በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እንዲከበር ‘ብርሃናችሁ ይብራ’

ይሖዋ እንዲከበር ‘ብርሃናችሁ ይብራ’

“ሰዎች . . . አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።”—ማቴ. 5:16

መዝሙሮች፦ 77, 59

1. ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርገን ምን ልዩ ምክንያት አለን?

የይሖዋ ሕዝቦች እያደረጉ ያሉትን እድገት መመልከት ምንኛ አስደሳች ነው! ባለፈው ዓመት በየወሩ ከ10,000,000 የሚበልጡ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተናል። ይህም የአምላክ አገልጋዮች ብርሃናቸውን እያበሩ እንዳሉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው! በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለእውነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም ለማሰብ እንሞክር። እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ ቤዛውን በማዘጋጀት ስላሳየው ፍቅር ተምረዋል።—1 ዮሐ. 4:9

2, 3. (ሀ) ‘እንደ ብርሃን አብሪዎች እንዳናበራ’ የትኞቹ ነገሮች አያግዱንም? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 በዓለም ዙሪያ የምንኖር የይሖዋ ምሥክሮች የምንናገረው ቋንቋ የተለያየ ነው። ይህ መሆኑ ግን አባታችንን ይሖዋን በአንድነት ከማወደስ አያግደንም። (ራእይ 7:9) የአፍ መፍቻ ቋንቋችንና የምንኖርበት ቦታ ቢለያይም ሁላችንም “በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን አብሪዎች” ማብራት እንችላለን።—ፊልጵ. 2:15

3 በየጊዜው እያደረግን ያለነው እድገት፣ በመካከላችን ያለው አንድነት እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተን ለመኖር የምናደርገው ጥረት ለይሖዋ ክብር ያመጣል። በእነዚህ መንገዶች ብርሃናችንን ማብራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።—ማቴዎስ 5:14-16ን አንብብ።

ግብዣውን ማቅረብ

4, 5. (ሀ) ብርሃናችንን ለማብራት ምሥራቹን ከመስበክ በተጨማሪ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ደግነት ማሳየታችን ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

4 “ማንኛውም ሰው፣ ብርሃኑን ለማብራት ፈቃደኛ እስካልሆነ ድረስ . . . በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ለጌታ ታማኝ መሆን አይችልም።” ይህ ሐሳብ የሚገኘው በሰኔ 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ በወጣ “በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማብራት” የሚል ርዕስ ላይ ነው። ርዕሱ አክሎም “ምሥራቹን ለምድር ሕዝቦች በመስበክና ከብርሃኑ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር” ብርሃናችንን ማብራት እንዳለብን ገልጿል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ብርሃናችንን ማብራት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ፣ ምሥራቹን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ከዚህም በተጨማሪ በምናሳየው ምግባር ይሖዋን ማስከበር እንችላለን። ምሥራቹን የምንሰብክላቸው ሰዎችም ሆነ ስንሰብክ የሚመለከቱን ሌሎች ግለሰቦች የምናሳየውን ባሕርይ ይታዘባሉ። ሰዎችን ስናነጋግር ፈገግ ብለን ወዳጃዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሰላምታ መስጠታችን፣ ሌሎች ለእኛም ሆነ ለምናመልከው አምላክ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

5 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 10:12) ኢየሱስና ሐዋርያቱ በሚሰብኩበት አካባቢ፣ ሰዎች ወደ ቤታቸው የመጣን ሰው ባያውቁትም እንኳ ወደ ውስጥ እንዲገባ የመጋበዝ ባሕል ነበራቸው። በዛሬው ጊዜ በብዙ አካባቢዎች እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ቀርቷል። ያም ቢሆን ወደ ቤታቸው የመጣንበትን ምክንያት በደግነትና ወዳጃዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት መንገድ ካስረዳናቸው የቤቱ ባለቤቶች ሊረጋጉ ይችላሉ። በዚህ ረገድ ፈገግታ ትልቅ ኃይል አለው። በጽሑፍ ጋሪ ተጠቅመን ስንመሠክርም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ በምንካፈልበት ጊዜ ሰዎችን ፈገግ ብለን ሰላም ስንላቸው ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። ደግነት ማሳየታችን ሰዎች ወደ እኛ ቀረብ ብለው ጽሑፎች እንዲወስዱ ብሎም ለመወያየት ፈቃደኛ እንዲሆኑ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

6. በዕድሜ የገፉ አንድ ባልና ሚስት አገልግሎታቸውን ለማስፋት ምን አድርገዋል?

