በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም”

“መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም”

“ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመሥከር ነው።”—ዮሐ. 18:37

መዝሙሮች፦ 15, 74

1, 2. (ሀ) ዓለማችን ከዕለት ወደ ዕለት ይበልጥ እየተከፋፈለ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን?

“ከልጅነቴ አንስቶ በርካታ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ተመልክቻለሁ።” ይህን ያለችው በደቡባዊ አውሮፓ የምትኖር አንዲት እህት ናት። ይህች እህት ቀደም ሲል የነበራትን ሕይወት አስመልክታ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በአገሬ ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት በመቃወም፣ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያመጡ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንባቸውን ሐሳቦች መደገፍ ጀመርኩ። እንዲያውም ለብዙ ዓመታት የወንድ ጓደኛዬ ሽብርተኛ ነበር።” በደቡባዊ አፍሪካ የሚኖር አንድ ወንድምም በዓመፅ ድርጊት መካፈል ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ይሰማው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የእኔ ጎሳ ከሌሎች ጎሳዎች ሁሉ እንደሚበልጥ አስብ ስለነበር የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆንኩ። ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ የሚደግፉ ሰዎችን የእኛ ጎሳ አባላት ቢሆኑም እንኳ በጦር እንድንገድል ተነግሮን ነበር።” በመካከለኛው አውሮፓ የምትኖር አንዲት እህት ደግሞ “ከእኔ የተለየ ዜግነት ወይም ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻ ነበረኝ” ብላለች።

2 እነዚህ ሦስት ሰዎች ቀደም ሲል የነበራቸው አስተሳሰብ፣ ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ተስፋፍቶ የሚታየውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። በርካታ ፖለቲካዊ ቡድኖች ነፃነት ለማግኘት ዓመፅ ያካሂዳሉ፤ በፖለቲካዊ አመለካከት ሳቢያ የሚታየው ክፍፍል እየተባባሰ መጥቷል፤ በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች፣ ለስደተኞች ያላቸው ጥላቻም እየጨመረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ በርካታ ሰዎች “ለመስማማት ፈቃደኞች [እንደማይሆኑ]” አስቀድሞ ተናግሯል፤ በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ሲፈጸም እያየን ነው። (2 ጢሞ. 3:1, 3) ታዲያ ክርስቲያኖች ክፍፍል በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖሩ አንድነታቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ከኢየሱስ ምሳሌ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፤ ኢየሱስ በሚኖርበት አገር ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሰፍኖ ነበር። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ ኢየሱስ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ቡድን ጋር መወገን ያልፈለገው ለምንድን ነው? የአምላክ አገልጋዮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ማንኛውንም ወገን መደገፍ እንደሌለባቸው ኢየሱስ ያሳየው እንዴት ነው? በዓመፅ ድርጊት መካፈል ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ እንደሌለ ያስተማረውስ በምን መንገድ ነው?

ኢየሱስ ነፃ ለመውጣት ስለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምን አመለካከት ነበረው?

3, 4. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ለውጥ እንደሚመጣ ይጠብቁ ነበር? (ለ) ይህ አመለካከት በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

3 ኢየሱስ ይሰብክላቸው የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ከሮም አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ይጓጉ ነበር። ዜለት በመባል የሚታወቀው አክራሪ የፖለቲካ ቡድን አባላት የሆኑ አይሁዳውያን በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንዲህ ያለው ስሜት እንዲቀሰቀስ ያደርጉ ነበር። ከእነዚህ አክራሪ አይሁዳውያን ብዙዎቹ የገሊላው ይሁዳ ተከታዮች ነበሩ። ይህ ሰው የኖረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሲሆን መሲሕ ነኝ በማለት ብዙዎችን አሳስቷል። አይሁዳዊው የታሪክ ምሁር ጆሴፈስ እንደተናገረው ይሁዳ “የአገሩን ሰዎች እንዲያምፁ ይቀሰቅስ እንዲሁም ለሮማውያን ግብር በመክፈላቸው ወኔ ቢሶች እንደሆኑ በመግለጽ ይዘልፋቸው ነበር።” ሮማውያን ይሁዳን በሞት ቀጥተውታል። (ሥራ 5:37) ዜለት ከሚባሉት አይሁዳውያን አንዳንዶቹ፣ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ የዓመፅ ድርጊቶችን እንኳ ከመፈጸም አይመለሱም ነበር።

