የጥናት ርዕስ 16
“ወንድምሽ ይነሳል”!
“ኢየሱስም [ለማርታ] ‘ወንድምሽ ይነሳል’ አላት።”—ዮሐ. 11:23
መዝሙር 151 አምላክ ይጣራል
ማስተዋወቂያ a
1. አንድ ልጅ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለውን እምነት የገለጸው እንዴት ነው?
ማቲው የተባለ አንድ ልጅ ከባድ የጤና እክል ስላለበት በተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል። በሰባት ዓመቱ እሱና ቤተሰቡ ወርሃዊውን የJW ብሮድካስቲንግ ፕሮግራም አብረው እየተመለከቱ ነበር። በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ፣ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በትንሣኤ ሲቀበሉ የሚያሳይ የሙዚቃ ቪዲዮ ነበር። b ፕሮግራሙ ሲያልቅ ማቲው ወደ ወላጆቹ ሄዶ እጃቸውን በመያዝ እንዲህ አላቸው፦ “እማዬ! አባዬ! አያችሁ? ብሞትም እንኳ በትንሣኤ እነሳለሁ። እዚያ እንገናኛለን፤ አይዟችሁ!” እነዚህ ወላጆች የትንሣኤ ተስፋ ለልጃቸው ምን ያህል እውን እንደሆነ ሲያውቁ ምን እንደተሰማቸው መገመት አያዳግትም።
2-3. በትንሣኤ ተስፋ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ አልፎ አልፎ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። (ዮሐ. 5:28, 29) ለምን? በድንገት ለሞት የሚዳርግ በሽታ ሊይዘን ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ልናጣ እንችላለን። (መክ. 9:11፤ ያዕ. 4:13, 14) የትንሣኤ ተስፋችን እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመወጣት ይረዳናል። (1 ተሰ. 4:13) ቅዱሳን መጻሕፍት የሰማዩ አባታችን በሚገባ እንደሚያውቀንና በጣም እንደሚወደን ማረጋገጫ ይሰጡናል። (ሉቃስ 12:7) ይሖዋ ትዝታችንና ባሕርያችን እንዳለ ሆኖ መልሶ ሊፈጥረን የሚችለው ምን ያህል ቢያውቀን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ይሖዋ በጣም ስለሚወደን ለዘላለም እንድንኖር አጋጣሚውን ከፍቶልናል፤ ብንሞት እንኳ ከሞት አስነስቶ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል!
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ መጀመሪያ ላይ፣ በትንሣኤ ተስፋ እንድናምን የሚያደርጉንን ምክንያቶች እንመለከታለን። ቀጥሎም “ወንድምሽ ይነሳል” የሚለው የጭብጡ ጥቅስ የሚገኝበትን እምነት የሚያጠናክር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመረምራለን። (ዮሐ. 11:23) በመጨረሻም የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ ሕያው እንዲሆንልን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?
4. በአንድ ተስፋ ለማመን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል? በምሳሌ አስረዳ።
4 በአንድ ተስፋ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ተስፋውን የሰጠን አካል ቃሉን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ ወይም ችሎታው እንዳለው እርግጠኛ ከሆንን ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ቤትህ በአውሎ ነፋስ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል እንበል። አንድ ወዳጅህ መጣና ‘ቤትህን ለማደስ እረዳሃለሁ’ አለህ። ይህን ያለህ ከልቡ ነው፤ ሊረዳህ እንደሚፈልግም እርግጠኛ ነህ። ግለሰቡ በሙያው የተካነ ግንበኛ ከሆነና የሚያስፈልገው መሣሪያ ሁሉ ካለው ደግሞ ቤትህን ለማደስ ችሎታው እንዳለው ታውቃለህ። በመሆኑም በሰጠህ ተስፋ ትተማመናለህ። አምላክ ስለሰጠን የትንሣኤ ተስፋስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው በእርግጥ አለው?
