የጥናት ርዕስ 19
ይሖዋ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በሰጠን ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር
“[ይሖዋ] ያለውን አያደርገውም?”—ዘኁ. 23:19
መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ
ማስተዋወቂያ a
1-2. አዲሱ ዓለም እስኪመጣ ድረስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ይሖዋ ይህንን ሥርዓት አጥፍቶ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ለሰጠን ተስፋ አድናቆት አለን። (2 ጴጥ. 3:13) አዲሱ ዓለም መቼ እንደሚመጣ ባናውቅም በጣም በቅርቡ እንደሚመጣ ማስረጃዎቹ በግልጽ ያሳያሉ።—ማቴ. 24:32-34, 36፤ ሥራ 1:7
2 እስከዚያው ግን፣ አዲሶችም ሆንን እውነት ውስጥ የቆየን ክርስቲያኖች በዚህ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ጠንካራ እምነት እንኳ ሊዳከም ይችላል። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ እምነት ማጣትን ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’ በማለት ጠርቶታል። (ዕብ. 12:1) እምነታችን እንዳይዳከም ከፈለግን አዲሱ ዓለም በቅርቡ እውን እንደሚሆን የሚያረጋግጠውን ማስረጃ ዘወትር መለስ ብለን ማሰብ ይኖርብናል።—ዕብ. 11:1
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ይሖዋ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በሰጠን ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። (1) በቤዛው ላይ ማሰላሰል፣ (2) በይሖዋ ኃይል ላይ ማሰላሰል እንዲሁም (3) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትሮ መካፈል። ቀጥሎም ይሖዋ ለዕንባቆም የተናገረው ሐሳብ በአሁኑ ጊዜ እምነታችንን የሚያጠናክረው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን፣ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በተሰጠን ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበራችን የትኞቹን ሁኔታዎች ለመወጣት እንደሚረዳን እንመልከት።
ጠንካራ እምነት የሚጠይቁ ሁኔታዎች
4. ጠንካራ እምነት የሚጠይቁት ውሳኔዎች የትኞቹ ናቸው?
4 በየዕለቱ ጠንካራ እምነት የሚጠይቁ ውሳኔዎችን እናደርጋለን። ለምሳሌ ከጓደኛ ምርጫ፣ ከመዝናኛ ምርጫ፣ ከትምህርት፣ ከትዳር፣ ከልጆች እንዲሁም ከሥራ ጋር በተያያዘ ውሳኔ እናደርጋለን። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘የማደርጋቸው ምርጫዎች ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋና በአምላክ አዲስ ዓለም እንደሚተካ እንደምተማመን ያሳያሉ? ወይስ “ሕይወት የአሁኑ ብቻ ነው” ብለው የሚያምኑ ሰዎች የሚያደርጉት ዓይነት ውሳኔ አደርጋለሁ?’ (ማቴ. 6:19, 20፤ ሉቃስ 12:16-21) አዲሱ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ ያለንን እምነት ካጠናከርን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።
5-6. የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን ጠንካራ እምነት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
5 በተጨማሪም ጠንካራ እምነት የሚጠይቁ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ስደት፣ የጤና እክል ወይም ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርግ ሌላ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። መጀመሪያ አካባቢ ፈተናውን በልበ ሙሉነት እንጋፈጥ ይሆናል። ብዙ ጊዜ ግን ፈተናዎች ረዘም ላለ ጊዜ ይዘልቃሉ፤ በዚህ ወቅት ለመጽናትና ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን ለመቀጠል ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል።—ሮም 12:12፤ 1 ጴጥ. 1:6, 7
6 በፈተና ውስጥ ስንሆን ይሖዋ ያዘጋጀው አዲስ ዓለም ጨርሶ እንደማይመጣ ሊሰማን ይችላል። ይህ ማለት እምነታችን ተዳክሟል ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ክረምቱ በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜ በጋ እንደማይመጣ ሊሰማን ይችላል። ያም ቢሆን በጋ መምጣቱ አይቀርም። በተመሳሳይም ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ አዲሱ ዓለም ጨርሶ እንደማይመጣ ሊሰማን ይችላል። እምነታችን ጠንካራ ከሆነ ግን አምላክ የሰጠው ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኞች እንሆናለን። (መዝ. 94:3, 14, 15፤ ዕብ. 6:17-19) እንዲህ ያለው እምነት በሕይወታችን የይሖዋን አምልኮ ማስቀደማችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።
7. ከየትኛው ዝንባሌ ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል?
