በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ሞገስ ማግኘት ይችል ነበር

የአምላክን ሞገስ ማግኘት ይችል ነበር

ይሖዋን ስናገለግል የእሱን ሞገስ ማግኘት እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። ይሁንና አምላክ ሞገስ የሚያሳየውና በረከቱን የሚያፈሰው ለምን ዓይነት ሰዎች ነው? በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ቀደም ሲል ከባድ ኃጢአት ፈጽመው የነበረ ቢሆንም የአምላክን ሞገስ አግኝተዋል። ሌሎች ደግሞ አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት ቢኖሯቸውም የአምላክን ሞገስ ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለዚህ “ይሖዋ ከእያንዳንዳችን በዋነኝነት የሚፈልገው ምንድን ነው?” ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። የይሁዳ ንጉሥ የነበረው የሮብዓም ታሪክ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሊረዳን ይችላል።

መጥፎ ጅምር

ሮብዓም፣ ለ40 ዓመታት በእስራኤል ላይ የገዛው የሰለሞን ልጅ ነው። (1 ነገ. 11:42) ሰለሞን በ997 ዓ.ዓ. ሞተ። ከዚያም ሮብዓም ንግሥናውን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም ተነስቶ በስተ ሰሜን ወደምትገኘው ወደ ሴኬም አቀና። (2 ዜና 10:1) ሮብዓም በአስደናቂ ጥበቡ የሚታወቀውን አባቱን ሰለሞንን ተክቶ እንደሚነግሥ ሲያስብ ስጋት አድሮበት ይሆን? ለነገሩ ሮብዓም ከባድ ችግሮችን የመፍታት ችሎታ ያለው መሆን አለመሆኑ የሚፈተንበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም።

ሮብዓም በእስራኤል ውስጥ ውጥረት እንደነገሠ አስተውሎ መሆን አለበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዳንድ ሰዎች ሕዝቡን ወክለው ወደ እሱ መጡና ያሳሰባቸውን ነገር እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ነገሩት፦ “አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር። አንተ ግን አባትህ የሰጠንን አስቸጋሪ ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር የምታቀልልን ከሆነ እናገለግልሃለን።”—2 ዜና 10:3, 4

ሮብዓም አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ተሰምቶት መሆን አለበት! የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ የተጫነባቸውን ቀንበር ቢያቀል፣ እሱና ቤተሰቡ እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ የነበሩት ሰዎች የቅንጦት ሕይወታቸውን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መተው ሊኖርባቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄ ለመቀበል አሻፈረኝ ቢል ሕዝቡ ያምፅበታል። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? አዲሱ ንጉሥ በመጀመሪያ፣ የሰለሞን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች ምክር ጠየቀ። ከዚያ በኋላ ግን ሮብዓም አብሮ አደጎቹ የነበሩትን ወጣቶች አማከረ። ሮብዓም ወጣቶቹ የሰጡትን ምክር በመከተል ሕዝቡን በጭካኔ ለመግዛት ወሰነ። “ቀንበራችሁን አከብደዋለሁ፤ ከቀድሞውም የከፋ አደርገዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ” በማለት ለሕዝቡ መልስ ሰጠ።—2 ዜና 10:6-14

ታዲያ ይህ ታሪክ ለእኛ ምን ያስተምረናል? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በዕድሜ የሚበልጡንን በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር መስማት ብዙውን ጊዜ የጥበብ እርምጃ ነው። እንዲህ ያሉት ክርስቲያኖች፣ በዕድሜ ያካበቱት ተሞክሮ ስላላቸው አንድ ውሳኔ የሚያስከትለውን ውጤት በማስተዋል ጥሩ ምክር ሊሰጡን ይችላሉ።—ኢዮብ 12:12

“የይሖዋን ቃል ሰሙ”

ሮብዓም ለሕዝቡ ዓመፅ ምላሽ ለመስጠት ሠራዊቱን አሰባሰበ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ነቢዩን ሸማያህን በመላክ ለሮብዓምና ለሠራዊቱ እንዲህ አላቸው፦ “ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት አትውጡ። ይህ እንዲሆን ያደረግኩት እኔ ስለሆንኩ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።”—1 ነገ. 12:21-24 *