4 ከሮም አገዛዝ ነፃ ለመውጣት የሚፈልጉት እነዚህ አክራሪዎች ብቻ አልነበሩም፤ አብዛኞቹ አይሁዳውያንም ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያስገኝ መሲሕ ይመጣል ብለው በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። መሲሑ ሲመጣ፣ አገራቸውን ክብር እንደሚያጎናጽፋትና ከሮም ባርነት ነፃ እንደሚያወጣቸው ተስፋ ያደርጉ ነበር። (ሉቃስ 2:38፤ 3:15) ብዙዎች፣ መሲሑ በእስራኤል ውስጥ መንግሥት እንደሚያቋቁም ብሎም በተለያዩ አገሮች ተበታትነው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ያምኑ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ በአንድ ወቅት ኢየሱስን “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል እንደጠየቀው እናስታውስ ይሆናል። (ማቴ. 11:2, 3) ዮሐንስ ይህን ያለው፣ አይሁዳውያን ተስፋ የሚያደርጓቸውን ነገሮች በሙሉ የሚፈጽም ሌላ ሰው ይመጣ እንደሆነ ለማወቅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ ያነጋገራቸው ሁለት ደቀ መዛሙርትም ከመሲሑ ጋር በተያያዘ ይፈጸማሉ ብለው የጠበቋቸው አንዳንድ ነገሮች እንዳልተፈጸሙ ገልጸዋል። (ሉቃስ 24:21ን አንብብ።) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የኢየሱስ ሐዋርያት “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ብለው ጠይቀውታል።—ሥራ 1:6

5. (ሀ) የገሊላ ሰዎች ኢየሱስን ለማንገሥ የፈለጉት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ እርማት የሰጣቸው እንዴት ነው?

5 አይሁዳውያን መሲሑ ችግሮቻቸውን እንደሚፈታላቸው ይጠብቁ ነበር። የገሊላ ሰዎች ኢየሱስን ለማንገሥ የሞከሩት ለዚህ መሆን አለበት። ኢየሱስ የላቀ ችሎታ ያለው መሪ እንደሚሆንላቸው አስበው ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አስደናቂ የንግግር ችሎታ አለው እንዲሁም የታመሙትን መፈወስ አልፎ ተርፎም የተራቡትን መመገብ ይችላል። ኢየሱስ 5,000 ወንዶችን ከመገበ በኋላ “ሰዎቹ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ።” (ዮሐ. 6:10-15) ሕዝቡ በማግስቱ ከገሊላ ባሕር ማዶ ሲያገኙት ግን ስሜታቸው ተረጋግቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሥራውን ዓላማ አብራራላቸው። ወደ ምድር የመጣው በመንፈሳዊ ሊረዳቸው እንጂ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት አይደለም። “ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 6:25-27

6. ኢየሱስ በምድር ላይ ፖለቲካዊ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት እንደሌለው ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

6 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ አንዳንድ ተከታዮቹ ኢየሩሳሌም ውስጥ መንግሥት ያቋቁማል ብለው እየጠበቁ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ አመለካከታቸውን ለማስተካከል ሲል ስለ ምናን የሚገልጽ ምሳሌ ነገራቸው። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰውና ኢየሱስን የሚያመለክተው “መስፍን” ወደ ሩቅ አገር መሄድ ነበረበት፤ ይህ ደግሞ ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው። (ሉቃስ 19:11-13, 15) ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ ለሮም ባለሥልጣናትም ነግሯቸዋል። ጳንጥዮስ ጲላጦስ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” በማለት ኢየሱስን ጠይቆት ነበር። (ዮሐ. 18:33) አገረ ገዢው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ኢየሱስ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳይፈጥር ስለሰጋ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም በጲላጦስ ዘመን ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነበር። ኢየሱስ ግን “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” በማለት መልሶለታል። (ዮሐ. 18:36) ኢየሱስ፣ መንግሥቱ የሚቋቋመው በሰማይ ስለሆነ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ እንደማይገባ ገልጿል። ወደ ምድር የመጣው “ስለ እውነት ለመመሥከር” እንደሆነ ለጲላጦስ ነግሮታል።ዮሐንስ 18:37ን አንብብ።

ትኩረትህ ያረፈው በምን ላይ ነው? በዓለም ላይ ባሉት ችግሮች ወይስ በአምላክ መንግሥት? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. ፖለቲካዊ ነፃነት ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በልባችንም ቢሆን ከመደገፍ መቆጠብ ከባድ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

