በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 26

የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውን እርዷቸው

የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውን እርዷቸው

“ሁላችሁም የአስተሳሰብ አንድነት ይኑራችሁ፤ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ ትሑታን ሁኑ።”—1 ጴጥ. 3:8

መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ

የትምህርቱ ዓላማ *

1. አፍቃሪውን አባታችንን ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

ይሖዋ በጣም ይወደናል። (ዮሐ. 3:16) እኛም አፍቃሪውን አባታችንን መምሰል እንፈልጋለን። በመሆኑም ‘የሌላውን ስሜት ለመረዳት፣ የወንድማማች መዋደድ ለማዳበር እንዲሁም ከአንጀት የምንራራ ለመሆን’ ጥረት እናደርጋለን፤ ለሁሉም ሰው በተለይ ደግሞ “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” እነዚህን ባሕርያት እናሳያለን። (1 ጴጥ. 3:8፤ ገላ. 6:10) የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት፣ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ልንረዳቸው እንፈልጋለን።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 የይሖዋ ቤተሰብ አባላት መሆን የሚፈልጉ ሁሉ፣ አስጨናቂ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። (ማር. 10:29, 30) የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በቀረበ መጠን፣ የሚያጋጥሙን ችግሮች እየጨመሩ መሄዳቸው አይቀርም። ታዲያ አንዳችን ሌላውን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ሎጥ፣ ኢዮብና ናኦሚ ከሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ ችግሮች እንዲሁም ሁኔታውን እንዲቋቋሙ ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምንችል እናያለን።

ትዕግሥተኛ ሁኑ

3. ሁለተኛ ጴጥሮስ 2:7, 8 እንደሚጠቁመው ሎጥ ምን የተሳሳተ ውሳኔ አድርጓል? ይህስ ምን አስከትሎበታል?

3 ሎጥ፣ አስጸያፊ ሥነ ምግባር ባላቸው የሰዶም ሰዎች መካከል ለመኖር ሲመርጥ የተሳሳተ ውሳኔ አድርጓል። (2 ጴጥሮስ 2:7, 8ን አንብብ።) አካባቢው ለም ቢሆንም ሎጥ ወደዚያ መሄዱ ከባድ መዘዝ አስከትሎበታል። (ዘፍ. 13:8-13፤ 14:12) ሚስቱ ከተማዋን ስለወደደቻት አሊያም በዚያ ከሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ጋር በጣም ስለተቀራረበች ሳይሆን አይቀርም ይሖዋን መታዘዝ ከባድ ሆነባት። አምላክ በዚያ አካባቢ ላይ ከሰማይ እሳትና ድኝ ባዘነበበት ወቅት ሕይወቷን አጥታለች። ሁለቱ የሎጥ ሴቶች ልጆችስ? ሊያገቧቸው የነበሩት ወንዶች ከሰዶም ጋር አብረው ጠፉ። ሎጥ ቤቱን፣ ንብረቱን ከሁሉ የከፋው ደግሞ ሚስቱን አጥቷል። (ዘፍ. 19:12-14, 17, 26) ሎጥ አስጨናቂ ሁኔታ በገጠመው በዚህ ወቅት ይሖዋ በትዕግሥት ይዞታል።

ይሖዋ፣ ሎጥንና ቤተሰቡን ለማዳን መላእክት በመላክ ርኅራኄ አሳይቷል (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. ይሖዋ ሎጥን በትዕግሥት የያዘው እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

4 ሎጥ በሰዶም ለመኖር ቢመርጥም እንኳ ይሖዋ እሱንና ቤተሰቡን ከጥፋት ለማዳን መላእክትን በመላክ ርኅራኄ አሳይቶታል። ይሁንና ሎጥ ሰዶምን በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ መላእክቱ የሰጡትን ማሳሰቢያ ወዲያውኑ ከመታዘዝ ይልቅ “ዘገየ።” በመሆኑም መላእክቱ እጁን በመያዝ እሱንና ቤተሰቡን ከከተማዋ ማስወጣት አስፈልጓቸው ነበር። (ዘፍ. 19:15, 16) ከዚያም ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ለሎጥ ነገሩት። ሎጥ ግን ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ ቅርብ ወዳለች አንዲት ከተማ ለመሄድ ጠየቀ። (ዘፍ. 19:17-20) ይሖዋም የሎጥን ጥያቄ በትዕግሥት ያዳመጠ ሲሆን ሎጥ ወደፈለገው ከተማ እንዲሸሽ ፈቀደለት። በኋላ ላይ ግን ሎጥ በዚያች ከተማ መኖር ስለፈራ ወደ ተራራማው አካባቢ ሄዶ መኖር ጀመረ፤ ይሖዋ መጀመሪያውኑም ቢሆን እንዲሄድ የነገረው ወደዚህ ቦታ ነበር። (ዘፍ. 19:30) ይሖዋ ያሳየው ትዕግሥት እንዴት አስደናቂ ነው! ታዲያ እሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