5-6. ይሖዋ ሙታንን የማስነሳት ፍላጎት እንዳለው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ፍላጎቱ አለው? ምንም ጥርጥር የለውም! በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ወደፊት ስለሚከናወነው ትንሣኤ እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል። (ኢሳ. 26:19፤ ሆሴዕ 13:14፤ ራእይ 20:11-13) ይሖዋ ደግሞ የገባውን ቃል ምንጊዜም ይፈጽማል። (ኢያሱ 23:14) እንዲያውም ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ይጓጓል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
6 እስቲ ኢዮብ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። ቢሞትም እንኳ ይሖዋ እሱን ለማስነሳት እንደሚጓጓ እርግጠኛ ነበር። (ኢዮብ 14:14, 15 ግርጌ) ይሖዋ የሞቱ አገልጋዮቹን በሙሉ መልሶ ለማየት ይናፍቃል። ከሞት ሊያስነሳቸው እንዲሁም አስደሳችና ጤናማ ሕይወት ሊሰጣቸው ይጓጓል። ስለ ይሖዋ እውነቱን የማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ ስለሞቱት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? አፍቃሪው አምላካችን እነሱንም ከሞት ማስነሳት ይፈልጋል። (ሥራ 24:15) የእሱ ወዳጆች የመሆንና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (ዮሐ. 3:16) በእርግጥም ይሖዋ ሙታንን የማስነሳት ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ማየት ይቻላል።
7-8. ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ኃይሉ እንዳለው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ኃይሉስ አለው? በሚገባ! እሱ “ሁሉን ቻይ” ነው። (ራእይ 1:8) በመሆኑም ሞትን ጨምሮ ማንኛውንም ጠላት ድል ለማድረግ ኃይሉ አለው። (1 ቆሮ. 15:26) ይህን ማወቃችን ያበረታታናል እንዲሁም ያጽናናናል። የእህት ኤማ አርኖልድን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እሷና ቤተሰቧ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባድ የእምነት ፈተና አጋጥሟቸው ነበር። ልጇ በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ወዳጆቿን በሞት በማጣቷ በሐዘን በተዋጠችበት ወቅት እሷን ለማጽናናት እንዲህ ብላት ነበር፦ “የሞቱ ሰዎች ሞተው የሚቀሩ ከሆነ ሞት ከአምላክ የበለጠ ኃይል ሊኖረው ነው ማለት ነው።” ከይሖዋ የበለጠ ኃይል ያለው ማንም እንደሌለ ደግሞ ግልጽ ነው! ሕይወትን የፈጠረው ሁሉን ቻይ አምላክ ለሞቱ ሰዎች ሕይወትን መልሶ የመስጠት ኃይል አለው።
8 ይሖዋ ሙታንን ማስነሳት እንደሚችል እርግጠኛ የምንሆንበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ገደብ የለሽ የማስታወስ ችሎታ ያለው መሆኑ ነው። እያንዳንዱን ኮከብ በስም ይጠራል። (ኢሳ. 40:26) የሞቱ ሰዎችንም ያስታውሳል። (ኢዮብ 14:13፤ ሉቃስ 20:37, 38) ከሞት ከሚያስነሳቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እያንዳንዷን ዝርዝር ጉዳይ በቀላሉ ማስታወስ ይችላል፤ ይህም ጄነቲካዊ መረጃቸውን፣ የሕይወት ተሞክሯቸውንና ትዝታዎቻቸውን ይጨምራል።
9. ይሖዋ የትንሣኤ ተስፋን እንደሚፈጽም የምታምነው ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ የሞቱትን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው ስለምናውቅ የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን። አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት የምንጥልበት ሌላም ምክንያት አለ፦ ይሖዋ ከዚህ ቀደም የሞቱትን አስነስቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ኢየሱስን ጨምሮ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች ሙታንን እንዲያስነሱ ኃይል ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ካከናወናቸው ትንሣኤዎች መካከል ስለ አንዱ የሚገልጸውን በዮሐንስ ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘውን ዘገባ እስቲ እንመልከት።
