የጥናት ርዕስ 25
የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ በይሖዋ ታመኑ
‘ብዙ ጭንቀት አለብኝ።’—1 ሳሙ. 1:15
መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ
የትምህርቱ ዓላማ *
1. ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ያለብን ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት በተናገረው ትንቢት ላይ “ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:34) ለዚህ ማስጠንቀቂያ ትኩረት መስጠት አለብን። ለምን? ምክንያቱም እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ እኛም አስጨናቂ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል።
2. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን አስጨናቂ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል?
2 አንዳንድ ጊዜ በርካታ ችግሮች ይደራረቡብናል። እስቲ አንዳንዶች ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች እንመልከት። ጆን * የተባለ ወንድም መልቲፕል ስክለሮሲስ የሚባል ሕመም አለበት፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለ19 ዓመታት አብራው የኖረችው የትዳር ጓደኛው ጥላው ሄደች፤ ይህ ሁኔታ ስሜቱን በጣም ጎድቶት ነበር። ከዚያም ሁለት ሴቶች ልጆቹ ይሖዋን ማገልገላቸውን አቆሙ። ቦብ እና ሊንዳ የተባሉት ባልና ሚስት ያጋጠሟቸው ችግሮች ደግሞ ከዚህ ይለያሉ። ሁለቱም ከሥራቸው ተፈናቀሉ፤ በኋላ ላይ ደግሞ ቤታቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ። ይህም እንዳይበቃ፣ ሊንዳ ለሕይወት አስጊ የሆነ የልብ በሽታ እንዳለባት ተነገራት፤ ከዚህም ሌላ በሽታ የመከላከል አቅሟን የሚያዳክም የጤና እክል አጋጠማት።
3. ፊልጵስዩስ 4:6, 7 እንደሚለው ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
3 ፈጣሪያችንና አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን የሚሰማንን ስሜት እንደሚረዳልን መተማመን እንችላለን። ደግሞም ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መቋቋም እንድንችል ሊረዳን ይፈልጋል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።) የይሖዋ አገልጋዮች በጽናት ስለተወጧቸው ችግሮች የሚገልጹ በርከት ያሉ ዘገባዎችን በአምላክ ቃል ውስጥ እናገኛለን። በተጨማሪም የአምላክ አገልጋዮች ያጋጠማቸውን አስጨናቂ ሁኔታ እንዲቋቋሙ ይሖዋ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ በቃሉ ውስጥ ሰፍሯል። እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
ኤልያስ—“እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው”
4. ኤልያስ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል? በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ እያለም ስለ ይሖዋ ምን ተሰምቶታል?
4 ኤልያስ ይሖዋን ያገለገለው አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ላይ ሲሆን ከበድ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውታል። ታማኝ ካልሆኑት የእስራኤል ነገሥታት አንዱ የሆነው አክዓብ፣ የባአል አምላኪ የሆነችውን ክፉዋን ኤልዛቤልን አግብቶ ነበር። ባልና ሚስቱ፣ የባአል አምልኮ በእስራኤል እንዲስፋፋ ያደረጉ ከመሆኑም ሌላ በርካታ የይሖዋ ነቢያትን አስገድለዋል። ኤልያስ ከዚህ መትረፍ ችሏል። በተጨማሪም በምድሪቱ ከባድ ረሃብ በነበረበት ወቅት በይሖዋ በመታመኑ በሕይወት ተርፏል። (1 ነገ. 17:2-4, 14-16) ከዚህም ሌላ ኤልያስ፣ በይሖዋ በመታመን የባአል ነቢያትንና አምላኪዎችን ተገዳድሯል። እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ማሳሰብ አስፈልጎት ነበር። (1 ነገ. 18:21-24, 36-38) ኤልያስ በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ይሖዋ እየደገፈው እንዳለ በግልጽ መመልከት ችሏል።
5-6. በ1 ነገሥት 19:1-4 ላይ እንደተገለጸው ኤልያስ ምን ተሰምቶት ነበር? ይሖዋስ ኤልያስን እንደሚወደው ያሳየው እንዴት ነው?
