ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
የመዘመር ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱን አራት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
የመዝሙር መጽሐፋችንን ከፍ አድርገን በመያዝ ቀጥ ብለን መቆማችን ጠቃሚ ነው። አየር በደንብ መሳብ ይኖርብናል። በተጨማሪም አፋችንን በደንብ መክፈታችን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለመዘመር ይረዳናል።—w17.11 ገጽ 5
በእስራኤል የሚገኙት የመማጸኛ ከተሞች ከነበሩበት ቦታ እንዲሁም ወደ ከተሞቹ ከሚወስዱት መንገዶች ምን ትምህርት እናገኛለን?
በመላው እስራኤል ስድስት የመማጸኛ ከተሞች ይገኙ ነበር፤ ወደ እነዚህ ከተሞች የሚወስዱት መንገዶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ይደረግ ነበር። በመሆኑም አንድ ሰው ብዙም ሳይቸገር በፍጥነት ወደ መማጸኛ ከተማ መድረስ ይችል ነበር።—w17.11 ገጽ 14
አምላክ፣ ኢየሱስ ቤዛ እንዲሆንልን ያደረገው ዝግጅት ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
ለዘላለም የመኖር ፍላጎታችንን ያሟላል። በተጨማሪም ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ስለሚያወጣን የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላል። አምላክ፣ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ኢየሱስን ቤዛ አድርጎ የሰጠን ለአዳም ዘሮች ፍቅር ስላለው ነው።—wp17.6 ከገጽ 6-7
በመዝሙር 118:22 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሚገልጸው እንዴት ነው?
አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመቀበል አሻፈረን በማለትና እሱን በማስገደል እንደናቁት አሳይተዋል። ሆኖም ኢየሱስ “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” እንደሚሆን የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም ከሞት መነሳት ነበረበት።—w17.12 ከገጽ 9-10
በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የሚካተቱት የብኩርና መብት ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ?
አንዳንድ የበኩር ልጆች በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም በዚህ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱት የበኩር ልጆች ብቻ አይደሉም። ዳዊት የእሴይ የመጀመሪያ ልጅ ባይሆንም መሲሑ የመጣው በዳዊት የዘር ሐረግ ነው።—w17.12 ከገጽ 14-15
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የሕክምና መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
የሙሴ ሕግ አንዳንድ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ያዝዝ ነበር። ሰዎች አስከሬን ከነኩ በኋላ መታጠብ ይጠበቅባቸው ነበር። ሕጉ ቆሻሻ በአግባቡ መወገድ እንዳለበት ይናገራል። በተጨማሪም ወንድ ልጅ የሚገረዘው በተወለደ በስምንተኛው ቀን ነበር፤ ይህም ደሙ ቶሎ መርጋት እንዲችል ያደርጋል።—wp18.1 ገጽ 7
ክርስቲያኖች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ራሳቸውን መውደዳቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ ትእዛዝ ተሰጥቶናል። (ማር. 12:31) ባሎችም “ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው” እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤፌ. 5:28) እርግጥ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ፍቅር ከመጠን ያለፈ ነው።—w18.01 ገጽ 23
መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
የአምላክን ቃል ማጥናትና ባጠናነው ላይ ማሰላሰል እንዲሁም የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ አለብን። ከዚህም ሌላ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን መፍቀድና የሌሎችን እርዳታ በአመስጋኝነት መቀበል ይኖርብናል።—w18.02 ገጽ 26
ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ኮከብ ቆጠራንና ጥንቆላን መጠቀም የሌለብን ለምንድን ነው?
የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፤ ዋናው ምክንያት ግን መጽሐፍ ቅዱስ ኮከብ ቆጠራንና ጥንቆላን የሚያወግዝ መሆኑ ነው።—wp18.2 ከገጽ 4-5
ሰዎች ቤታቸው ሲጋብዙን ግብዣውን ከተቀበልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
የቀረበልንን ግብዣ ከተቀበልን ቃላችንን መጠበቅ አለብን። (መዝ. 15:4) ያለበቂ ምክንያት ግብዣውን መሰረዝ አይኖርብንም። የጋበዘን ሰው እኛን ለማስተናገድ ብዙ ዝግጅት አድርጎ ሊሆን ይችላል።—w18.03 ገጽ 18
የተሾሙ ወንዶች ከጢሞቴዎስ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
ጢሞቴዎስ ለሰዎች ከልቡ ይጨነቅ እንዲሁም መንፈሳዊ ጉዳዮችን ያስቀድም ነበር። በቅዱስ አገልግሎት በትጋት ተካፍሏል፤ በተጨማሪም የተማረውን ነገር በሥራ ላይ አውሏል። ከዚህም ሌላ ሁልጊዜ ራሱን ያሠለጥንና በይሖዋ መንፈስ ይተማመን ነበር። ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች የጢሞቴዎስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።—w18.04 ከገጽ 13-14