ይሖዋና ኢየሱስ አንድ እንደሆኑ ሁላችንም አንድ እንሁን
“የምለምንህ . . . ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው።”—ዮሐ. 17:20, 21
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ባቀረበው የመጨረሻ ጸሎት ላይ ምን ልመና አቅርቧል? (ለ) ኢየሱስ የአንድነትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው ለምን ሊሆን ይችላል?
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ በመካከላቸው ያለው አንድነት እንደሚያሳስበው የሚያሳይ ሐሳብ ተናግሯል። ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ባቀረበው ጸሎት ላይ፣ እሱና አባቱ አንድ እንደሆኑ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ አንድ እንዲሆኑ ያለውን ፍላጎት ገልጿል። (ዮሐንስ 17:20, 21ን አንብብ።) በደቀ መዛሙርቱ መካከል የሚኖረው አንድነት፣ የአምላክን ፈቃድ እንዲያደርግ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ይሖዋ መሆኑን የሚመሠክር ግልጽ ማስረጃ ይሆናል። ፍቅር የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ሲሆን እንዲህ ያለው ፍቅር ለአንድነታቸው አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ዮሐ. 13:34, 35
2 ኢየሱስ የአንድነትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው ሐዋርያቱ በዚህ ረገድ ድክመት እንዳላቸው ስላስተዋለ ሊሆን ይችላል። ሐዋርያቱ ከዚያ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ባሳለፉት የመጨረሻ ምሽትም “ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?” በሚለው ጉዳይ ላይ ተከራክረው ነበር። (ሉቃስ 22:24-27፤ ማር. 9:33, 34) በሌላ ጊዜ ደግሞ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሲመጣ የተሻለውን ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል።—ማር. 10:35-40
3. የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንድነት እንዳይኖራቸው ያደረጉት የትኞቹ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ? ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
3 የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንድነት እንዳይኖራቸው ሊያደርግ የሚችለው ከሌሎች ልቀው ለመታየት ያላቸው ፍላጎት ብቻ አልነበረም። በኢየሱስ ዘመን የሚኖሩ
ሰዎች በመካከላቸው ጭፍን ጥላቻ ስለነበረ እርስ በርስ ተከፋፍለው ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ ያለውን አመለካከት ማስወገድ ነበረባቸው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን፦ ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ጭፍን ጥላቻ ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም እሱ ምን አድርጓል? ኢየሱስ፣ ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲይዙና በመካከላቸው እውነተኛ አንድነት እንዲኖር ተከታዮቹን የረዳቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ያስተማረው ነገር እኛም አንድነታችንን እንድንጠብቅ የሚረዳንስ እንዴት ነው?ሰዎች ለኢየሱስና ለተከታዮቹ የነበራቸው ጭፍን ጥላቻ
4. አንዳንዶች ለኢየሱስ ጭፍን አመለካከት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