6 በእንግሊዝ የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ አንድ ባልና ሚስት ከባድ የጤና ችግር ስላለባቸው ከቤት ወደ ቤት ማገልገል በጣም ያስቸግራቸዋል። በመሆኑም የቤታቸው ደጃፍ ላይ ሆነው ምሥራቹን በመስበክ ‘ብርሃናቸውን ለማብራት’ አሰቡ። ባልና ሚስቱ የሚኖሩት በአንድ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ነው፤ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመውሰድ በሚመጡበት ሰዓት ላይ አረጋውያኑ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ጠረጴዛ ላይ ደርድረው ይጠብቃሉ። ብዙዎች ጽሑፎቹን ሲያዩ የማወቅ ጉጉት ስላደረባቸው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 እና 2⁠ን እንዲሁም ብሮሹሮችን ወስደዋል። አረጋውያኑ ባሉበት ጉባኤ ውስጥ የምትገኝ አንዲት አቅኚ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከአረጋውያኑ ጋር አብራ ማገልገል ጀመረች። ይህች እህት የምታሳየውን ወዳጃዊ ስሜት እንዲሁም ባልና ሚስቱ ሌሎችን ለመርዳት የሚያደርጉትን ልባዊ ጥረት ያስተዋለ አንድ አባት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማምቷል።

7. ወደ አካባቢያችሁ የሚመጡ የሌላ አገር ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

7 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙዎች አገራቸውን ትተው በመሰደድ በሌሎች አገራት ውስጥ ለመኖር ተገድደዋል። እነዚህ ስደተኞች ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው እንዲያውቁ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? ወደምትኖሩበት አካባቢ የመጡ የሌላ አገር ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ ሰላምታ የሚሰጥበትን መንገድ ለመማር ለምን አትሞክሩም? ጄ ደብልዩ ላንግዌጅ (JW Language) የተባለው አፕሊኬሽን በዚህ ረገድ ይረዳችኋል። ከሰላምታ በተጨማሪ ከሰዎቹ ጋር ውይይት ለመጀመር የሚያስችሏችሁን አንዳንድ አገላለጾች መማርም ትችላላችሁ። ሰዎቹ ቆም ብለው ሲያናግሯችሁ jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ልታስተዋውቋቸው እንዲሁም በቋንቋቸው የሚገኙ የተለያዩ ቪዲዮዎችንና ጽሑፎችን ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ።—ዘዳ. 10:19

8, 9. (ሀ) በሳምንቱ መሃል በምናደርገው ስብሰባ ላይ ምን ጠቃሚ ሥልጠና እናገኛለን? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

8 አፍቃሪ የሆነው አባታችን ይሖዋ፣ በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ለመርዳት ሲል የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባን አዘጋጅቶልናል። በዚህ ስብሰባ ላይ የምናገኘው ጠቃሚ ሥልጠና፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና ጥናት ለመምራት ድፍረት እንዲኖረን ብዙዎቻችንን ረድቶናል።

9 በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ አዳዲስ ሰዎች፣ ትናንሽ ልጆችም ሐሳብ እንደሚሰጡ መመልከታቸው አስገርሟቸዋል። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በራሳቸው አባባል ሐሳብ እንዲሰጡ በማሠልጠን እነሱም ብርሃናቸውን እንዲያበሩ እርዷቸው። አንዳንድ አዳዲስ ሰዎች፣ ልጆች የሚሰጡትን ከልብ የመነጨ መልስ መስማታቸው ወደ እውነት እንዲሳቡ አድርጓቸዋል።—1 ቆሮ. 14:25

አንድነታችንን ማጠናከር

10. የቤተሰብ አምልኮ አንድነትን ለማጠናከር ምን አስተዋጽኦ ያደርጋል?

10 ብርሃናችንን ማብራት የምንችልበት ሌላው መንገድ፣ በቤተሰባችንም ሆነ በጉባኤ ውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር ነው። ወላጆች የቤተሰባቸውን አንድነት ማጠናከር ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ፣ ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ ነው። ብዙዎች በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት የJW ብሮድካስቲንግን ወርሃዊ ፕሮግራም የመመልከት ልማድ አላቸው። ፕሮግራሙን ከተመለከታችሁ በኋላ በቪዲዮው ላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችሉ ለምን አትወያዩም? የቤተሰቡ ራስ፣ ጥናቱን በሚመራበት ወቅት ለአንድ ትንሽ ልጅና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ታዳጊ የሚያስፈልገው ሥልጠና እንደሚለያይ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። እንግዲያው ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ከጥናቱ ጥቅም እንዲያገኙ የሚረዱ ጠቃሚ ነጥቦችን አንስታችሁ ተወያዩ።—መዝ. 148:12, 13

ለአረጋውያን ትኩረት መስጠታችን ያበረታታናል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11-13. ሁላችንም ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግና ሌሎችም ብርሃናቸውን እንዲያበሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