5-6. በ1 ተሰሎንቄ 5:14 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ አምላክን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

5 እንደ ሎጥ ሁሉ የመንፈሳዊው ቤተሰባችን አባላትም የተሳሳተ ውሳኔ ያደርጉ ይሆናል፤ በዚህም የተነሳ ከባድ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ምን እናደርጋለን? የተሳሳተ ውሳኔ ያደረገው ሰው፣ የዘራውን እያጨደ እንደሆነ ለመናገር እንፈተን ይሆናል፤ ደግሞም እውነታው ይህ ሊሆን ይችላል። (ገላ. 6:7) ሆኖም ይሖዋ ሎጥን በያዘበት መንገድ ወንድማችንን ብንረዳው የተሻለ ይሆናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ፣ መላእክቱን የላከው ሎጥን እንዲያስጠነቅቁት ብቻ ሳይሆን በሰዶም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ለማምለጥ እንዲረዱትም ጭምር ነበር። እኛም ወንድማችን የተሳሳተ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነ ካስተዋልን ማስጠንቀቅ ያስፈልገን ይሆናል። ሆኖም በዚህ ብቻ ሳንወሰን እሱን መርዳት እንችላለን። የተሰጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ቢዘገይም እንኳ ትዕግሥት ማሳየት ይኖርብናል። እንደ ሁለቱ መላእክት እንሁን። ተስፋ ቆርጠን ከወንድማችን ከመራቅ ይልቅ እሱን መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:18) በምሳሌያዊ አነጋገር እጁን ይዘን ልንረዳው ማለትም የተሰጠውን መልካም ምክር በተግባር እንዲያውል እርዳታ ልናደርግለት ይገባል።1 ተሰሎንቄ 5:14ን አንብብ።

7. ይሖዋ ለሎጥ የነበረው ዓይነት አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ በሎጥ ድክመቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ቢችልም እንዲህ አላደረገም። እንዲያውም ይሖዋ፣ ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሎጥን ጻድቅ ሰው ብሎ እንዲጠራው አድርጓል። ይሖዋ ስህተቶቻችንን እንደማይቆጥርብን ማወቃችን በጣም ያስደስተናል! (መዝ. 130:3) ታዲያ ይሖዋ ለሎጥ የነበረው ዓይነት አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ትኩረት የምናደርገው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ ከሆነ እነሱን በትዕግሥት መያዝ ይቀለናል። እነሱም የምንሰጣቸውን እርዳታ መቀበል አይከብዳቸውም።

ሩኅሩኅ ሁኑ

8. ርኅራኄ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

8 ከሎጥ በተለየ መልኩ ኢዮብ መከራ የደረሰበት፣ የተሳሳተ ውሳኔ በማድረጉ አይደለም። ኢዮብ ከባድ ችግሮች አጋጥመውታል፤ ንብረቱን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን ቦታ እንዲሁም ጤንነቱን አጥቷል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ እሱና ባለቤቱ ልጆቻቸውን በሙሉ ማጣታቸው ነው። ይህም እንዳይበቃ፣ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጅ ተብዬዎች ኢዮብን ወንጅለውታል። ሦስቱ የኢዮብ አጽናኞች ለእሱ ርኅራኄ ማሳየት የከበዳቸው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ያጋጠመውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አለመሞከራቸው ነው። በዚህም የተነሳ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ስለደረሱ ያለርኅራኄ በኢዮብ ላይ ፈርደዋል። እኛስ ተመሳሳይ ስህተት እንዳንሠራ ምን ሊረዳን ይችላል? አንድ ሰው ስላለበት ሁኔታ የተሟላ መረጃ ያለው፣ ይሖዋ ብቻ መሆኑን እናስታውስ። ችግር የደረሰበት ሰው የሚናገረውን ነገር በትኩረት እናዳምጥ። የሚናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን ሥቃዩም ይሰማን። የወንድማችንን ወይም የእህታችንን ስሜት መረዳት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።

9. ርኅራኄ ምን ከማድረግ እንድንቆጠብ ያደርገናል? ለምንስ?

