በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም ሕሊናችሁን አሠልጥኑ

የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም ሕሊናችሁን አሠልጥኑ

“በማሳሰቢያዎችህ ላይ [አሰላስላለሁ]።”—መዝ. 119:99

መዝሙሮች፦ 127, 88

1. የሰው ልጆችን ከእንስሳት የሚለያቸው አንዱ ነገር ምንድን ነው?

የሰው ልጆችን ከእንስሳት የሚለያቸው አንዱ ነገር ሕሊና ያላቸው መሆኑ ነው። የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የሆኑት አዳምና ሔዋን ሕሊና ነበራቸው። የይሖዋን ትእዛዝ ከጣሱ በኋላ መደበቃቸው ይህን ያሳያል። እነዚህ ባልና ሚስት የተደበቁት ሕሊናቸው ስለወቀሳቸው ነው።

2. ሕሊናችን ከኮምፓስ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

2 ሕሊናቸው በሚገባ ያልሠለጠነ ሰዎች፣ የማይሠራ ኮምፓስ ካለው መርከብ ጋር ይመሳሰላሉ። * ኮምፓሱ በትክክል በማይሠራ መርከብ መጓዝ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ነፋስና ሞገድ፣ መርከቡ በቀላሉ አቅጣጫውን እንዲስት ሊያደርጉት ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን በትክክል የሚሠራ ኮምፓስ፣ የመርከቡ ነጂ መስመሩን ጠብቆ እንዲጓዝ ሊረዳው ይችላል። ሕሊናችን ከኮምፓስ ጋር ይመሳሰላል። ሕሊና፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳንና በትክክለኛው አቅጣጫ የሚመራን ችሎታ ነው። እርግጥ ነው፣ ሕሊናችን በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመራን መሠልጠን አለበት።

3. ሕሊናችን በሚገባ ካልሠለጠነ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

3 ሕሊናችን በሚገባ ካልሠለጠነ መጥፎ ነገር እንዳንፈጽም ማስጠንቀቂያ አይሰጠንም። (1 ጢሞ. 4:1, 2) እንዲያውም እንዲህ ያለው ሕሊና ‘መጥፎውን ጥሩ’ አድርገን እንድናስብ ሊገፋፋን ይችላል። (ኢሳ. 5:20) ኢየሱስ ተከታዮቹን “እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 16:2) ደቀ መዝሙሩን እስጢፋኖስን የገደሉት ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው፤ የይሖዋን አገልጋዮች ከሚያሳድዱ ሌሎች ሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ሥራ 6:8, 12፤ 7:54-60) ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ሃይማኖተኛ ሰዎች እንደ ነፍስ ማጥፋት ያሉ አሰቃቂ የክፋት ድርጊቶችን በመፈጸም፣ እናመልካለን የሚሉት አምላክ ያወጣቸውን ሕጎች መጣሳቸው ምንኛ የሚያስገርም ነው! (ዘፀ. 20:13) የእነዚህ ሰዎች ሕሊና እያታለላቸው እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም!

4. ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ምን ሊረዳን ይችላል?

4 ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ምን ሊረዳን ይችላል? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ።” (2 ጢሞ. 3:16) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት፣ ባጠናነው ነገር ላይ ማሰላሰልና የተማርነውን በሕይወታችን ውስጥ በተግባር ማዋል ይኖርብናል፤ ይህም የአምላክን ዓይነት አስተሳሰብ ይበልጥ እንድናዳብር ይረዳናል። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ በማዳበር ሕሊናችንን ካሠለጠንነው አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል። የይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕሊናችንን ለማሠልጠን የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በአምላክ ሕጎች ሕሊናችሁን አሠልጥኑ

5, 6. የአምላክን ሕጎች መታዘዛችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

5 የአምላክ ሕጎች ሕሊናችንን እንዲያሠለጥኑት፣ እነዚህን ሕጎች ከማንበብ ወይም ከማወቅ ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል። ለሕጎቹ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር ይኖርብናል። የአምላክ ቃል “ክፉ የሆነውን ጥሉ፤ መልካም የሆነውንም ውደዱ” ይላል። (አሞጽ 5:15) ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቁልፉ፣ ይሖዋ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ እንቅልፍ አልወስድ ብሎህ ተቸግረሃል እንበል። ሐኪምህ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ እንዲኖርህ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንድታደርግና በሕይወትህ ውስጥ ሌሎች አስፈላጊ ለውጦችን እንድታደርግ የሚረዳህ ጠቃሚ ምክር ሰጠህ። ምክሩን በተግባር ስታውል ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ቻልክ! ሐኪሙ ላደረገልህ እርዳታ በጣም አመስጋኝ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም።

