የጥናት ርዕስ 17
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
ከመንፈሳዊው ገነት ፈጽሞ አትውጣ
“በምፈጥረው ነገር ለዘላለም ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ።”—ኢሳ. 65:18
ዓላማ
መንፈሳዊው ገነት የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነና ሌሎችን ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት መሳብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1. መንፈሳዊው ገነት ምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን ሊሆን ይገባል?
በዛሬው ጊዜ መልካም ሥራ በመሥራት የተጠመዱ ብዙ ሰዎችን ያቀፈ ምሳሌያዊ ቦታ አለ። ይህ ምሳሌያዊ ቦታ እውነተኛ ሰላም በሚያጣጥሙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሞላ ነው። በዚህ ቦታ ውስጥ ያሉት ሰዎች ከዚህ ቦታ ፈጽሞ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ሌሎች ብዙ ሰዎችም በዚህ ቦታ አብረዋቸው እንዲኖሩ ይፈልጋሉ። ይህ ቦታ ምንድን ነው? መንፈሳዊው ገነት a ነው!
2. መንፈሳዊው ገነት አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ሰይጣን በጥላቻ፣ በክፋትና በአደገኛ ሁኔታዎች በሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ይሖዋ እንዲህ ያለ ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠሩ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነው። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:12) አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይህ ሥርዓት ሊያደርስብን የሚችለውን ጉዳት ስለሚያውቅ በመንፈሳዊ ለማበብ የሚያስችለን ደህንነቱ የተጠበቀ ሁኔታ አመቻችቶልናል። የአምላክ ቃል መንፈሳዊውን ገነት እንደ አስተማማኝ “መጠጊያ” እና “ውኃ እንደሚጠግብ የአትክልት ቦታ” አድርጎ ገልጾታል። (ኢሳ. 4:6፤ 58:11) በዚህ ገነት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች የይሖዋ በረከት ስላልተለያቸው በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናትም አስደሳችና የተረጋጋ ሕይወት መምራት ችለዋል።—ኢሳ. 54:14፤ 2 ጢሞ. 3:1
3. ኢሳይያስ ምዕራፍ 65 በጥንት ጊዜ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው ተናግሮ ነበር። ይህን መግለጫ በኢሳይያስ ምዕራፍ 65 ላይ እናገኛለን። ትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በ537 ዓ.ዓ. ነው። በዚያ ወቅት፣ ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ይሖዋ ሕዝቦቹን ባርኳቸዋል፤ እንዲሁም የወደመችውን የኢየሩሳሌም ከተማ መልሰው ውብ አድርገው እንዲገነቡና ቤተ መቅደሱን በድጋሚ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።—ኢሳ. 51:11፤ ዘካ. 8:3
4. ኢሳይያስ ምዕራፍ 65 በዘመናችን ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
4 የኢሳይያስ ትንቢት ለሁለተኛ ጊዜ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው በ1919 በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ነፃ በወጡበት ጊዜ ነው። ከዚያም መንፈሳዊው ገነት ቀስ በቀስ በመላዋ ምድር መስፋፋት ጀመረ። ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ብዙ ጉባኤዎችን ያቋቁሙ እና ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ያንጸባርቁ ነበር። ቀደም ሲል ዓመፀኛና ጨካኝ የነበሩ ወንዶችና ሴቶች “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን . . . አዲሱን ስብዕና መልበስ” ችለዋል። (ኤፌ. 4:24) እርግጥ ነው፣ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተገለጹት ብዙዎቹ በረከቶች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜም እንኳ የተትረፈረፈ በረከት እያገኘን ነው። ይህ መንፈሳዊ ገነት የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነና ከዚህ ገነት ፈጽሞ መውጣት የሌለብን ለምን እንደሆነ እንመልከት።
መንፈሳዊው ገነት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
5. በኢሳይያስ 65:13 ላይ ቃል እንደተገባልን መንፈሳዊው ገነት ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
5 ለጤና ተስማሚና መንፈስን የሚያድስ። የኢሳይያስ ትንቢት በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ባሉ ሰዎችና ከመንፈሳዊው ገነት ውጭ ባሉ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ግልጽ በሆነ መንገድ ይናገራል። (ኢሳይያስ 65:13ን አንብብ።) ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ነገር በተትረፈረፈ ሁኔታ ያሟላላቸዋል። መንፈስ ቅዱስን፣ በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን እንዲሁም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ስለሰጠን ‘መብላት፣ መጠጣትና መደሰት’ እንችላለን። (ከራእይ 22:17 ጋር አወዳድር።) ከዚህ በተቃራኒ ከመንፈሳዊው ገነት ውጭ ያሉ ሰዎች ‘ይራባሉ፣ ይጠማሉ እንዲሁም ኀፍረት ይከናነባሉ።’ የሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች አይሟሉላቸውም።—አሞጽ 8:11
6. ኢዩኤል 2:21-24 ይሖዋ ያደረገልንን መንፈሳዊ ዝግጅቶች የሚገልጸው እንዴት ነው? እነዚህ ዝግጅቶች የሚጠቅሙንስ እንዴት ነው?