4 ለኢየሱስም እንኳ ጭፍን አመለካከት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ፊልጶስ፣ መሲሑን እንዳገኘ ለናትናኤል ሲነግረው ናትናኤል “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” ብሎታል። (ዮሐ. 1:46) ናትናኤል በሚክያስ 5:2 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ሳያውቅ አይቀርም፤ እንዲሁም መሲሑ እንደ ናዝሬት ካለች ያን ያህል ቦታ የማይሰጣት ከተማ ሊመጣ እንደማይችል ተሰምቶት መሆን አለበት። በተመሳሳይም ትልቅ ቦታ ያላቸው የይሁዳ ሰዎች፣ ኢየሱስን የገሊላ ሰው በመሆኑ ንቀውታል። (ዮሐ. 7:52) ብዙዎቹ የይሁዳ ሰዎች፣ የገሊላ ሰዎችን ዝቅ አድርገው ያዩአቸው ነበር። ሌሎች አይሁዳውያን ደግሞ ኢየሱስን ለመስደብ ሲሉ “ሳምራዊ” በማለት ጠርተውታል። (ዮሐ. 8:48) ሳምራውያን በዘራቸውም ሆነ በሃይማኖታቸው ከአይሁዳውያን የተለዩ ነበሩ። የይሁዳም ሆነ የገሊላ ሰዎች ለሳምራውያን ንቀት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ከእነሱ ጋር አይቀራረቡም ነበር።—ዮሐ. 4:9
5. ሰዎች ለኢየሱስ ተከታዮች ጭፍን ጥላቻ እንደነበራቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የኢየሱስን ተከታዮችም ይንቋቸው ነበር። ፈሪሳውያን የኢየሱስን ተከታዮች ‘የተረገመ ሕዝብ’ ብለው ጠርተዋቸዋል። (ዮሐ. 7:47-49) ፈሪሳውያን፣ በረቢዎች ትምህርት ቤት ገብተው ያልተማሩትን ወይም የእነሱን ወግ የማይከተሉትን ሰዎች በሙሉ ተራና የማይረቡ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። (ሥራ 4:13 ግርጌ) ሰዎቹ ለኢየሱስና ለደቀ መዛሙርቱ ጭፍን ጥላቻ እንዲኖራቸው ያደረገው፣ በወቅቱ የነበረው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ እንዲሁም የዘር ክፍፍል ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ለሌሎች ጭፍን ጥላቻ ነበራቸው፤ በመሆኑም በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር አመለካከታቸውን መለወጥ ያስፈልጋቸው ነበር።
6. ጭፍን ጥላቻ በእኛም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
6 በዛሬው ጊዜም በአካባቢያችን የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ለሌሎች ጭፍን ጥላቻ አላቸው። ሌሎች ለእኛ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ይኖራቸው ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ እኛ ራሳችን ለሌሎች ጭፍን ጥላቻ ሊኖረን ይችላል። በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ባለው ዘመን በአቦሪጂኖች ላይ ስለደረሰው በደል ብሎም በአሁኑ ጊዜ ስለሚፈጸምባቸው ግፍ ሳስብ ለነጮች ያለኝ ጥላቻ እየጨመረ መጣ። እኔ ራሴ የደረሰብኝ በደልም ለእነሱ የመረረ ጥላቻ እንዲያድርብኝ አድርጎ ነበር።” በካናዳ የሚኖር ወንድም ደግሞ በቋንቋቸው ምክንያት ለአንዳንድ ሰዎች ጭፍን ጥላቻ እንደነበረው ተናግሯል። “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች እንደሚበልጡ ይሰማኝ የነበረ ሲሆን እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ጥላቻ ነበረኝ” ብሏል።
7. ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ጭፍን ጥላቻ ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም እሱ ምን አድርጓል?
7 በኢየሱስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዘመናችን ያሉ ሰዎችም ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ ሊኖራቸው ይችላል። ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመው ምን አድርጓል? አንደኛ ነገር፣ ከአድልዎ ሙሉ በሙሉ በመራቅ ጭፍን ጥላቻ እንደሌለው አሳይቷል። ለሀብታሞችም ሆነ ለድሆች፣ ለፈሪሳውያንም ሆነ ለሳምራውያን ሌላው ቀርቶ ለቀረጥ ሰብሳቢዎችና ለኃጢአተኞችም ጭምር ሰብኳል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ሌሎችን በጥርጣሬ ዓይን እንዳይመለከቱ ወይም ለሰዎች ጭፍን አመለካከት እንዳይኖራቸው በንግግሩና በድርጊቱ አስተምሯቸዋል።
