በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 15

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

ለይሖዋ ድርጅት ያለህን አድናቆት አሳድግ

ለይሖዋ ድርጅት ያለህን አድናቆት አሳድግ

“የአምላክን ቃል የነገሯችሁን በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ።”ዕብ. 13:7

ዓላማ

ለይሖዋ ድርጅት ያለህን አድናቆት ማሳደግና ይዘህ መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?

1. የይሖዋ ሕዝቦች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተደራጁት እንዴት ነበር?

 ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሥራ ሲሰጣቸው ሥራውን በተደራጀ መልኩ እንዲያከናውኑት ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 14:33) ለምሳሌ አምላክ ምሥራቹ በመላው ምድር እንዲሰበክ ይፈልጋል። (ማቴ. 24:14) ይሖዋ ይህን ሥራ እንዲመራ ኢየሱስን ሾሞታል። ኢየሱስም ሥራው በተደራጀ መልኩ እንዲከናወን አድርጓል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤዎች በተለያዩ ቦታዎች ሲቋቋሙ አመራር የሚሰጡ ሽማግሌዎች ተሹመው ነበር። (ሥራ 14:23) በኢየሩሳሌም ደግሞ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን ያቀፈ ማዕከላዊ የሽማግሌዎች አካል ነበር፤ እነዚህ ወንድሞች የሚያደርጉትን ውሳኔ ሁሉም ጉባኤዎች መታዘዝ ነበረባቸው። (ሥራ 15:2፤ 16:4) ጉባኤዎቹ የተሰጣቸውን መመሪያ በመታዘዛቸው “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።”—ሥራ 16:5

2. ከ1919 ወዲህ ይሖዋ መመሪያና መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበ ያለው እንዴት ነው?

2 ይሖዋ በዛሬው ጊዜም ሕዝቦቹን ማደራጀቱን ቀጥሏል። ከ1919 ወዲህ ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ለማደራጀትና ለተከታዮቹ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ጥቂት ቅቡዓን ወንዶችን የያዘ ቡድን እየተጠቀመ ነው። a (ሉቃስ 12:42) ይሖዋ ይህ ቡድን የሚያከናውነውን ሥራ እየባረከው እንደሆነ በግልጽ ይታያል።—ኢሳ. 60:22፤ 65:13, 14

3-4. (ሀ) የተደራጀን መሆናችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ባንደራጅ ኖሮ ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ ማከናወን አንችልም ነበር። (ማቴ. 28:19, 20) ለምሳሌ የአገልግሎት ክልል ባይመደብልን ኖሮ ምን እንደሚፈጠር እስቲ ለማሰብ ሞክር። ሁሉም ሰው የፈለገበት ቦታ ያገለግላል። አንዳንድ ክልሎች በተለያዩ አስፋፊዎች በተደጋጋሚ ይሠራሉ፤ ሌሎች ክልሎች ደግሞ ጨርሶ ሊረሱ ይችላሉ። መደራጀት ያሉትን ሌሎች ጥቅሞችስ ማሰብ ትችላለህ?

4 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ዘመን ተከታዮቹን እንዳደራጃቸው ሁሉ በዛሬው ጊዜም እያደራጀን ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌና ድርጅታችን ይህን ምሳሌ እየተከተለ ያለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። ለይሖዋ ድርጅት ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን።

ድርጅታችን የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላል

5. ድርጅታችን የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተልበት አንዱ መንገድ የትኛው ነው? (ዮሐንስ 8:28)

5 ኢየሱስ ምን ማድረግና ምን መናገር እንዳለበት የተማረው ከሰማዩ አባቱ ነው። የይሖዋ ድርጅትም የኢየሱስን ምሳሌ ስለሚከተል የሚያስተምራቸው የሥነ ምግባር ትምህርቶችና የሚሰጣቸው መመሪያዎች በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ ናቸው። (ዮሐንስ 8:28ን አንብብ፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17) የአምላክን ቃል እንድናነብና በሥራ ላይ እንድናውል ዘወትር ማሳሰቢያ ይሰጠናል። ይህን ምክር መከተላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

6. በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

6 በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና በእጅጉ እንጠቀማለን። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር ከድርጅቱ ከምናገኘው መመሪያ ጋር ማወዳደር እንችላለን። የተሰጠን መመሪያ ቅዱሳን መጻሕፍትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ስንገነዘብ በይሖዋ ድርጅት ላይ ያለን እምነት ያድጋል።—ሮም 12:2

7. ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ምንድን ነው? የይሖዋ ድርጅት የእሱን ምሳሌ የሚከተለውስ እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” ሰብኳል። (ሉቃስ 4:43, 44) ደቀ መዛሙርቱንም ስለ መንግሥቱ እንዲሰብኩ አዟቸዋል። (ሉቃስ 9:1, 2፤ 10:8, 9) በዛሬው ጊዜም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የታቀፉ ሁሉ፣ የሚኖሩት የትም ይሁን የት እንዲሁም ያላቸው ኃላፊነት ምንም ይሁን ምን የመንግሥቱን መልእክት ይሰብካሉ።

8. ምን ልዩ መብት አግኝተናል?

8 ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ መብታችንን እጅግ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ይህ መብት የሚሰጠው ለሁሉም አይደለም። ለምሳሌ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ አጋንንት ስለ እሱ እንዲመሠክሩ አልፈቀደላቸውም። (ሉቃስ 4:41) በዛሬው ጊዜም አንድ ሰው ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አብሮ መስበክ ከመጀመሩ በፊት ብቃቱን ማሟላት ይጠበቅበታል። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን በመስበክ ለዚህ መብት ያለንን አድናቆት ማሳየት እንችላለን። እንደ ኢየሱስ ሁሉ የእኛም ዓላማ የመንግሥቱን እውነት በሰዎች ልብ ውስጥ መዝራትና ውኃ ማጠጣት ነው።—ማቴ. 13:3, 23፤ 1 ቆሮ. 3:6

9. ድርጅቱ የአምላክን ስም የሚያሳውቀው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ የአምላክን ስም አሳውቋል። ኢየሱስ ወደ ሰማዩ አባቱ ሲጸልይ “ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 17:26) የይሖዋ ድርጅትም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ነው። አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ስም በተገቢው ቦታ በመመለስ ስሙን በማሳወቅ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በአሁኑ ጊዜ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል ከ270 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። ተጨማሪ መረጃ ሀ4 እና ሀ5 ላይ የአምላክ ስም ተመልሶ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለገባበት መንገድ ዝርዝር ሐሳብ ማግኘት ትችላለህ። በጥናት መጽሐፍ ቅዱስ (በአማርኛ አይገኝም) ውስጥ በሚገኘው ተጨማሪ መረጃ ሐ ላይ የአምላክ ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 237 ጊዜ እንዲገባ የተደረገው ለምን እንደሆነ ሰፊ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

10. በምያንማር የምትኖር አንዲት ሴት ከሰጠችው አስተያየት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

10 እንደ ኢየሱስ እኛም በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁ መርዳት እንፈልጋለን። በምያንማር የምትኖር የ67 ዓመት ሴት፣ አምላክ ስም እንዳለው ባወቀችበት ጊዜ አልቅሳለች፤ እንዲህም ብላለች፦ “የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ስሰማ የመጀመሪያዬ ነው። . . . ልማር የምችለው ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ እውነት የለም።” ይህ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የይሖዋን ስም መማራቸው በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

ለድርጅታችን አድናቆት ማሳየታችሁን ቀጥሉ

11. ሽማግሌዎች ለይሖዋ ድርጅት ያላቸውን አድናቆት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ሽማግሌዎች ለአምላክ ድርጅት አድናቆት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? መመሪያ ሲሰጣቸው በጥንቃቄ ማንበብና በተቻላቸው መጠን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አለባቸው። ለምሳሌ በጉባኤ ውስጥ ክፍሎችንና ጸሎቶችን እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን በጎች እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸውም መመሪያ ይሰጣቸዋል። ሽማግሌዎች ድርጅታዊ መመሪያዎችን የሚከተሉ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋ እንደሚወዳቸውና እንደሚንከባከባቸው እንዲተማመኑ ይረዷቸዋል።

ሽማግሌዎች ከይሖዋ ድርጅት ለምናገኘው መመሪያ አድናቆት እንዲኖረን ይረዱናል (ከአንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) b


12. (ሀ) አመራር ከሚሰጡን ወንድሞች ጋር መተባበር ያለብን ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 13:7, 17) (ለ) አመራር የሚሰጡን ወንድሞች ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ ማተኮር ያለብን ለምንድን ነው?