7 እኛም እንደ ኢየሱስ ተልዕኳችን ምን እንደሆነ ሁልጊዜ የምናስታውስ ከሆነ ፖለቲካዊ ነፃነት ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በልባችንም ቢሆን አንደግፍም። በእርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ለውጥ እንደሚያስፈልግ ይበልጥ እየተሰማቸው ነው። ብሔራዊ ስሜት እየተስፋፋ ሲሆን ብዙዎች ሕይወታቸውን የሚያሻሽለው ፖለቲካዊ ነፃነት ማግኘታቸው እንደሆነ ያስባሉ። ደስ የሚለው ነገር፣ ወንድሞች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ በመጠመድ ክርስቲያናዊ አንድነታቸውን ጠብቀው መኖር ችለዋል። ለፍትሕ መጓደልም ሆነ ለሚያጋጥሙን ሌሎች ችግሮች መፍትሔ ማስገኘት የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ ይተማመናሉ።”

ኢየሱስ መከፋፈል የሚፈጥሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ምን አድርጓል?

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚኖሩ አይሁዳውያን ምን ዓይነት ግፍ ይፈጸምባቸው ነበር?

8 ሰዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸው አንዱ ነገር በአካባቢያቸው የሚፈጸመው የፍትሕ መጓደል እየተባባሰ መሄዱ ነው። በኢየሱስ ዘመን ግብር የመክፈል ጉዳይ በጣም አወዛጋቢ ነበር። እንዲያውም ቀደም ሲል የተጠቀሰው የገሊላው ይሁዳ ለማመፅ እንዲነሳሳ ያደረገው፣ የሮም መንግሥት ሁሉም ሰው ግብር እንዲከፍል ለማድረግ ሲል ሕዝቡ እንዲመዘገብ ትእዛዝ ማስተላለፉ ነው። የኢየሱስን አድማጮች ጨምሮ የሮም ተገዢዎች ለመሬት፣ ለቤትና ለሌሎች ብዙ ነገሮች ግብር እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸው ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ በሙስና የተጠላለፉ መሆናቸው ሕዝቡ ከባድ ሸክም እንደተጫነበት እንዲሰማው አድርጎታል። እነዚህ ቀረጥ ሰብሳቢዎች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ገንዘብ በመክፈል ሥልጣን የሚያገኙ ሲሆን በሥልጣናቸው ተጠቅመው ሕዝቡን ይመዘብሩ ነበር። ለምሳሌ በኢያሪኮ የሚኖረው ዘኬዎስ የተባለ የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ ሕዝቡን በመበዝበዝ ሀብት አካብቶ ነበር። (ሉቃስ 19:2, 8) ሌሎች ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጉ የነበረ ይመስላል።

9, 10. (ሀ) የኢየሱስ ጠላቶች ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ኢየሱስን ሊያጠምዱት የሞከሩት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሰጠው ምላሽ ምን ትምህርት እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

9 የኢየሱስ ጠላቶች፣ ከግብር ጋር በተያያዘ አንዱን ጎራ ደግፎ እንዲናገር የሚያደርግ ጥያቄ በማቅረብ ኢየሱስን ሊያጠምዱት ሞክረው ነበር። ጥያቄው የተነሳው በሮም ተገዢዎች ላይ የሚጣለውን የአንድ ዲናር ግብር በተመለከተ ነው። (ማቴዎስ 22:16-18ን አንብብ።) ይህ ግብር በሮም አገዛዝ ሥር መሆናቸውን ስለሚያስታውሳቸው አይሁዳውያን በጣም ይጠሉት ነበር። ‘የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች’ ይህን ጥያቄ ያነሱት፣ ኢየሱስ ግብር መክፈል ተገቢ እንዳልሆነ ቢናገር በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ወንጀል ሊከሱት እንደሚችሉ አስበው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ግብር መክፈል ተገቢ እንደሆነ ቢናገር የተከታዮቹን ድጋፍ ሊያጣ ይችላል።

10 ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የትኛውንም ወገን ላለመደገፍ ጥንቃቄ አድርጓል። “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 22:21) ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ አጭበርባሪዎች እንደሆኑ ያውቅ ነበር፤ ያም ቢሆን በዚህ ላይ ትኩረት አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ትኩረቱ ያረፈው ለሰው ልጆች ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ሊያመጣ በሚችለው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። በዚህ ረገድ ለሁሉም ተከታዮቹ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። የኢየሱስ ተከታዮች፣ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ አንድ ጉዳይ ምንም ያህል ተገቢ ወይም ትክክል ቢመስልም የትኛውንም ወገን አይደግፉም። ክርስቲያኖች ትኩረት የሚያደርጉት በአምላክ መንግሥትና ጽድቅ ላይ ነው። በመሆኑም የትኛውንም ወገን በተመለከተ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚል አቋም አይዙም፤ እንዲሁም ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ የተቃውሞ ሐሳብ አይሰነዝሩም።—ማቴ. 6:33

11. ፍትሕ እንዲሰፍን ያለንን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለን ከሁሉ የተሻለው መንገድ የትኛው ነው?