ፍቅርና ትሕትና በማዳበር ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ
8. በክርስቲያኖች መካከል ላለው አንድነት በጣም አስፈላጊ የሆነው መሠረታዊ እውነታ ምንድን ነው? አብራራ።
8 ኢየሱስ ለአንድነታችን በጣም አስፈላጊ የሆነውን መሠረታዊ እውነታ ለተከታዮቹ ሲናገር “ሁላችሁም ማቴዎስ 23:8, 9ን አንብብ።) “ወንድማማቾች” እንድንባል የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ሁላችንም የአዳም ልጆች መሆናችን ነው። (ሥራ 17:26) ምክንያቱ ግን ይህ ብቻ አይደለም። የኢየሱስ ተከታዮች፣ ይሖዋን እንደ ሰማያዊ አባታቸው አድርገው ስለሚቀበሉ ሁሉም ወንድማማችና እህትማማች እንደሆኑ ኢየሱስ ገልጿል። (ማቴ. 12:50) በተጨማሪም የክርስቶስ ተከታዮች በፍቅርና በእምነት የተሳሰረ የአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባላት ናቸው። ሐዋርያት በጻፏቸው ደብዳቤዎች ላይ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ‘ወንድሞች’ እና ‘እህቶች’ ብለው የጠሯቸው ለዚህ ነው።—ሮም 1:13፤ 1 ጴጥ. 2:17፤ 1 ዮሐ. 3:13 *
ወንድማማቾች ናችሁ” ብሏቸዋል። (9, 10. (ሀ) አይሁዳውያን በዘራቸው ሊኮሩ የማይገባው ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ከእኛ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጎ መመልከት ተገቢ አለመሆኑን ያስተማረው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
9 ኢየሱስ፣ እንደ ወንድማማችና እንደ እህትማማች ልንተያይ እንደሚገባ ከተናገረ በኋላ የትሕትናን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 23:11, 12ን አንብብ።) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በሐዋርያቱ መካከል አንድነት እንዳይኖር ያደረገው ተገቢ ያልሆነ ኩራት ነው። በተጨማሪም በኢየሱስ ዘመን ሰዎች በዘራቸው በጣም ይኮሩ ነበር። ይሁንና አይሁዳውያን የአብርሃም ዘሮች መሆናቸው እንዲኮሩ ሊያደርጋቸው ይገባል? በርካታ አይሁዳውያን እንዲህ ይሰማቸው ነበር። ሆኖም መጥምቁ ዮሐንስ “አምላክ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆች ማስነሳት [አይሳነውም]” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 3:8
10 ኢየሱስ በዘር መኩራት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግሯል። ከጸሐፍት ወገን የሆነ አንድ ሰው “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ብሎ ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ አጋጣሚውን በመጠቀም፣ በዘር መኩራት ተገቢ አለመሆኑን አስተምሯል። ኢየሱስ፣ በጉዞ ላይ እያለ ዘራፊዎች የደበደቡትን አንድ አይሁዳዊ በደግነት ስለተንከባከበ ሳምራዊ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። በዚያ የሚያልፉ አይሁዳውያን ጉዳት የደረሰበትን ሰው ቢያዩትም ችላ ብለውት ሄዱ፤ ሳምራዊው ግን ለግለሰቡ አዘነለት። ኢየሱስ ምሳሌውን ከደመደመ በኋላ፣ ጥያቄውን ያቀረበለትን ሰው እንደ ሳምራዊው እንዲሆን ነገረው። (ሉቃስ 10:25-37) አይሁዳውያን፣ እውነተኛ ባልንጀራ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ከሳምራዊ መማር እንደሚችሉ ኢየሱስ በግልጽ አሳይቷል።
11. የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለሌላ አገር ሰዎች ከአድልዎ ነፃ የሆነ አመለካከት ማዳበር የሚያስፈልጋቸው ለምን ነበር? ኢየሱስ ይህን እንዲያደርጉ የረዳቸው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንዲሰብኩ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 1:8) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ተልእኮ ለመወጣት፣ ኩራትንና ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ ነበረባቸው። ኢየሱስ፣ የሌላ አገር ሰዎች ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ጎላ አድርጎ በመናገር ተከታዮቹ ለሁሉም ብሔራት ለመስበክ አእምሯቸውን እንዲያዘጋጁ ቀደም ብሎ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ፣ የሌላ አገር ተወላጅ የሆነ አንድ የጦር መኮንን ያሳየውን ታላቅ እምነት አድንቋል። (ማቴ. 8:5-10) ባደገባት በናዝሬት ደግሞ፣ ይሖዋ ለባዕድ አገር ሰዎች ሞገስ እንዳሳያቸው የተናገረ ሲሆን በሰራፕታ ትኖር የነበረችውን ፊንቄያዊት መበለት እንዲሁም የሥጋ ደዌ ይዞት የነበረውን ሶርያዊውን ንዕማንን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። (ሉቃስ 4:25-27) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት ሰብኳል፤ እንዲሁም አንዳንድ ሳምራውያን መልእክቱን ለመስማት ፍላጎት ስላሳዩ በሳምራውያን ከተማ ሁለት ቀን አሳልፏል።—ዮሐ. 4:21-24, 40
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ ነበረባቸው
12, 13. (ሀ) ሐዋርያት ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት በመስበኩ ምን ተሰማቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስ የሰጠው ትምህርት በደንብ እንዳልገባቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
12 ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ የነበራቸውን ጭፍን ጥላቻ ማስወገድ ቀላል አልሆነላቸውም። ኢየሱስ አንዲትን ሳምራዊት ማስተማሩ በጣም አስገርሟቸው ነበር። (ዮሐ. 4:9, 27) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ አጠያያቂ ምግባር ያላትን ሳምራዊት ይቅርና ማንኛዋንም ሴት በአደባባይ አያነጋግሩም ነበር። ኢየሱስ ሳምራዊቷን ካነጋገረ በኋላ ሐዋርያቱ ምግብ እንዲበላ ጎተጎቱት። ኢየሱስ ግን በሚያደርገው መንፈሳዊ ውይይት ተጠምዶ ስለነበር ረሃቡን ማስታገስ በኋላ ሊደርስ የሚችል ጉዳይ እንደሆነ ተሰምቶታል። ኢየሱስ፣ ለአንዲት ሳምራዊትም ቢሆን ምሥራቹ መሰበኩ የአባቱ ፈቃድ መሆኑን ያውቅ ነበር፤ ይህ ሥራ ለእሱ እንደ ምግብ ነበር።—ዮሐ. 4:31-34
13 ያዕቆብና ዮሐንስ ግን ኢየሱስ የሰጠው ትምህርት በደንብ አልገባቸውም። ከኢየሱስ ጋር ሆነው በሰማርያ እያለፉ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ማደሪያ ለማግኘት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሆኖም ሳምራውያኑ ሊቀበሏቸው ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ያዕቆብና ዮሐንስ በዚህ እጅግ በመበሳጨታቸው እሳት ከሰማይ አውርደው መንደሯን ለማጥፋት ሐሳብ አቀረቡ። ኢየሱስ ግን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጣቸው። (ሉቃስ 9:51-56) በእንግድነት ሊቀበሏቸው ፈቃደኛ ያልሆኑት፣ የትውልድ አካባቢያቸው በሆነው በገሊላ የሚኖሩ ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ ያዕቆብና ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አያቀርቡ ይሆናል። ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ያለ የጥላቻ ስሜት እንዲያሳዩ ያደረጋቸው ለሰማርያ ሰዎች የነበራቸው ጭፍን አመለካከት ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ የሰበከላቸው በርካታ ሳምራውያን ምሥራቹን እንደተቀበሉ ሲያይ ከዚያ ቀደም በቁጣ የተናገረው ነገር አሳፍሮት መሆን አለበት።—ሥራ 8:14, 25
14. የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ችግር መፍትሔ ያገኘው እንዴት ነው?
