በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 14

መዝሙር 56 እውነትን የራስህ አድርግ

‘ወደ ጉልምስና ለመድረስ ተጣጣሩ’

‘ወደ ጉልምስና ለመድረስ ተጣጣሩ’

“ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር።”ዕብ. 6:1

ዓላማ

የጎለመሱ ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንደሆነ እንዲሁም ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ውሳኔዎች እንደሚያደርጉ እንመለከታለን።

1. ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

 ባለትዳሮች በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ከሚደሰቱባቸው ወቅቶች አንዱ ልጃቸው የሚወለድበት ቀን ነው። ይሁንና ወላጆች ሕፃን ልጃቸውን በጣም ቢወዱትም ለዘላለም ሕፃን ሆኖ እንዲኖር አይፈልጉም። እንዲያውም ልጃቸው ካላደገ በጣም መጨነቃቸው አይቀርም። በተመሳሳይም ይሖዋ “ሀ” ብለን ኢየሱስን መከተል ስንጀምር በጣም ይደሰታል፤ ሆኖም በመንፈሳዊ ሕፃን ሆነን እንድንቀር አይፈልግም። (1 ቆሮ. 3:1) ከዚህ ይልቅ ‘የጎለመስን’ ክርስቲያኖች እንድንሆን ይጠብቅብናል።—1 ቆሮ. 14:20

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 የጎለመሰ ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና መድረስ የምንችለው እንዴት ነው? ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ እድገት እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው? ከልክ በላይ በራሳችን ከመተማመን መቆጠብ ያለብንስ ለምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን።

የጎለመሰ ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

3. የጎለመሰ ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የጎለመሰ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የበሰለ፣” “ፍጹም” ወይም “ሙሉ” የሚል ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። a (1 ቆሮ. 2:6) አንድ ሕፃን አድጎ ጎልማሳ እንደሚሆነው ሁሉ እኛም ከመንፈሳዊ ሕፃንነት አልፈን እድገት ስናደርግ የጎለመስን ክርስቲያኖች መሆን እንችላለን። እርግጥ ነው፣ እዚህ ግብ ላይ ከደረስን በኋላም እንኳ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን ማቆም አይኖርብንም። (1 ጢሞ. 4:15) ወጣቶችን ጨምሮ ሁላችንም በመንፈሳዊ ጎልማሳ መሆን እንችላለን። ይሁንና አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ መጎልመሱ የሚታወቀው እንዴት ነው?

4. አንድ ክርስቲያን መጎልመሱ የሚታወቀው እንዴት ነው?

4 የጎለመሰ ክርስቲያን ይሖዋ የሚጠብቅበትን ነገር በሙሉ ያደርጋል፤ ከአምላክ መመሪያዎች መካከል መርጦ የሚያስቀረው አይኖርም። እርግጥ ነው፣ ፍጹም ሰው ስላልሆነ ስህተት መሥራቱ አይቀርም። ያም ቢሆን፣ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንደሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ያሳያል። አዲሱን ስብዕና ይለብሳል፤ እንዲሁም አስተሳሰቡን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት ሁልጊዜ ጥረት ያደርጋል። (ኤፌ. 4:22-24) በይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርቶ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ውሳኔዎች ለማድረግ ራሱን አሠልጥኗል። በመሆኑም ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን ነገር ለመወሰን ዝርዝር መመሪያ አያስፈልገውም። ራሱን የመገሠጽ ችሎታ ስላለው አንድ ውሳኔ ካደረገ በኋላ ለውሳኔው ራሱን ያስገዛል።—1 ቆሮ. 9:26, 27

5. ያልጎለመሰ ክርስቲያን ምን ሊያጋጥመው ይችላል? (ኤፌሶን 4:14, 15)

