የጥናት ርዕስ 17
ያልተጠበቁ ችግሮች ሲያጋጥሙህ ይሖዋ ይረዳሃል
“የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።”—መዝ. 34:19
መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት
ማስተዋወቂያ a
1. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ነን?
የይሖዋ ሕዝቦች ስለሆንን፣ እሱ እንደሚወደንና ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንድንመራ እንደሚፈልግ እርግጠኞች ነን። (ሮም 8:35-39) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ እንደምንጠቀምም እናውቃለን። (ኢሳ. 48:17, 18) ይሁንና ያልጠበቅናቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንስ?
2. ምን ዓይነት ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? በችግሮቹ የተነሳ ምን ብለን ልናስብ እንችላለን?
2 ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ችግር ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ አንድ የቤተሰባችን አባል ቅር ሊያሰኘን ይችላል። በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የምናከናውነውን ነገር የሚገድብ ከባድ የጤና እክል ሊያጋጥመን ይችላል። በምንኖርበት አካባቢ አውዳሚ የተፈጥሮ አደጋ ሊደርስ ይችላል። ወይም ደግሞ በእምነታችን ምክንያት ስደት ይደርስብን ይሆናል። እንዲህ ያሉ መከራዎች ሲያጋጥሙን እንደሚከተለው ብለን እንጠይቅ ይሆናል፦ ‘ይህ ነገር እየደረሰብኝ ያለው ለምንድን ነው? ያጠፋሁት ነገር አለ? ይሖዋ እኔን መባረኩን አቁሟል ማለት ነው?’ አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ! በርካታ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቷቸዋል።—መዝ. 22:1, 2፤ ዕን. 1:2, 3
3. ከመዝሙር 34:19 ምን እንማራለን?
3 መዝሙር 34:19ን አንብብ። በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ልብ በል። (1) ጻድቅ የሆኑ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። (2) ይሖዋ ከሚያጋጥመን መከራ ይታደገናል። ይሖዋ የሚታደገን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለንን ሕይወት በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን በመርዳት ነው። ይሖዋ እሱን በማገልገል ደስታ እንደምናገኝ ቃል ቢገባልንም በአሁኑ ዘመን ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምንመራ ዋስትና አልሰጠንም። (ኢሳ. 66:14) እሱ እንድንኖር የሚፈልገውን ሕይወት ለዘላለም በምናጣጥምበት በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) እስከዚያው ግን ለእያንዳንዱ ቀን የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል።—ሰቆ. 3:22-24
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ በዘመናችን የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት። ከእነሱ ምሳሌ እንደምንረዳው ሁላችንም ያልተጠበቁ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ ከታመንን እሱ ምንጊዜም ይደግፈናል። (መዝ. 55:22) ታሪኮቹን ስንመረምር እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘እኔ በዚያ ሰው ቦታ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ ነበር? እነዚህ ታሪኮች በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት የሚያጠናክሩት እንዴት ነው? ከእነዚህ ታሪኮች ያገኘሁትን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል የምችለው እንዴት ነው?’
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን
5. ያዕቆብ በላባ ምክንያት ምን ችግር አጋጥሞታል? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
5 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ያልጠበቋቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ያዕቆብን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አባቱ የይሖዋ አምላኪ ከሆነው ከላባ ልጆች መካከል ሚስት እንዲያገባ አዘዘው፤ ይሖዋ አትረፍርፎ እንደሚባርከውም ነገረው። (ዘፍ. 28:1-4) ስለዚህ ያዕቆብ ትክክለኛውን ነገር አደረገ። ከከነዓን ምድር ወጥቶ ወደ ላባ ቤት ተጓዘ። ላባ ሊያና ራሔል የተባሉ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት። ያዕቆብ ታናሽየዋን የላባ ልጅ ማለትም ራሔልን ስለወደዳት እሷን ለማግባት ሲል ሰባት ዓመት አባቷን ለማገልገል ተስማማ። (ዘፍ. 29:18) ሆኖም ሁኔታዎች ያዕቆብ ባሰበው መንገድ አልሄዱም። ላባ ታላቋን ልጁን ሊያን በመዳር ያዕቆብን አታለለው። እርግጥ ከሳምንት በኋላ ራሔልን እንዲያገባ ፈቀደለት፤ ሆኖም በምላሹ ለሰባት ተጨማሪ ዓመታት እንዲያገለግለው ጠየቀው። (ዘፍ. 29:25-27) ላባ ከሥራው ጋር በተያያዘም ያዕቆብን አጭበርብሮታል። በድምሩ ላባ ያዕቆብን ለ20 ዓመት በዝብዞታል!—ዘፍ. 31:41, 42
6. ያዕቆብ ምን ሌሎች መከራዎች አጋጥመውታል?