14 በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ ውስጥ በተፈጸመ አድልዎ ምክንያት ችግር ተፈጠረ። ደቀ መዛሙርቱ ለመበለቶች ምግብ በሚያከፋፍሉበት ወቅት፣ ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ መበለቶች ቸል ተብለው ነበር። (ሥራ 6:1) መበለቶቹ ቸል የተባሉት የሌላ አገር ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሐዋርያቱ የምግብ ክፍፍሉን በበላይነት የሚከታተሉ ብቃት ያላቸው ወንድሞችን በመሾም ለችግሩ ፈጣን እልባት አበጁ። መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው እነዚህ ወንድሞች በሙሉ የግሪክኛ ስም ነበራቸው። ይህም የተበደሉትን መበለቶች አጽናንቷቸው መሆን አለበት።
15. ጴጥሮስ ሁሉንም ሰው ያለአድልዎ በመያዝ ረገድ ምን ማሻሻያ አድርጓል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
15 በ36 ዓ.ም. ክርስቲያኖች ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች መስበክ ጀመሩ። ከዚያ ቀደም ብሎ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚቀራረበው ከአይሁዳውያን ጋር ብቻ ነበር። ክርስቲያኖች ማዳላት እንደሌለባቸው አምላክ በግልጽ ካሳወቀው በኋላ ግን ጴጥሮስ ሮማዊ ወታደር ለሆነው ለቆርኔሌዎስ ሰብኳል። (የሐዋርያት ሥራ 10:28, 34, 35ን አንብብ።) ከዚያ በኋላ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ከሆኑ አማኞች ጋር አብሮ ይመገብና ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ከዓመታት በኋላ ግን ጴጥሮስ በአንጾኪያ በነበረበት ወቅት፣ አይሁዳውያን ካልሆኑት ክርስቲያኖች ጋር አብሮ መብላት አቁሞ ራሱን ከእነሱ አገለለ። (ገላ. 2:11-14) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ለጴጥሮስ ተገቢውን ተግሣጽ የሰጠው ሲሆን ጴጥሮስም እርማቱን ተቀብሏል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ጴጥሮስ በትንሿ እስያ ለሚኖሩ አይሁዳውያንና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች የመጀመሪያ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት መላውን የወንድማማች ማኅበር መውደድ አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ገልጿል።—1 ጴጥ. 1:1፤ 2:17
16. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ስም አትርፈው ነበር?
16 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሐዋርያት “ሁሉንም ዓይነት ሰዎች” መውደድ እንዳለባቸው ከኢየሱስ ምሳሌ ተምረዋል። (ዮሐ. 12:32፤ 1 ጢሞ. 4:10) ሐዋርያቱ አመለካከታቸውን ለማስተካከል ጊዜ ቢወስድባቸውም ይህን ማድረግ ችለዋል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ባለው ፍቅር ተለይተው ይታወቁ ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረው ተርቱሊያን የተባለ ጸሐፊ፣ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ስለ ክርስቲያኖች ሲናገሩ “እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ፣ . . . አልፎ ተርፎም አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ተመልከቱ” እንዳሉ ገልጿል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “አዲሱን ስብዕና” ስለለበሱ፣ ልክ እንደ አምላክ ሁሉንም ሰዎች በእኩል ዓይን ማየት ችለው ነበር።—ቆላ. 3:10, 11
17. ጭፍን ጥላቻን ከልባችን ውስጥ ነቅለን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
17 እኛም ብንሆን ጭፍን ጥላቻን ከልባችን ውስጥ ነቅለን ለማስወገድ ጊዜ ይወስድብን ይሆናል። በፈረንሳይ የምትኖር አንዲት እህት በዚህ ረገድ የምታደርገውን ትግል
ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ፍቅር ማሳየት፣ ለሌሎች ማካፈል እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት ሰዎች መውደድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ይሖዋ አስተምሮኛል። ያም ሆኖ ለሌሎች ያለኝን ጭፍን አመለካከት ለማስወገድ አሁንም እየታገልኩ ነው፤ በእርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ስለዚህ ጉዳይ አዘውትሬ የምጸልየውም ለዚህ ነው።” በስፔን የምትኖር አንዲት እህትም ተመሳሳይ ትግል ማድረግ አስፈልጓታል፤ እንዲህ ብላለች፦ “በዘራቸው ምክንያት የምጠላቸው ሰዎች ነበሩ፤ ይህን ስሜት በማሸነፍ ረገድ አብዛኛውን ጊዜ ቢሳካልኝም አንዳንድ ጊዜ ግን መታገል ያስፈልገኛል። የማደርገውን ትግል መቼም ቢሆን ማቆም እንደሌለብኝ አውቃለሁ። አንድነት ያለው ቤተሰብ አባል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፤ ለዚህም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።” ሁላችንም ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ያስፈልገናል። እንደ እነዚህ ሁለት እህቶች ሁሉ እኛም ልናስወግደው የሚገባ የጭፍን ጥላቻ ርዝራዥ በውስጣችን ይኖር ይሆን?ፍቅር እያደገ ሲሄድ ጭፍን ጥላቻ ይወገዳል
18, 19. (ሀ) ሁሉንም ሰው እንድንቀበል የሚያነሳሳን ምንድን ነው? (ለ) ይህን ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
18 በአንድ ወቅት ሁላችንም “ባዕዳን” ይኸውም ከአምላክ የራቅን እንደነበርን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ኤፌ. 2:12) ይሖዋ ግን ‘በፍቅር ማሰሪያ’ ወደ ራሱ ስቦናል። (ሆሴዕ 11:4፤ ዮሐ. 6:44) ክርስቶስም ቢሆን የአምላክ ቤተሰብ አባላት መሆን የምንችልበትን አጋጣሚ በመክፈት ተቀብሎናል። (ሮም 15:7ን አንብብ።) ፍጽምና የሌለን ቢሆንም ኢየሱስ በደግነት ተቀብሎናል፤ ከዚህ አንጻር ሌሎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ጨርሶ ልናስበው የማይገባ ነገር ነው!
19 ወደዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ እየተጠጋን ስንሄድ፣ ጭፍን አመለካከትና ጥላቻ ይበልጥ እየተስፋፉ እንደሚሄዱ ጥያቄ የለውም። (ገላ. 5:19-21፤ 2 ጢሞ. 3:13) እኛ ግን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን፣ አድልዎ የሌለበትንና ሰላማዊ የሆነውን ሰማያዊ ጥበብ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። (ያዕ. 3:17, 18) ከሌሎች አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት፣ ባሕላቸውን ማክበር አልፎ ተርፎም ቋንቋቸውን መማር ያስደስተናል። ይህን ስናደርግ በጉባኤያችን ውስጥ ሰላም እንደ ወንዝ፣ ፍትሕ ደግሞ እንደ ባሕር ሞገድ ይሆናል።—ኢሳ. 48:17, 18
20. ፍቅር አመለካከታችንን እና ስሜታችንን ሲቀርጸው ውጤቱ ምን ይሆናል?
20 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አውስትራሊያዊት እህት “የእውነተኛ እውቀት በር ወለል ብሎ ተከፈተልኝ” በማለት ተናግራለች። አክላም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷ እንዴት እንደጠቀማት ስትገልጽ “አዲስ ልብና አስተሳሰብ ማዳበር ቻልኩ፤ በመሆኑም በውስጤ ሥር ሰድዶ የነበረው ጭፍን አመለካከትና ጥላቻ ከሰመ” ብላለች። ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነው ካናዳዊ ወንድም ደግሞ “ብዙውን ጊዜ ለዘረኝነት መንስኤው፣ አለማወቅ መሆኑንና የሰዎች ማንነት በተወለዱበት አካባቢ ላይ የተመካ አለመሆኑን” እንደተገነዘበ ተናግሯል። ይህ ወንድም እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆነች እህት አግብቷል! እነዚህ ሰዎች ካደረጉት የአመለካከት ለውጥ ማየት እንደሚቻለው፣ ክርስቲያናዊ ፍቅር ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ ይችላል፤ ደግሞም ያሸንፋል። በእርግጥም ፍቅር በማይበጠስ ማሰሪያ ያስተሳስረናል።—ቆላ. 3:14