12 ሽማግሌዎች መመሪያ ሲሰጡን በፈቃደኝነት ልንታዘዝ ይገባል። እንዲህ ካደረግን አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ሥራቸውን መሥራት ቀላል ይሆንላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አመራር ለሚሰጡን ወንድሞች እንድንታዘዝና እንድንገዛ ያበረታታናል። (ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።) ሆኖም እንዲህ ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች ፍጹማን አይደሉም። ይሁንና በመልካም ባሕርያቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ በድክመታቸው ላይ ካተኮርን ጠላቶቻችንን መተባበር ይሆንብናል። በምን መንገድ? ምክንያቱም እንዲህ ካደረግን በአምላክ ድርጅት ላይ ያለን እምነት እየተሸረሸረ ይሄዳል፤ ተቃዋሚዎቻችንም ቢሆኑ ማድረግ የሚፈልጉት ይህንኑ ነው። ታዲያ ጠላቶቻችን የሚጠቀሙበትን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ለመለየትና ከዚያ ለመራቅ ምን ማድረግ እንችላለን?

ሌሎች አድናቆታችሁን እንዲቀንሱት አትፍቀዱ

13. የአምላክ ጠላቶች የድርጅቱን ስም ለማጠልሸት የሚሞክሩት እንዴት ነው?

13 የአምላክ ጠላቶች የድርጅቱን መልካም ገጽታዎች መጥፎ አስመስለው ለማቅረብ ይሞክራሉ። ለምሳሌ ይሖዋ አገልጋዮቹ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ እንደሚፈልግ ከቅዱሳን መጻሕፍት ተምረናል። የኃጢአት ጎዳና የሚከተሉና ንስሐ የማይገቡ ሁሉ ከጉባኤው እንዲወገዱ መመሪያ ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 5:11-13፤ 6:9, 10) ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ በጥብቅ እንከተላለን። እንዲህ ስናደርግ ግን ተቃዋሚዎቻችን የሌሎችን ምርጫ እንደማናከብር፣ በሌሎች ላይ እንደምንፈርድና ፍቅር እንደሌለን በመግለጽ ይከሱናል።

14. ስለ ድርጅቱ የሚነገሩ የሐሰት ወሬዎች ምንጭ ማን ነው?

14 የጥቃቱን ምንጭ ለዩ። ከሐሰት ወሬዎች በስተ ጀርባ ያለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። እሱ “የውሸት አባት” ነው። (ዮሐ. 8:44፤ ዘፍ. 3:1-5) በመሆኑም ሰይጣን ደጋፊዎቹን በመጠቀም ስለ ይሖዋ ድርጅት የሐሰት ወሬዎችን እንደሚያናፍስ መጠበቅ ይኖርብናል። ይህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ታይቷል።

15. የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስና በተከታዮቹ ላይ ምን አድርሰውባቸዋል?

15 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ፍጹም ነበር፤ እንዲሁም አስደናቂ ተአምራትን ፈጽሟል። ያም ቢሆን የሰይጣን ደጋፊዎች ስለ እሱ ብዙ ውሸት ተናግረዋል። ለምሳሌ የሃይማኖት መሪዎቹ፣ ኢየሱስ አጋንንትን የሚያስወጣው “በአጋንንት አለቃ” ኃይል እንደሆነ ለሕዝቡ ተናግረዋል። (ማር. 3:22) ኢየሱስ ለፍርድ ቀርቦ በነበረበት ጊዜ የሃይማኖት መሪዎቹ ‘አምላክን ተሳድቧል’ ብለው የከሰሱት ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡን እሱ እንዲገደል እንዲጠይቁ አግባብተዋል። (ማቴ. 27:20) ከጊዜ በኋላም የክርስቶስ ተከታዮች ምሥራቹን ሲሰብኩ ተቃዋሚዎቻቸው “ሰዎች በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው” እና እንዲያሳድዷቸው አደረጉ። (ሥራ 14:2, 19) የሐዋርያት ሥራ 14:2⁠ን በተመለከተ የታኅሣሥ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች መልእክቱን ለመቀበል እምቢ ማለታቸው ሳይበቃቸው ክርስቲያኖች በአሕዛብ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ የስም ማጥፋት ዘመቻ አፋፍመው ነበር።”