5 አንደኛ ነገሥት 19:1-4ን አንብብ። ኤልያስ፣ ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው ስትዝትበት ግን በፍርሃት ተዋጠ። በመሆኑም ወደ ቤርሳቤህ ሸሸ። በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ‘እንዲሞት መለመን ጀመረ።’ ኤልያስ ይህን ያህል ተስፋ የቆረጠው ለምንድን ነው? ይህ ነቢይ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው” ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር። (ያዕ. 5:17) በጣም ከመጨነቁና ከመዛሉ የተነሳ ሁኔታዎች ከአቅሙ በላይ እንደሆኑ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ኤልያስ፣ ሕዝቡ ይሖዋን እንዲያመልክ የሚያደርገው ጥረት መና እንደቀረ፣ በእስራኤል ያለው ሁኔታ ምንም እንዳልተሻሻለና ይሖዋን እያገለገለ ያለው እሱ ብቻ እንደሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 18:3, 4, 13፤ 19:10, 14) ይህ ታማኝ ነቢይ እንዲህ የተሰማው መሆኑ ያስገርመን ይሆናል። ይሖዋ ግን የኤልያስን ስሜት ተረድቶለታል።
6 ኤልያስ ስሜቱን አውጥቶ በመናገሩ ይሖዋ አልተቆጣውም። እንዲያውም ኃይሉ እንዲታደስ አድርጓል። (1 ነገ. 19:5-7) ከዚያም ይሖዋ፣ ታላቅ ኃይሉን ለኤልያስ በማሳየት ይህ ነቢይ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል በደግነት ረድቶታል። በኋላም ይሖዋ፣ ባአልን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ 7,000 አገልጋዮች በእስራኤል እንዳሉት ለነቢዩ ነገረው። (1 ነገ. 19:11-18) ይሖዋ ኤልያስን እንደሚወደው በእነዚህ መንገዶች አሳይቶታል።
ይሖዋ እርዳታ የሚያደርግልን እንዴት ነው?
7. ይሖዋ ኤልያስን የረዳበት መንገድ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?
7 የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሟችኋል? ይሖዋ የኤልያስን ስሜት እንደተረዳለት ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው! ይህን ማወቃችን የእኛንም ጭንቀት እንደሚረዳልን ያረጋግጥልናል። ይሖዋ አቅማችንን እንዲሁም ሐሳባችንንና ስሜታችንን ያውቃል። (መዝ. 103:14፤ 139:3, 4) እንደ ኤልያስ በይሖዋ ከታመንን፣ እሱ ጭንቀት የሚፈጥሩብንን ችግሮች መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።—መዝ. 55:22
8. ይሖዋ ጭንቀታችሁን ለመቋቋም የሚረዳችሁ እንዴት ነው?
8 የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ አሉታዊ አመለካከት ያድርባችሁና ተስፋ ትቆርጡ ይሆናል። እንዲህ ከተሰማችሁ ይሖዋ ጭንቀታችሁን ለመቋቋም እንደሚረዳችሁ አስታውሱ። ይሖዋ የሚረዳችሁ እንዴት ነው? የሚያሳስባችሁን ነገር አውጥታችሁ እንድትነግሩት ጋብዟችኋል። እርዳታ ለማግኘት የምታቀርቡትን ልመና ይሰማል። (መዝ. 5:3፤ 1 ጴጥ. 5:7) ስለዚህ ያጋጠሟችሁን ችግሮች በተመለከተ አዘውትራችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። ይሖዋ ለኤልያስ እንዳደረገው በቀጥታ ባያነጋግራችሁም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስና በድርጅቱ በኩል መልስ ይሰጣችኋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምታነቧቸው ታሪኮች መጽናኛና ተስፋ ይሰጧችኋል። በተጨማሪም ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ያበረታቷችኋል።—ሮም 15:4፤ ዕብ. 10:24, 25
9. እምነት የሚጣልበት ወዳጅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
9 ኤልያስ፣ ካሉበት ኃላፊነቶች አንዳንዶቹን ለኤልሳዕ እንዲሰጠው ይሖዋ ነግሮት ነበር፤ በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ ኤልያስ ጭንቀቱን የሚያካፍለው ወዳጅ እንዲያገኝ አድርጓል። እኛም በተመሳሳይ የሚሰማንን ነገር አውጥተን ለምናምነው ወዳጃችን መናገራችን፣ ጭንቀታችን ቀለል እንዲለን ሊረዳን ይችላል። (2 ነገ. 2:2፤ ምሳሌ 17:17) የልባችሁን የምታካፍሉት ሰው እንደሌለ ከተሰማችሁ፣ ሊያበረታታችሁ የሚችል የጎለመሰ ክርስቲያን ለማግኘት እንዲረዳችሁ ይሖዋን ጠይቁት።
10. የኤልያስ ተሞክሮ ምን ተስፋ ይሰጠናል? በኢሳይያስ 40:28, 29 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
10 ኤልያስ ያጋጠመውን አስጨናቂ ሁኔታ እንዲቋቋምና ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት እንዲያገለግል ይሖዋ ረድቶታል። የኤልያስ ተሞክሮ ተስፋ ይሰጠናል። እኛም በጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ኃይላችን የሚሟጠጥበትና ስሜታችን የሚደቆስበት ጊዜ ይኖራል። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ግን እሱን ማገልገላችንን ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል።—ኢሳይያስ 40:28, 29ን አንብብ።
ሐና፣ ዳዊትና “አሳፍ” በይሖዋ ታምነዋል
11-13. በጥንት ዘመን የነበሩ ሦስት የአምላክ አገልጋዮች ምን አስጨናቂ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር?
