በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰላምታ ያለው ኃይል

ሰላምታ ያለው ኃይል

“ሰላም! እንደምን ነህ?”

ከሰዎች ጋር ስንገናኝ በዚህ መንገድ ሰላምታ መስጠታችን የተለመደ ነው። እንዲያውም ከሰዎቹ ጋር እንጨባበጥ አልፎ ተርፎም ተቃቅፈን እንሳሳም ይሆናል። ሰዎች ሰላምታ የሚለዋወጡበት መንገድ እንደየባሕሉ ቢለያይም ሰላምታ የመስጠትን አስፈላጊነት ግን ሁሉም ሰው ይስማማበታል። እንዲያውም ሰዎችን ሰላም አለማለት ወይም ሌሎች ሰላም ሲሉን ምላሽ አለመስጠት አክብሮት ማጣት አሊያም ነውር እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

ይሁንና ሌሎችን ሰላም ማለት ቀላል የሚሆንላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ዓይናፋር ስለሆኑ ወይም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስለሚመለከቱ ሌሎችን ሰላም ማለት ያስፈራቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከእነሱ የተለየ ዘር፣ ባሕል ወይም ሁኔታ ያላቸውን ሰዎች ሰላም ማለት ይቸግራቸዋል። ይሁን እንጂ አጠር ያለ ሰላምታ እንኳ ትልቅ ጥቅም ያስገኛል።

ለመሆኑ ‘ሰላምታ መስጠት ምን ጥቅም አለው? ሰላምታ መስጠትን በተመለከተ ከአምላክ ቃል ምን ትምህርት አገኛለሁ?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ አስፈላጊ ነው።

“ሁሉንም ዓይነት ሰው” ሰላም በሉ

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና ለመምጣት የመጀመሪያው ሰው የሆነውን ቆርኔሌዎስን ‘አምላክ አያዳላም’ ብሎታል። (ሥራ 10:34) ከጊዜ በኋላም ጴጥሮስ፣ አምላክ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ” እንደሚፈልግ ጽፏል። (2 ጴጥ. 3:9) እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ ወደ አእምሯችን የሚመጡት እውነትን እያጠኑ ያሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” በማለትም አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥ. 2:17) እንግዲያው ዘራቸው፣ ባሕላቸው ወይም ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ሰላም ማለታችን ተገቢ አይደለም? እንዲህ ማድረጋችን ለእነሱ አክብሮትና ፍቅር እንዳለን ያሳያል።

ሐዋርያው ጳውሎስ የጉባኤውን አባላት “ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን ሁሉ . . . እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ሮም 15:7) ጳውሎስ “የብርታት ምንጭ” የሆኑለትን ወንድሞች ለይቶ በመጥቀስ ስለ እነሱ ተናግሯል። ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ኃይለኛ ጥቃት በሚሰነዝርበት በዛሬው ጊዜ ያሉ ወንድሞችና እህቶችማ የበለጠ ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም።—ቆላ. 4:11፤ ራእይ 12:12, 17

በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ሰላምታ መስጠት፣ ሰዎች ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸው እንዲሰማቸው ከማድረግ ያለፈ ጥቅም አለው።

ማጽናኛ፣ ማበረታቻና ፍቅር

የአምላክ ልጅ ወደ ምድር መጥቶ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ ጉዳዩን ለማርያም እንዲነግራት ይሖዋ ገብርኤልን ላከው። መልአኩ ለማርያም መልእክቱን ከመናገሩ በፊት “እጅግ የተባረክሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” አላት። ማርያም አንድ መልአክ ያነጋገራት ለምን እንደሆነ ስላልገባት ‘በጣም ደነገጠች።’ መልአኩም መደንገጧን ሲያይ “ማርያም ሆይ፣ በአምላክ ፊት ሞገስ ስላገኘሽ አትፍሪ” በማለት አረጋጋት። ገብርኤል ቀጥሎም መሲሑን እንድትወልድ አምላክ እንደመረጣት ለማርያም ነገራት። ማርያምም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት የተሰጣትን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸች።—ሉቃስ 1:26-38

መልአኩ የይሖዋ መልእክተኛ ሆኖ ማገልገልን እንደ ልዩ መብት እንደተመለከተው ግልጽ ነው፤ ፍጹም ያልሆነችን አንዲት ሴት ማናገር ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ ተልእኮ እንደሆነ አልተሰማውም። መልእክቱን ከመናገሩ በፊት ለማርያም ሰላምታ ሰጥቷታል። ከዚህ ምሳሌ ምን መማር እንችላለን? ሌሎችን ሰላም ማለትና ማበረታታት እንዳለብን እንማራለን። ጥቂት ቃላት በመናገር ብቻ ሌሎችን ማበረታታትና በይሖዋ ሕዝቦች መካከል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ እንችላለን።

ጳውሎስ በትንሿ እስያና በአውሮፓ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን ያውቅ ነበር። የጻፋቸው ደብዳቤዎች በስም ለጠቀሳቸው በርካታ ሰዎች የላካቸውን ሰላምታዎች ይዘዋል። ሮም ምዕራፍ 16 ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። በዚህ ምዕራፍ ላይ ጳውሎስ ጥቂት ለማይባሉ የእምነት አጋሮቹ ሰላምታ ልኳል። ለምሳሌ፣ ፌበን የተባለችውን እህት በስም ጠቅሶ ስለ እሷ ተናግሯል፤ ወንድሞቹንም “በጌታ የእምነት ባልደረባችሁ እንደመሆኗ መጠን ለቅዱሳን በሚገባ ሁኔታ ተቀበሏት፤ የምትፈልገውንም እርዳታ ሁሉ አድርጉላት” በማለት አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ “እኔ ብቻ ሳልሆን በአሕዛብ መካከል የሚገኙ ጉባኤዎችም ሁሉ ያመሰግኗቸዋል” በማለት ለተናገረላቸው ለጵርስቅላና ለአቂላም ሰላምታ አቅርቧል። ሐዋርያው፣ “የምወደውን ኤጲኔጦስን” እንዲሁም “በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩትን ጥራይፊናና ጥራይፎሳ የተባሉትን ሴቶች ሰላም በሉልኝ” በማለት ጽፏል፤ ስለ እነዚህ ክርስቲያኖች እምብዛም የማይታወቅ ቢሆንም ጳውሎስ ትኩረት ሰጥቶ ሰላምታ ልኮላቸዋል። በእርግጥም ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ሰላምታ መስጠት ያስደስተው ነበር።—ሮም 16:1-16