6 በተመሳሳይም ፈጣሪያችን የሰጠን ሕጎች ኃጢአት መሥራት ከሚያስከትለው መዘዝ ይጠብቁናል፤ እንዲሁም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ይረዱናል። ለምሳሌ ከውሸት፣ ከማጭበርበር፣ ከስርቆት፣ ከፆታ ብልግና፣ ከዓመፅ እንዲሁም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ የሚመክሩንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች መታዘዛችን ምን ያህል እንደሚጠቅመን እናስብ። (ምሳሌ 6:16-19ን አንብብ፤ ራእይ 21:8) የይሖዋን መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘውን ታላቅ ጥቅም በሕይወታችን ውስጥ ስንመለከት ለይሖዋም ሆነ ለሕጎቹ ያለን ፍቅርና አድናቆት እየጨመረ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም።

7. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ እውነተኛ ታሪኮችን ማንበባችንና ባነበብነው ላይ ማሰላሰላችን ምን ጥቅም አለው?

7 ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን አካሄድ ለማወቅ፣ የአምላክን ሕጎች መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳችን ሕይወት ማየት አያስፈልገንም። በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ከሠሩት ስህተት መማር እንችላለን። ምሳሌ 1:5 “ጥበበኛ ሰው ያዳምጣል፤ ደግሞም ተጨማሪ ትምህርት ይቀስማል” ይላል። ከሁሉ የተሻለ ትምህርት መቅሰም የምንችለው ከአምላክ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን እውነተኛ ታሪኮች ስናነብና ስናሰላስልባቸው ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ዳዊት የይሖዋን ትእዛዝ በመጣስ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር መፈጸሙ ከፍተኛ ሥቃይ አስከትሎበታል። (2 ሳሙ. 12:7-14) ይህን ዘገባ ስናነብ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል እንችላለን፦ ‘ዳዊት እንዲህ ዓይነት መዘዝ ውስጥ ላለመግባት ምን ማድረግ ይችል ነበር? እኔስ እንደ ዳዊት ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመኝ ምን አደርጋለሁ? እንደ ዳዊት ኃጢአት እፈጽማለሁ ወይስ እንደ ዮሴፍ እሸሻለሁ?’ (ዘፍ. 39:11-15) ኃጢአት በሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች ላይ ማሰላሰላችን ‘ክፉ የሆነውን ለመጥላት’ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።

8, 9. (ሀ) ሕሊናችን ምን ለማድረግ ሊረዳን ይችላል? (ለ) የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕሊናችንን ለማሠልጠን የሚረዱን እንዴት ነው?

8 አምላክ የሚጠላቸውን ድርጊቶች ላለመፈጸም እንደምንጠነቀቅ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀጥተኛ ትእዛዝ የማይሰጡባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች በሕይወታችን ውስጥ ያጋጥሙናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን አምላክን የሚያስደስተውንና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አካሄድ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችን በዚህ ረገድ ይረዳናል።

9 ይሖዋ ስለሚወደን ሕሊናችንን ለመቅረጽ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ” ብሏል። (ኢሳ. 48:17, 18) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በጥሞና የምናሰላስልና ወደ ልባችን ጠልቀው እንዲገቡ የምናደርግ ከሆነ ሕሊናችንን ማሠልጠን፣ ማስተካከልና መቅረጽ እንችላለን። ይህ ደግሞ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ ያስችለናል።

በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመሩ

10. መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? ኢየሱስ በመሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ያስተማረው እንዴት ነው?