11 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች ሰዎችም ከበድ ያሉ አስጨናቂ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር። ለምሳሌ ሐና፣ መሃን መሆን የሚያስከትለውን የኃፍረት ስሜት እንዲሁም የጣውንቷን የሚያቆስል ንግግር ችላ መኖር ነበረባት። (1 ሳሙ. 1:2, 6) ሐና ባጋጠማት አስጨናቂ ሁኔታ በጣም ከመማረሯ የተነሳ ዘወትር ታለቅስ ነበር፤ ምግብ መብላትም አቅቷት ነበር።—1 ሳሙ. 1:7, 10
12 ንጉሥ ዳዊትም በጭንቀት የተዋጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። እስቲ ስላጋጠሙት ችግሮች እናስብ። በፈጸማቸው በርካታ ስህተቶች የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃይ ነበር። (መዝ. 40:12) የሚወደው ልጁ አቢሴሎም ዓምፆበታል፤ በኋላም አቢሴሎም በዚሁ ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል። (2 ሳሙ. 15:13, 14፤ 18:33) እንዲሁም ከቅርብ ወዳጆቹ አንዱ ዳዊትን ክዶታል። (2 ሳሙ. 16:23 እስከ 17:2፤ መዝ. 55:12-14) ዳዊት ከጻፋቸው መዝሙሮች ብዙዎቹ፣ ያደረበትን የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ ላይ ያለውን ጽኑ እምነት የሚያሳዩ ናቸው።—መዝ. 38:5-10፤ 94:17-19
13 ከጊዜ በኋላ ደግሞ አንድ መዝሙራዊ በክፉዎች አኗኗር መቅናት ጀመረ። ይህ መዝሙራዊ፣ ‘በታላቁ የአምላክ መቅደስ’ ያገለግል የነበረ ሲሆን ከሌዋዊው አሳፍ ዘሮች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። መዝሙራዊው ከመጨነቁ ብዛት፣ ደስታ ርቆትና በሕይወቱ እርካታ አጥቶ ነበር። እንዲያውም አምላክን ማገልገል በረከት የሚያስገኝ ነገር መሆኑን መጠራጠር ጀምሮ ነበር።—መዝ. 73:2-5, 7, 12-14, 16, 17, 21
14-15. እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለትን በተመለከተ ከሦስቱ የአምላክ አገልጋዮች ምን እንማራለን?