7 ጠንካራ እምነት የሚፈልገው ሌላው ነገር ደግሞ የስብከቱ ሥራችን ነው። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች ስለ መጪው አዲስ ዓለም የሚገልጸው “ምሥራች” የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ ሕዝ. 33:32) ጥርጣሬያቸው እንዲጋባብን መፍቀድ አይኖርብንም። እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳያጋጥመን እምነታችንን በቀጣይነት ማጠናከር ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።
በቤዛው ላይ አሰላስሉ
8-9. በቤዛው ላይ ማሰላሰላችን እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?
8 እምነታችንን ማጠናከር የምንችልበት አንዱ መንገድ በቤዛው ላይ ማሰላሰል ነው። ቤዛው አምላክ የገባው ቃል እንደሚፈጸም ዋስትና ይሰጠናል። ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀልን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ቤዛውን ለማዘጋጀት ምን ያህል መሥዋዕት እንደከፈለ በጥሞና የምናሰላስል ከሆነ አምላክ በአዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንደምንኖር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ያለንን እምነት እናጠናክራለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
9 አምላክ ቤዛውን ለማዘጋጀት ምን ያህል መሥዋዕት እንደከፈለ እስቲ አስቡት። ይሖዋ የሚወደውን የበኩር ልጁን፣ የቅርብ ወዳጁን ከሰማይ ወደ ምድር በመላክ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ከዚያም ተሠቃይቶ በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰቀለ። በእርግጥም ይሖዋ በጣም ውድ ዋጋ ከፍሎልናል! አፍቃሪው አምላካችን ውድ ልጁ ተሠቃይቶ እንዲሞት የፈቀደው ለአጭር ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንድንኖር ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ጴጥ. 1:18, 19) ይሖዋ የከፈለው ዋጋ በጣም ውድ ከመሆኑ አንጻር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እንደሚያደርገን ምንም ጥርጥር የለውም።
በይሖዋ ኃይል ላይ አሰላስሉ
10. በኤፌሶን 3:20 መሠረት ይሖዋ ምን ማድረግ ይችላል?
10 እምነታችንን ማጠናከር የምንችልበት ሁለተኛው መንገድ በይሖዋ ኃይል ላይ ማሰላሰል ነው። ይሖዋ ቃል የገባውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል አለው። እውነት ነው፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር በሰዎች ዓይን የማይቻል ነገር ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሰው ልጆች ጨርሶ ማድረግ የማይችሉትን ነገር እንደሚያከናውን ቃል የገባባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ። ምክንያቱም እሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። (ኢዮብ 42:2፤ ማር. 10:27) በመሆኑም ይሖዋ ጨርሶ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን ቃል መግባቱ አያስገርምም።—ኤፌሶን 3:20ን አንብብ።
11. ይሖዋ ከሰጣቸው አስደናቂ ተስፋዎች መካከል አንዱን ጥቀስ። (“ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አስደናቂ ተስፋዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
11 ይሖዋ በጥንት ዘመን ለሕዝቦቹ ቃል የገባቸውን የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አብርሃምና ሣራ በስተ እርጅናቸው ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘፍ. 17:15-17) በተጨማሪም ዘሮቹ የከነአንን ምድር እንደሚወርሱ ለአብርሃም ነግሮታል። የአብርሃም ዘሮች የሆኑት እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያዎች በነበሩባቸው በርካታ ዓመታት ይህ ቃል ሊፈጸም የሚችል አይመስልም ነበር። ሆኖም ቃሉ ተፈጽሟል። በኋላም ይሖዋ፣ ኤልሳቤጥ በስተ እርጅናዋ ልጅ እንደምትወልድ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ድንግል ለነበረችው ለማርያም የአምላክን ልጅ እንደምትወልድ ቃል ገብቶላታል፤ ይህም ይሖዋ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ያደርጋል።—ዘፍ. 3:15
12. በኢያሱ 23:14 እና በኢሳይያስ 55:10, 11 ላይ ስለ ይሖዋ ኃይል ምን ማረጋገጫ እናገኛለን?