11 ብዙዎች የይሖዋ ምሥክር ከመሆናቸው በፊት አጥብቀው የሚያምኑበት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነበራቸው፤ አሁን ግን ይህን አመለካከታቸውን ማስተካከል ችለዋል። በታላቋ ብሪታንያ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማኅበረሰብ ጥናት ትምህርት ከተከታተልኩ በኋላ፣ መሠረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት የሚል አመለካከት አዳበርኩ። ጥቁሮች ብዙ ግፍ ስለደረሰብን ስለ ጥቁሮች መብት ለመከራከር ቆርጬ ተነሳሁ። ከዚህ ጋር የተያያዙ ክርክሮችን የማሸነፍ ችሎታ ቢኖረኝም የሚሰማኝ ብስጭት ሊወገድ አልቻለም። በዘር ምክንያት ለሚፈጸም ኢፍትሐዊ ድርጊት መንስኤ የሚሆነው ነገር ከሰዎች ልብ ውስጥ መወገድ እንዳለበት በወቅቱ አልተገነዘብኩም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ግን በቅድሚያ የራሴን ልብ መለወጥ እንዳለብኝ ተማርኩ። እንዲህ ያለውን ማስተካከያ እንዳደርግ በትዕግሥት የረዳችኝ ደግሞ ነጭ የቆዳ ቀለም ያላት እህት ነበረች። በአሁኑ ወቅት በምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ በዘወትር አቅኚነት የማገለግል ሲሆን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመስበክ ጥረት አደርጋለሁ።”

“ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ”

12. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከምን ዓይነት “እርሾ” እንዲጠበቁ አሳስቧቸዋል?

12 በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሃይማኖታዊ ቡድኖች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው የተለመደ ነበር። በክርስቶስ ዘመን በፓለስቲና ምድር የነበረው ሕይወት (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “አይሁዳውያን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተከፋፍለው የነበረ ሲሆን እነዚህ ቡድኖች በዛሬው ጊዜ እንዳሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ማለት ይቻላል” በማለት ይናገራል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “‘ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ’” ሲል በግልጽ አሳስቧቸዋል። (ማር. 8:15) ኢየሱስ፣ “ሄሮድስ” ሲል የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ማመልከቱ ሳይሆን አይቀርም። በሌላ በኩል ደግሞ ፈሪሳውያን፣ አይሁዳውያንን ከሮም አገዛዝ ነፃ ለማውጣት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ይደግፉ ነበር። የማቴዎስ ዘገባ እንደሚያሳየው ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሐሳብ በተናገረበት ወቅት ሰዱቃውያንንም ጠቅሷል። ሰዱቃውያን የፖለቲካው ሥርዓት ባለበት እንዲቀጥል ይፈልጉ ነበር። በርካታ ሰዱቃውያን በሮማውያን አስተዳደር ውስጥ ፖለቲካዊ ሥልጣን ነበራቸው። ከዚህ አንጻር ኢየሱስ፣ እነዚህ ሦስት ቡድኖች ከሚያስፋፉት ትምህርት ወይም እርሾ እንዲጠበቁ ደቀ መዛሙርቱን አበክሮ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 16:6, 12) ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ ሕዝቡ ሊያነግሡት ከሞከሩ ብዙም ሳይቆይ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

13, 14. (ሀ) ሃይማኖታዊ ቡድኖች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው ኢፍትሐዊ ድርጊት እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ኢፍትሐዊ ድርጊት መፈጸሙ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ሰበብ የማይሆነው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

