የሕይወት ታሪክ
በጭንቀቶቼ ሁሉ ማጽናኛ አግኝቻለሁ
በኢንደስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ ሱከር የምትባል ጥንታዊት ከተማ ትገኛለች። ኅዳር 9, 1929 አሁን የፓኪስታን ግዛት በሆነችው በዚህች ከተማ ውስጥ ተወለድኩ። በዚያው ጊዜ አካባቢ አንድ እንግሊዛዊ ሚስዮናዊ ደማቅ ቀለም ያላቸው መጻሕፍት ለወላጆቼ ሰጥቷቸው ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት እነዚያ መጻሕፍት እውነትን እንዳውቅ ረድተውኛል።
እነዚያ መጻሕፍት ዘ ሬንቦ ሴት (ኅብረ ቀለማት) ተብለው ይጠሩ ነበር። በመጻሕፍቱ ላይ የሚገኙት ውብ ሥዕሎች በጣም ይማርኩኝ ነበር። በዚህም የተነሳ ገና ከትንሽነቴ ጀምሮ እነዚያ ግሩም መጻሕፍት የያዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የማወቅ ጉጉት አደረብኝ።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዳመና በሕንድ ላይ እያንዣበበ በነበረበት ወቅት የእኔም ሕይወት ምስቅልቅሉ ወጣ። ወላጆቼ ተለያይተው መኖር ጀመሩ፤ በኋላም ተፋቱ። ሁለቱንም ስለምወዳቸው የተለያዩበት ምክንያት ጨርሶ ሊገባኝ አልቻለም። ስሜቴ በጣም ተጎዳ፤ እንዲሁም ማንም እንደማይፈልገኝ ተሰማኝ። ወንድም ወይም እህት ስላልነበረኝ በወቅቱ በጣም የሚያስፈልገኝን ማጽናኛና ድጋፍ ማግኘት አልቻልኩም።
እኔና እናቴ የምንኖረው በከራቺ ነበር። አንድ ቀን ፍሬድ ሃርዴከር የሚባል አረጋዊ ሐኪም በራችንን አንኳኳ። እነዚያን አሥር መጻሕፍት ለወላጆቼ እንደሰጣቸው ሚስዮናዊ ሁሉ ይህ ሰውም የይሖዋ ምሥክር ነበር። ይህ ወንድም፣ እናቴን መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ጋበዛት። እናቴ ማጥናት ባትፈልግም እኔ ግብዣውን ልቀበል እንደምችል ነገረችው። በቀጣዩ ሳምንት ከወንድም ሃርዴከር ጋር ማጥናት ጀመርኩ።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በወንድም ሃርዴከር ክሊኒክ በሚደረግ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ። በስብሰባው ላይ 12 የሚሆኑ በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙ ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች ያጽናኑኝ ከመሆኑም ሌላ እንደ ልጃቸው ይንከባከቡኝ ነበር። ዓይን ለዓይን እየተያየን መነጋገር እንድንችል ሲሉ አብረውኝ ይቀመጡ እንዲሁም እንደ ልብ ወዳጅ ያዋሩኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ደግሞም በወቅቱ የሚያስፈልገኝ እንዲህ ዓይነት አሳቢነት ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ወንድም ሃርዴከር በመስክ አገልግሎት አብሬው እንድካፈል ጋበዘኝ። በእጅ የሚያዝ የሸክላ ማጫወቻ እንዴት መጠቀም እንደምችል ያስተማረኝ ሲሆን አጫጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በዚህ ማጫወቻ አማካኝነት ለሰዎች እናሰማ ነበር። አንዳንዶቹ ንግግሮች ኃይለኛ በመሆናቸው ሸክላዎቹ በያዙት መልእክት የማይደሰቱ የቤት ባለቤቶች ያጋጥሙን ነበር። ያም ቢሆን ለሌሎች መመሥከር በጣም ያስደስተኝ ነበር። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበረኝ ይህን እውነት ለሌሎች ማካፈል እወድ ነበር።
የጃፓን ሠራዊት ሕንድን ለመውረር በተቃረበበት ወቅት የብሪታንያ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያሳድሩት ጫና እየተባባሰ መጣ። ሐምሌ 1943 ደግሞ ይህ ጫና በእኔም ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አሳደረ። የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ቄስ የነበረው ርዕሰ መምህራችን ከትምህርት ቤት አባረረኝ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመግጠሜ ለሌሎቹ ተማሪዎች መጥፎ ምሳሌ እንደሆንኩ ለእናቴ ነገራት። እሷም በጣም ስለደነገጠች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዳልገናኝ ከለከለችኝ። ቆየት ብሎም በስተ ሰሜን 1,370 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በፐሻወር ከተማ ወደሚኖረው አባቴ ላከችኝ። በዚያም መንፈሳዊ ምግብ ማግኘትና ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መሰብሰብ ባለመቻሌ በመንፈሳዊ ተዳከምኩ።