ኢየሱስ የቅርብ ወዳጁን በሞት አጣ
10. ኢየሱስ ከዮርዳኖስ ማዶ እየሰበከ ባለበት ወቅት በቢታንያ ምን ተፈጠረ? ኢየሱስስ ምን አደረገ? (ዮሐንስ 11:1-3)
10 ዮሐንስ 11:1-3ን አንብብ። በቢታንያ በ32 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ የተከናወነውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ኢየሱስ በቢታንያ የቅርብ ጓደኞች አሉት፤ እነሱም አልዓዛርና ሁለት እህቶቹ ማለትም ማርያምና ማርታ ናቸው። (ሉቃስ 10:38-42) ሆኖም አልዓዛር በጠና በመታመሙ እህቶቹ ተጨነቁ። ስለዚህ ወደ ኢየሱስ መልእክተኛ ላኩ፤ ኢየሱስ ከዮርዳኖስ ማዶ ከቢታንያ የሁለት ቀን የእግር መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል። (ዮሐ. 10:40) የሚያሳዝነው፣ መልእክተኛው ኢየሱስ ጋር በደረሰበት ወቅት አልዓዛር ሞተ። ኢየሱስ ወዳጁ እንደሞተ ቢያውቅም ባለበት ቦታ ለሁለት ቀን ቆየ፤ ከዚያም ወደ ቢታንያ ጉዞ ጀመረ። በመሆኑም ኢየሱስ ቢታንያ በደረሰበት ወቅት አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል። ኢየሱስ ወዳጆቹን የሚጠቅምና አምላክን የሚያስከብር ነገር ለማድረግ አቅዷል።—ዮሐ. 11:4, 6, 11, 17
11. ከዚህ ዘገባ ስለ ወዳጅነት ምን ትምህርት እናገኛለን?
11 ከዚህ ዘገባ ስለ ወዳጅነት ጥሩ ትምህርት እናገኛለን። ማርያምና ማርታ ወደ ኢየሱስ መልእክተኛ ሲልኩ ኢየሱስን ወደ ቢታንያ እንዲመጣ አልጠየቁትም። ወዳጁ እንደታመመ ብቻ ነው የነገሩት። (ዮሐ. 11:3) አልዓዛር ሲሞት ኢየሱስ ካለበት ቦታ ሆኖ ከሞት ሊያስነሳው ይችል ነበር። ሆኖም ወደ ቢታንያ ሄዶ ከወዳጆቹ ከማርያምና ከማርታ ጎን ለመሆን መርጧል። ሳትጠይቀው የሚደርስልህ ወዳጅ አለህ? እንዲህ ያለው ወዳጅ ‘በመከራ ቀን’ እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ምሳሌ 17:17) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል እኛም ለሌሎች እንዲህ ያለ ወዳጅ እንሁን! እስቲ ወደ ዘገባው እንመለስና ቀጥሎ ምን እንደተከናወነ እንመልከት።
12. ኢየሱስ ለማርታ ምን ቃል ገባላት? በዚህ ቃል ልትተማመን የምትችለውስ ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 11:23-26)
12 ዮሐንስ 11:23-26ን አንብብ። ማርታ፣ ኢየሱስ ወደ ቢታንያ እንደተቃረበ ሰማች። ወዲያውኑ እሱን ለመቀበል ሄዳ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። (ዮሐ. 11:21) እውነት ነው፣ ኢየሱስ አልዓዛርን ሊፈውሰው ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ነገር ለማድረግ አስቧል። “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት ቃል ገባላት። ኢየሱስ በዚህ ቃል ላይ እንድታምን የሚያደርግ ተጨማሪ ምክንያትም ለማርታ ሰጣት፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” አላት። አዎ፣ አምላክ ለኢየሱስ በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ቀደም ሲል አንዲትን ትንሽ ልጅ ከሞተች ብዙም ሳይቆይ አስነስቷል። በተጨማሪም አንድን ወጣት ከሞት አስነስቷል፤ ይህንንም ያደረገው ወጣቱ በሞተበት ዕለት ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:49-55) ሆኖም ከሞተ አራት ቀን የሆነውንና ሰውነቱ መበስበስ የጀመረን ሰው ሊያስነሳ ይችላል?
“አልዓዛር፣ ና ውጣ!”
