በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 16

መዝሙር 64 በመከሩ ሥራ በደስታ መካፈል

በአገልግሎትህ ይበልጥ ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

በአገልግሎትህ ይበልጥ ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

“ይሖዋን በደስታ አገልግሉት።”መዝ. 100:2

ዓላማ

ይህ ርዕስ በአገልግሎት የምናገኘውን ደስታ ማሳደግ የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁመናል።

1. አንዳንዶች ለሌሎች ስለመመሥከር ምን ይሰማቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን የምንሰብከው የሰማዩን አባታችንን ስለምንወደውና ሰዎች እሱን እንዲያውቁት መርዳት ስለምንፈልግ ነው። ብዙ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስደስታቸዋል። አንዳንዶች ግን በስብከቱ ሥራ መካፈል ያን ያህል አያስደስታቸውም። ለምን? አንዳንዶቹ ዓይናፋር ናቸው፤ እንዲሁም በራስ የመተማመን ስሜት ይጎድላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሳይጋበዙ ወደ ሰዎች ቤት መሄድ ይጨንቃቸዋል። አንዳንዶች በአገልግሎት ተቃውሞ ሊያጋጥመኝ ይችላል ብለው ይፈራሉ። በምንም ምክንያት ከሌሎች ጋር መጋጨት የማይፈልጉም አሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በጣም የሚወዱት ቢሆንም ለማያውቁት ሰው ምሥራቹን መስበክ ይከብዳቸዋል። ያም ሆኖ የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ፤ በዚህ ሥራም አዘውትረው ይካፈላሉ። ይሖዋ በእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ምንኛ ይደሰት ይሆን!

በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስደስትሃል? (አንቀጽ 1⁠ን ተመልከት)


2. በአገልግሎትህ ደስታ ማግኘት ከባድ ከሆነብህ ተስፋ መቁረጥ የሌለብህ ለምንድን ነው?

2 አንተስ እንዲህ ባሉ ስሜቶች የተነሳ ከአገልግሎትህ ደስታ ማግኘት ከብዶህ ያውቃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ፍርሃት የሚሰማህ መሆኑ ትሑት እንደሆንክና የሌሎችን ትኩረት መሳብ እንደማትፈልግ እንዲሁም ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር እንደምትፈልግ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው በተለይ ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ ተነሳስቶ ሳለ አሉታዊ ምላሽ እንዲሰጠው አይፈልግም። የሰማዩ አባትህ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በሙሉ ያውቃል፤ እንዲሁም ሊረዳህ ይፈልጋል። (ኢሳ. 41:13) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ እነዚህን ስሜቶች መቋቋምና በአገልግሎት የምታገኘውን ደስታ ማሳደግ የምትችልባቸውን አምስት መንገዶች እንመለከታለን።

የአምላክ ቃል ብርታት ይሁንህ

3. ነቢዩ ኤርምያስ ለሌሎች እንዲሰብክ የረዳው ምንድን ነው?

3 ባለፉት ዘመናት ከባድ ኃላፊነት የተሰጣቸው የአምላክ አገልጋዮች ከቃሉ ብርታት ማግኘት ችለዋል። የነቢዩ ኤርምያስን ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ የሰጠውን የመስበክ ኃላፊነት ለመቀበል አመንትቶ ነበር። ኤርምያስ “እኔ ገና ልጅ ስለሆንኩ ምን ብዬ እንደምናገር አላውቅም” ብሎ ነበር። (ኤር. 1:6) ታዲያ ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? አምላክ ከተናገረው ቃል ብርታት አግኝቷል። እንዲህ ብሏል፦ “በአጥንቶቼም ውስጥ እንደገባ የሚነድ እሳት ሆነብኝ፤ አፍኜ መያዝ አቃተኝ።” (ኤር. 20:8, 9) ኤርምያስ ያገለገለው በአስቸጋሪ ክልል ውስጥ ቢሆንም እንዲያውጅ የተሰጠው መልእክት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል ብርታት ሰጥቶታል።

4. የአምላክን ቃል ማንበባችንና ማሰላሰላችን የሚረዳን እንዴት ነው? (ቆላስይስ 1:9, 10)