5 በሌላ በኩል ደግሞ ያልጎለመሰ ክርስቲያን ‘በማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ’ በቀላሉ ይታለላል፤ የሴራ ተንታኞችንና ከሃዲዎችን ሊያምን ይችላል። b (ኤፌሶን 4:14, 15ን አንብብ።) በሌሎች የመቅናት፣ ክፍፍል የመፍጠር፣ በቀላሉ የመበሳጨት ወይም ለፈተና እጅ የመስጠት ዝንባሌ ይኖረው ይሆናል።—1 ቆሮ. 3:3

6. አንድ ክርስቲያን ወደ ጉልምስና ደረጃ የሚደርስበት መንገድ ልጆች ከሚያድጉበት መንገድ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን ወደ ጉልምስና ደረጃ የሚደርስበትን መንገድ አንድ ሕፃን እድገት ከሚያደርግበት መንገድ ጋር ያመሳስለዋል። ሕፃናት ማስተዋል ይጎድላቸዋል፤ በመሆኑም የአዋቂ ክትትልና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ አንዲት እናት፣ ልጇ ትንሽ ሳለች እጇን ይዛ መንገድ ታሻግራት ይሆናል። ልጅቷ እያደገች ስትሄድ ግን ብቻዋን መንገድ እንድትሻገር እናቷ ትፈቅድላት ይሆናል፤ ያም ቢሆን መንገድ ስትሻገር ግራ ቀኟን እንድታይ ታሳስባታለች። ልጅቷ አዋቂ ከሆነች በኋላ ግን እንዲህ ካሉ አደገኛ ሁኔታዎች ራሷን መጠበቅ ትችላለች። ትናንሽ ልጆች ከአደገኛ ሁኔታዎች ለመራቅ የአዋቂዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልጎለመሱ ክርስቲያኖችም ከመንፈሳዊ አደጋዎች ለመራቅና ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ውሳኔዎች ለማድረግ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በአንጻሩ ግን፣ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመጠቀም ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ፤ ከዚያም ተገቢውን ውሳኔ ይወስናሉ።

ያልጎለመሱ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ መማር ይኖርባቸዋል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7. የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሌሎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል?

7 ታዲያ የጎለመሱ ክርስቲያኖች የማንም እርዳታ አያስፈልጋቸውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። የጎለመሱ ክርስቲያኖችም እርዳታ መጠየቅ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይኖራል። ሆኖም አንድ ያልጎለመሰ ክርስቲያን፣ ሌሎች ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲነግሩት ወይም በእሱ ፋንታ ውሳኔ እንዲያደርጉለት ይጠብቅ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የጎለመሰ ክርስቲያን ከሌሎች ጥበብና ተሞክሮ ለመጠቀም ጥረት ቢያደርግም ይሖዋ “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” እንዲሸከም እንደሚጠብቅበት ይገነዘባል።—ገላ. 6:5

8. የጎለመሱ ክርስቲያኖች የተለያዩ ሊሆኑ የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

8 ሁሉም አዋቂዎች አንድ ዓይነት መልክና ቁመና እንደማይኖራቸው ሁሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖችም ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ በጥበባቸው፣ በድፍረታቸው፣ በልግስናቸው ወይም በአሳቢነታቸው ተለይተው ሊታወቁ ይችላሉ። በተጨማሪም ሁለት የጎለመሱ ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የተለያየ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፤ ሆኖም ሁለቱም መደምደሚያዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ተቀባይነት ይኖራቸዋል። በተለይ ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ይህን ስለሚገነዘቡ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች በሌሎች ላይ ለመፍረድ አይቸኩሉም። ከዚህ ይልቅ አንድነታቸውን በመጠበቅ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።—ሮም 14:10፤ 1 ቆሮ. 1:10

ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና መድረስ የምንችለው እንዴት ነው?

