የጥናት ርዕስ 26
“ወደ እኔ ተመለሱ”
“ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።”—ሚል. 3:7
መዝሙር 102 ‘ደካማ የሆኑትን እርዱ’
ማስተዋወቂያ *
1. ይሖዋ ከባዘኑ በጎቹ አንዱ ሲመለስ ምን ይሰማዋል?
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ፣ እያንዳንዱን በግ በደግነት ከሚንከባከብ ጥሩ እረኛ ጋር ራሱን አመሳስሏል። ከመንጋው መካከል አንድ በግ እንኳ ቢጠፋ በጉን ፈልጎ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። ይሖዋ እሱን ለተዉት እስራኤላውያን “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ብሏቸው ነበር። ይሖዋ “አልለወጥም” ስላለ አሁንም እንደዚሁ እንደሚሰማው እርግጠኞች ነን። (ሚል. 3:6, 7) ከባዘኑ በጎቹ መካከል አንዱም እንኳ ሲመለስ ይሖዋም ሆነ መላእክቱ ታላቅ ደስታ እንደሚሰማቸው ኢየሱስ ተናግሯል።—ሉቃስ 15:10, 32
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ከይሖዋ የራቁ ሰዎችን ስለ መርዳት የሚገልጹ ሦስት የኢየሱስ ምሳሌዎችን እንመረምራለን። የጠፉ በጎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት የሚያስፈልጉንን አንዳንድ ባሕርያትም እንመለከታለን። በተጨማሪም በመንፈሳዊ የደከሙትን ለመደገፍ የምናደርገው ጥረት የሚክስ ነው የምንልበትን ምክንያት እናያለን።
የጠፋውን ሳንቲም ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
3-4. በሉቃስ 15:8-10 ላይ የተጠቀሰችው ሴት የጠፋባትን ድራክማ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደረገችው ለምንድን ነው?
3 ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ ሰዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። በሉቃስ ወንጌል ላይ ተመዝግቦ በሚገኝ አንድ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ፣ አንዲት ሴት የጠፋባትን ውድ ነገር ይኸውም ድራክማ ሳንቲም ለማግኘት ስላደረገችው ፍለጋ ገልጿል። ምሳሌው በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው የጠፋውን ነገር ለማግኘት በተደረገው ፍለጋ ላይ ነው።—ሉቃስ 15:8-10ን አንብብ።
4 ኢየሱስ፣ ሴትየዋ የጠፋባትን ውድ ድራክማ ሳንቲም ስታገኝ ምን እንደተሰማት ገልጿል። በኢየሱስ ዘመን፣ አንዳንድ አይሁዳዊ እናቶች ልጃቸው ስታገባ በሠርጓ ቀን አሥር ድራክማ ሳንቲሞች የመስጠት ልማድ የነበራቸው
ይመስላል። ይህች ሴት የጠፋባት፣ በሠርጓ ቀን ከተሰጧት ሳንቲሞች አንዱ ሊሆን ይችላል። ሴትየዋ ሳንቲሙ ወለሉ ላይ እንደወደቀ ገምታ ነበር። ስለዚህ መብራት አብርታ ፈለገችው፤ ሆኖም ልታገኘው አልቻለችም። በዘይት የሚሠራው መብራቷ ደግሞ ትንሿን የብር ሳንቲም ለማግኘት የሚያስችል በቂ ብርሃን አልሰጣት ይሆናል። በመጨረሻም መላውን ቤት በደንብ አድርጋ ጠረገችው። ከዚያም ከጥራጊው መሃል፣ የመብራቱ ብርሃን ሲያርፍበት የሚያብረቀርቅ ነገር አየች፤ የሚያብረቀርቀው ነገር ውድ የሆነው ድራክማ ሳንቲሟ ነበር። ሴትየዋ ምንኛ ተደስታ ይሆን! የደስታዋ ተካፋይ እንዲሆኑ ጓደኞቿንና ጎረቤቶቿን ጠራች።5. ከጉባኤው የራቁ ሰዎችን ፈልገን ማግኘት ከባድ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
5 ከኢየሱስ ምሳሌ እንደምንመለከተው የጠፋን ነገር ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተመሳሳይም ከጉባኤ የራቁ ሰዎችን ፈልገን ለማግኘት ብዙ ጥረት ማድረግ ሊኖርብን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ከጉባኤው ከራቁ በርካታ ዓመታት አልፈው ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አሁን በሚኖሩበት አካባቢ ያሉት ወንድሞች አያውቋቸው ይሆናል። ያም ቢሆን ከእነዚህ የቀዘቀዙ ሰዎች አንዳንዶቹ ወደ ይሖዋ ለመመለስ እንደሚጓጉ ጥያቄ የለውም። ከእውነተኛ አገልጋዮቹ ጋር ሆነው ይሖዋን ማምለክ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
6. የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን ለማግኘት በሚደረገው ፍለጋ ሁሉም የጉባኤው አስፋፊዎች መካፈል የሚችሉት እንዴት ነው?
