በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራስን መግዛት—የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ

ራስን መግዛት—የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ

“ከአንድ ዘመዴ ጋር ተጣላንና ጉሮሮውን እንቅ አደረግሁት። ልገድለው ፈልጌ ነበር።”—ፖል

“ቤት ውስጥ በትንሽ በትልቁ ቱግ እላለሁ። የቤት ዕቃም ሆነ የልጆች መጫወቻ ያገኘሁትን ማንኛውም ነገር እሰባብራለሁ።”—ማርኮ

እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን ይህን ያህል አንቆጣም። ይሁንና ሁላችንም ራሳችንን መቆጣጠር የሚከብደን ጊዜ አለ። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የኃጢአት ዝንባሌዎችን መውረሳችን ነው። (ሮም 5:12) እንደ ፖልና ማርኮ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ቁጣቸውን መቆጣጠር ይከብዳቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሐሳባቸውን መቆጣጠር ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። በሚያስፈራቸው ነገር ላይ ያውጠነጥናሉ አሊያም አሉታዊ ሐሳቦች ወደ አእምሯቸው እየመጡ ያስቸግሯቸዋል። አንዳንዶች የፆታ ብልግና ለመፈጸም፣ ከመጠን በላይ ለመጠጣት ወይም ዕፆችን ለመውሰድ የሚገፋፋቸውን ስሜት ማሸነፍ ይከብዳቸዋል።

ሐሳባቸውን፣ ምኞታቸውንና ድርጊታቸውን የማይቆጣጠሩ ሰዎች በራሳቸው ላይ ጉዳት ያመጣሉ። እኛ ግን ይህ እንዳይደርስብን ማድረግ እንችላለን። እንዴት? ራስን የመግዛትን ባሕርይ በማዳበር ነው። ይህን ባሕርይ ለማዳበር የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች መመርመራችን ይጠቅመናል፦ (1) ራስን መግዛት ምንድን ነው? (2) አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (3) ‘ከመንፈስ ፍሬ’ ገጽታዎች አንዱ የሆነውን ይህን ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (ገላ. 5:22, 23) ከዚህም በተጨማሪ ራሳችንን መግዛት አቅቶን ስህተት በምንሠራበት ወቅት ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን።

ራስን መግዛት ምንድን ነው?

ራሱን የሚገዛ ሰው፣ በስሜት ተገፋፍቶ አንድን ነገር ከማድረግ ይቆጠባል። አምላክን የሚያሳዝን ነገር ላለመናገር ወይም ላለማድረግ ይጠነቀቃል።

ራስን መግዛት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ኢየሱስ በግልጽ አሳይቷል

ኢየሱስ፣ ራስን መግዛት ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በሕይወቱ አሳይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ ሰጠ።” (1 ጴጥ. 2:23) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ወቅት ተቃዋሚዎቹ ሲያፌዙበት እንዲህ ያለውን ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። (ማቴ. 27:39-44) ከዚያ ቀደም ብሎም፣ በጥላቻ የተሞሉ የሃይማኖት መሪዎች በንግግሩ ሊያጠምዱት በሞከሩበት ወቅት ራስን የመግዛትን ባሕርይ አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል። (ማቴ. 22:15-22) በቁጣ የተሞሉ አይሁዳውያን በድንጋይ ሊወግሩት በሞከሩበት ወቅትም ራስን በመግዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ብድር ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ “ተሰወረና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ።”—ዮሐ. 8:57-59

እኛስ እንደ ኢየሱስ መሆን እንችላለን? በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይህን ማድረግ እንችላለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “[ክርስቶስ] የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 2:21) ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ኢየሱስ ራሱን በመግዛት ረገድ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ መከተል እንችላለን። ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ራስን መግዛት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን ራሳችንን መግዛት ይኖርብናል። ይሖዋን ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ስናገለግል ብንቆይም እንኳ ድርጊታችንን ወይም ንግግራችንን ካልተቆጣጠርን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ሊበላሽ ይችላል።

ሙሴን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ሙሴ በዚያ ወቅት “በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ ነበር።” (ዘኁ. 12:3) ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የእስራኤላውያንን ማጉረምረም ችሎ ከኖረ በኋላ ግን በአንድ ወቅት ራሱን መቆጣጠር አቃተው። ሕዝቡ ውኃ በማጣታቸው በድጋሚ ሲያጉረመርሙ ሙሴ ተቆጣ። “እናንተ ዓመፀኞች ስሙ! ከዚህ ዓለት ለእናንተ ውኃ ማፍለቅ አለብን?” በማለት ሕዝቡን በቁጣ ተናገራቸው።—ዘኁ. 20:2-11

ሙሴ ራሱን ሳይቆጣጠር ቀረ። ተአምራዊ በሆነ መንገድ ውኃ ላወጣላቸው ለይሖዋ እውቅና አልሰጠም። (መዝ. 106:32, 33) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ከለከለው። (ዘኁ. 20:12) ሙሴ በዚያ ወቅት ራሱን አለመቆጣጠሩ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሳይቆጨው አልቀረም።—ዘዳ. 3:23-27

ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በእውነት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ብንቆይም፣ የሚያበሳጩንን ወይም እርማት የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች አክብሮት በጎደለው መንገድ ፈጽሞ ልንናገራቸው አይገባም። (ኤፌ. 4:32፤ ቆላ. 3:12) እርግጥ ነው፣ በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ ታጋሽ መሆን ይበልጥ ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። ሆኖም የሙሴን ታሪክ እናስታውስ። ራሳችንን ሳንቆጣጠር በመቅረታችን በፈጸምነው አንድ ስህተት የተነሳ፣ ለረጅም ዓመታት አምላክን በታማኝነት በማገልገል ያሳለፍነው ታሪክ እንዲበላሽ አንፍቀድ። ታዲያ ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን?