13 ሃይማኖታዊ ቡድኖች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው በቀላሉ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው አስተምሯል። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስን ለመግደል እንዲነሱ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ነው። እነዚህ ሰዎች፣ ሕዝቡ የኢየሱስን ትምህርት በመስማት እነሱን መከተሉን እንዳያቆም ብሎም በፖለቲካና በሃይማኖት ረገድ ያላቸውን ተሰሚነት እንዳያጡ ሰግተው ነበር። “እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ቦታችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል” በማለት ተናግረዋል። (ዮሐ. 11:48) በመሆኑም ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ፣ ኢየሱስ እንዲገደል ሴራ ጠነሰሰ።—ዮሐ. 11:49-53፤ 18:14

14 ቀያፋ፣ ኢየሱስን እንዲያስሩት ወታደሮች የላከው ጨለማን ተገን አድርጎ ነበር። ኢየሱስ ይህ እንደሚሆን ስላወቀ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ሰይፍ እንዲይዙ ነገራቸው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሊያስተምራቸው ያሰበውን ጠቃሚ ትምህርት ለማስተላለፍ ሁለት ሰይፎች በቂ ነበሩ። (ሉቃስ 22:36-38) በዚያው ምሽት ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን ሊያስሩ ከመጡት ሰዎች የአንዱን ጆሮ በሰይፍ ቆረጠው። ጴጥሮስ ይህን ያደረገው፣ ሰዎቹ ኢየሱስን በሌሊት በማሰር እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊ ድርጊት መፈጸማቸው አበሳጭቶት ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 18:10) ይሁንና ኢየሱስ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” አለው። (ማቴ. 26:52, 53) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ጠቃሚ ትምህርት፣ ተከታዮቹ የዓለም ክፍል መሆን እንደሌለባቸው በመግለጽ በዚያው ምሽት አቅርቦት ከነበረው ጸሎት ጋር የሚስማማ ነው። (ዮሐንስ 17:16ን አንብብ።) ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ እርምጃ የመውሰድ መብት ያለው አምላክ ብቻ ነው።

15, 16. (ሀ) ክርስቲያኖች በግጭቶች ውስጥ እንዳይገቡ የአምላክ ቃል የረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለምና በሕዝቡ መካከል ምን ዓይነት ልዩነት ይመለከታል?

15 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው በደቡባዊ አውሮፓ የምትኖር እህት ይህን እውነታ ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “የዓመፅ ድርጊት፣ ፍትሕ ለማስፈን እንደማይረዳ ተመልክቻለሁ። የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ሌሎች ብዙዎች ደግሞ በምሬት ይዋጣሉ። በምድር ላይ እውነተኛ ፍትሕ ሊያሰፍን የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመማሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። ላለፉት 25 ዓመታት ይህን እውነት ስሰብክ ቆይቻለሁ።” በደቡባዊ አፍሪካ የሚኖረው ወንድምም በጦሩ ፋንታ “የመንፈስን ሰይፍ” ይኸውም የአምላክን ቃል ታጥቋል፤ በአሁኑ ጊዜ ይህ ወንድም ለየትኛውም ጎሳ አባላት የሰላምን መልእክት ያውጃል። (ኤፌ. 6:17) በመካከለኛው አውሮፓ የምትኖረው እህት ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ፣ ቀደም ሲል ትጠላው የነበረ ዘር ያለውን ወንድም አግብታለች። ሦስቱም ሰዎች እንዲህ ያለ ለውጥ ያደረጉት ክርስቶስን ለመምሰል ስለፈለጉ ነው።

16 በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ለውጥ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ዘር፣ ጸጥ ማለት ከማይችል የሚናወጥ ባሕር ጋር ያመሳስለዋል። (ኢሳ. 17:12፤ 57:20, 21፤ ራእይ 13:1) ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሰዎች እርምጃ ለመውሰድ እንዲነሳሱ፣ እንዲከፋፈሉ እንዲሁም ዓመፅ እንዲቀሰቅሱ ቢያደርጓቸውም እኛ ግን ሰላማዊ ለመሆንና አንድነታችንን ለመጠበቅ ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋ እንዲህ ባለው የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በሕዝቡ መካከል ያለውን አንድነት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!—ሶፎንያስ 3:17ን አንብብ።

17. (ሀ) አንድነታችንን ለማጠናከር የሚረዱን ሦስት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለማጠናከር የሚረዱንን ሦስት ነገሮች ተመልክተናል፦ (1) ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን የሚያስተካክለው በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ እንተማመናለን፤ (2) በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የትኛውንም ጎራ አንደግፍም፤ እንዲሁም (3) በዓመፅ ድርጊቶች አንካፈልም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ጭፍን ጥላቻ አንድነታችንን ሊያናጋው ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።