6 የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን በመፈለጉ ሥራ ማን መካፈል ይችላል? ሽማግሌዎች፣ አቅኚዎች፣ የቤተሰባቸው አባላት እንዲሁም የጉባኤ አስፋፊዎች በሌላ አባባል ሁላችንም እነዚህን ሰዎች በመፈለጉ ሥራ እርዳታ ማበርከት እንችላለን። የቀዘቀዘ ጓደኛ ወይም ዘመድ አለህ? ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ወይም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ስትካፈል የቀዘቀዘ ሰው አግኝተሃል? ግለሰቡ፣ ሽማግሌዎች መጥተው እንዲያነጋግሩት የሚፈልግ ከሆነ አድራሻውን በአካባቢው ላሉት የጉባኤ ሽማግሌዎች ልትሰጣቸው እንደምትችል ንገረው።
7. ቶማስ የተባለ ሽማግሌ ከሰጠው ሐሳብ ምን ትማራለህ?
7 ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ ሰዎችን ለማግኘት በተለይ ሽማግሌዎች ምን እርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ? በስፔን የሚኖር ቶማስ * የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ የሰጠውን ሐሳብ እንመልከት። ቶማስ ከ40 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ጉባኤው እንዲመለሱ ረድቷል። እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያ፣ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች የሚኖሩበትን ቦታ ያውቁ እንደሆነ የተለያዩ ወንድሞችንና እህቶችን እጠይቃለሁ። አሊያም ደግሞ ወደ ስብሰባዎች መምጣት ያቆመ የሚያውቁት ሰው ካለ እጠይቃቸዋለሁ። አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት በፍለጋው ሥራ መሳተፋቸው ስለሚያስደስታቸው በፈቃደኝነት ይተባበራሉ። የቀዘቀዙ ወንድሞችንና እህቶችን በምጎበኝበት ጊዜ ደግሞ ስለ ልጆቻቸውና ስለ ዘመዶቻቸው እጠይቃቸዋለሁ። አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ስብሰባ ይመጡ ነበር፤ ምናልባትም በአንድ ወቅት ልጆቻቸው አስፋፊዎች ነበሩ። በመሆኑም እነሱም ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።”
የጠፉትን የይሖዋ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንዲመለሱ እርዷቸው
8. በሉቃስ 15:17-24 ላይ በተጠቀሰው ስለጠፋው ልጅ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ አባትየው ንስሐ የገባውን ልጁን የያዘው እንዴት ነው?