10 መሠረታዊ ሥርዓት የሚለው አገላለጽ ለአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ወይም ድርጊት መሠረት የሚሆነውን እውነታ አሊያም አስተምህሮት ያመለክታል። የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶች መረዳታችን የእሱን አስተሳሰብ እንዲሁም አንዳንድ ሕጎችን ያወጣበትን ምክንያት ለመገንዘብ ያስችለናል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ዝንባሌዎች ወይም ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ውጤት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ሲል የተለያዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተምሯቸዋል። ለምሳሌ ቂም መያዝ የዓመፅ ድርጊት ወደመፈጸም፣ የፍትወት ስሜት ደግሞ ምንዝር ወደመፈጸም ሊመራ እንደሚችል አስተምሯል። (ማቴ. 5:21, 22, 27, 28) ሕሊናችንን በሚገባ ለማሠልጠን በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ይኖርብናል፤ ይህም ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ ውሳኔዎች ለማድረግ ያስችለናል።—1 ቆሮ. 10:31

ጎልማሳ ክርስቲያን የሌሎችን ሕሊና ያከብራል (አንቀጽ 11, 12⁠ን ተመልከት)

11. በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ያላቸው ሁለት ክርስቲያኖች የተለያየ ውሳኔ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው?

11 በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ያላቸው ሁለት ክርስቲያኖች ስለ አንድ ጉዳይ ያላቸው አመለካከት በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። የአልኮል መጠጥን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ በተገቢው መጠን አልኮል መጠጣትን አይከለክልም። ሆኖም ከመጠን በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (ምሳሌ 20:1፤ 1 ጢሞ. 3:8) ታዲያ አንድ ክርስቲያን የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሊያሳስበው የሚገባው ጉዳይ ከመጠኑ አለማለፉ ብቻ ነው? በፍጹም። አንድ ክርስቲያን ሕሊናው አልኮል እንዲጠጣ ቢፈቅድለትም እንኳ የሌሎችን ሕሊና ከግምት ማስገባት ይኖርበታል።

12. በሮም 14:21 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሌሎችን ሕሊና እንድናከብር የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች የሌሎችን ሕሊና ማክበራቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲገልጽ “ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 14:21) ከአንተ የተለየ ሕሊና ያለውን ወንድም ላለማሰናከል ስትል መብትህ የሆኑ ነገሮችን ለመተው ፈቃደኛ ነህ? እንደምትሆን የታወቀ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችን ወደ እውነት ከመምጣታቸው በፊት አልኮል ከመጠን በላይ ይጠጡ ነበር፤ አሁን ግን ፈጽሞ አልኮል ላለመጠጣት ወስነዋል። ማናችንም ብንሆን ወንድማችን ቀደም ሲል የነበረው ጎጂ ልማድ እንዲያገረሽበት አስተዋጽኦ ማድረግ አንፈልግም። (1 ቆሮ. 6:9, 10) እንግዲያው አንድ ወንድም መጠጥ እንዲጠጣ ያቀረብንለትን ግብዣ ባይቀበል ልንጫነው አይገባም።

13. ጢሞቴዎስ ሌሎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ለመርዳት ሲል ምን አድርጓል?

13 ጢሞቴዎስ፣ ምሥራቹን የሚሰብክላቸውን አይሁዳውያን ላለማሰናከል ሲል በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ ተገርዟል፤ ይህን ማድረጉ ሥቃይ እንዳስከተለበት ጥያቄ የለውም። ጢሞቴዎስ እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰዱ የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አመለካከት እንደነበረው የሚያሳይ ነው። (ሥራ 16:3፤ 1 ቆሮ. 9:19-23) አንተስ ሌሎችን ለመጥቀም ስትል እንደ ጢሞቴዎስ የግል ምርጫህን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ?

“ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር”

14, 15. (ሀ) ጉልምስና ላይ መድረስ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ለሌሎች ፍቅር ማሳየታችን ጎልማሳ ክርስቲያኖች መሆናችንን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

14 ሁላችንም “ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን” መሄድና “ወደ ጉልምስና ለመድረስ [መጣጣር]” ይኖርብናል። (ዕብ. 6:1) ጉልምስና ያለምንም ጥረት የሚደረስበት ነገር አይደለም፤ ጳውሎስ እንዳለው ‘መጣጣር’ ማለትም ተግተን መሥራት ያስፈልገናል። እድገት አድርገን ጉልምስና ላይ ለመድረስ፣ እውቀታችንና የማስተዋል ችሎታችን እየጨመረ መሄድ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብ የምንበረታታው ለዚህ ነው። (መዝ. 1:1-3) ይህን የማድረግ ግብ አውጥተሃል? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብህ፣ የይሖዋን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ማስተዋል እንድትችልና የአምላክን ቃል በጥልቀት እንድታውቅ ይረዳሃል።