መንፈሳዊ ጤንነቴ ተመለሰልኝ
በ1947 ሥራ ፍለጋ ወደ ከራቺ ተመለስኩ። እዚያ እያለሁ ወደ ዶክተር ሃርዴከር ክሊኒክ ሄድኩ። እሱም ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገልኝ።
ወንድም ሃርዴከር፣ ሕክምና ለማግኘት የመጣሁ ስለመሰለው “ምንህን ነው ያመመህ?” ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “ዶክተር፣ የታመምኩት በአካላዊ ሳይሆን በመንፈሳዊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እፈልጋለሁ” ብዬ መለስኩለት።
“ታዲያ መቼ መጀመር ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “ከተቻለ አሁኑኑ” አልኩት።
በዚያው ምሽት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመርኩ ሲሆን ያደረግነው ውይይት አስደሳች ነበር። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር እንደገና በመቀላቀሌ መረጋጋት ተሰማኝ። እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዳልገናኝ ለማገድ ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም ይሖዋን ለማገልገል ቆርጬ ስለነበር አልተሳካላትም። ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን ነሐሴ 31, 1947 በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ በወቅቱ 17 ዓመቴ ነበር።
በአቅኚነት አገልግሎት ያገኘሁት ደስታ
አቅኚ ከሆንኩ በኋላ መጀመሪያ የተመደብኩት የብሪታንያ ጦር ሠፈር በነበረችው በክዌታ ነው። በ1947 አገሪቱ ሕንድና ፓኪስታን ተብላ ለሁለት ተከፈለች። * ይህን ክስተት ተከትሎ በሕዝቡ መካከል ሃይማኖታዊ ክፍፍልና ዓመፅ ተቀሰቀሰ፤ በዚህም የተነሳ 14 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ይህ በታሪክ ከተመዘገቡ መጠነ ሰፊ የሕዝብ ፍልሰቶች አንዱ ነው። በሕንድ የነበሩ ሙስሊሞች ወደ ፓኪስታን ሲሄዱ በፓኪስታን የነበሩ ሂንዱዎችና ሲኮች ደግሞ ወደ ሕንድ ፈለሱ። በዚህ ትርምስ መሃል ከከራቺ ወደ ክዌታ ስሄድ፣ አብዛኛውን መንገድ የተጓዝኩት በሕዝብ በተጨናነቀ ባቡር ላይ ከውጭ በኩል ያለውን ብረት ሙጭጭ አድርጌ ይዤ ነበር።
ክዌታ ውስጥ በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ከሚገኝ ጆርጅ ሲንግ የሚባል ልዩ አቅኚ ጋር ተገናኘሁ። ጆርጅ በኮረብታማው ክልል ሳገለግል እየነዳሁ (ወይም እየገፋሁ) የምጠቀምበት አንድ አሮጌ ብስክሌት ሰጠኝ። አብዛኛውን ጊዜ የምሰብከው ብቻዬን ነበር። በስድስት ወራት ውስጥ 17 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ያገኘሁ ሲሆን ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ወደ እውነት መጥተዋል። ከጥናቶቼ አንዱ የሆነው ሳዲቅ ማሲ የሚባል የጦር መኮንን፣ እኔና ጆርጅ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ ወደሆነው ወደ ኡርዱ እንድንተረጉም ረድቶናል። ውሎ አድሮ ሳዲቅ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ሆኗል።
ከጊዜ በኋላ ወደ ከራቺ ተመለስኩና ከጊልያድ ትምህርት ቤት ተመርቀው በቅርቡ ከመጡ ሄንሪ ፊንች እና ሃሪ ፎረስት የሚባሉ ሚስዮናውያን ጋር ማገልገል ጀመርኩ። እነዚህ ወንድሞች በጣም ጠቃሚ ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና ሰጥተውኛል! በአንድ ወቅት ከወንድም ፊንች ጋር በሰሜናዊ ፓኪስታን ለማገልገል ሄደን ነበር። ግዙፍ በሆነው የተራራ ሰንሰለት ግርጌ የሚኖሩ ቅን የሆኑ ብዙ ሰዎች አገኘን፤ የኡርዱ ቋንቋ የሚናገሩት እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ነበሩ።