8 ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉናል? ኢየሱስ ቤቱን ትቶ ስለሄደው አባካኝ ልጅ ከተናገረው ምሳሌ አንዳንድ ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 15:17-24ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ልጁ ከጊዜ በኋላ ወደ ልቦናው እንደተመለሰና ወደ ቤቱ ለመመለስ እንደወሰነ ተናግሯል። አባትየው ልጁን ሲያየው እየሮጠ ወደ እሱ በመሄድ አንገቱ ላይ ተጠመጠመ፤ በዚህ መንገድ እንደሚወደው አረጋገጠለት። ልጅየው ሕሊናው ረብሾት እንዲሁም አባቱ እንደ ልጁ ሊቆጥረው እንደማይገባ ተሰምቶት ነበር። ልጁ የልቡን አውጥቶ የተናገረ ሲሆን አባትየውም ስሜቱን ተረድቶለት ነበር። ከዚያም አባትየው ልጁ ወደ ቤት በመመለሱ ምን ያህል እንደተደሰተ ልጁ እንዲገነዘብ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ወሰደ፤ ልጁን እንደ ቅጥር ሠራተኛ ሳይሆን እንደ ውድ የቤተሰቡ አባል አድርጎ እንደተቀበለው ማሳየት ፈልጎ ነበር። በመሆኑም ድግስ ያዘጋጀ ከመሆኑም ሌላ ንስሐ የገባውን ልጁን ጥሩ ልብስ አለበሰው።
9. የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት የትኞቹን ባሕርያት ልናሳይ ይገባል? (“ መመለስ የሚፈልጉትን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
9 ይሖዋ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው አባት ነው። የቀዘቀዙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይወዳቸዋል፤ ወደ እሱ እንዲመለሱም ይፈልጋል። እኛም ይሖዋን በመምሰል ወደ ጉባኤው እንዲመለሱ ልንረዳቸው እንችላለን። ይህን ለማድረግ ትዕግሥተኛ መሆን፣ ስሜታቸውን መረዳት እንዲሁም ፍቅር ማሳየት ያስፈልገናል። እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
10. አንድን ሰው በመንፈሳዊ እንዲያገግም ለመርዳት ትዕግሥት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 የቀዘቀዘ ሰው በመንፈሳዊ ለማገገም ጊዜ ስለሚወስድበት ትዕግሥተኛ መሆን ይጠበቅብናል። ቀዝቅዘው የነበሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ወደ ጉባኤው መመለስ የቻሉት ሽማግሌዎችና ሌሎች የጉባኤው አስፋፊዎች በተደጋጋሚ ከረዷቸው በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትኖር ናንሲ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤ ውስጥ ያለች አንዲት የቅርብ ወዳጄ በጣም ረድታኛለች። እንደ ታላቅ እህቷ በማየት ፍቅር አሳይታኛለች። ከዚህ ቀደም ያሳለፍናቸውን አስደሳች ጊዜያት እንዳስታውስ ረዳችኝ። ስሜቴን አውጥቼ ስናገር በትዕግሥት ታዳምጠኝ ነበር፤ ምክር በሚያስፈልገኝ ጊዜ ደግሞ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትልም። እውነተኛ ወዳጅ ሆናልኛለች፤ በማንኛውም ጊዜ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ነበረች።”
11. በሌሎች የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ስሜታቸውን መረዳት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ያዕ. 1:19) ቀዝቅዛ የነበረች ማሪያ የተባለች እህት “የሚያዳምጠኝ፣ የሚያጽናናኝ፣ በደግነት የሚመክረኝና የሚረዳኝ ሰው ያስፈልገኝ ነበር” ብላለች።
11 ቁስልን እንደሚጠግን ቅባት ሁሉ የሌሎችን ስሜት መረዳትም የተጎዳ ልብን ይፈውሳል። አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች በጉባኤ ውስጥ ባለ ሰው ቅር ተሰኝተው ሊሆን ይችላል፤ ከዓመታት በኋላም ይህ ስሜት አልጠፋ ይሆናል። ይህም ወደ ይሖዋ እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ይሰማቸው ይሆናል። በመሆኑም የሚያዳምጣቸውና ስሜታቸውን የሚረዳላቸው ሰው ይፈልጋሉ። (12. ይሖዋ የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን በፍቅር እንደገና ወደ ሕዝቡ የሚስባቸው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