15 ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው ከሁሉ የሚበልጠው ሕግ የፍቅር ሕግ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 13:35) የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ፍቅርን “ንጉሣዊ ሕግ” ሲል ጠርቶታል። (ያዕ. 2:8) ጳውሎስ ደግሞ “ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው” ብሏል። (ሮም 13:10) ፍቅር የዚህን ያህል ጎላ ተደርጎ መገለጹ አያስገርምም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐ. 4:8) የአምላክ ፍቅር ከስሜት ባለፈ በተግባር ተገልጿል። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።” (1 ዮሐ. 4:9) እኛም ለይሖዋና ለልጁ፣ ለክርስቲያን ወንድሞቻችን አልፎ ተርፎም ለመላው የሰው ዘር ፍቅር ማሳየታችን ጎልማሳ ክርስቲያኖች መሆናችንን ያረጋግጣል።—ማቴ. 22:37-39

በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ሕሊናችን ይበልጥ አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. በመንፈሳዊ እየጎለመስን ስንሄድ ለመሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ ትኩረት መስጠት የምንጀምረው ለምንድን ነው?

16 በመንፈሳዊ እየጎለመስን ስንሄድ፣ ለመሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንጀምራለን። ምክንያቱም ሕጎች የሚሠሩት ለተወሰኑ ሁኔታዎች ብቻ ነው፤ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግን ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ትንሽ ልጅ መጥፎ ጓደኝነት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ላይገነዘብ ይችላል፤ በመሆኑም አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጃቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲሉ ሕግ ያወጡለታል። (1 ቆሮ. 15:33) ልጁ እየበሰለ ሲሄድ ግን የማሰብ ችሎታው ስለሚዳብር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ማመዛዘን ይጀምራል። በመሆኑም ጥሩ ጓደኞች የመምረጥ ችሎታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይሄዳል። (1 ቆሮንቶስ 13:11⁠ን እና 14:20ን አንብብ።) በይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ጊዜ ወስደን የምናሰላስል ከሆነ የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ ስለምናዳብር ሕሊናችን ይበልጥ አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል።

17. ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን ነገሮች ተሟልተውልናል የምንለው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋን የሚያስደስቱ ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዱን ነገሮች በሙሉ ተሟልተውልናል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ [ሆነን እንድንገኝ]” ይረዱናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ስለዚህ “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ለማስተዋል የሚያስችሉንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ጥረት እናድርግ። (ኤፌ. 5:17) የይሖዋ ድርጅት ያዘጋጀልንን ለጥናት የሚረዱ መሣሪያዎች በሚገባ እንጠቀምባቸው፤ ከእነዚህም መካከል የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ)፣ የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች፣ ዎችታወር ላይብረሪ (እንግሊዝኛ)፣ የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም ጄ ደብልዩ ላይብረሪ (JW Library) የተባለው አፕሊኬሽን ይገኙበታል። እነዚህ መሣሪያዎች የተዘጋጁት ከግልና ከቤተሰብ ጥናታችን ሙሉ ጥቅም እንድናገኝ ለመርዳት ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና በረከት ያስገኛል

18. የይሖዋን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስንከተል ምን በረከት እናገኛለን?

18 የይሖዋን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል በረከት ያስገኛል፤ መዝሙር 119:97-100 ይህን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ትእዛዝህ ለዘላለም ስለማይለየኝ፣ ከጠላቶቼ ይበልጥ ጥበበኛ ያደርገኛል። በማሳሰቢያዎችህ ላይ ስለማሰላስል፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥልቅ ማስተዋል አለኝ። መመሪያዎችህን ስለማከብር፣ ከሽማግሌዎች ይበልጥ በማስተዋል እመላለሳለሁ።” በአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ጊዜ ወስደን ‘ካሰላሰልን’ ጥበብና ማስተዋል የሚንጸባረቅበት ውሳኔ የማድረግ ችሎታችን ይዳብራል። ሕሊናችንን በአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማሠልጠን ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርግ ከሆነ “እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ” መድረስ እንችላለን።—ኤፌ. 4:13

^ አን.2 ኮምፓስ፣ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚያመለክት ባለማግኔት ቀስት ያለው መሣሪያ ነው። በትክክል የሚሠራ ኮምፓስ ያለው ሰው አቅጣጫውን ሳይስት መጓዝ ይችላል።