9 ርኅራኄ፣ ሌሎች ከገጠማቸው ችግር ጋር በተያያዘ ሐሜት ከማሰራጨት እንድንቆጠብ ያደርገናል። ሐሜተኛ ሰው ጉባኤውን ከማነጽ ይልቅ መከፋፈል እንዲፈጠር ያደርጋል። (ምሳሌ 20:19፤ ሮም 14:19) ሐሜት፣ ደግነትና አሳቢነት የጎደለው ድርጊት ሲሆን መከራ እየደረሰበት ያለውን ሰው ይበልጥ ይጎዳዋል። (ምሳሌ 12:18፤ ኤፌ. 4:31, 32) በግለሰቡ መልካም ባሕርያት ላይ ትኩረት ማድረጋችንና ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቋቋም እንዴት ልንረዳው እንደምንችል ማሰባችን ምንኛ የተሻለ ይሆናል!

የእምነት ባልንጀራችሁ ‘እንዳመጣለት ቢናገር’ በትዕግሥት አዳምጡት፤ ተገቢውን ጊዜ መርጣችሁ የሚያጽናና ሐሳብ አካፍሉት (ከአንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት) *

10. በኢዮብ 6:2, 3 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን እንማራለን?

10 ኢዮብ 6:2, 3ን አንብብ። ኢዮብ ‘እንዳመጣለት የተናገረባቸው’ ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ በተናገራቸው ነገሮች በኋላ ላይ ተጸጽቷል። (ኢዮብ 42:6) እንደ ኢዮብ ሁሉ በዛሬው ጊዜም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ያጋጠመው አንድ ሰው እንዳመጣለት ሊናገርና በኋላ ላይ ሊቆጭ ይችላል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ግለሰቡን ከመንቀፍ ይልቅ ርኅራኄ ልናሳየው ይገባል። የይሖዋ ዓላማ በአሁኑ ጊዜ እንደምናየው በችግርና በመከራ የተሞላ ሕይወት እንድንመራ አለመሆኑን እናስታውስ። በመሆኑም አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመው፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢናገር የሚያስገርም አይሆንም። ግለሰቡ ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ እኛ የተሳሳተ ነገር ቢናገርም እንኳ በዚህ ቶሎ መናደድ ወይም እንዲህ በማለቱ በእሱ ላይ መፍረድ የለብንም።—ምሳሌ 19:11

11. ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጡ የኤሊሁን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

11 አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጠመው ሰው፣ አንዳንድ ጊዜ ምክር ወይም እርማት ሊያስፈልገውም ይችላል። (ገላ. 6:1) ሽማግሌዎች ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? የኤሊሁን ምሳሌ መከተላቸው ይጠቅማቸዋል፤ ኤሊሁ የኢዮብን ስሜት እንደተረዳለት በሚያሳይ መንገድ በጥሞና አዳምጦታል። (ኢዮብ 33:6, 7) ኤሊሁ ምክር የሰጠው የኢዮብን አመለካከት ከተረዳለት በኋላ ነው። የኤሊሁን ምሳሌ የሚከተሉ ሽማግሌዎች፣ ምክር የሚሰጡትን ሰው በትኩረት የሚያዳምጡት ከመሆኑም ሌላ ግለሰቡ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ካደረጉ በኋላ ምክር ቢሰጡ ግለሰቡ ምክሩን መቀበል ይበልጥ ቀላል ይሆንለታል።

አጽናኗቸው

12. ናኦሚ ባሏንና ሁለት ልጆቿን በሞት ማጣቷ ምን እንዲሰማት አድርጓል?

12 ናኦሚ ይሖዋን የምትወድ ታማኝ ሴት ነበረች። ባሏንና ሁለት ወንዶች ልጆቿን በሞት ካጣች በኋላ ግን ስሟ ናኦሚ መሆኑ ቀርቶ “ማራ” እንዲባል ፈልጋ ነበር፤ “ማራ” የሚለው ስም “መራራ” የሚል ትርጉም አለው። (ሩት 1:3, 5, 20 ግርጌ፣ 21) ናኦሚ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስባት፣ ምራቷ ሩት ከጎኗ አልተለየችም። ሩት፣ ናኦሚ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ከማድረግ በተጨማሪ አጽናንታታለች። ሩት ናኦሚን እንደምትወዳትና ከጎኗ እንደምትሆን ከልብ በመነጩ ያልተወሳሰቡ ቃላት ገልጻላታለች።—ሩት 1:16, 17

13. የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው የእኛ ድጋፍ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

13 የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባል የሆነ ሰው የትዳር ጓደኛውን በሞት ሲያጣ የእኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ባልና ሚስት፣ አጠገብ ለአጠገብ ከተተከሉ ሁለት ዛፎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የዛፎቹ ሥሮች እርስ በርስ ይተሳሰራሉ። በመሆኑም አንደኛው ዛፍ ሲነቀል ሌላኛው ዛፍ ይጎዳል። በተመሳሳይም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን በሞት ሲያጣ ስሜቱ በጣም ሊደቆስ ይችላል፤ ይህ ሁኔታም ለረጅም ጊዜ ይዘልቅ ይሆናል። ባሏ በድንገት የሞተባት ፖላ * እንዲህ ብላለች፦ “ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ፤ ረዳት የለሽ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ያጣሁት የልብ ወዳጄን ነው። ከባለቤቴ ጋር የማላወራው ምንም ነገር አልነበረም። ደስታዬን የሚጋራኝ እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥመኝ የሚደግፈኝ እሱ ነበር። ሲከፋኝ የሚያጽናናኝም እሱ ነበር። እሱን ሳጣ ግማሽ አካሌን ያጣሁ ያህል ተሰማኝ።”

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? (ከአንቀጽ 14-15⁠ን ተመልከት) *

14-15. የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣን ሰው ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?

14 የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣን ሰው ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው? ልናደርገው የሚገባው የመጀመሪያው ነገር ግለሰቡን ማነጋገር ነው፤ ይህን ማድረግ ቢጨንቀን ወይም ምን ማለት እንዳለብን ግራ ቢገባንም እንኳ ሐዘን የደረሰበትን ሰው ከማነጋገር ወደኋላ ማለት የለብንም። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፖላ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች፣ ሐዘን የደረሰበትን ሰው ማዋራት ሊጨንቃቸው እንደሚችል ይገባኛል። ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳይናገሩ ይፈሩ ይሆናል። ሆኖም ምንም ነገር አለመናገራቸው የባሰ እንደሆነ ይሰማኛል።” ሐዘን የደረሰበት ሰው ጥልቀት ያለው ሐሳብ እንድንናገር አይጠብቅብንም። ፖላ “ወዳጆቼ ‘ባለቤትሽን በማጣትሽ በጣም አዝነናል’ ማለታቸው ብቻ ለእኔ በቂ ነው” ብላለች።

15 ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ባለቤቱን በሞት ያጣው ዊልያም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሌሎች፣ ባለቤቴ ስላደረገቻቸው መልካም ነገሮች ሲናገሩ ደስ ይለኛል፤ ባለቤቴን እንደሚወዷትና እንደሚያከብሯት ያረጋግጥልኛል። እንዲህ ማድረጋቸው በጣም ጠቅሞኛል። ባለቤቴ ለእኔ በጣም ውድ ስለሆነችና በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለነበራት፣ ሰዎች ስለ እሷ ሲናገሩ በእጅጉ እጽናናለሁ።” ቢያንካ የተባለች ባሏ የሞተባት ሴትም እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች አብረውኝ ሲጸልዩና ጥቅሶች ሲያነቡልኝ እጽናናለሁ። ስለ ባለቤቴ አንስተው ማውራታቸው እንዲሁም እኔ ስለ እሱ ሳወራ ማዳመጣቸው ጠቅሞኛል።”

16. (ሀ) የሚወደውን ሰው በሞት ላጣ ግለሰብ ምን ልናደርግለት ይገባል? (ለ) ያዕቆብ 1:27 ምን ኃላፊነት እንዳለብን ይናገራል?