6 ያዕቆብ ሌሎች መከራዎችም አጋጥመውታል። ትልቅ ቤተሰብ የነበረው ቢሆንም ልጆቹ እርስ በርስ የማይስማሙበት ጊዜ ነበር። እንዲያውም የገዛ ወንድማቸውን ዮሴፍን ለባርነት ሸጠውታል። ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ ቤተሰባቸውን ያሳፈሩ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ አምጥተዋል። በተጨማሪም ያዕቆብ የሚወዳት ሚስቱ ራሔል ሁለተኛ ልጇን ስትወልድ ሞተችበት። በኋላም ከባድ ረሃብ በመከሰቱ ያዕቆብ በስተ እርጅናው ወደ ግብፅ ለመሰደድ ተገደደ።—ዘፍ. 34:30፤ 35:16-19፤ 37:28፤ 45:9-11, 28
7. ይሖዋ ለያዕቆብ ሞገሱ እንዳልተለየው ያሳየው እንዴት ነው?
7 ያዕቆብ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም በይሖዋና እሱ በገባው ቃል ላይ ያለውን እምነት አላጣም። ይሖዋም የእሱ ሞገስ እንዳልተለየው ለያዕቆብ አረጋግጦለታል። ለምሳሌ ላባ ቢያታልለውም ይሖዋ ያዕቆብን በቁሳዊ አበልጽጎታል። በተጨማሪም ያዕቆብ፣ ‘ሞቷል’ ብሎ ከሚያስበው ልጁ ጋር ከረጅም ጊዜ በኋላ ሲገናኝ ይሖዋን ምን ያህል አመስግኖት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ያዕቆብ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው ያጋጠመውን መከራ በጽናት መወጣት ችሏል። (ዘፍ. 30:43፤ 32:9, 10፤ 46:28-30) እኛም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ካለን ያልተጠበቁ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት እንችላለን።
8. ንጉሥ ዳዊት ምን ማድረግ ፈልጎ ነበር?
8 ንጉሥ ዳዊት ከይሖዋ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የፈለገውን ነገር ሁሉ ማከናወን አልቻለም። ለምሳሌ ዳዊት ለአምላኩ ቤተ መቅደስ የመገንባት ልባዊ ፍላጎት ነበረው። ይህን ፍላጎቱንም ለነቢዩ ናታን ነገረው። በምላሹም ናታን “እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ስለሆነ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው። (1 ዜና 17:1, 2) ዳዊት እነዚህን ቃላት ሲሰማ ምንኛ ተበረታቶ ይሆን! ምናልባትም ለዚህ ትልቅ ፕሮጀክት ወዲያውኑ ዝግጅት ማድረግ ጀምሮ ሊሆን ይችላል።
9. ዳዊት የሚያሳዝን ዜና ሲሰማ ምን አደረገ?
9 ብዙም ሳይቆይ ግን የይሖዋ ነቢይ አሳዛኝ ዜና ይዞ መጣ። “በዚያው ሌሊት” ይሖዋ ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ዳዊት ሳይሆን ከልጆቹ አንዱ እንደሆነ ለናታን ነገረው። (1 ዜና 17:3, 4, 11, 12) ዳዊት ይህን ሲሰማ ምን አደረገ? ግቡን አስተካከለ። ልጁ ሰለሞን ፕሮጀክቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ላይ ትኩረት አደረገ።—1 ዜና 29:1-5
10. ይሖዋ ዳዊትን የባረከው እንዴት ነው?
