በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሰዎች ውጫዊ ገጽታ ባሻገር ለመመልከት ትሞክራላችሁ?

ከሰዎች ውጫዊ ገጽታ ባሻገር ለመመልከት ትሞክራላችሁ?

በካናዳ የሚኖር ዶን የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማነጋገር ልዩ ጥረት ያደርጋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ስለ አንዱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በመንደር ውስጥ ባሉ መንገዶች ላይ ካየኋቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ሁሉ እንደ ፒተር ያለ ቁሽሽ ያለ ሰው አይቼ አላውቅም። ፈጽሞ ሰው እንዲቀርበው የማይፈልግ አስቸጋሪ ሰው ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች ሊረዱት ሞክረው አልተሳካላቸውም።” ይሁንና ዶን ተስፋ ሳይቆርጥ ለ14 ዓመታት ያህል ለዚህ ሰው ደግነት ለማሳየት በተለያዩ ጊዜያት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

አንድ ቀን ፒተር ዶንን እንዲህ ብሎ ጠየቀው፦ “ሰዉ ሁሉ ተስፋ ቆርጦ ትቶኛል። አንተ ግን የማትተወኝ ለምንድን ነው? ስለ እኔ ምን አስጨነቀህ?” ዶን ሦስት ጥቅሶችን በዘዴ በመጠቀም የፒተርን ልብ ለመንካት ሞከረ። በመጀመሪያ፣ አምላክ ስም እንዳለው ያውቅ እንደሆነ ከጠየቀው በኋላ መዝሙር 83:18ን በማውጣት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ እንዲያነብ ጋበዘው። ከዚያም ስለ እሱ የሚጨነቀው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት ሮም 10:13, 14ን እንዲያነብ አደረገ፤ ጥቅሱ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል። በመጨረሻም ዶን ማቴዎስ 9:36ን ካነበበለት በኋላ ፒተር ራሱም ጥቅሱን እንዲያነብ ጋበዘው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ ሕዝቡን] ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” በዚህ ጊዜ ፒተር ዓይኖቹ እንባ አቅርረው “እኔም ከእነዚህ በጎች እንደ አንዱ እቆጠራለሁ?” በማለት ጠየቀ።

ፒተር ለውጥ ማድረግ ጀመረ። ሰውነቱን ታጠበ፣ ጺሙን አስተካከለ እንዲሁም ዶን የሰጠውን ጥሩ ልብስ ለበሰ። ከዚያ በኋላ ፒተር ንጽሕናውን ይጠብቅ ጀመር።

ፒተር የዕለት ተዕለት ውሎውን በማስታወሻ የማስፈር ልማድ ነበረው። መጀመሪያ አካባቢ ማስታወሻው ላይ የጻፋቸው ነገሮች የሕይወቱን አሉታዊ ገጽታ የሚገልጹ ነበሩ፤ በኋላ ላይ የጻፋቸው ነገሮች ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። ካሰፈራቸው ማስታወሻዎች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፦ “ዛሬ የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ተማርኩ። አሁን ስጸልይ ወደ ይሖዋ መጸለይ እችላለሁ። ስሙን ማወቅ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው። ዶን፣ አምላክ የግል ወዳጄ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሳነጋግረው እንደሚሰማኝ ነግሮኛል።”

ፒተር የመጨረሻውን ማስታወሻ የጻፈው ለወንድሙና ለእህቱ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦

“ዛሬ ብዙም ጤንነት አይሰማኝም። እርጅና መጣ መሰለኝ። ብቻ የዛሬዋ ዕለት በሕይወት የምኖርባት የመጨረሻዋ ቀን ብትሆን እንኳ ጓደኛዬን [ዶንን]ዳግመኛ በገነት ውስጥ እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ። መቼም ይህን ማስታወሻ ስታነቡ እኔ በሕይወት የለሁም። ሆኖም በቀብር ሥነ ሥርዓቴ ላይ እናንተ የማታውቁት ሰው ከተገኘ አነጋግሩት፤ እባካችሁ ይህችን ትንሽ ሰማያዊ መጽሐፍም አንብቧት። * መጽሐፏ ጓደኛዬን ዳግመኛ በገነት እንደማገኘው ትናገራለች። ይህ እንደሚፈጸም ሙሉ እምነት አለኝ። የሚወዳችሁ ወንድማችሁ፣ ፒተር።”

የፒተር እህት ኡሚ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ፒተርን አግኝቼው ነበር። ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ደስተኛ ሆኖ አየሁት። እንዲያውም ፊቱ ላይ ፈገግታ ይነበብ ነበር።” ኡሚ ዶንን እንዲህ ብላዋለች፦ “መጽሐፉን አነበዋለሁ፤ መቼም የወንድሜን ልብ መንካት ከቻለ በእርግጥም ልዩ መጽሐፍ መሆን አለበት።” በተጨማሪም ኡሚ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማምታለች።

እኛም ከሰዎች ውጫዊ ገጽታ ባሻገር ለመመልከት፣ እውነተኛ ፍቅር ለማሳየትና ሁሉንም ዓይነት ሰዎች በትዕግሥት ለመያዝ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (1 ጢሞ. 2:3, 4) እንዲህ ካደረግን ልክ እንደ ፒተር ብዙም ለመቅረብ የማይጋብዙ፣ ግን ቅን የሆኑ ሰዎችን ልብ መንካት እንችል ይሆናል። ‘ልብን የሚያየው’ አምላክ ትክክለኛ ዝንባሌ ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ የእውነት ዘር እንዲያድግ እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ሳሙ. 16:7፤ ዮሐ. 6:44

^ አን.7 ፒተር የጠቀሰው “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት” የተባለውን መጽሐፍ ሲሆን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ጽሑፍ ነው፤ አሁን መታተም አቁሟል።