16 ሩት፣ መበለት ከሆነችው ከናኦሚ ጎን እንዳልተለየች ሁሉ እኛም የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ሰዎች ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፖላ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ እንደሞተ አካባቢ ብዙዎች ድጋፍ አድርገውልኛል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁሉም ወደ ዕለታዊ ሕይወታቸው ተመለሱ። እኔ ግን ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ሐዘን የደረሰበት ግለሰብ፣ የሚወደውን ሰው በሞት ካጣ ከወራት ሌላው ቀርቶ ከዓመታት በኋላም እንኳ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሌሎች መገንዘባቸው በጣም አስፈላጊ ነው።” በእርግጥ ሁኔታው ከሰው ሰው ይለያያል። አንዳንዶች ሁኔታውን ለመቀበል ብዙ ጊዜ ላይወስድባቸው ይችላል። ሌሎች ግን ከሚወዱት ሰው ጋር ያከናውኑት የነበረው እያንዳንዱ ነገር ሐዘናቸውን ይቀሰቅስባቸዋል። ሰዎች የሚያዝኑበት መንገድ የተለያየ ነው። ይሖዋ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን የመርዳት መብትና ኃላፊነት እንደሰጠን እናስታውስ።ያዕቆብ 1:27ን አንብብ።

17. የትዳር ጓደኛቸው ጥሏቸው የሄደ ሰዎች የእኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

17 አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸው ጥሏቸው በመሄዱ ለከባድ ሐዘንና ጭንቀት ይዳረጋሉ። ጆይስ፣ ባሏ ሌላ ሴት ወዶ ጥሏት ሄዷል፤ ስለ ሁኔታው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ፍቺው ያስከተለብኝ ሥቃይ፣ ባሌ ቢሞት ኖሮ ከሚሰማኝ ሐዘን የሚብስ ይመስለኛል። ባለቤቴ በአደጋ ወይም በሕመም ምክንያት ቢሞት ኖሮ ሁኔታው ከቁጥጥሩ ውጭ ነበር። ሆኖም ባለቤቴ ጥሎኝ የሄደው በምርጫው ነው። በመሆኑም እንዳዋረደኝና እንዳቃለለኝ ተሰማኝ።”

18. የትዳር ጓደኛቸውን ያጡ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

18 በተለያየ ምክንያት የትዳር ጓደኛቸውን ላጡ ሰዎች በትናንሽ ነገሮች ደግነት ስናሳይ፣ እንደምንወዳቸው እናረጋግጥላቸዋለን። እነዚህ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥሩ ወዳጆች ያስፈልጓቸዋል። (ምሳሌ 17:17) ታዲያ ወዳጅ ልትሆኗቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ቀለል ያለ ምግብ ሠርታችሁ ቤታችሁ ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ። አብረዋችሁ እንዲዝናኑ ወይም ከእናንተ ጋር አገልግሎት እንዲወጡ ልትጠይቋቸው ትችሉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ እንዲገኙ አልፎ አልፎ ጋብዟቸው። እንዲህ ስታደርጉ “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ” እንዲሁም ‘ለመበለቶች ጠባቂ’ የሆነውን የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛላችሁ።—መዝ. 34:18፤ 68:5

19. በ1 ጴጥሮስ 3:8 ላይ እንደተገለጸው ቁርጥ ውሳኔያችን ምንድን ነው?

19 የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምድርን መግዛት ሲጀምር “የሚያስጨንቁ ነገሮች [ሁሉ] ይረሳሉ።” “የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም” የተባለለትን ጊዜ መምጣት በጉጉት እንጠባበቃለን። (ኢሳ. 65:16, 17) ያ ጊዜ እስኪመጣ ግን እርስ በርስ መደጋገፋችንን እና የመንፈሳዊ ቤተሰባችንን አባላት በሙሉ እንደምንወዳቸው በቃልም ሆነ በተግባር ማሳየታችንን እንቀጥል።1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።

መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

^ አን.5 ሎጥ፣ ኢዮብና ናኦሚ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ቢሆኑም በሕይወታቸው ውስጥ አስጨናቂ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸው ጊዜያት ነበሩ። ይህ ርዕስ ከእነሱ ተሞክሮ ምን እንደምንማር ይገልጻል። በተጨማሪም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ትዕግሥትና ርኅራኄ ማሳየት እንዲሁም እነሱን ማጽናናት አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ተበሳጭቶ ‘እንዳመጣለት ሲናገር’ አንድ ሽማግሌ በትዕግሥት ሲያዳምጠው። የተበሳጨው ወንድም ከተረጋጋ በኋላ ሽማግሌው በደግነት ምክር ይሰጠዋል።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት ባልና ሚስት፣ ባለቤቱን በቅርቡ በሞት ካጣ ወንድም ጋር ሲጨዋወቱ። ከእሷ ጋር ስላሳለፏቸው አስደሳች ጊዜያት እያወሩለት ነው።