9. መንፈሳዊ ጉልምስና በራሱ የሚመጣ ነገር ነው? አብራራ።

9 አንድ ልጅ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትልቅ ሰው መሆኑ አይቀርም። መንፈሳዊ ጉልምስና ግን በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም። ለምሳሌ በቆሮንቶስ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ምሥራቹን ተቀብለዋል፤ ተጠምቀዋል፤ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ለረጅም ጊዜ አስተምሯቸዋል። (ሥራ 18:8-11) ያም ቢሆን ከተጠመቁ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም ብዙዎቹ በመንፈሳዊ አልጎለመሱም ነበር። (1 ቆሮ. 3:2) እኛስ መንፈሳዊ እድገታችን አዝጋሚ እንዳይሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

10. ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ይሁዳ 20)

10 ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ በመጀመሪያ ጎልማሳ የመሆን ፍላጎት ልናዳብር ይገባል። ‘አላዋቂነትን የሚወዱ’ ማለትም በመንፈሳዊ ሕፃን ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሰዎች እድገት ማድረግ አይችሉም። (ምሳሌ 1:22) ትልቅ ሰው ከሆኑ በኋላም ያለወላጆቻቸው እርዳታ ውሳኔ ማድረግ እንደማይችሉ ሰዎች መሆን አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የራሳችን ኃላፊነት እንደሆነ አምነን መቀበል ይኖርብናል። (ይሁዳ 20ን አንብብ።) በአሁኑ ወቅት ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግክ ከሆነ ይሖዋ ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርብህም ሆነ ኃይል እንድታገኝ’ እንዲረዳህ ጸልይ።—ፊልጵ. 2:13

11. ይሖዋ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ እንድንደርስ የሚረዳን እንዴት ነው? (ኤፌሶን 4:11-13)

11 ይሖዋ በራሳችን ጥረት ብቻ ጉልምስና ደረጃ ላይ እንድንደርስ አይጠብቅብንም። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እረኞችና አስተማሪዎች ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች በመንፈሳዊ “ሙሉ ሰው ወደ መሆን ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ” እንድንደርስ እኛን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። (ኤፌሶን 4:11-13ን አንብብ።) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት “የክርስቶስ አስተሳሰብ” እንዲኖረን ይረዳናል። (1 ቆሮ. 2:14-16) በተጨማሪም አምላክ በመንፈስ መሪነት አራቱ ወንጌሎች እንዲጻፉልን አድርጓል፤ እነዚህ ወንጌሎች ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ አስተሳሰቡ፣ አነጋገሩና ድርጊቱ ምን ይመስል እንደነበር ያስተምሩናል። የኢየሱስን አስተሳሰብና ምግባር በመኮረጅ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ የመድረስ ግባችንን ማሳካት እንችላለን።

ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ

12. ‘ስለ ክርስቶስ የተማርነው መሠረታዊ ትምህርት’ ሲባል ምን ማለት ነው?

12 ወደ ጉልምስና ደረጃ ለመድረስ “ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት” ማለትም መሠረታዊ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች አልፈን መሄድ ይኖርብናል። ከእነዚህ መሠረታዊ ትምህርቶች መካከል ስለ ንስሐ፣ ስለ እምነት፣ ስለ ጥምቀትና ስለ ትንሣኤ የሚናገሩት ትምህርቶች ይገኙበታል። (ዕብ. 6:1, 2) እነዚህ ትምህርቶች የክርስትና መሠረት ናቸው። በዚህም የተነሳ በጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ሕዝቡን ባስተማረበት ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ተናግሯል። (ሥራ 2:32-35, 38) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እነዚህን መሠረታዊ ትምህርቶች መቀበል ይኖርብናል። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ የትንሣኤን ትምህርት የማይቀበል ሁሉ ክርስቲያን ሊባል እንደማይችል ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:12-14) ሆኖም የእውነትን መሠረታዊ እውቀት በማግኘት ብቻ ረክተን መቀመጥ የለብንም።