14 ሦስቱም የይሖዋ አገልጋዮች እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ዞር ብለዋል። ያስጨነቃቸውን ነገር በተመለከተ ወደ ይሖዋ አጥብቀው ጸልየዋል። የተጨነቁበትን ምክንያት በግልጽ ነግረውታል። ይሖዋ ወደሚመለክበት ቦታ መሄዳቸውንም አላቆሙም።—1 ሳሙ. 1:9, 10፤ መዝ. 55:22፤ 73:17፤ 122:1
15 ይሖዋም በርኅራኄ ተነሳስቶ ለእያንዳንዳቸው መልስ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ሐና ውስጣዊ ሰላም አግኝታለች። (1 ሳሙ. 1:18) ዳዊትም “የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 34:19) ከአሳፍ ዘሮች አንዱ የሆነው መዝሙራዊ ደግሞ ይሖዋ ‘ቀኝ እጁን እንደያዘው’ እና ፍቅር በሚንጸባረቅበት ምክር እንደሚመራው ከጊዜ በኋላ ተገንዝቧል። “እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል። . . . ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 73:23, 24, 28) ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ጊዜ፣ በጣም የሚያስጨንቁ ችግሮች ያጋጥሙናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሌሎችን እንዴት እንደረዳ በሚገልጹ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን፣ ይሖዋ እንዲረዳን አዘውትረን ወደ እሱ መጸለያችን እንዲሁም እሱ የሚሰጠንን መመሪያ መታዘዛችን ጭንቀታችንን ለመቋቋም ይረዳናል።—መዝ. 143:1, 4-8
በይሖዋ በመታመን ጭንቀትን መቋቋም
16-17. (ሀ) ራሳችንን ከሌሎች ማግለል የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ኃይላችንን ማደስ የምንችለው እንዴት ነው?
16 ከሦስቱ የአምላክ አገልጋዮች የምንማረው ሌላም አስፈላጊ ነገር አለ፤ ከይሖዋም ሆነ ከሕዝቡ ራሳችንን ማግለል የለብንም። (ምሳሌ 18:1) ባለቤቷ ጥሏት በሄደ ጊዜ በጭንቀት ተውጣ የነበረችው ናንሲ እንዲህ ብላለች፦ “ማንንም ማየትም ሆነ ማነጋገር የማልፈልግባቸው ብዙ ቀናት ነበሩ። ራሴን ከሌሎች ባገለልኩ መጠን ግን ይበልጥ በሐዘን እየተዋጥኩ እሄድ ነበር።” ናንሲ፣ ችግር ያጋጠማቸው ሌሎች ሰዎችን መርዳት ስትጀምር ሁኔታዎች ተለወጡ። እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ሲነግሩኝ አዳምጣቸዋለሁ። ስለ እነሱና ስላጋጠሟቸው ችግሮች ባሰብኩ ቁጥር በራሴ ችግሮች ላይ ብዙም እንደማላተኩር አስተዋልኩ።”
17 እኛም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ኃይላችንን ማደስ እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይሖዋ ለእኛ ‘ረዳትና አጽናኝ’ ለመሆን የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ ያገኛል። (መዝ. 86:17) በስብሰባዎች ላይ በቅዱስ መንፈሱ፣ በቃሉ እንዲሁም በአገልጋዮቹ አማካኝነት ያበረታታናል። ስብሰባዎች “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” የሚያደርግ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥሩልናል። (ሮም 1:11, 12) ሶፊያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “መጽናት የቻልኩት በይሖዋና በወንድማማች ማኅበራችን እርዳታ ነው። ከሁሉ የበለጠ የጠቀሙኝ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ናቸው። በአገልግሎትና በጉባኤ የማደርገውን እንቅስቃሴ በጨመርኩ መጠን፣ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይበልጥ አቅም እንደማገኝ አስተውያለሁ።”
18. የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማን ይሖዋ ምን ሊሰጠን ይችላል?
18 የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚያድርብን ጊዜ፣ ይሖዋ ወደፊት ዘላቂ እፎይታ እንደሚሰጠን ብቻ ሳይሆን አሁንም ጭንቀትን ለመቋቋም እንደሚረዳን ልናስታውስ ይገባል። ይሖዋ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም ‘ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ’ እንዲኖረን ያደርጋል።—ፊልጵ. 2:13
19. ሮም 8:37-39 ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?
19 ሮም 8:37-39ን አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ታዲያ አስጨናቂ ሁኔታ የገጠማቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ላጋጠማቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ርኅራኄ በማሳየት ብሎም እነሱን በመደገፍ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይብራራል።
መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት
^ አን.5 ከልክ ያለፈ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ የሚዘልቅ ጭንቀት በአካላችንም ሆነ በስሜታችን ላይ ጉዳት ያስከትላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ኤልያስ ያጋጠመውን አስጨናቂ ሁኔታ እንዲቋቋም ይሖዋ የረዳው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመን የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያሳዩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እናያለን።
^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።