10 ይሖዋ ቤተ መቅደሱን የሚገነባለት እሱ እንዳልሆነ ለዳዊት ከነገረው በኋላ ወዲያውኑ ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ከዘሮቹ መካከል አንዱ ለዘላለም እንደሚነግሥ ቃል ገባለት። (2 ሳሙ. 7:16) በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት ዳዊት፣ ንጉሡ ኢየሱስ ከእሱ የትውልድ መስመር እንደመጣ ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት ጥያቄ የለውም! ከዚህ ዘገባ እንደምንማረው፣ በይሖዋ አገልግሎት ያሰብነውን ሁሉ ማከናወን ባንችልም እንኳ አምላካችን ጨርሶ ያልጠበቅናቸውን በረከቶች አዘጋጅቶልን ሊሆን ይችላል።
11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት በጠበቁት ጊዜ ባይመጣም የተባረኩት እንዴት ነው? (የሐዋርያት ሥራ 6:7)
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ያልተጠበቁ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ይጓጉ ነበር፤ ሆኖም መቼ እንደሚመጣ አያውቁም። (ሥራ 1:6, 7) ታዲያ ምን አደረጉ? በስብከቱ ሥራ ተጠመዱ። ምሥራቹ እየተስፋፋ ሲሄድ ይሖዋ ጥረታቸውን እንደባረከላቸው የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አገኙ።—የሐዋርያት ሥራ 6:7ን አንብብ።
12. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ረሃብ በተከሰተ ጊዜ ምን አደረጉ?
12 በአንድ ወቅት “በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ረሃብ” ተከስቶ ነበር። (ሥራ 11:28) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችም ከዚህ አላመለጡም። ይህ ከባድ የምግብ እጥረት ምን ዓይነት ችግር ፈጥሮባቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር እንዴት ማቅረብ እንደሚችሉ ተጨንቀው መሆን አለበት። አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲያስቡ የነበሩ ወጣቶችስ? እነሱስ ቢሆኑ ዕቅዳቸውን ለሌላ ጊዜ ማሸጋገር እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ይሆን? ሁሉም ክርስቲያኖች ከሁኔታው አንጻር ማስተካከያ አድርገዋል። ሁኔታቸው በፈቀደ መጠን መስበካቸውን ቀጥለዋል። እንዲሁም ያሏቸውን ቁሳዊ ነገሮች በይሁዳ ለሚኖሩ የእምነት አጋሮቻቸው በደስታ አካፍለዋል።—ሥራ 11:29, 30
13. ክርስቲያኖች በረሃቡ ወቅት ምን በረከቶች አግኝተዋል?
13 ክርስቲያኖች በረሃቡ ወቅት ምን በረከቶች አግኝተዋል? እርዳታ የደረሳቸው ወንድሞች የይሖዋን እጅ በቀጥታ ማየት ችለዋል። (ማቴ. 6:31-33) የእርዳታ እጃቸውን ከዘረጉላቸው የእምነት አጋሮቻቸው ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ ተሰምቷቸው መሆን አለበት። መዋጮ ያደረጉ ወይም በሌላ መንገድ በእርዳታ ሥራው የተካፈሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ አጣጥመዋል። (ሥራ 20:35) ሁሉም ከሁኔታው አንጻር ማስተካከያ በማድረጋቸው ይሖዋ ባርኳቸዋል።
14. በርናባስና ሐዋርያው ጳውሎስ ምን አጋጠማቸው? ውጤቱስ ምን ሆነ? (የሐዋርያት ሥራ 14:21, 22)
14 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ ስደት ይደርስባቸው ነበር፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ስደት የደረሰባቸው ጨርሶ ባልጠበቁት ጊዜ ነው። በርናባስና ሐዋርያው ጳውሎስ በልስጥራ አካባቢ ሲሰብኩ ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጀመሪያ ላይ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገላቸው፤ ሰዎቹም ያዳምጧቸው ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ተቃዋሚዎች “ሕዝቡን አግባቡ”፤ በመሆኑም ሞቅ አድርገው የተቀበሏቸው እነዚያው ሰዎች ጳውሎስን በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ትተውት ሄዱ። (ሥራ 14:19) ሆኖም በርናባስና ጳውሎስ ሌላ ቦታ መስበካቸውን ቀጠሉ። ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? “በርካታ ደቀ መዛሙርት” አፈሩ። እንዲሁም በንግግራቸውና በምሳሌነታቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን አጠናከሩ። (የሐዋርያት ሥራ 14:21, 22ን አንብብ።) በርናባስና ጳውሎስ ድንገተኛ ስደት ቢደርስባቸውም መስበካቸውን ስላላቆሙ ብዙዎች ተጠቅመዋል። እኛም ይሖዋ የሰጠንን ሥራ ማከናወናችንን እስካላቆምን ድረስ እንባረካለን።
በዘመናችን
15. ወንድም አሌክሳንደር ማክሚላን ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
15 ከ1914 በፊት በነበሩት ጥቂት ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች በጉጉት የሚጠብቋቸው ነገሮች ነበሩ። ወንድም አሌክሳንደር ማክሚላንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በወቅቱ እንደነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ሁሉ ወንድም ማክሚላንም ሰማያዊ ሽልማቱን በቅርቡ እንደሚያገኝ ይጠብቅ ነበር። መስከረም 1914 በሰጠው ንግግር ላይ “ይህ የመጨረሻ ንግግሬ ሳይሆን አይቀርም” ብሎ ነበር። እርግጥ ያ የመጨረሻ ንግግሩ አልነበረም። ወንድም ማክሚላን ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንዳንዶቻችን ወዲያውኑ ወደ ሰማይ እንሄዳለን ብለን መደምደማችን የችኮላ አስተሳሰብ ነበር።” አክሎም “ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር በጌታ ሥራ መጠመድ ነው” ብሏል። ደግሞም ወንድም ማክሚላን ይህንኑ አድርጓል። ቀናተኛ ሰባኪ ነበር። በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት እስር ቤት የገቡ በርካታ ወንድሞችን የማበረታታት መብት አግኝቷል። በተጨማሪም ዕድሜው በገፋበት ወቅትም እንኳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በታማኝነት ይገኝ ነበር። ወንድም ማክሚላን ሽልማቱን እየተጠባበቀ በነበረበት ወቅት በጌታ ሥራ መጠመዱ የጠቀመው እንዴት ነው? በ1966 ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “እምነቴ ልክ እንደ በፊቱ ጠንካራ ነው” ሲል ጽፏል። ይህ ለሁላችንም የሚሆን ግሩም ምሳሌ ነው! በተለይ ከጠበቁት በላይ ለረጅም ጊዜ ፈተናዎችን የተቋቋሙ ክርስቲያኖች የእሱ ዓይነት አመለካከት ማዳበራቸው ጠቃሚ ነው።—ዕብ. 13:7
16. ወንድም ጄኒንዝ እና ባለቤቱ ምን ያልተጠበቀ ፈተና አጋጠማቸው? (ያዕቆብ 4:14)
16 በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ያልተጠበቀ የጤና እክል ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ ወንድም ኸርበርት ጄኒንዝ፣ b እሱና ባለቤቱ ጋና ውስጥ በሚስዮናዊነት ያሳለፉትን ጊዜ በጣም ይወዱት እንደነበር በሕይወት ታሪኩ ላይ ገልጿል። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ከባድ የስሜት መለዋወጥ ችግር እንዳለበት በሕክምና ተረጋገጠ። ወንድም ጄኒንዝ ስላጋጠመው ነገር ሲናገር ያዕቆብ 4:14ን በመጥቀስ “‘ነገ’ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም” ብሏል። (ጥቅሱን አንብብ።) እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እውነታውን ተቀብለን ጋናን እና እዚያ የሚኖሩ ብዙ የቅርብ ወዳጆቻችንን ትተን [ለሕክምና] ወደ ካናዳ ለመመለስ ዝግጅት አደረግን።” ወንድም ጄኒንዝ እና ባለቤቱ ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ይሖዋ በታማኝነት እሱን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።
17. የወንድም ጄኒንዝ ተሞክሮ የእምነት ባልንጀሮቹን ያበረታታቸው እንዴት ነው?