ሮብዓም ጭራሽ መዋጋት የለበትም ማለት ነው? ይህ ሮብዓምን ምን ያህል አሳስቦት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ተገዢዎቹን “በእሾህ አለንጋ” እንደሚገርፋቸው ሲዝት የነበረው ንጉሥ፣ የተነሳበትን ዓመፅ ሳያስቆም እጁን አጣጥፎ እንደተቀመጠ ሲያይ ሕዝቡስ ምን ይላል? (ከ2 ዜና መዋዕል 13:7 ጋር አወዳድር።) ያም ቢሆን ንጉሡና ሠራዊቱ “የይሖዋን ቃል ሰሙ፤ ይሖዋ እንደነገራቸውም ወደየቤታቸው ተመለሱ።”

ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? አምላክን መታዘዝ ለፌዝ ሊዳርገን ቢችልም እንኳ እሱን መታዘዛችን የጥበብ እርምጃ ነው። አምላክን መታዘዝ የእሱን ሞገስና በረከት ለማግኘት ያስችላል።—ዘዳ. 28:2

ታዲያ ሮብዓም መታዘዙ ምን ውጤት አስገኘ? ሮብዓም አምላክን በመታዘዝ፣ አዲስ የተቋቋመውን ሰሜናዊ መንግሥት ለመውጋት የነበረውን ዕቅድ ተወ፤ ከዚያም በግዛቱ ሥር ባሉት የይሁዳና የቢንያም ነገድ ክልሎች ውስጥ ከተሞች መገንባት ጀመረ። በርካታ ከተሞችንም “እጅግ አጠናከራቸው።” (2 ዜና 11:5-12) ከዚህም በላይ ለተወሰነ ጊዜ የይሖዋን ሕግ ተከትሏል። በኢዮርብዓም ግዛት ሥር የነበረውና አሥሩን ነገዶች ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ጣዖት አምልኮ ውስጥ ሲዘፈቅ፣ በእስራኤል መንግሥት ውስጥ የነበሩ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መቆም የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ “ለሮብዓም ድጋፍ” ሰጥተዋል። (2 ዜና 11:16, 17) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ሮብዓም ታዛዥ መሆኑ ንግሥናውን አጠናክሮለታል።

ለፈጸመው ኃጢአት በመጠኑ ንስሐ ገብቷል

ሮብዓም ንግሥናው በሚገባ ከተጠናከረ በኋላ አንድ ያልተጠበቀ ነገር አደረገ። የይሖዋን ሕግ ትቶ በጣዖት አምልኮ ተዘፈቀ! ሮብዓም ይህን ያደረገው አሞናዊት የነበረችው እናቱ ተጽዕኖ ስላሳደረችበት ይሆን? (1 ነገ. 14:21) ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ብሔሩ በሙሉ የእሱን አካሄድ ተከተለ። በዚህም የተነሳ ይሖዋ፣ የግብፁ ንጉሥ ሺሻቅ ብዙዎቹን የይሁዳ ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር እንዲያውላቸው ፈቀደለት፤ ሮብዓም ከተሞቹን አጠናክሯቸው የነበረ ቢሆንም በሺሻቅ ከመያዝ አላመለጡም!—1 ነገ. 14:22-24፤ 2 ዜና 12:1-4

የሺሻቅ ሠራዊት የሮብዓም መናገሻ ወደሆነችው ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ነገሮች ይበልጥ ተባባሱ። በዚህ ጊዜ ነቢዩ ሸማያህ ለሮብዓምና ለመኳንንቱ “እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቻችኋለሁ” በማለት የአምላክን መልእክት ነገራቸው። ታዲያ ሮብዓም ለዚህ ተግሣጽ አዘል መልእክት ምን ምላሽ ሰጠ? መጽሐፍ ቅዱስ “የእስራኤል መኳንንትና ንጉሡ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ‘ይሖዋ ጻድቅ ነው’ አሉ” በማለት ይናገራል፤ በእርግጥም ሮብዓምና መኳንንቱ ለመልእክቱ በጎ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ሮብዓምንና ኢየሩሳሌምን ከጥፋት ታደጋቸው።—2 ዜና 12:5-7, 12