4 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት ለክርስቲያኖች ብርታት ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ጉባኤ ደብዳቤ በጻፈበት ጊዜ ወንድሞቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው ‘ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ እንዲመላለሱ’ እና ‘በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው ገልጿል። (ቆላስይስ 1:9, 10ን አንብብ።) ይህ መልካም ሥራ ምሥራቹን መስበክን ያካትታል። ስለዚህ የአምላክን ቃል ስናነብና ባነበብነው ላይ ስናሰላስል በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ያድጋል፤ እንዲሁም የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈላችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል።

5. ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንና ጥናታችን የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

5 ከአምላክ ቃል የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንድንችል በችኮላ ሳይሆን ተረጋግተንና ጊዜ ወስደን ማንበብ፣ ማጥናትና ማሰላሰል ይኖርብናል። አንድን ጥቅስ መረዳት ከከበደህ ችላ ብለኸው አትለፍ። ከዚህ ይልቅ የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች ወይም ሌላ የማጥኛ መሣሪያ በመጠቀም በጥቅሱ ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎችን ለማግኘት ሞክር። ጊዜ ወስደህ የምታጠና ከሆነ የአምላክ ቃል እውነት በመሆኑ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። (1 ተሰ. 5:21) ይበልጥ እርግጠኛ በሆንክ መጠን ደግሞ የተማርከውን ነገር ለሌሎች ማካፈል ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል።

ለአገልግሎት በሚገባ ተዘጋጅ

6. ለአገልግሎት በሚገባ መዘጋጀት ያለብን ለምንድን ነው?

6 ለአገልግሎት በደንብ ከተዘጋጀህ ከሌሎች ጋር መነጋገር እየቀለለህ ይሄዳል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ አገልግሎት ከመላኩ በፊት እንዲዘጋጁ ረድቷቸዋል። (ሉቃስ 10:1-11) እነሱም ኢየሱስ ያስተማራቸውን ተግባራዊ ስላደረጉ በአገልግሎት ባገኙት ስኬት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል።—ሉቃስ 10:17

7. ለአገልግሎት መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ለአገልግሎት መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? መልእክቱን በራሳችን አነጋገርና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስረዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማሰብ አለብን። በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ሁለት ወይም ሦስት ዓይነት ምላሾችን አስቀድመን ማሰባችንና ምን መልስ እንደምንሰጥ መዘጋጀታችንም ይጠቅመናል። ከዚያም ሰዎችን ዘና ብለን በፈገግታ ማነጋገር እንዲሁም ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት እንችላለን።

ለአገልግሎት በደንብ ተዘጋጅ (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


8. ክርስቲያኖች ሐዋርያው ጳውሎስ በምሳሌው ላይ ከጠቀሳቸው የሸክላ ዕቃዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ “ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” በማለት በስብከቱ ሥራ የሚኖረንን ድርሻ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ገልጿል። (2 ቆሮ. 4:7) ውድ ሀብት የተባለው ምንድን ነው? ሕይወት አድን የሆነው የመንግሥቱን መልእክት የመስበኩ ሥራ ነው። (2 ቆሮ. 4:1) የሸክላ ዕቃ የተባሉትስ እነማን ናቸው? ምሥራቹን ለሰዎች የሚያደርሱት የአምላክ አገልጋዮች ናቸው። በጳውሎስ ዘመን ነጋዴዎች እንደ ምግብ፣ የወይን ጠጅ እና ገንዘብ የመሰሉ ውድ ነገሮችን ለማጓጓዝ የሸክላ ዕቃዎችን ይጠቀሙ ነበር። ይሖዋም በተመሳሳይ ውድ የሆነውን ምሥራች በአደራ ሰጥቶናል። በይሖዋ እርዳታ ይህን ምሥራች ለሰዎች የማዳረሱን ሥራ በታማኝነት ለማከናወን ብርታት ይኖረናል።

ድፍረት እንድታገኝ ጸልይ

9. የሰዎችን ወይም የተቃውሞን ፍርሃት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ወይም ተቃውሞን እንፈራ ይሆናል። ይህን ፈተና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያቱ መስበክ እንዲያቆሙ በታዘዙ ጊዜ ያቀረቡትን ጸሎት አስታውስ። በፍርሃት ከመሸነፍ ይልቅ “[ቃሉን] በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ” ይሖዋ እንዲረዳቸው ጠይቀዋል። ይሖዋም ለጸሎታቸው አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 4:18, 29, 31) እኛም አልፎ አልፎ ሰዎችን የምንፈራ ከሆነ የይሖዋን እርዳታ በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል። ለሰዎች ያለህ ፍቅር ከፍርሃትህ በላይ እንዲያይል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።