17 ወንድም ጄኒንዝ በሕይወት ታሪኩ ላይ በሐቀኝነት ያሰፈረው ሐሳብ ብዙዎችን በእጅጉ አበረታቷል። አንዲት እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “እንደዚህ ተሞክሮ ስሜቴን በጥልቅ የነካው የለም። . . . ወንድም ጄኒንዝ ሕክምና ለመከታተል ሲል የተሰጠውን የአገልግሎት ምድብ ትቶ መምጣቱ እኔም ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።” በተመሳሳይም አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለአሥር ዓመት በጉባኤ ሽማግሌነት ካገለገልኩ በኋላ በአእምሮ ሕመም ምክንያት ይህን ልዩ መብት ለማቆም ተገደድኩ። . . . የሕይወት ታሪኮች በማነብበት ወቅት እኔ ከደረሰብኝ ችግር ጋር በማነጻጸር ስለማዝን እነዚህን ተሞክሮዎች ማንበብ አያስደስተኝም ነበር። ይሁን እንጂ ወንድም ጄኒንዝ ያሳየው ጽናት አበረታቶኛል።” እነዚህ ሐሳቦች እንደሚያሳዩት፣ ያልተጠበቁ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋማችን ሌሎችን ያበረታታል። ሕይወታችን ባሰብነው አቅጣጫ ባይሄድም እንኳ እምነትና ጽናት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ መሆን እንችላለን።—1 ጴጥ. 5:9
18. ሥዕሎቹ እንደሚያሳዩት በናይጄርያ ከምትኖረው መበለት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 እንደ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሉ ችግሮች በብዙ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ለምሳሌ በናይጄርያ የምትኖር አንዲት መበለት ገንዘብና ምግብ ተቸግራ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት ልጇ፣ ያለቻቸውን ትንሽ ሩዝ ከቀቀሉ በኋላ ምን እንደሚበሉ ጠየቀቻት። እህታችን የሰራፕታዋን መበለት ምሳሌ በመከተል የመጨረሻ ምግባቸውን አዘጋጅተው ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እንዳለባቸው ለልጇ ነገረቻት። (1 ነገ. 17:8-16) በዚያ ዕለት ምሳቸውን ምን እንደሚበሉ ማሰብ እንኳ ከመጀመራቸው በፊት ከእምነት ባልንጀሮቻቸው አስቤዛ ደረሳቸው። ምግቡ ለሁለት ሳምንት በቅቷቸዋል። እህታችን፣ ለልጇ የነገረቻትን ነገር ይሖዋ ያን ያህል በጥሞና ማዳመጡ በጣም እንዳስደነቃት ተናግራለች። በእርግጥም በይሖዋ ከታመንን በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ወደ እሱ እንድንቀርብ ሊረዱን ይችላሉ።—1 ጴጥ. 5:6, 7
19. ወንድም አሌክሲ የርሾቭ ምን ዓይነት ስደት ደርሶበታል?
19 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሳይጠብቁት ስደት ደርሶባቸዋል። በሩሲያ የሚኖረውን ወንድም አሌክሲ የርሾቭን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወንድም የርሾቭ በ1994 በተጠመቀበት ጊዜ በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች አንጻራዊ ነፃነት ነበራቸው። ከዓመታት በኋላ ግን በሩሲያ ያለው ሁኔታ ተቀየረ። በ2020 ፖሊሶች የወንድም የርሾቭን ቤት በረበሩ፤ እንዲሁም ብዙ ንብረቶቹን ወረሱ። ከወራት በኋላ ደግሞ መንግሥት የወንጀል ክስ መሠረተበት። የሚያሳዝነው፣ ክሶቹ የተመሠረቱት መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ፍላጎት እንዳለው በማስመሰል ከአንድ ዓመት በላይ ሲሰልለው የቆየ ሰው የቀረጻቸውን ቪዲዮዎች መሠረት በማድረግ ነው። እንዴት ያለ ክህደት ነው!
20. ወንድም የርሾቭ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ያጠናከረው እንዴት ነው?
20 የወንድም የርሾቭ መከራ ያስገኘው መልካም ውጤት አለ? አዎ። ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ተጠናክሯል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ አዘውትረን አብረን እንጸልያለን። ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ ይህን ሁኔታ መቋቋም እንደማልችል አውቃለሁ።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የግል ጥናት ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል። የጥንት ታማኝ አገልጋዮች በተዉት ምሳሌ ላይ አሰላስላለሁ። አለመረበሽና በይሖዋ መታመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ የሚያጎሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አሉ።”
21. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ትምህርት አግኝተናል?
21 በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ትምህርት አግኝተናል? በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስንኖር ያልጠበቅናቸው ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ያም ቢሆን ግን ይሖዋ አገልጋዮቹ በእሱ እስከታመኑ ድረስ ይረዳቸዋል። የጭብጡ ጥቅስ እንደሚገልጸው “የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።” (መዝ. 34:19) እኛም በሚያጋጥሙን መከራዎች ላይ ሳይሆን ይሖዋ እኛን ለማበርታት ባለው ኃይል ላይ ማተኮራችንን እንቀጥል። እንደዚያ ካደረግን እኛም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ማለት እንችላለን።—ፊልጵ. 4:13
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
a በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስንኖር ያልተጠበቁ ችግሮች ሊያጋጥሙን ቢችሉም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚደግፍ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ በጥንት ዘመን አገልጋዮቹን የረዳቸው እንዴት ነው? ዛሬስ እኛን እየደገፈን ያለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥና በዘመናችን ያሉ ምሳሌዎችን መመርመራችን እኛም በይሖዋ ከታመንን እሱ እንደሚደግፈን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።
b የታኅሣሥ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 24-28ን ተመልከት።