ራስን የመግዛትን ባሕርይ ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?

መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልይ። ለምን? ራስን መግዛት የአምላክ መንፈስ ፍሬ አንዱ ገጽታ ነው፤ ይሖዋ ደግሞ ለሚለምኑት መንፈሱን ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:13) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:13) በተጨማሪም ሌሎች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ለምሳሌ ፍቅርን እንድናዳብር ይረዳናል፤ ፍቅር ደግሞ ራሳችንን መግዛት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል።—1 ቆሮ. 13:5

ራስን መግዛት ከባድ እንዲሆንብህ ከሚያደርግ ማንኛውም ነገር ራቅ

ራስን መግዛት ከባድ እንዲሆንብህ ከሚያደርግ ማንኛውም ነገር ራቅ። ለምሳሌ፣ መጥፎ ነገሮችን ከሚያሳዩ የኢንተርኔት ድረ ገጾችና መዝናኛዎች ራቅ። (ኤፌ. 5:3, 4) እንዲያውም መጥፎ ነገር ለማድረግ እንድንፈተን ከሚያደርግ ማንኛውም ነገር መሸሽ ይኖርብናል። (ምሳሌ 22:3፤ 1 ቆሮ. 6:12) ለምሳሌ ያህል፣ የፆታ ርኩሰት ለመፈጸም የሚፈተን ሰው ከፍቅር መጻሕፍትና ፊልሞች ሙሉ በሙሉ መራቅ ሊያስፈልገው ይችላል።

እርግጥ ነው፣ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ሊያስቸግረን ይችላል። ሆኖም ጥረት ካደረግን ይሖዋ ራሳችንን ለመቆጣጠር የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል። (2 ጴጥ. 1:5-8) ይሖዋ ሐሳባችንን፣ ንግግራችንን እና ድርጊታችንን መቆጣጠር እንድንችል ይረዳናል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፖልና ማርኮ ለዚህ ማስረጃ ይሆናሉ፤ ሁለቱም የግልፍተኝነት ባሕርያቸውን ማሸነፍ ችለዋል። የሌላ ወንድምን ምሳሌም እንመልከት፤ ይህ ወንድም መኪና በሚያሽከረክርበት ወቅት ብዙ ጊዜ ቁጣውን መቆጣጠር ይከብደው ነበር፤ ይባስ ብሎም ከሌሎች ጋር ንትርክ ውስጥ ይገባ ነበር። ታዲያ ምን አደረገ? እንዲህ ብሏል፦ “በየቀኑ አጥብቄ እጸልይ ነበር። ራስን ስለ መግዛት የሚያወሱ ርዕሶችን አጠናሁ፤ እንዲሁም በዚህ ረገድ የሚረዱኝን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በቃሌ ያዝኩ። ራስን መግዛትን ለማዳበር ለዓመታት ጥረት ሳደርግ ብቆይም አሁንም ቁጣዬን መቆጣጠር እንዳለብኝ በእያንዳንዱ ቀን መጀመሪያ ላይ ራሴን ማስታወስ ያስፈልገኛል። ከዚህም ሌላ ቀጠሮ ሲኖረኝ እንዳልቻኮል ቀደም ብዬ እወጣለሁ።”

ራሳችንን መግዛት አቅቶን ስህተት ብንሠራ

አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን መግዛት ያቅተናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋን በጸሎት ማነጋገር ያሸማቅቀን ይሆናል። ይሁንና ጸሎት በተለይ የሚያስፈልገን በዚህ ወቅት ነው። ስለዚህ ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ እንጸልይ። ይቅር እንዲለን እንለምነው፤ የእሱን እርዳታ እንፈልግ እንዲሁም ስህተታችንን ላለመድገም ቆራጥ እንሁን። (መዝ. 51:9-11) ይሖዋ ምሕረት ለማግኘት የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት አይንቅም። (መዝ. 102:17) ሐዋርያው ዮሐንስ፣ የአምላክ ልጅ ደም “ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” ሲል ተናግሯል። (1 ዮሐ. 1:7፤ 2:1፤ መዝ. 86:5) ይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮቹን፣ የሌሎችን በደል በተደጋጋሚ ይቅር እንዲሉ እንደሚጠብቅባቸው እናስታውስ። ከዚህ አንጻር እሱም ለእኛ እንዲህ እንደሚያደርግልን መተማመን እንችላለን።—ማቴ. 18:21, 22፤ ቆላ. 3:13

እስራኤላውያን በምድረ በዳ እያሉ ሙሴ ቁጣውን መቆጣጠር ባልቻለበት ወቅት ይሖዋ አዝኖበት ነበር። ያም ቢሆን ይቅር ብሎታል። እንዲያውም የአምላክ ቃል ሙሴን የሚጠቅሰው አስደናቂ የእምነት ሰው እንደሆነ አድርጎ ነው። (ዘዳ. 34:10፤ ዕብ. 11:24-28) ይሖዋ ለሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ አልፈቀደለትም፤ ሆኖም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከሞት አስነስቶ የዘላለም ሕይወት ይሰጠዋል። እኛም አስፈላጊ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማዳበር ጥረት ማድረጋችንን የምንቀጥል ከሆነ ተመሳሳይ ሽልማት እናገኛለን።—1 ቆሮ. 9:25