12 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ከገመድ ወይም ከማሰሪያ ጋር ያመሳስለዋል። የአምላክ ፍቅር ከገመድ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ውስጥ ላለመስመጥ እየታገልክ ሳለ አንድ ሰው የሚያንሳፍፍ ጃኬት ወረወረልህ። ጃኬቱ ለመንሳፈፍ የምታደርገውን ትግል ስለሚያቀልልህ ግለሰቡ ያደረገልህን እርዳታ እንደምታደንቅ ጥያቄ የለውም። ይሁንና ጃኬቱ ብቻውን ሕይወትህን ያተርፍልሃል ማለት አይደለም። ውኃው ቀዝቃዛ ነው፤ በመሆኑም ወደ ሕይወት አድን ጀልባ መድረስ ካልቻልክ በሕይወት አትተርፍም። ከጀልባው ላይ ሆኖ ገመድ የሚወረውርልህና ስቦ የሚያወጣህ ሰው ያስፈልግሃል። ይሖዋ ከእሱ ርቀው ስለነበሩ እስራኤላውያን ሲናገር ‘በፍቅር ማሰሪያ ሳብኳቸው’ ብሏል። (ሆሴዕ 11:4) በዛሬው ጊዜም አምላክ እሱን ማገልገላቸውን ያቆሙ እንዲሁም በተለያዩ ችግሮችና ጭንቀቶች የተዋጡ አገልጋዮቹን በተመለከተ እንዲህ ይሰማዋል። እንደሚወዳቸው እንዲገነዘቡ ይፈልጋል፤ እንዲሁም ወደ ራሱ ሊስባቸው ይፈልጋል። ደግሞም ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ በአንተ ሊጠቀም ይችላል።
13. ፍቅር ማሳየት ምን ያህል ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
13 ለቀዘቀዙ ሰዎች፣ ይሖዋም ሆነ እኛ እንደምንወዳቸው ማረጋገጣችን አስፈላጊ ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ፓብሎ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ቀዝቅዞ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቀን ጠዋት ላይ ከቤቴ እየወጣሁ ሳለ አንዲት ደስ የሚሉ አረጋዊት እህት አገኙኝ፤ ከዚያም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ አነጋገሩኝ። በዚህ ጊዜ እንደ ልጅ ማልቀስ ጀመርኩ። ወደ እኔ የላካቸው ይሖዋ እንደሆነ እንደተሰማኝ ነገርኳቸው። ወደ ይሖዋ ለመመለስ የወሰንኩት በዚያች ቅጽበት ነበር።”
የደከሙትን በፍቅር ደግፏቸው
14. በሉቃስ 15:4, 5 ላይ በሚገኘው ምሳሌ መሠረት እረኛው የጠፋችውን በግ ካገኛት በኋላ ምን አደረገ?
14 ለቀዘቀዙ አስፋፊዎች ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው የጠፋ ልጅ ሁሉ እነዚህ ሰዎችም ስሜታቸው በጣም ስለተጎዳ ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ከዚህም ሌላ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ባጋጠማቸው ነገር የተነሳ በመንፈሳዊ መዳከማቸው አይቀርም። ስለዚህ በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ መርዳት ያስፈልገናል። ስለጠፋችው በግ በሚናገረው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ፣ እረኛው በጓን በጫንቃው ላይ ተሸክሞ ወደ መንጋው እንደሚወስዳት ገልጿል። እረኛው የጠፋችውን በግ ፈልጎ ለማግኘት ብዙ ጊዜና ጥረት እንደጠየቀበት የታወቀ ነው። ካገኛትም በኋላ ግን በጓን ተሸክሞ ወደ መንጋው መውሰድ እንደሚያስፈልገው ይገነዘባል፤ ምክንያቱም በጓ ወደ መንጋው ለመመለስ አቅም አይኖራትም።—ሉቃስ 15:4, 5ን አንብብ።
15. ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ በመንፈሳዊ የደከሙ ሰዎችን መደገፍ የምንችለው እንዴት ነው? (“ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
15 አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ያሉባቸውን ድክመቶች እንዲያሸንፉ ለመርዳት ብዙ ጊዜና ጥረት ሊጠይቅብን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ መንፈስ፣ ቃሉ እንዲሁም በጉባኤው አማካኝነት የምናገኛቸው ጽሑፎች በሚሰጡን ሮም 15:1) እንዴት? ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ “አብዛኞቹ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ወደ ይሖዋ ለመመለስ ከወሰኑ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል” ብሏል። * ታዲያ አንድን የቀዘቀዘ ሰው እንድታስጠና ብትጠየቅ የተሰጠህን መብት በደስታ ትቀበላለህ? ሽማግሌው አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ጥናቱን እንዲመራ የተመደበው አስፋፊ፣ የቀዘቀዘው ሰው የልቡን አውጥቶ ለመናገር ነፃነት እንዲሰማው የሚያደርግ ጥሩ ወዳጅ ሊሆንለት ይገባል።”
እርዳታ ተጠቅመን በመንፈሳዊ እንዲያገግሙ ልናግዛቸው እንችላለን። (በሰማይም ሆነ በምድር ደስታ ይሆናል
16. መላእክት እንደሚረዱን እንዴት እናውቃለን?