ሰላምታ የተላከላቸው ወንድሞችና እህቶች ጳውሎስ ስለ እነሱ ጥሩ ትዝታ እንዳለው ማወቃቸው ምን ያህል አስደስቷቸው እንደሚሆን አስበው። ለጳውሎስ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ተጠናክሮ መሆን አለበት! ሌሎች ክርስቲያኖችም ጳውሎስ የላከውን፣ ፍቅር የተንጸባረቀበት ሰላምታ መስማታቸው እንዳበረታታቸውና በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ እንደረዳቸው ጥያቄ የለውም። አዎን፣ ልባዊ አሳቢነትንና አድናቆትን የሚገልጹ ሰላምታዎች ወዳጅነትን ያጠናክራሉ እንዲሁም የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችን አንድነት ያጎለብታሉ።

ጳውሎስ ፑቲዮሉስ ወደብ ላይ ደርሶ ወደ ሮም ለማቅናት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት የአካባቢው ክርስቲያኖች እሱን ለማግኘት መጥተው ነበር። ጳውሎስ ወንድሞቹን ከርቀት ሲያይ “አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ።” (ሥራ 28:13-15) አንዳንድ ጊዜ፣ ሰላምታ መስጠት የምንችለው ፈገግ በማለት አሊያም ከርቀት እጃችንን በማውለብለብ ብቻ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋችን የተጨነቀን ወይም ያዘነን ሰው ሊያበረታታው ይችላል።

ጥሩ መሠረት

ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ለእምነት ባልንጀሮቹ ጠንከር ያለ ምክር መስጠት አስፈልጎት ነበር። በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከዓለም ጋር ወዳጅነት በመመሥረት በመንፈሳዊ አመንዝሮች ሆነው ነበር። (ያዕ. 4:4) ይሁንና ያዕቆብ በደብዳቤው መግቢያ ላይ ምን እንዳለ ልብ እንበል፦

“የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ፣ በየቦታው ለተበተኑት ለ12ቱ ነገዶች፦ ሰላምታ ይድረሳችሁ!” (ያዕ. 1:1) ያዕቆብ ደብዳቤውን የጀመረበት መንገድ አምላክ፣ እሱንም ሆነ መልእክቱን የሚያነቡትን ክርስቲያኖች እኩል አድርጎ እንደሚያያቸው የእምነት ባልንጀሮቹን አስታውሷቸው መሆን አለበት፤ ይህም ምክሩን መቀበል ቀላል እንዲሆንላቸው ሳያደርግ አልቀረም። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ትሕትና የሚንጸባረቅበት ሰላምታ፣ ከበድ ያሉ ጉዳዮችን አንስቶ መወያየት እንኳ ቀላል እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል።

ለሌሎች የምንሰጠው ሰላምታ አጭር ቢሆንም እንኳ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኝ፣ ከልብ የመነጨና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይገባዋል። ሰላም የምንላቸው ሰዎች ልብ እንዳሉን ባይሰማንም እንኳ በዚህ መንገድ ሰላምታ መስጠታችን አስፈላጊ ነው። (ማቴ. 22:39) በአየርላንድ የምትኖር አንዲት እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እህታችን ወደ ስብሰባ አዳራሽ የደረሰችው ልክ ሊጀመር ሲል ነበር። እየተጣደፈች ስትገባ አንድ ወንድም አያትና ፈገግ ብሎ “ሰላም፣ ስላየሁሽ ደስ ብሎኛል” አላት። እህትም ምንም ሳትለው ሄዳ ተቀመጠች።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይህች እህት ወደዚያ ወንድም ቀርባ፣ ከቤተሰቧ ጋር በተያያዘ አስጨናቂ ሁኔታ አጋጥሟት እንደነበረ ነገረችው። አክላም እንዲህ አለችው፦ “ያን ዕለት በጣም ተረብሼ ነበር፤ ወደ ስብሰባ የመጣሁትም ታግዬ ነው። ከአንተ ሰላምታ በቀር በስብሰባው ላይ ምን ትምህርት እንደተሰጠ ትዝ የሚለኝ ነገር የለም። ሰላምታህ በጣም አበረታቶኛል። አመሰግንሃለሁ።”

ይህ ወንድም ለእህት የሰጣት አጭር ሰላምታ የዚህን ያህል ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ አላወቀም ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እነዚያ ጥቂት ቃላት ለእሷ ምን ያህል ትልቅ ትርጉም እንደነበራቸው ስትነግረኝ እሷን ሰላም በማለቴ በጣም ደስ አለኝ። እህት ምን እንደተሰማት ሳውቅ እኔም ተደሰትኩ።”

ሰለሞን “ቂጣህን በውኃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀናት በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና” በማለት ጽፏል። (መክ. 11:1) ሁሉንም ሰው በተለይም የእምነት አጋሮቻችንን ሰላም ማለታችን ለእኛም ሆነ ለእነሱ ደስታ ያስገኛል። እንግዲያው ሰላምታ ኃይል እንዳለው ምንጊዜም እናስታውስ።