ድፍረት ለማግኘት ጸልይ (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)


10. ይሖዋ ምሥክሮቹ እንድንሆን የሰጠንን ኃላፊነት እንድንወጣ የሚረዳን እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 43:10-12)

10 ይሖዋ ምሥክሮቹ እንድንሆን ሾሞናል፤ እንዲሁም ደፋሮች እንድንሆን እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳይያስ 43:10-12ን አንብብ።) ይህን የሚያደርግባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት። አንደኛ፣ ኢየሱስ በስብከቱ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር ነው። (ማቴ. 28:18-20) ሁለተኛ፣ ይሖዋ መላእክቱን እኛን እንዲያግዙን መድቧቸዋል። (ራእይ 14:6) ሦስተኛ፣ የተማርናቸውን ነገሮች እንድናስታውስ ይሖዋ ረዳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል። (ዮሐ. 14:25, 26) አራተኛ፣ ይሖዋ አብረውን የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ሰጥቶናል። የይሖዋ እርዳታና አፍቃሪ የሆነው የወንድማማች ማኅበራችን ድጋፍ ስላለን በስብከቱ ሥራ ስኬታማ መሆን እንችላለን።

አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ፤ እንዲሁም ትክክለኛው አመለካከት ይኑርህ

11. በአገልግሎት ላይ ብዙ ሰዎችን ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 በክልልህ ውስጥ ያሉትን አብዛኞቹን ሰዎች ቤታቸው ልታገኛቸው አለመቻልህ ተስፋ አስቆርጦሃል? ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘አብዛኞቹ ሰዎች በዚህ ሰዓት የት ሊገኙ ይችላሉ?’ (ሥራ 16:13) ‘ሥራ ሄደው ወይም ገበያ ወጥተው ይሆን?’ ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ በመንገድ ላይ ብታገለግል ተጨማሪ ሰዎችን ታገኝ ይሆን? ጆሹዋ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በገበያ ስፍራ እና በመኪና ማቆሚያዎች በማገልገል ለመስበክ የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ አግኝቻለሁ።” ከዚህም ሌላ እሱና ባለቤቱ ብሪጅት አመሻሽ ላይና እሁድ ከሰዓት በኋላ ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ተጨማሪ ሰዎችን ማግኘት ችለዋል።—ኤፌ. 5:15, 16

ፕሮግራምህን አስተካክል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)


12. ሰዎች የሚያምኑበትን ወይም የሚያሳስባቸውን ነገር ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ሰዎች ለመልእክታችን ብዙም ፍላጎት የማያሳዩ ከሆነ የሚያምኑበትን ወይም የሚያሳስባቸውን ነገር ለማወቅ ሞክር። ጆሹዋ እና ብሪጅት በትራክቶቻችን የፊት ገጽ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አለህ? የሚለውን ትራክት ካሳዩ በኋላ “አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያምናሉ፤ ሌሎች ግን እንደዚያ አይሰማቸውም። አንተ ምን ትላለህ?” በማለት ይጠይቃሉ። በዚህ መንገድ ከብዙ ሰዎች ጋር ውይይት መጀመር ችለዋል።

13. ሰዎች መልእክታችንን ባይቀበሉም እንኳ በአገልግሎታችን ስኬታማ ነን ልንል የምንችለው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 27:11)

13 በአገልግሎታችን ስኬታማ መሆናችን የተመካው በምናገኘው ውጤት ላይ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋና ልጁ የሚጠብቁብንን ነገር አድርገናል፤ ምሥክርነት ሰጥተናል። (ሥራ 10:42) የምናነጋግረው ሰው ባናገኝ ወይም ሰዎች መልእክታችንን ቢቃወሙ እንኳ ደስተኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም የሰማዩን አባታችንን እንዳስደሰትነው እናውቃለን።—ምሳሌ 27:11ን አንብብ።

14. ሌሎች አስፋፊዎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሲያገኙ መደሰት የምንችለው ለምንድን ነው?