6 ኢዩኤል በትንቢቱ ላይ እንደ እህል፣ የወይን ጠጅ እና የወይራ ዘይት ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች እንደ ምሳሌ በመጠቀም ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንፈሳዊ ምግብን ጨምሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሙሉ አትረፍርፎ እንደሚሰጣቸው ገልጿል። (ኢዩ. 2:21-24) ይህን የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻችን፣ በድረ ገጻችን እንዲሁም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎቻችን አማካኝነት ነው። ከእነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በየዕለቱ መጠቀም እንችላለን፤ ይህም ጤናማ እንድንሆንና መንፈሳችን እንዲታደስ ይረዳናል።
7. ‘ልባችን በደስታ’ እንዲሞላ የሚያደርገው ምንድን ነው? (ኢሳይያስ 65:14)
7 ደስታና እርካታ የሚያስገኝ። የአምላክ አገልጋዮች ልባቸው በአድናቆት ስለሚሞላ በደስታ “እልል ይላሉ።” (ኢሳይያስ 65:14ን አንብብ።) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት የሚያንጹ እውነቶችና ይሖዋ ቃል የገባልን ነገሮች እንዲሁም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተው ጠንካራ ተስፋችን ‘ልባችን በደስታ’ እንዲሞላ ያደርጋሉ። ስለ እነዚህ ነገሮች ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ስንነጋገር እውነተኛ ደስታ እናገኛለን።—መዝ. 34:8፤ 133:1-3
8. የመንፈሳዊው ገነት ሁለት ዋነኛ መገለጫዎች ምንድን ናቸው?
8 በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለው ፍቅርና አንድነት የመንፈሳዊው ገነት ሁለት ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው። ይህ “የአንድነት ማሰሪያ” በአዲሱ ዓለም የሚኖረው ሕይወት ምን ዓይነት እንደሚሆን ይጠቁመናል፤ በዚያ ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች ከአሁኑም ይበልጥ ፍቅርና አንድነት ይኖራቸዋል። (ቆላ. 3:14) አንዲት እህት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትገናኝ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “በቤተሰቤ መካከል ሆኜም እንኳ እንዴት ደስተኛ መሆን እንደምችል አላውቅም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ የተመለከትኩት በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ነው።” እውነተኛ ደስታና እርካታ ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ይህን መንፈሳዊ ገነት መቅመስ አለበት። ዓለም ለይሖዋ አገልጋዮች ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን፣ በይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ መካከል ግን የተከበረ ስም አላቸው።—ኢሳ. 65:15
9. ኢሳይያስ 65:16, 17 ስለሚያስጨንቁን ነገሮች ምን ተስፋ ይዟል?