ከዚያ በኋላ ሮብዓም በደቡባዊው መንግሥት ላይ መግዛቱን ቀጠለ። ሮብዓም ከመሞቱ በፊት፣ በርካታ ለነበሩት ወንዶች ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በብዛት ሰጣቸው፤ ይህን ያደረገው አልጋ ወራሽ በሚሆነው በወንድማቸው በአቢያህ ላይ እንዳያምፁበት አስቦ ሳይሆን አይቀርም። (2 ዜና 11:21-23) በዚህ ጊዜ ሮብዓም በወጣትነቱ ሲያደርግ ከነበረው በተለየ መልኩ ማስተዋል የታከለበት እርምጃ ወስዷል።

ሮብዓም ጥሩ ንጉሥ ነበር ወይስ መጥፎ?

ሮብዓም አንዳንድ መልካም ነገሮችን የሠራ ቢሆንም የአምላክን ሞገስ ሳያገኝ ቀርቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሮብዓም የግዛት ዘመን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “ክፉ ነገር አደረገ” ይላል። ዘገባው ይህን ያደረገበትን ምክንያት ሲገልጽ “ይሖዋን ለመፈለግ ከልቡ ቆርጦ [አልተነሳም]” በማለት ይናገራል።—2 ዜና 12:14

ከንጉሥ ዳዊት በተቃራኒ ሮብዓም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና አልመሠረተም

ይህ ታሪክ የሚያስተላልፈውን ትምህርት ልብ በል፦ ሮብዓም አምላክን የታዘዘባቸው ጊዜያት ነበሩ። ደግሞም የይሖዋን ሕዝብ የሚጠቅሙ አንዳንድ ነገሮችን አድርጓል። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ሳይመሠርት ቀርቷል፤ በተጨማሪም ይሖዋን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት አልነበረውም። በዚህም ምክንያት መጥፎ ድርጊት የፈጸመ ሲሆን በጣዖት አምልኮም ተዘፍቋል። ይህን ስታነብ ‘ሮብዓም የአምላክን ተግሣጽ የተቀበለው ከልቡ ንስሐ ስለገባና ይሖዋን ማስደሰት ስለፈለገ ሳይሆን ሌሎች እንዲህ እንዲያደርግ ስለገፋፉት ነበር ማለት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። (2 ዜና 11:3, 4፤ 12:6) ሮብዓም የኋላ ኋላ መጥፎ ነገር ማድረጉን ቀጥሏል። ከአያቱ ከንጉሥ ዳዊት በጣም የተለየ ሰው ነበር! እርግጥ ነው፣ ዳዊት ኃጢአት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ያም ቢሆን ዳዊት በዋነኝነት ተለይቶ የሚታወቀው ለይሖዋ ባለው ፍቅር፣ ለእውነተኛ አምልኮ ያደረ ሰው በመሆኑና ለፈጸማቸው ኃጢአቶች ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ነው።—1 ነገ. 14:8፤ መዝ. 51:1, 17፤ 63:1

በእርግጥም ከሮብዓም ታሪክ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ማቅረባችንና በይሖዋ አገልግሎት ተግተን መሥራታችን የሚያስመሰግን ነው። ይሁንና የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከሁሉ አስቀድመን እውነተኛውን አምልኮ መደገፍና ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አለብን።

ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ለማዳበር መጣራችን ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ይረዳናል። እየነደደ ያለ እሳት እንዳይጠፋ እንጨት መማገድ እንዳለብን ሁሉ ለአምላክ ያለን ፍቅር እንዳይቀንስም ቃሉን አዘውትረን ማንበብ፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም በጸሎት መጽናት ይኖርብናል። (መዝ. 1:2፤ ሮም 12:12) በዚህ መልኩ ለይሖዋ ፍቅር ካዳበርን በምናደርገው ነገር ሁሉ እሱን ለማስደሰት እንነሳሳለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ልባዊ ንስሐ ለመግባትም ይገፋፋናል። ከሮብዓም በተለየ መልኩ በእውነተኛው አምልኮ ጸንተን መቀጠል እንችላለን።—ይሁዳ 20, 21

^ አን.9 ሰለሞን ታማኝነቱን ባለመጠበቁ ምክንያት መንግሥቱ እንደሚከፈል አምላክ ቀደም ብሎ ገልጾ ነበር።—1 ነገ. 11:31