14 ሌሎች አስፋፊዎች ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በሚያገኙበት ጊዜም ደስተኞች መሆን እንችላለን። አንድ መጠበቂያ ግንብ ሥራችንን የጠፋን ልጅ ከመፈለግ ጋር አመሳስሎታል። ልጁን ለመፈለግ ብዙ ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይሰማራሉ። ልጁ ሲገኝ የሚደሰተው ያገኘው ሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ነው። በተመሳሳይም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የቡድን ሥራ ነው። ክልሉን ለመሸፈን ሁሉም አስፋፊዎች ያስፈልጋሉ። አንድ አዲስ ሰው በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር ደግሞ ሁሉም ይደሰታሉ።

ለይሖዋ እና ለሰዎች ባለህ ፍቅር ላይ አተኩር

15. ማቴዎስ 22:37-39 የሚናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረጋችን የአገልግሎት ቅንዓታችንን ለማሳደግ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 ለይሖዋ እና ለሰዎች ባለን ፍቅር ላይ በማተኮር ለስብከቱ ሥራ ያለንን ቅንዓት ማሳደግ እንችላለን። (ማቴዎስ 22:37-39ን አንብብ።) ይሖዋ በዚህ ሥራ ስንካፈል ምን ያህል እንደሚደሰትና ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ የሚሰማቸውን ደስታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር! ለመልእክታችን አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ስለሚያገኙት መዳንም አስብ።—ዮሐ. 6:40፤ 1 ጢሞ. 4:16

ለይሖዋና ለሰዎች ባለን ፍቅር ላይ ማተኮር በአገልግሎት ይበልጥ ደስተኞች ለመሆን ይረዳናል (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)


16. ከቤት መውጣት ባንችልም እንኳ በአገልግሎት ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

16 ሁኔታህ ከቤት ለመውጣት የማይፈቅድልህ ከሆነስ? እንዲህ ከሆነ፣ ለይሖዋና ለሰዎች ያለህን ፍቅር ለማሳየት ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሳሙኤል እና ዳኒያ በቤታቸው ለመቆየት ተገደው ነበር። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አዘውትረው በስልክና በደብዳቤ ምሥክርነት ይካፈሉ እንዲሁም በዙም አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመሩ ነበር። ሳሙኤል የካንሰር ሕክምና ለመከታተል ወደ ሐኪም ቤት በሚሄድበት ጊዜ ለሚያገኛቸው ሰዎች ይመሠክር ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ፈታኝ ሁኔታዎች በአእምሮ፣ በአካልም ሆነ በመንፈሳዊ እንድንዝል ሊያደርጉን ይችላሉ። ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ደስታ ማግኘት ያስፈልገናል።” በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ዳኒያ ወድቃ ጉዳት ስለደረሰባት ለሦስት ወራት የአልጋ ቁራኛ ሆነች። ከዚያም ለስድስት ወራት ያህል ለመንቀሳቀስ ዊልቼር ያስፈልጋት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታዬ የፈቀደልኝን ሁሉ ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ክትትል ለምታደርግልኝ ነርስና ዕቃዎችን ቤታችን ለማድረስ ለሚመጡ ሰዎች መመሥከር ችያለሁ። እንዲሁም የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በሚሸጥ ድርጅት ውስጥ ከምትሠራ አንዲት ሴት ጋር ጥሩ የስልክ ውይይት አድርጌያለሁ።” ሳሙኤል እና ዳኒያ ሁኔታቸው ቢገድባቸውም የሚችሉትን ነገር ሁሉ አድርገዋል፤ በዚህም ደስታ አግኝተዋል።

17. በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት ነጥቦች የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

17 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት ሁሉንም አንድ ላይ ተግባራዊ ካደረግናቸው ነው። እያንዳንዱ ነጥብ አንድን ምግብ ለመሥራት እንደሚያገለግል ግብዓት ሊቆጠር ይችላል። ሁሉም ግብዓቶች ሲዋሃዱ ጣፋጭ የሆነ ምግብ ይገኛል። በተመሳሳይም ሁሉንም ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋምና በአገልግሎታችን ይበልጥ ደስተኞች መሆን እንችላለን።

የሚከተሉት ነገሮች በአገልግሎታችን ደስተኞች እንድንሆን የሚረዱን እንዴት ነው?

  • ጊዜ ወስዶ በደንብ መዘጋጀት

  • ድፍረት ለማግኘት መጸለይ

  • ለይሖዋና ለሰዎች ባለን ፍቅር ላይ ማተኮር

መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”