9 ዘና የሚያደርግና የመረጋጋት ስሜት የሚፈጥር። ኢሳይያስ 65:14 ከመንፈሳዊው ገነት ውጭ ለመኖር የሚመርጡ ሰዎች ‘ከልባቸው ሐዘን የተነሳ እንደሚጮኹና መንፈሳቸው ስለተሰበረም ዋይ ዋይ እንደሚሉ’ ይናገራል። ይሁንና በአምላክ ሕዝብ ላይ ሥቃይና ጭንቀት ስላስከተሉት ነገሮችስ ምን ማለት ይቻላል? ወደፊት እነዚህ ነገሮች ‘ይረሳሉ፤ እንዲሁም ከአምላክ ዓይን ይሰወራሉ።’ (ኢሳይያስ 65:16, 17ን አንብብ።) ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ ያስወግድልናል፤ እነዚህ ትውስታዎች የሚያስከትሉብንም ሥቃይ በጊዜ ሂደት ይጠፋል።
10. ከክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መሆን በረከት እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 በአሁኑ ወቅትም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ይህ ክፉ ዓለም በሚያሳድርብን ጭንቀት ላይ መብሰልሰል ትተን እንረጋጋለን። የአምላክ መንፈስ ፍሬ ክፍል የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ደግነትንና ገርነትን በማንጸባረቅ መንፈሳዊው ገነት ውስጥ ላለው መረጋጋት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ገላ. 5:22, 23) በአምላክ ድርጅት ውስጥ መታቀፍ እንዴት ያለ በረከት ነው! ከመንፈሳዊው ገነት ሳይወጡ የሚኖሩ ሰዎች፣ አምላክ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” እንደሚፈጥር የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ ሲፈጸም የመመልከት አጋጣሚ ያገኛሉ።
11. በኢሳይያስ 65:18, 19 መሠረት ይሖዋ የፈጠረው መንፈሳዊ ገነት ምን ስሜት ይፈጥርብናል?
11 በአመስጋኝነትና በአድናቆት ስሜት እንድንሞላ የሚያደርግ። ከዚህ በመቀጠል ኢሳይያስ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ በመሆናችን ‘ደስ ሊለንና ሐሴት ልናደርግ’ የሚገባው ለምን እንደሆነ ገልጿል። ይህን መንፈሳዊ ገነት የፈጠረው ይሖዋ ነው። (ኢሳይያስ 65:18, 19ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ሰዎች በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ካሉት በመንፈሳዊ ድርቅ የተመቱ ድርጅቶች ወጥተው ውብ ወደሆነው መንፈሳዊ ገነት እንዲገቡ እንድንጋብዝ እየተጠቀመብን ያለው ለዚህ ነው። በእውነት ውስጥ በመሆናችን ምክንያት ላገኘናቸው በረከቶች በጣም አመስጋኞች ነን፤ ለሌሎችም ይህንን ለመናገር እንጓጓለን።—ኤር. 31:12
12. በኢሳይያስ 65:20-24 ላይ ስለተጠቀሱት ተስፋዎች ስታስብ ምን ይሰማሃል? ለምንስ?
12 በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ በመኖራችን ምክንያት ላገኘናቸው ተስፋዎችም አመስጋኞች ነን። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ስለምናያቸውና ስለምናደርጋቸው ነገሮች እስቲ ቆም ብለህ አስብ! መጽሐፍ ቅዱስ “ለጥቂት ቀን ብቻ የሚኖር ሕፃንም ሆነ ዕድሜ የማይጠግብ አረጋዊ አይኖርም” ይላል። ‘ቤቶችን እንሠራለን፤ በዚያም እንኖራለን፤ ወይንንም እንተክላለን፤ ፍሬውንም እንበላለን።’ ‘ይሖዋ ስለሚባርከን በከንቱ አንለፋም።’ እውነተኛ ዓላማ ያለው አስተማማኝና አርኪ ሕይወት እንደሚኖረን ቃል ገብቶልናል። ‘ገና ሳንጣራ’ እያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ነገር ያውቃል፤ “የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት” ያሟላል።—ኢሳ. 65:20-24፤ መዝ. 145:16
13. ኢሳይያስ 65:25 ሰዎች ይሖዋን ማገልገል ሲጀምሩ በሕይወታቸው ላይ የሚያደርጉትን ለውጥ የሚገልጸው እንዴት ነው?