13. በዮሐንስ 11:32-35 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ማርያምና ሌሎቹ ሰዎች ሲያለቅሱ ሲያይ ምን ተሰማው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ዮሐንስ 11:32-35ን አንብብ። ቀጥሎ ምን እንደተከናወነ ልብ በል። የአልዓዛር ሌላኛዋ እህት የሆነችው ማርያም ኢየሱስን ለማግኘት ወጣች። እሷም እንደ እህቷ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። እሷም ሆነች አብረዋት ያሉት ሰዎች በሐዘን ተውጠዋል። ኢየሱስም ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ። ኢየሱስ ወዳጆቹ ያሉበት ሁኔታ በጣም ስላሳዘነው እንባውን አፈሰሰ። የቤተሰብን አባል በሞት ማጣት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይረዳል። እንባቸውን እንዲያፈስሱ ምክንያት የሆነውን ነገር ለማስወገድ እንደጓጓ ጥያቄ የለውም!
14. ኢየሱስ ማርያም ስታለቅስ ከተሰማው ስሜት ስለ ይሖዋ ምን እንማራለን?
14 ኢየሱስ ማርያም ስታለቅስ የተሰማው ስሜት ይሖዋ ከአንጀት የሚራራ አምላክ መሆኑን ያስተምረናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ የአባቱን አስተሳሰብና ስሜት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 12:45) በመሆኑም ኢየሱስ ሐዘን ላይ ላሉ ወዳጆቹ እጅግ ከማዘኑ የተነሳ እንባውን እንዳፈሰሰ ስናነብ ይሖዋም ስናለቅስ ሲያይ እጅግ እንደሚያዝን እንማራለን። (መዝ. 56:8) ይህን ማወቅህ ከአንጀት ወደሚራራው አምላካችን እንድትቀርብ አያነሳሳህም?
15. በዮሐንስ 11:41-44 መሠረት በአልዓዛር መቃብር አካባቢ ምን ተከናወነ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 ዮሐንስ 11:41-44ን አንብብ። ኢየሱስ ወደ አልዓዛር መቃብር ሄደና ድንጋዩን እንዲያነሱት ጠየቃቸው። ማርታ አስከሬኑ ሊሸት እንደሚችል በመግለጽ ሐሳቡን ተቃወመች። “ኢየሱስም ‘ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?’ አላት።” (ዮሐ. 11:39, 40) ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመልክቶ በሕዝቡ ፊት ጸለየ። ቀጥሎ ለሚከናወነው ነገር ክብር ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ ለማሳየት ፈልጓል። ከዚያም ኢየሱስ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ተጣራ። አልዓዛርም ከመቃብሩ ወጣ! ኢየሱስ አንዳንዶች ‘ሊሆን አይችልም’ ያሉትን ነገር አደረገ። c
16. በዮሐንስ ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ዘገባ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?
16 በዮሐንስ ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ዘገባ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እንዴት? ኢየሱስ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት ቃል እንደገባላት አስታውስ። (ዮሐ. 11:23) እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ይህን ቃል ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ አለው። እንባውን ማፍሰሱ ሞትንና ተከትሎ የሚመጣውን ሐዘን ለማስወገድ ከልቡ እንደሚጓጓ ያሳያል። አልዓዛር ከመቃብሩ ሲወጣ ደግሞ ኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው ታይቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ ለማርታ “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” እንዳላት ልብ በል። (ዮሐ. 11:40) አምላክ የሰጠው የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸም እንድናምን የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ። ይሁንና ይህ ተስፋ ይበልጥ ሕያው እንዲሆንልን ምን ማድረግ እንችላለን?
የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ ሕያው እንዲሆንልን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
17. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የትንሣኤ ዘገባዎችን ስናነብ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
17 ስለ ትንሣኤ የሚገልጹ ታሪኮችን አንብብ እንዲሁም አሰላስልባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የኖሩ ስምንት ሰዎችን ታሪክ ይዟል። d እያንዳንዱን ታሪክ በጥልቀት ለማጥናት ለምን ጥረት አታደርግም? በምታጠናበት ጊዜ እነዚህ ሰዎች ምናብ የወለዳቸው ሳይሆኑ በእውን የኖሩ ሰዎች እንደሆኑ አስታውስ። ከታሪኮቹ ምን ትምህርት እንደምታገኝ ቆም ብለህ አስብ። እያንዳንዱ ታሪክ አምላክ የሞቱትን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው የሚያረጋግጠው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ከሌሎቹ ትንሣኤዎች ሁሉ ይበልጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ አሰላስል። የኢየሱስ ትንሣኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዓይን ምሥክሮች እንዳሉትና ለእምነታችን አስተማማኝ መሠረት እንደሆነ አትዘንጋ።—1 ቆሮ. 15:3-6, 20-22
18. ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገሩ መዝሙሮቻችንን ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
18 ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገሩትን ‘መንፈሳዊ መዝሙሮች’ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። e (ኤፌ. 5:19) እነዚህ መዝሙሮች የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልን የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ በዚህ ውድ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። መዝሙሮቹን አዳምጣቸው፤ ተለማመዳቸው፤ እንዲሁም በቤተሰብ አምልኮ ወቅት በስንኞቹ ላይ ተወያዩ። ስንኞቹ በአእምሮህና በልብህ ላይ እንዲቀረጹ አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሕይወትህን አደጋ ላይ የሚጥል ፈተና ሲያጋጥምህ ወይም የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ የይሖዋ መንፈስ እነዚህን መዝሙሮች እንድታስታውስና ከመዝሙሮቹ መጽናኛና ብርታት እንድታገኝ ይረዳሃል።
19. ስለ ትንሣኤ ምን ነገር በዓይነ ሕሊናችን ልንሥል እንችላለን? (“ ምን ብለህ ትጠይቃቸዋለህ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
19 በዓይነ ሕሊና የመሣል ችሎታህን ተጠቀም። ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረንን ሕይወት በዓይነ ሕሊናችን የመሣል ችሎታ ሰጥቶናል። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረውን ሁኔታ በመሣል ብዙ ጊዜ ከማሳለፌ የተነሳ በገነት ውስጥ ያሉት አበቦች መዓዛ እንኳ ይሸተኛል።” በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ የእምነት ሰዎችን ስታገኛቸው ይታይህ። እነማንን ለማግኘት ትጓጓለህ? ምን ብለህ ትጠይቃቸዋለህ? በሞት የተለዩህን ወዳጅ ዘመዶችህን ስታገኝም ይታይህ። ያኔ የሚኖረውን ሁኔታ በዝርዝር ለማሰብ ሞክር። ስታወሩ፣ ስትተቃቀፉ፣ በደስታ ስትላቀሱ ይታይህ።
20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
20 ይሖዋ የትንሣኤን ተስፋ ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ አለው። በዚህ ውድ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ፣ ለእያንዳንዳችን ‘ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ይነሳሉ!’ የሚል ቃል ወደገባልን አምላካችን ይበልጥ እንቀርባለን።
መዝሙር 147 የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተሰጥቶናል
a አንድ ወዳጅህን ወይም የቤተሰብህን አባል በሞት አጥተህ ከሆነ የትንሣኤ ተስፋ በጣም እንደሚያጽናናህ ጥያቄ የለውም። ይሁንና በዚህ ተስፋ የምታምንበትን ምክንያት ለሌሎች ማብራራት የምትችለው እንዴት ነው? የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ ሕያው እንዲሆንልህ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው? የዚህ ርዕስ ዓላማ ሁላችንም በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት እንድናጠናክር መርዳት ነው።
b የሙዚቃ ቪዲዮው ሩቅ አይደለም ያ ጊዜ የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በኅዳር 2016 ብሮድካስት ላይ ታይቶ ነበር።
c በጥር 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ኢየሱስ አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ለመድረስ አራት ቀን የፈጀበት ለምን ነበር?” የሚል ርዕስ ተመልከት።
d በነሐሴ 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4 ላይ የሚገኘውን “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ትንሣኤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
e ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ ከተባለው መጽሐፍ ላይ የሚከተሉትን መዝሙሮች ተመልከት፦ “በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ” (መዝሙር 139)፣ “ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!” (መዝሙር 144) እና “አምላክ ይጣራል” (መዝሙር 151)። በተጨማሪም jw.org ላይ የሚገኙትን “ሩቅ አይደለም ያ ጊዜ፣” “ያ ዘመን ሲመጣ” እና “እይማ” የተባሉትን ኦሪጅናል መዝሙሮች ተመልከት።