16. የሐሰት ወሬዎችን ስንሰማ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

16 ሰይጣን ውሸት ያስፋፋው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቻ አይደለም። ዛሬም “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። (ራእይ 12:9) የይሖዋን ድርጅት ወይም አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች በተመለከተ አሉታዊ ወሬዎችን ከሰማህ፣ የአምላክ ጠላቶች በኢየሱስም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን እንዳደረጉባቸው አስታውስ። በዛሬው ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት የይሖዋ ሕዝቦች ስደት እየደረሰባቸውና ስማቸው እየጠፋ ነው። (ማቴ. 5:11, 12) የሐሰት ወሬዎች ምንጭ ማን እንደሆነ ካወቅንና አፋጣኝ እርምጃ ከወሰድን አንታለልም። ይህ አፋጣኝ እርምጃ ምንድን ነው?

17. የሐሰት ወሬዎች ጉዳት እንዳያደርሱብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (2 ጢሞቴዎስ 1:13) (“ የሐሰት ወሬዎች ስንሰማ ምን ማድረግ ይኖርብናል?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

17 ከሐሰት ወሬዎች ራቅ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የውሸት ታሪኮችን ስንሰማ ምን ማድረግ እንዳለብን ግልጽ መመሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ‘ለፈጠራ ወሬዎች ትኩረት እንዳይሰጡ’ ወንድሞችን እንዲያዝዝ እንዲሁም ‘አምላክን ከሚጻረሩ የውሸት ታሪኮች እንዲርቅ’ መመሪያ ሰጥቶታል። (1 ጢሞ. 1:3, 4፤ 4:7) አንድ ሕፃን ልጅ መሬት ላይ ያገኘውን ነገር ሁሉ አንስቶ አፉ ውስጥ ሊከት ይችላል፤ ጎልማሳ ሰው ግን አደጋውን ስለሚያውቅ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አያደርግም። እኛም ከሐሰት ወሬዎች የምንርቀው የመረጃው ምንጭ ማን እንደሆነ ስለምናውቅ ነው። ከዚህ ይልቅ የእውነትን “ትክክለኛ ትምህርት” አጥብቀን እንይዛለን።—2 ጢሞቴዎስ 1:13ን አንብብ።

18. ለይሖዋ ድርጅት ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 እስካሁን የተመለከትነው የአምላክ ድርጅት የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተልባቸውን ሦስት መንገዶች ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ድርጅቱ የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተልባቸውን ሌሎች መንገዶች ለማስተዋል ሞክር። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለድርጅቱ ያላቸውን አድናቆት እንዲያሳድጉ እርዳቸው። በተጨማሪም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገልና ፈቃዱን ለመፈጸም ከሚጠቀምበት ድርጅት ጋር በመጣበቅ አድናቆትህን ማሳየትህን ቀጥል። (መዝ. 37:28) እንግዲያው አፍቃሪና ታማኝ ከሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች ጋር የመተባበር መብታችንን ምንጊዜም ከፍ አድርገን እንመልከተው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • የአምላክ ሕዝቦች የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

  • ለይሖዋ ድርጅት አድናቆት ማሳየታችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

  • የሐሰት ወሬዎች ስንሰማ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች

a የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ! በተባለው መጽሐፍ ገጽ 102-103 ላይ የሚገኘውን “በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ ሽማግሌዎች ጉባኤው ስለሚያደርገው የአደባባይ ምሥክርነት ከተወያዩ በኋላ አንድ የቡድን የበላይ ተመልካች አስፋፊዎች ጀርባቸውን ለግድግዳው እንዲሰጡ መመሪያ ሲሰጣቸው።