11 ወጣቶች ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግና ሌሎችም ብርሃናቸውን እንዲያበሩ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ በዕድሜ ለገፉ የጉባኤው አባላት ትኩረት ለመስጠት ለምን ግብ አታወጣም? በእውነት ውስጥ ባሳለፏቸው ዓመታት ስላገኙት ተሞክሮ እንዲነግሩህ በአክብሮት ልትጠይቃቸው ትችላለህ። እንዲህ በማድረግህ እንደምትበረታታ ጥያቄ የለውም፤ ከዚህም ሌላ አንተም ሆንክ እነሱ የእውነትን ብርሃን ይበልጥ ለማብራት ትነሳሳላችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንም ወደ ስብሰባ አዳራሻችን የሚመጡ ሰዎችን ጥሩ አድርገን ለመቀበል ጥረት ማድረግ እንችላለን። ይህን ማድረጋችን አንድነታችንን ከማጠናከርም ባሻገር ወደ ስብሰባችን የሚመጡ ሰዎች አብረውን የእውነትን ብርሃን እንዲያበሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። አዲሶችን በፈገግታ ሰላም ልንላቸው፣ የሚቀመጡበት ቦታ እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንዲሁም ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር ልናስተዋውቃቸው እንችላለን። ይህም የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋል።

12 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንድትመራ ከተመደብክ፣ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በአገልግሎት እንዲካፈሉ በመርዳት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለህ። አረጋውያኑ ለእነሱ አመቺ የሆነ የአገልግሎት ክልል እንዲኖራቸው ልታደርግ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ሊያግዟቸው ከሚችሉ ወጣቶች ጋር ልትመድባቸው ትችል ይሆናል። በጤንነታቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በአገልግሎት ብዙ ማከናወን ለማይችሉ ክርስቲያኖችም አሳቢነት ማሳየት ያስፈልጋል። በእርግጥም አስተዋይ መሆንህና አሳቢነት ማሳየትህ፣ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እንዲሁም አዲሶችም ሆኑ በእውነት ውስጥ የቆዩ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በቅንዓት እንዲሰብኩ ሊረዳቸው ይችላል።—ዘሌ. 19:32

13 መዝሙራዊው “ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 133:1, 2ን አንብብ።) እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክ አንድ ላይ መሰብሰባቸው፣ አንዳቸው በሌላው ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ያስችላቸው ነበር። መዝሙራዊው ይህን ሁኔታ፣ አስደሳች መዓዛ ካለውና ቆዳን ከሚያለመልም ዘይት ጋር አመሳስሎታል። እኛም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ደግነትና ወዳጃዊ ስሜት በማሳየት መንፈሳቸው እንዲታደስ ማድረግ እንችላለን። ይህም የጉባኤው አንድነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ያበረክታል። በዚህ ረገድ ለምታደርገው ጥረት ልትመሰገን ይገባሃል። ‘ልብህን ወለል አድርገህ በመክፈት’ ይህን ልማድህን ይበልጥ ማጠናከር ትችል ይሆን?—2 ቆሮ. 6:11-13

14. በምትኖርበት አካባቢ የእውነት ብርሃን ደምቆ እንዲበራ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

14 በምትኖርበት አካባቢ የእውነት ብርሃን ይበልጥ ደምቆ እንዲበራ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው? ደግነት የሚንጸባረቅበት አነጋገርህ እንዲሁም ምግባርህ ጎረቤቶችህ ወደ እውነት እንዲሳቡ ሊያደርግ ይችላል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ጎረቤቶቼ ለእኔ ምን አመለካከት አላቸው? ቤቴንና አካባቢዬን ንጹሕና ያልተዝረከረከ በማድረግ ሰፈሩ ያማረ እንዲሆን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ? ቅድሚያውን ወስጄ ሌሎችን እረዳለሁ?’ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜ፣ ደግነትና ጥሩ ምግባር ማሳየታቸው በዘመዶቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸው፣ በሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም አብረዋቸው በሚማሩ ልጆች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ብትጠይቃቸው ግሩም ተሞክሮዎችን ትሰማለህ።—ኤፌ. 5:9

ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ

15. ምንጊዜም ነቅተን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን እንደሆነ ማስታወሳችን ብርሃናችንን በድምቀት ማብራታችንን ለመቀጠል ያነሳሳናል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ደጋግሞ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 24:42፤ 25:13፤ 26:41) ‘ታላቁ መከራ’ ብዙ እንደሚቆይ እንዲያውም በእኛ የሕይወት ዘመን እንደማይመጣ የምናስብ ከሆነ የስብከቱን ሥራ በጥድፊያ ስሜት እንደማናከናውን የታወቀ ነው። (ማቴ. 24:21) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካዳበርን ብርሃናችን በድምቀት ከመብራት ይልቅ እየደበዘዘ ሊመጣ ብሎም ከናካቴው ሊጠፋ ይችላል።

16, 17. ምንጊዜም ነቅተን ለመጠበቅ የሚረዳን ምንድን ነው?