13 ሰላም የሰፈነበትና አስተማማኝ። ቀደም ሲል የአውሬ ዓይነት ባሕርይ የነበራቸው ብዙ ሰዎች በይሖዋ መንፈስ እርዳታ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ችለዋል። (ኢሳይያስ 65:25ን አንብብ።) የነበሯቸውን መጥፎ ባሕርያት አሸንፈዋል። (ሮም 12:2፤ ኤፌ. 4:22-24) እርግጥ አሁንም ቢሆን እኛ የአምላክ ሕዝቦች ፍጹማን አይደለንም፤ ስለዚህ ስህተት መሥራታችን አይቀርም። ሆኖም ይሖዋ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ ሊበጠስ በማይችል የፍቅርና የሰላም ሰንሰለት አስተሳስሯል። (ቲቶ 2:11) ይህ ሁሉን ቻዩ አምላክ ብቻ ሊፈጽመው የሚችል ተአምር ነው!
14. የአንድ ወንድም ተሞክሮ ኢሳይያስ 65:25 እውነት መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
14 በእርግጥ ሰዎች ባሕርያቸውን መቀየር ይችላሉ? አንድ ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ወጣት ሥነ ምግባር የጎደለውና በዓመፅ የተሞላ ሕይወት ይመራ የነበረ ሲሆን ገና 20 ዓመት እንኳ ሳይሞላው በተደጋጋሚ እስር ቤት ገብቶ ነበር። በመኪና ስርቆት፣ በዝርፊያና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ተከሶ ታስሯል። ከማንኛውም ሰው ጋር ለመደባደብ ዝግጁ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ እውነትን ሲሰማና በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ሲገኝ የሕይወትን ዓላማ እንዳገኘ ተረዳ፤ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ይሖዋን ለማገልገልም ተነሳሳ። ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ ኢሳይያስ 65:25 በእሱ ሕይወት ፍጻሜውን ያገኘበት መንገድ ያስደንቀዋል። እንደ አንበሳ ዓመፀኛ የነበረው ሰው እንደ በግ ግልገል ሰላማዊ መሆን ችሏል።
15. ሌሎች መንፈሳዊውን ገነት እንዲቀላቀሉ መጋበዝ የምንፈልገው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
15 ኢሳይያስ 65:13 የሚጀምረው “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል” በማለት ነው። ቁጥር 25 ደግሞ የሚደመድመው “ይላል ይሖዋ” በሚሉት ቃላት ነው። እሱ የገባው ቃል ምንጊዜም ቢሆን ይፈጸማል። (ኢሳ. 55:10, 11) መንፈሳዊው ገነት አሁንም በእውን ያለ ነገር ነው። ይሖዋ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የወንድማማች ማኅበር ፈጥሯል። በእሱ ሕዝቦች መካከል በመሆናችን በዚህ በዓመፅ የተሞላ ዓለም ውስጥ አንጻራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት አግኝተናል። (መዝ. 72:7) በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ፣ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችንን እንዲቀላቀሉ መርዳት እንፈልጋለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በማተኮር ነው።—ማቴ. 28:19, 20
ሌሎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት መሳብ የምንችለው እንዴት ነው?
16. ሰዎች ወደ መንፈሳዊው ገነት የሚሳቡት እንዴት ነው?