ከሁለት ዓመት በኋላ እኔ ራሴ በጊልያድ ትምህርት ቤት የመሠልጠን አጋጣሚ አገኘሁ፤ ወደ ፓኪስታን ከተመለስኩ በኋላ አልፎ አልፎ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግል ነበር። የምኖረው በላሆር በሚገኝ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ከሌሎች ሦስት ሚስዮናውያን ወንድሞች ጋር ነበር።የገጠመኝን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም
የሚያሳዝነው በ1954 በላሆር በነበሩት ሚስዮናውያን መካከል አለመግባባት ተፈጠረ፤ በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው የአንዳንዶቹን ሚስዮናውያን የአገልግሎት ምድብ ለመለወጥ ተገደደ። እኔም በውዝግቡ ውስጥ አንዱን ወገን በመደገፍ ጥበብ የጎደለው እርምጃ በመውሰዴ ጠንከር ያለ ምክር ተሰጠኝ። የተሰጠኝን ኃላፊነት በሚገባ እንዳልተወጣሁ ስለተሰማኝ በጣም አዘንኩ። በሌላ አካባቢ እንደ አዲስ አገልግሎቴን ለማከናወን ስላሰብኩ መጀመሪያ ወደ ከራቺ ከዚያም ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ ሄድኩ።
በለንደን በነበርኩበት ጉባኤ ውስጥ ብዙ የለንደን ቤቴል ቤተሰብ አባላት ነበሩ። የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች የሆነው ፕራይስ ሂዩዝ የተባለ ደግ ወንድም፣ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ሥልጠና ሰጠኝ። አንድ ቀን ወንድም ሂዩዝ፣ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በበላይነት የሚመራው ጆሴፍ ራዘርፎርድ በአንድ ወቅት ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቶት እንደነበር ነገረኝ። ወንድም ሂዩዝ ጥፋቱን ለማስተባበል በሞከረ ጊዜ ወንድም ራዘርፎርድ ኃይለኛ ተግሣጽ ሰጠው። ወንድም ሂዩዝ ይህን ገጠመኝ ሲያስታውስ ፊቱ ላይ ፈገግታ የሚነበብ መሆኑ አስገረመኝ። እርግጥ በወቅቱ ነገሩ አናዶት ነበር። ሆኖም የተሰጠው ጠንከር ያለ ምክር አስፈላጊ እንደነበርና ምክሩ የይሖዋ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ በኋላ ላይ መገንዘቡን ገለጸልኝ። (ዕብ. 12:6) ወንድም ሂዩዝ የሰጠኝ ሐሳብ በጣም ያስገረመኝ ሲሆን እንደገና ደስተኛ ሆኜ እንዳገለግል ረዳኝ።
በዚያው ጊዜ አካባቢ እናቴ ወደ ለንደን ተዛወረች፤ እዚያ እያለች፣ ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጆን ባር መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ያቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። እናቴ መንፈሳዊ እድገት አድርጋ በ1957 ተጠመቀች። ከጊዜ በኋላ እንደተገነዘብኩት አባቴም ከመሞቱ በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠና ነበር።
በ1958 በለንደን የምትኖረውንና የዴንማርክ ዜግነት ያላትን ሊኔ የተባለች እህት አገባሁ። በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያ ልጃችንን ጄንን ወለድን፤ ውሎ አድሮም አራት ተጨማሪ ልጆች ወልደናል። እኔም በፉላም ጉባኤ ውስጥ አንዳንድ የአገልግሎት መብቶችን አገኘሁ። ከጊዜ በኋላ ግን የሊኔ ጤንነት በመታወኩ ሞቃት የአየር ንብረት ወዳለው ቦታ መዛወር አስፈለገን። በመሆኑም በ1967 በአደሌድ፣ አውስትራሊያ መኖር ጀመርን።
ልብ የሚሰብር መከራ ደረሰብን
በአደሌድ ባለው ጉባኤያችን ውስጥ በዕድሜ የገፉ 12 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ ቅድሚያውን ወስደው በቅንዓት ይሳተፉ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እኛም በአዲሱ አካባቢ ጥሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመርን።