16 ይህ አስቸጋሪ ዘመን እየተባባሰ በሄደ መጠን ሁላችንም ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል። ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እርምጃ እንደሚወስድ ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለውም። (ማቴ. 24:42-44) እስከዚያው ድረስ ግን ምንጊዜም ንቁ ሆነን በትዕግሥት እንጠባበቅ። የአምላክን ቃል በየዕለቱ እናንብብ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች እንሁን። (1 ጴጥ. 4:7) ምንጊዜም ነቅተው በመጠበቅና ብርሃናቸውን በማብራት ደስታ ያገኙ ወንድሞችና እህቶች ከተዉት ግሩም አርዓያ ትምህርት እንውሰድ። ለምሳሌ በሚያዝያ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-21 ላይ የሚገኘውን “ለሰባ ዓመታት የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ መያዝ” የሚለውን ተሞክሮ ማንበባችን ይጠቅመናል።

17 በይሖዋ አገልግሎት ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ። ለሌሎች ደግነት አሳዩ፤ እንዲሁም ከእምነት አጋሮቻችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ። ይህን ማድረጋችሁ ታላቅ ደስታ ያስገኝላችኋል፤ ጊዜውም ሳታስቡት ያልፋል። (ኤፌ. 5:16) የይሖዋ አገልጋዮች ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ ብዙ ነገሮችን አከናውነዋል። ዛሬም በይሖዋ መንፈስ እየተመራን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በርካታ ሥራዎችን እያከናወንን ነው። በቀድሞ ዘመን የኖሩ ወንድሞቻችን ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ ብርሃናችን ደምቆ እየበራ ነው።

ሽማግሌዎች የሚያደርጉልን እረኝነት በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው ጥበብ ለመጠቀም ያስችለናል (አንቀጽ 18, 19⁠ን ተመልከት)

18, 19. የጉባኤ ሽማግሌዎች ምንጊዜም ንቁና ቀናተኛ ሆነን እንድናገለግል የሚረዱን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

18 ፍጽምና የሌለን ሰዎች መሆናችን ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዳናገለግል እንደማያግደን ማወቅ የሚያበረታታ ነው። ደግሞም ይሖዋ እኛን ለመርዳት ሲል “ሰዎችን” ይኸውም የጉባኤ ሽማግሌዎችን ‘ስጦታ አድርጎ ሰጥቶናል።’ (ኤፌሶን 4:8, 11, 12ን አንብብ።) እንግዲያው የጉባኤ ሽማግሌዎች እረኝነት ሲያደርጉላችሁ፣ ከሚሰጧችሁ ጥበብ ያዘለ ምክር ጥቅም ለማግኘት ጥረት አድርጉ።

19 ለምሳሌ፣ በእንግሊዝ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ ችግር ስላጋጠማቸው ሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲረዷቸው ጠየቁ። ሚስትየው፣ ባለቤቷ ቅድሚያውን ወስዶ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ እየመራ እንዳልሆነ ተሰምቷት ነበር። ባለቤቷም ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንደሌለውና የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ቋሚ እንዲሆን ማድረግ እንዳልቻለ ተናገረ። ሽማግሌዎቹ፣ የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ ለባልና ሚስቱ ነገሯቸው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይንከባከባቸው እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ከግምት ያስገባ ነበር። ሽማግሌዎቹ፣ በዚህ ረገድ ኢየሱስን እንዲመስል ባልየውን አበረታቱት። ሚስትየዋን ደግሞ እንደ ኢየሱስ ትዕግሥተኛ እንድትሆን መከሯት። በተጨማሪም እነዚህ ባልና ሚስት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ የሚረዷቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ሽማግሌዎቹ አካፈሏቸው። (ኤፌ. 5:21-29) ከጊዜ በኋላም ሽማግሌዎቹ ባልየውን ላደረገው ጥረት አመሰገኑት። የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥልበት እንዲሁም ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ጥሩ አድርጎ ለመምራት የይሖዋን መንፈስ እርዳታ እንዲጠይቅ ማበረታቻ ሰጡት። ሽማግሌዎቹ በፍቅርና በአሳቢነት ተነሳስተው ለዚህ ቤተሰብ ያደረጉት እርዳታ ቤተሰቡ ብርሃኑን ማብራቱን እንዲቀጥል አድርጓል።

20. ብርሃናችን እንዲበራ ማድረጋችን ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

20 መዝሙራዊው “ይሖዋን የሚፈሩ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ ደስተኞች ናቸው” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 128:1) ሌሎች ይሖዋን እንዲያመልኩ ግብዣ በማቅረብ፣ አንድነታችን እንዲጠናከር አስተዋጽኦ በማድረግ እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተን በመጠበቅ ብርሃናችንን ስናበራ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። በተጨማሪም ብዙዎች መልካም ሥራችንን በመመልከት አባታችንን ለማክበር ይነሳሳሉ።—ማቴ. 5:16