16 ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ የቀዘቀዙ ሰዎችን ማግኘት እንድንችል መላእክት ይረዱናል። (ራእይ 14:6) በኢኳዶር የሚኖረውን የሲልቭዮን ምሳሌ እንመልከት፤ ሲልቭዮ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ መመለስ እንዲችል አጥብቆ ጸልዮ ነበር። ሲልቭዮ እየጸለየ ሳለ የበሩ ደወል ተደወለ። በሩ ላይ ሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር። እነዚህ ሽማግሌዎች ሲልቭዮ የሚያስፈልገውን እርዳታ ወዲያውኑ መስጠት ጀመሩ።
17. በመንፈሳዊ የደከሙ ሰዎችን ስንረዳ ምን ወሮታ እናገኛለን?
17 በመንፈሳዊ የደከሙ ሰዎችን ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ስንረዳ ታላቅ ደስታ እናገኛለን። ለቀዘቀዙ ሰዎች ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሳልቫዶር የተባለ አቅኚ የተናገረውን ልብ በል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከደስታዬ የተነሳ እንባዬን መቆጣጠር ያቅተኛል። ይሖዋ ውድ ከሆኑት በጎቹ አንዱን ከሰይጣን ዓለም እንደታደገውና እኔም በዚህ ሥራ ከእሱ ጋር የመተባበር መብት እንዳገኘሁ ሳስብ በጣም እደሰታለሁ።”—ሥራ 20:35
18. የቀዘቀዝክ አስፋፊ ከሆንክ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
18 አንተም ከይሖዋ ሕዝቦች ርቀህ ከሆነ ይሖዋ አሁንም እንደሚወድህ እርግጠኛ ሁን። ወደ እሱ እንድትመለስ ይፈልጋል። በእርግጥ ወደ እሱ ለመመለስ ልትወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ። ሆኖም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው አባት ሁሉ ይሖዋም የምትመለስበትን ጊዜ እየተጠባበቀ ነው፤ ወደ ቤቱ ስትመለስም እጁን ዘርግቶ በደስታ ይቀበልሃል።
መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች
^ አን.5 ይሖዋ ከጉባኤው የራቁ አገልጋዮቹ ወደ እሱ እንዲመለሱ ይፈልጋል። “ወደ እኔ ተመለሱ” በማለት ያቀረበውን ግብዣ መቀበል የሚፈልጉ ሰዎችን ለማበረታታት ማድረግ የምንችለው ብዙ ነገር አለ። ይህ ርዕስ እነዚህን ሰዎች መርዳት የምንችልበትን መንገድ ያብራራል።
^ አን.7 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.15 አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን ለመርዳት ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ የተባለውን መጽሐፍ የተወሰኑ ምዕራፎች ማስጠናት ይቻላል፤ ሌሎች ደግሞ ወደ ይሖዋ ቅረብ ከሚለው መጽሐፍ ላይ አንዳንድ ምዕራፎችን ከአስጠኚያቸው ጋር ቢከልሱ ይጠቀሙ ይሆናል። እንዲህ ያለውን ጥናት ማን ቢመራ የተሻለ እንደሚሆን የሚወስነው የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ነው።
^ አን.68 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሦስት ወንድሞች፣ ወደ ጉባኤ መመለስ የሚፈልግን አንድ ወንድም እየረዱት ነው። ይህን የሚያደርጉት እሱን አዘውትረው በመጠየቅ፣ እንደሚወዱት በማሳየት እንዲሁም ስሜቱን እንደሚረዱለት በሚያሳይ መንገድ በማዳመጥ ነው።