13. ዕብራውያን 5:14 ላይ ከተጠቀሰው ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 መሠረታዊ ከሆኑት ትምህርቶች በተለየ መልኩ ጠንካራ ምግብ የይሖዋን ሕጎች ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ሥርዓቶቹንም ያካትታል፤ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች የእሱን አስተሳሰብ ለመረዳት ያግዙናል። እንዲህ ካለው ምግብ ለመጠቀም የአምላክን ቃል ማጥናትና ማሰላሰል እንዲሁም አቅማችን በፈቀደ መጠን በሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ ራሳችንን እናሠለጥናለን። cዕብራውያን 5:14ን አንብብ።

ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ይረዳናል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት) d


14. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ወደ ጉልምስና ደረጃ እንዲደርሱ የረዳቸው እንዴት ነው?

14 ብዙውን ጊዜ፣ ያልጎለመሱ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማመዛዘንና በሥራ ላይ ማዋል የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ይቸገራሉ። አንዳንዶች ስለ ጉዳዩ የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ከሌለ የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሕግ በማያስፈልግበት ቦታ ሕግ እንዲሰጣቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። ለምሳሌ በቆሮንቶስ የነበሩት ክርስቲያኖች ለጣዖት የተሠዋ እንስሳን ሥጋ ከመብላት ጋር በተያያዘ ጳውሎስ መመሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከመናገር ይልቅ ሕሊና ስለሚጫወተው ሚና እና እያንዳንዱ ሰው ስላለው ‘የመምረጥ መብት’ ነገራቸው። እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ሳያሰናክል ሕሊናው የሚፈቅድለትን ነገር ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጠቀሰላቸው። (1 ቆሮ. 8:4, 7-9) በዚህ መንገድ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉላቸው ወይም ሕግ እንዲሰጧቸው ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም እንዲችሉ ሲል በመንፈሳዊ እንዲያድጉ እየረዳቸው ነበር።

15. ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የረዳቸው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጻፈላቸው ሐሳብ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። አንዳንዶቹ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን አቁመው ነበር። እንዲያውም “ጠንካራ [መንፈሳዊ] ምግብ ከመመገብ ይልቅ እንደገና ወተት መፈለግ” ጀምረው ነበር። (ዕብ. 5:12) በጉባኤው አማካኝነት ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ ካለው እውነት ጋር እኩል መሄድ ተስኗቸዋል። (ምሳሌ 4:18) ለምሳሌ ከ30 ዓመት ገደማ በፊት ሕጉ በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት የተሻረ ቢሆንም በርካታ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሁንም የሙሴን ሕግ ይከተሉ ነበር። (ሮም 10:4፤ ቲቶ 1:10) መቼም እነዚያ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በ30 ዓመት ውስጥ አስተሳሰባቸውን ያስተካክላሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ ያነበበ ማንኛውም ሰው ይህ መጽሐፍ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ እንደያዘ ማስተዋሉ አይቀርም። ይህ መልእክት እነዚያ ክርስቲያኖች በክርስትና ውስጥ ያለው የአምልኮ ሥርዓት የላቀ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንዲሁም አይሁዳውያን ቢቃወሟቸውም በድፍረት መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።—ዕብ. 10:19-23

ከልክ በላይ በራስ መተማመን ያለው አደጋ

16. ወደ ጉልምስና ከመድረስ በተጨማሪ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ወደ ጉልምስና ለመድረስ ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም ጎልማሳ ሆነን ለመኖርም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህም ከልክ በላይ በራስ ከመተማመን መቆጠብን ይጠይቃል። (1 ቆሮ. 10:12) አሁንም እድገት እያደረግን መሆኑን ለማረጋገጥ ‘ዘወትር ራሳችንን መፈተሽ’ ይኖርብናል።—2 ቆሮ. 13:5

17. ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ጎልማሳ ሆኖ የመኖርን አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጎልማሳ ሆኖ የመኖርን አስፈላጊነት በድጋሚ ጎላ አድርጎ ገልጿል። እነዚያ ክርስቲያኖች ወደ ጉልምስና ደረጃ የደረሱ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ ዓለማዊ አስተሳሰብ ወጥመድ እንዳይሆንባቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ቆላ. 2:6-10) በተጨማሪም ያንን ጉባኤ በደንብ የሚያውቀው ኤጳፍራ፣ እነዚያ ክርስቲያኖች “ፍጹም” ወይም ጎልማሳ ሆነው ‘እስከ መጨረሻው እንዲቆሙ’ ዘወትር ይጸልይ ነበር። (ቆላ. 4:12) ነጥቡ ምንድን ነው? ጳውሎስም ሆነ ኤጳፍራ ጎልማሳ ሆኖ ለመቀጠል፣ ጥረት ማድረግና የአምላክን ድጋፍ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል። የቆላስይስ ክርስቲያኖች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሙሉ ተቋቁመው ጎልማሳ ሆነው እንዲቀጥሉ ይፈልጉ ነበር።

18. አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ምን ሊያጋጥመው ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

18 ጳውሎስ፣ አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን የአምላክን ሞገስ ለዘለቄታው ሊያጣ እንደሚችል ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አስጠንቅቋቸዋል። አንድ ክርስቲያን ልቡ በጣም ከመደንደኑ የተነሳ ንስሐ መግባት ሊሳነውና የአምላክን ይቅርታ ሳያገኝ ሊቀር ይችላል። ደስ የሚለው፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በዚያ ደረጃ ርቀው አልሄዱም። (ዕብ. 6:4-9) በዛሬው ጊዜ ስላሉ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ወይም ከተወገዱ በኋላ ንስሐ ስለገቡ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? በትሕትና ንስሐ መግባታቸው ጳውሎስ ከጠቀሳቸው የአምላክን ሞገስ ለዘለቄታው የሚያጡ ሰዎች የተለዩ እንደሆኑ ይጠቁማል። ይሁንና ወደ ይሖዋ ሲመለሱ እሱ የሚሰጠው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ሕዝ. 34:15, 16) ሽማግሌዎች፣ ተሞክሮ ያለው አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ እንዲበረቱ እገዛ እንዲያደርግላቸው ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ።

ይሖዋ በመንፈሳዊ ለመበርታት እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ክርስቲያኖች ይረዳል (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)


19. ምን ዓይነት ግብ ሊኖረን ይገባል?

19 ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ለመድረስ እየተጣጣርክ ከሆነ ግብህ ላይ መድረስ ትችላለህ። ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገብህን እንዲሁም አስተሳሰብህን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት ጥረት ማድረግህን ቀጥል። አሁንም የጎለመስክ ክርስቲያን ከሆንክ ደግሞ ጉልምስናህን አጥብቀህ ያዝ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ጎልማሳ ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

  • ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና መድረስ የምንችለው እንዴት ነው?

  • ከልክ በላይ በራሳችን መተማመን የሌለብን ለምንድን ነው?

መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!

a የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት “የጎለመሰ” እና “ያልጎለመሰ” የሚሉትን ቃላት ባይጠቀሙም ይህን ሐሳብ የሚያስተላልፉ አገላለጾች አሏቸው። ለአብነት ያህል የምሳሌ መጽሐፍ ወጣት የሆነንና ተሞክሮ የሌለውን ሰው ጥበበኛ ከሆነና ማስተዋል ካለው ሰው ጋር ያነጻጽራል።—ምሳሌ 1:4, 5

b jw.org እና JW ላይብረሪ ላይ “ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች” በሚለው ተከታታይ ርዕስ ሥር ያለውን “ከተሳሳተ መረጃ ራስህን ጠብቅ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c በዚህ መጽሔት ላይ የወጣውን “የጥናት ፕሮጀክት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የመዝናኛ ምርጫ በሚያደርግበት ወቅት ከአምላክ ቃል ያገኛቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ሲያውል።