16 መንፈሳዊው ገነት ለሌሎች የሚስብ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እያንዳንዳችን አስፈላጊ ሚና እንጫወታለን። ይህን ኃላፊነታችንን መወጣት የምንችለው ይሖዋን የምንመስል ከሆነ ነው። ይሖዋ ሰዎችን ያለፈቃዳቸው ወደ ድርጅቱ እንዲገቡ አያስገድዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ወደ ራሱ ‘የሚስባቸው’ በፍቅር ነው። (ዮሐ. 6:44፤ ኤር. 31:3) ስለ ይሖዋ ፍቅርና ስለ ማራኪ ባሕርያቱ የተማሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እሱ መሳባቸው አይቀርም። እኛስ መልካም ባሕርያትና ጥሩ ምግባር በማሳየት ሌሎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት መሳብ የምንችለው እንዴት ነው?
17. ሰዎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት መሳብ የምንችለው እንዴት ነው?
17 ሌሎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት መሳብ የምንችልበት አንዱ መንገድ የእምነት አጋሮቻችንን በፍቅርና በደግነት በመያዝ ነው። ጳውሎስ በጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ ላይ የተገኙ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተናግሮ ነበር። ዛሬም በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ አዳዲስ ሰዎች ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ እንፈልጋለን። (1 ቆሮ. 14:24, 25፤ ዘካ. 8:23) ስለሆነም “እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችንን መቀጠል አለብን።—1 ተሰ. 5:13
18. ሰዎችን ወደ ድርጅታችን የሚስባቸው ምን ሊሆን ይችላል?
18 ምንጊዜም ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ይሖዋ በሚያያቸው መንገድ ለመመልከት ጥረት ማድረግ አለብን። ይህን የምናደርገው ወደፊት በሚጠፋው አለፍጽምናቸው ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ በማተኮር ነው። ‘አንዳችን ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምንራራ በመሆን እንዲሁም እርስ በርሳችን በነፃ ይቅር በመባባል’ በመካከላችን የሚፈጠረውን ማንኛውንም ቅራኔ በፍቅር መፍታት እንችላለን። (ኤፌ. 4:32) ይህም፣ ሌሎች በዚሁ መንገድ እንዲይዟቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት ይስባቸዋል። b
ከመንፈሳዊው ገነት አትውጣ
19. (ሀ) “ ቢወጡም ተመልሰዋል” በሚለው ሣጥን ውስጥ እንደተገለጸው አንዳንዶች ወደ መንፈሳዊው ገነት ከተመለሱ በኋላ ምን ብለዋል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
19 ለመንፈሳዊው ገነታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህ መንፈሳዊ ገነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተውቧል፤ በውስጡ ያሉት ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎችም ቁጥራቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨምሯል። ይሖዋ ለፈጠረልን ለዚህ ገነት ለዘላለም አመስጋኞች ሆነን እንቀጥል። እፎይታ፣ እርካታ፣ መረጋጋትና ሰላም ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት መምጣትና እዚያው መቆየት ይኖርበታል። ነገር ግን ሰይጣን እኛን አታልሎ ከመንፈሳዊው ገነት ለማስወጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ ስለሌለ ንቁዎች መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 12:9) እንዲሳካለት ልንፈቅድ አይገባም። እንግዲያው የዚህን መንፈሳዊ ገነት ውበት፣ ንጽሕና እና ሰላም በንቃት እንጠብቅ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
-
መንፈሳዊው ገነት ምንድን ነው?
-
በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ምን በረከቶችን እናገኛለን?
-
ሌሎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት መሳብ የምንችለው እንዴት ነው?
መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “መንፈሳዊ ገነት” የሚለው አገላለጽ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ያሉበትን ደህንነቱ የተጠበቀ ሁኔታ ያመለክታል። በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ከይሖዋ ጋርም ሆነ እርስ በርሳችን ያለን ግንኙነት ሰላማዊ ነው።
b የት ናቸው?—አሌና ዥትኒኮቫ፦ ሕልሜ እውን የሆነልኝ እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት፤ ከዚያም አንዲት እህት በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ በመሆኗ ያገኘቻቸውን በረከቶች ልብ በል።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ብዙዎች እርስ በርስ ሲጨዋወቱ አንድ ወንድም ለብቻው ተገልሎ ቁጭ ብሏል።