በ1979 አምስተኛ ልጃችን የሆነው ዳንኤል ሲወለድ እኔና ሊኔ በጣም ደስ ብሎን ነበር። ይሁንና ዳንኤል ዳውን ሲንድሮም * የተባለው ሕመም ስለነበረበት በሕይወት ብዙ መቆየት እንደማይችል ተነገረን። በወቅቱ የተሰማንን ከፍተኛ ጭንቀትና ሥቃይ አሁንም እንኳ መግለጽ ያዳግተኛል። ሌሎቹን አራት ልጆቻችንን ችላ ሳንል ዳንኤልን ለመንከባከብ የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። ዳንኤል በልቡ ላይ ባሉ ሁለት ቀዳዳዎች ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ኦክስጅን ስለሚያጥረው በአስቸኳይ ሆስፒታል መውሰድ ያስፈልገን ነበር። ዳንኤል ታማሚ ቢሆንም በጣም አስተዋይና አፍቃሪ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋን በጣም ይወድ ነበር። ምግብ ቀርቦ በቤተሰብ ስንጸልይ ትናንሽ እጆቹን አቆላልፎ በመጨበጥ ራሱን ዘንበል አድርጎ ከልብ በመነጨ ስሜት “አሜን” ይላል። ይህን ሳይል ምግቡን በፍጹም አይበላም ነበር።
ዳንኤል አራት ዓመት ሲሆነው የደም ካንሰር ያዘው። እኔና ሊኔ ኃይላችን ተሟጦና ስሜታችን ተደቁሶ ነበር። በከፍተኛ ጭንቀት ከመዋጤ የተነሳ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቼን ማከናወን የማልችልበት ደረጃ ላይ እየደረስኩ እንደሆነ ተሰማኝ። አንድ ምሽት፣ በጣም ተስፋ ቆርጠን ሳለ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን የሆነው ኔቪል ብሮሚች ወደ ቤታችን መጣ። ወንድም ብሮሚች እንባ እየተናነቀው እቅፍ አደረገን። ሁላችንም ተንሰቅስቀን አለቀስን። ፍቅርና ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ንግግሩ በእጅጉ አጽናናን። ወንድም ብሮሚች ወደ ቤቱ የሄደው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ዳንኤል ሞተ። በሕይወታችን ውስጥ ካጋጠሙን መከራዎች ሁሉ ይበልጥ የጎዳን እሱን ማጣታችን ነው። ሆኖም ዳንኤልን ከይሖዋ ፍቅር ምንም ነገር ሌላው ቀርቶ ሞትም እንኳ ሊለየው እንደማይችል እርግጠኞች መሆናችን ሐዘናችንን ለመቋቋም ረድቶናል። (ሮም 8:38, 39) ዳንኤል በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ሲያገኝ ከእሱ ጋር ለመገናኘት እጅግ እንናፍቃለን!—ዮሐ. 5:28, 29
ሌሎችን መርዳት ያስደስተኛል
በከባድ ሕመም ምክንያት ሕይወቴ አደጋ ላይ የወደቀባቸው ጊዜያት ቢኖሩም አሁንም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ። ያሳለፍኳቸው መከራዎች፣ ለሌሎች በተለይም ችግሮች ላሉባቸው ሰዎች ርኅራኄ እንዳሳይና የእነሱን ስሜት እንድረዳ አድርገውኛል። በእነሱ ላይ ላለመፍረድ ጥረት አደርጋለሁ። ከዚህ ይልቅ ራሴን እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፦ ‘በሕይወታቸው ውስጥ ያሳለፉት ነገር በአስተሳሰባቸውና በስሜታቸው ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? እንደማስብላቸው ላሳያቸው የምችለው እንዴት ነው? የይሖዋን ፈቃድ እንዲያደርጉ ላበረታታቸው የምችለውስ እንዴት ነው?’ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞች እረኝነት ማድረግ በጣም ያስደስተኛል! በእርግጥም ሌሎችን ሳጽናና እና መንፈሳቸው እንዲታደስ ሳደርግ እኔ ራሴ እጽናናለሁ እንዲሁም መንፈሴ ይታደሳል።
“በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ” በማለት እንደተናገረው መዝሙራዊ ይሰማኛል። (መዝ. 94:19) ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ሃይማኖታዊ ተቃውሞና ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ሲደርሱብኝ እንዲሁም በመንፈስ ጭንቀት ስዋጥ የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም። በእርግጥም ይሖዋ እውነተኛ አባት ሆኖልኛል!
^ አን.19 መጀመሪያ ላይ ፓኪስታን፣ ምዕራብ ፓኪስታንን (የአሁኗ ፓኪስታን) እና ምሥራቅ ፓኪስታንን (የአሁኗ ባንግላዴሽ) አጣምራ የያዘች አገር ነበረች።
^ አን.29 የሰኔ 2011 ንቁ! ላይ የሚገኘውን “ዳውን ሲንድሮም ያለበትን ልጅ ማሳደግ ያለው ፈተና እና የሚያስገኘው ወሮታ” የሚል ርዕስ ተመልከት።