12 ይሖዋ የገባቸውን ቃሎች በመፈጸም ረገድ ባስመዘገበው ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን አዲስ ዓለም ለማምጣት ኃይል እንዳለው ያለንን እምነት ያጠናክረዋል። (ኢያሱ 23:14፤ ኢሳይያስ 55:10, 11ን አንብብ።) ይህ ደግሞ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የተሰጠን ተስፋ በእርግጥ እውን እንደሚሆን ለሌሎች ለማስረዳት ያስችለናል። ይሖዋ ራሱ ስለ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ሲናገር “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት [ናቸው]” ብሏል።—ራእይ 21:1, 5
በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመዱ
13. የጉባኤ ስብሰባዎች እምነታችንን የሚያጠናክሩት እንዴት ነው? አብራራ።
13 እምነታችንን ማጠናከር የምንችልበት ሦስተኛው መንገድ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትሮ መካፈል ነው። ከጉባኤ ስብሰባዎች የምናገኘውን ጥቅም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ለአሥርተ ዓመታት በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች የተካፈለችው አና እንዲህ ብላለች፦ “ስብሰባዎች እምነቴን በእጅጉ ያጠናክሩልኛል። የተናጋሪው የማስተማር ችሎታ ውስን ቢሆንም አሊያም አዲስ ነገር ባያስተምረንም እንኳ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለኝን ግንዛቤ የሚያሰፋ ነገር ማግኘቴ አይቀርም፤ ይህ ደግሞ እምነቴን ያጠናክረዋል።” b አድማጮች የሚሰጡት ሐሳብም እምነታችንን ያጠናክረዋል።—ሮም 1:11, 12፤ 10:17
14. አገልግሎት እምነታችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
14 እምነታችንን ለማጠናከር የሚረዳን ሌላው ነገር በመስክ አገልግሎት መካፈል ነው። (ዕብ. 10:23) ይሖዋን ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ያገለገሉት እህት ባርባራ እንዲህ ብለዋል፦ “የስብከቱ ሥራ ምንጊዜም እምነቴን ያጠናክርልኛል። ይሖዋ ስለሰጠን አስደናቂ ተስፋ ለሌሎች በተናገርኩ ቁጥር እምነቴ ይበልጥ ጠንካራና ሕያው ይሆናል።”
15. የግል ጥናት እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
15 እምነታችንን የሚያጠናክርልን ሌላው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ደግሞ የግል ጥናት ነው። ለምሳሌ ሱዛን ዝርዝር የጥናት ፕሮግራም ማውጣቷ እንደጠቀማት ይሰማታል። እንዲህ ብላለች፦ “እሁድ እሁድ ለቀጣዩ ሳምንት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እዘጋጃለሁ። ሰኞና ማክሰኞ ለሳምንቱ መሃል ስብሰባ እዘጋጃለሁ። በሌሎቹ ቀናት ደግሞ የግል ጥናት ፕሮጀክት አካሂዳለሁ።” ሱዛን ለጥናት ቋሚ ፕሮግራም መመደቧ እምነቷን በቀጣይነት ለማጠናከር ረድቷታል። ለአሥርተ ዓመታት በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያገለገለችው አይሪን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናቷ እምነቷን አጠናክሮላታል። “ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች በዝርዝር መፈጸማቸው በጣም ያስደንቀኛል” ብላለች። c
“ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማል!”
16. ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠው ማረጋገጫ ለእኛም ይሠራል የምንለው ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 10:36, 37)
16 አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የዚህን ሥርዓት መጨረሻ ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቁ ኖረዋል። በሰዎች ዓይን፣ አምላክ የገባው ቃል ፍጻሜ የዘገየ ሊመስል ይችላል። ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲህ እንደሚሰማቸው ያውቃል። እንዲያውም ለነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶታል፦ “ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ገና ይጠብቃልና፤ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፤ ደግሞም አይዋሽም። ቢዘገይ እንኳ በተስፋ ጠብቀው! ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማልና። ራእዩ አይዘገይም!” (ዕን. 2:3) ይሖዋ ይህን ማረጋገጫ የሰጠው ለዕንባቆም ብቻ ነው? ወይስ እነዚህ ቃላት ለእኛም ይሠራሉ? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ይህን ሐሳብ አዲሱን ዓለም ከሚጠባበቁ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ ተጠቅሞበታል። (ዕብራውያን 10:36, 37ን አንብብ።) በእርግጥም መዳናችን እንደዘገየ ሆኖ ቢሰማንም እንኳ “ያላንዳች ጥርጥር [ይፈጸማል።] ራእዩ አይዘገይም!”
17. አንዲት እህት ይሖዋ ለዕንባቆም የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ያዋሉት እንዴት ነው?
17 በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች “በተስፋ ጠብቀው” የሚለውን ማበረታቻ ለአሥርተ ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለምሳሌ እህት ሉዊስ ይሖዋን ማገልገል የጀመሩት በ1939 ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “በወቅቱ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከመጨረሴ በፊት አርማጌዶን የሚመጣ መስሎኝ ነበር። ሆኖም እንደጠበቅኩት አልሆነም። ባለፉት ዓመታት፣ ይሖዋ የገባውን ቃል እስኪፈጽም ድረስ ለረጅም ዓመታት መጠበቅ ያስፈለጋቸውን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ታሪክ ማንበቤ ጠቅሞኛል፤ ለምሳሌ የኖኅን፣ የአብርሃምንና የዮሴፍን ታሪክ አነብባለሁ። እኔም ሆንኩ ሌሎች በተስፋ መጠበቃችን አዲሱ ዓለም ቅርብ እንደሆነ እንድንተማመን ረድቶናል።” ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ ሌሎች ክርስቲያኖችም በዚህ ይስማማሉ።
18. የፍጥረት ሥራዎችን መመልከታችን አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?
18 እውነት ነው፣ አዲሱ ዓለም ገና አልመጣም። ሆኖም አሁን ያሉት ከዋክብት፣ ዛፎች፣ እንስሳት እንዲሁም ሰዎች ያልነበሩበት ጊዜ እንደነበር አስታውስ። እነዚህ ነገሮች ያልነበሩበት ጊዜ ቢኖርም ማንም ሰው እውን መሆናቸውን አይጠራጠርም። እነዚህ ነገሮች ሊኖሩ የቻሉት ይሖዋ ስለፈጠራቸው ብቻ ነው። (ዘፍ. 1:1, 26, 27) በተመሳሳይም አምላካችን አዲስ ዓለም የማምጣት ዓላማ አለው። ይህን ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰዎች ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ለዘላለም ይኖራሉ። ይሖዋ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ አዲሱ ዓለም ዛሬ ያለውን ጽንፈ ዓለም ያህል እውን ይሆናል።—ኢሳ. 65:17፤ ራእይ 21:3, 4
19. እምነታችሁን ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው?
19 እስከዚያው ግን፣ የምታገኟቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅማችሁ እምነታችሁን አጠናክሩ። ለቤዛው አድናቆት አዳብሩ። በይሖዋ ኃይል ላይ አሰላስሉ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመዱ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ “አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት [ከሚወርሱት]” መካከል ትሆናላችሁ።—ዕብ. 6:11, 12፤ ሮም 5:5
መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ
a በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አያምኑም። ይህ ተስፋ የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እኛ ግን ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች ነን። ያም ቢሆን እምነታችን ምንጊዜም ሕያው እንዲሆን ከፈለግን በቀጣይነት ልናጠናክረው ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ርዕስ መልሱን ይሰጠናል።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
c የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ላይ “ትንቢት” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ሥር ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጋር የተያያዙ በርካታ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ በጥር 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ይሖዋ የሚናገረው ትንቢት ይፈጸማል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።