብ አስከሬን ተሸክመው የሚወጡ ሰዎችን ተመለከተ። ሁኔታው በጣም የሚያሳዝን ነው። አንዲት መበለት ብቸኛ ልጇን በሞት አጥታለች። ሆኖም እናቲቱ ብቻዋን አይደለችም፤ ብዙ የከተማዋ ሕዝብ ከእሷ ጋር ነበር። ኢየሱስ ሰዎቹን ካስቆመ በኋላ፣ በሐዘን ለተደቆሰችው እናት አስደናቂ ነገር አደረገላት፤ ልጇን ከሞት አስነሳላት። በወንጌሎች ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ኢየሱስ የፈጸማቸው ሦስት ትንሣኤዎች መካከል የመጀመሪያው ይሄኛው ነው።
14. በሉቃስ ምዕራፍ 7 ላይ በሚገኘው ዘገባ ውስጥ የትኞቹን ትኩረት የሚስቡ ነጥቦች እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 በሉቃስ ምዕራፍ 7 ላይ ከሚገኘው ዘገባ አንዳንድ ትኩረት የሚስቡ ነጥቦችን እንመልከት። ኢየሱስ ለእናትየዋ በጣም ያዘነላት ‘ካያት’ በኋላ እንደሆነ ልብ ብላችኋል? (ቁጥር 13) ስለዚህ ያየው ነገር አንጀቱ እንዲንሰፈሰፍ አድርጎታል። ምናልባትም ከልጇ አስከሬን ፊት ፊት እየሄደች ስቅስቅ ብላ ስታለቅስ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ለእናትየዋ በማዘን ብቻ አልተወሰነም። ርኅራኄ አሳይቷታል። በሚያጽናና የድምፅ ቃና “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። ከዚያም እሷን ለመርዳት እርምጃ ወሰደ። ልጁን ከሞት በማስነሳት “ለእናቱ ሰጣት።”—ቁጥር 14, 15
15. ከኢየሱስ ተአምር ምን እንማራለን?
15 ኢየሱስ የመበለቷን ልጅ ከሞት እንዳስነሳ ከሚገልጸው ዘገባ ምን እንማራለን? ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች ርኅራኄ ስለማሳየት ግሩም ትምህርት እናገኛለን። እርግጥ እኛ ኢየሱስ እንዳደረገው ሙታንን ማስነሳት አንችልም። ሆኖም ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ትኩረት ሰጥተን በመመልከት እንደ ኢየሱስ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። የሚያጽናኑ ቃላትን በመናገር እንዲሁም እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ነገር በማድረግ ቅድሚያውን ወስደን ርኅራኄ ልናሳያቸው እንችላለን። d (ምሳሌ 17:17፤ 2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 1 ጴጥ. 3:8) ጥቂት ቃላት መናገራችን ወይም ቀለል ያሉ ነገሮችን ማድረጋችን እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
16. በሥዕሉ ላይ እንደሚታየው፣ ልጇን በሞት ያጣችው እናት ካጋጠማት ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 አንድ ተሞክሮ እንመልከት። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንዲት እህት በጉባኤ ስብሰባ ላይ መዝሙር እየዘመረች ሳለች በአቅራቢያዋ ያለች አንዲት እናት ስታለቅስ ተመለከተች። መዝሙሩ ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገር ነበር። ያቺ እናት ደግሞ በቅርቡ ሴት ልጇን በሞት አጥታለች። እህት ይህን ስለተገነዘበች ወዲያውኑ ወደ እናትየው ሄዳ እቅፍ አድርጋት የቀሩትን የመዝሙሩን ስንኞች አብራት ዘመረች። እናትየው ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ልቤ ለወንድሞችና ለእህቶች ባለኝ ፍቅር ተሞላ።” ስብሰባ በመሄዷ በጣም ተደሰተች። ‘እርዳታ የምናገኘው ሌላ የትም ሳይሆን በስብሰባ አዳራሽ ነው’ ብላለች። ‘መንፈሳቸው ለተደቆሰባቸው’ ሐዘንተኞች ርኅራኄ ለማሳየት የምናደርጋቸውን ጥቃቅን ነገሮች እንኳ ይሖዋ እንደሚያስተውልና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝ. 34:18
አስደሳች የጥናት ፕሮጀክት
17. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ትምህርት አግኝተናል?
17 ስለ ኢየሱስ ተአምራት የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች አስደሳች የጥናት ፕሮጀክት ሊሆኑልን ይችላሉ። ይሖዋና ኢየሱስ በጣም እንደሚወዱን፣ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ የመፍታት ኃይል እንዳለው እንዲሁም መንግሥቱ ስለሚያመጣቸው በረከቶች የሚገልጹት ተስፋዎች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንደምንችል ያስተምሩናል። እነዚህን ዘገባዎች በምንመረምርበት ወቅት የኢየሱስን ባሕርያት መኮረጅ ስለምንችልባቸው መንገዶች ማሰላሰል እንችላለን። በግል ጥናታችሁ ወይም በቤተሰብ አምልኳችሁ ወቅት ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ሌሎች ተአምራት ለማጥናት ለምን ጥረት አታደርጉም? ከእነዚህ ዘገባዎች የምታገኟቸውን ትምህርቶች አስተውሉ፤ ከዚያም ያገኛችሁትን ትምህርት ለሌሎች አካፍሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከሌሎች ጋር የሚያንጹ ጭውውቶችን ማድረግ ትችላላችሁ።—ሮም 1:11, 12
18. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
18 በወንጌሎች ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ኢየሱስ የፈጸማቸው ሦስት ትንሣኤዎች መካከል የመጨረሻው የተከናወነው በኢየሱስ አገልግሎት መገባደጃ አካባቢ ነው። ሆኖም ይሄኛው ትንሣኤ ከሌሎቹ ይለያል። ኢየሱስ ያስነሳው በጣም የሚወደውን ጓደኛውን ነው፤ ትንሣኤው የተከናወነበት ሁኔታም ለየት ያለ ነው። ስለዚህ ተአምር ከሚገልጸው የወንጌል ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለውስ እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመልስልናል።
መዝሙር 20 ውድ ልጅህን ሰጠኸን
a ኃይለኛ ማዕበልን ጸጥ አሰኝቷል፤ የታመሙትን ፈውሷል፤ የሞቱትንም አስነስቷል። በእርግጥም ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት ማንበብ እጅግ ያስደስታል። እነዚህ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩልን እንዲያዝናኑን ሳይሆን እንዲያስተምሩን ነው። እነዚህን ዘገባዎች መለስ ብለን ስንመረምር ይሖዋንና ኢየሱስን በተመለከተ እምነት የሚያጠናክሩ ትምህርቶች እናገኛለን። እንዲሁም ልናዳብራቸው ስለሚገቡ ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርያት እንማራለን።
b አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “በምሥራቃውያን ዘንድ እንግዳን ማስተናገድ እንደ ቅዱስ ኃላፊነት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ጋባዡን የሚያሳስበው ለእንግዶቹ የሚበቃ ምግብ ማቅረቡ ብቻ አልነበረም። በተለይ በሠርግ ድግስ ላይ፣ ጋባዡ እንግዶቹን ጥሩ አድርጎ አስተናግዷል የሚባለው ምግቡና መጠጡ ሞልቶ ሲትረፈረፍ ብቻ ነው።”
c የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ የፈጸማቸውን ከ30 የሚበልጡ ተአምራት ለይተው ይጠቅሳሉ። በቡድን ደረጃ የተጠቀሱ ሌሎች በርካታ ተአምራትም አሉ። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ‘የከተማዋ ሰው ሁሉ’ ወደ እሱ መጥቶ ነበር፤ እሱም “በተለያየ በሽታ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ፈወሰ።”—ማር. 1:32-34
d ሐዘን የደረሰባቸውን ለማጽናናት ምን መናገር ወይም ማድረግ እንደምንችል ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማግኘት በኅዳር 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ኢየሱስ እንዳደረገው ሐዘንተኞችን አጽናኑ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ ሙሽሮቹና እንግዶቻቸው ኢየሱስ ያዘጋጀላቸውን ጥሩ የወይን ጠጅ እያጣጣሙ፤ ኢየሱስ ከጀርባ ቆሟል።