የጥናት ርዕስ 25
ሽማግሌዎች—ከጌድዮን ምሳሌ ተማሩ
“ስለ ጌድዮን . . . እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል።”—ዕብ. 11:32
መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን
ማስተዋወቂያ a
1. በ1 ጴጥሮስ 5:2 መሠረት ሽማግሌዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው?
ክርስቲያን ሽማግሌዎች የይሖዋን ውድ በጎች እንዲንከባከቡ አደራ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ታታሪ ወንዶች፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። እንዲሁም መንጋውን ‘በሚገባ የሚጠብቁ እረኞች’ ለመሆን ተግተው ይሠራሉ። (ኤር. 23:4፤ 1 ጴጥሮስ 5:2ን አንብብ።) በጉባኤዎቻችን ውስጥ እንዲህ ያሉ ወንዶች በመኖራቸው ምንኛ አመስጋኞች ነን!
2. አንዳንድ ሽማግሌዎች የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?
2 ሽማግሌዎች ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ወቅት በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጉባኤውን መንከባከብ ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ቶኒ፣ ከሚቀበለው ሥራ ጋር በተያያዘ ይበልጥ ልኩን ማወቅ እንዳለበት ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል፦ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጀመረበት ወቅት ስብሰባዎችንና የአገልግሎት እንቅስቃሴዎችን ከማደራጀት ጋር የተያያዙ ብዙ ሥራዎችን ተቀበልኩ። ሥራዬን ለማከናወን ምንም ያህል ጥረት ባደርግ ሥራው ሊያልቅ አልቻለም። ውሎ አድሮ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ ለግል ጥናትና ለጸሎት የማውለው ጊዜ ማጣት ጀመርኩ።” በኮሶቮ የሚኖር ኢሊር የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ደግሞ የተለየ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል። በአካባቢው ጦርነት በተከሰተበት ወቅት ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን መከተል ከባድ ሆኖበት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ቅርንጫፍ ቢሮው በአደገኛ አካባቢ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን እንድረዳ ኃላፊነት ሲሰጠኝ ድፍረት ማሳየት ከብዶኝ ነበር። ፈርቼ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የተሰጠኝ መመሪያ ምክንያታዊ እንደሆነ አልተሰማኝም።” ቲም የተባለ በእስያ የሚኖር ሚስዮናዊ የዕለት ተዕለት ኃላፊነቶቹን መወጣት በራሱ ከባድ ሆኖበት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ አእምሮዬ ይዝል፣ ጉልበቴም ይሟጠጥ ነበር።” ታዲያ እንዲህ ካሉ ፈተናዎች ጋር የሚታገሉ ሽማግሌዎችን ምን ሊረዳቸው ይችላል?
3. መስፍኑ ጌድዮን የተወውን ምሳሌ መመርመራችን ሁላችንንም የሚጠቅመን እንዴት ነው?
3 ሽማግሌዎች መስፍኑ ጌድዮን ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ዕብ. 6:12፤ 11:32) ጌድዮን የአምላክን ሕዝቦች የታደጋቸው ከመሆኑም ሌላ እረኛ ሆኖላቸው ነበር። (መሳ. 2:16፤ 1 ዜና 17:6) እንደ ጌድዮን ሁሉ፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎችም በጣም አስቸጋሪ በሆነ ዘመን ውስጥ የአምላክን ሕዝቦች የመንከባከብ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ሥራ 20:28፤ 2 ጢሞ. 3:1) ጌድዮን ልክን በማወቅ፣ በትሕትናና በታዛዥነት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ኃላፊነቱን በተወጣበት ወቅት ጽናቱ ተፈትኖ ነበር። ሽማግሌዎች ሆንንም አልሆንን ሁላችንም ለሽማግሌዎች ያለንን አድናቆት ማሳደግ እንችላለን። ታታሪ የሆኑትን እነዚህን መንፈሳዊ ወንዶች ልንደግፋቸው እንችላለን።—ዕብ. 13:17
ልክን በማወቅና በትሕትና ረገድ ፈተና ሲገጥማችሁ
4. ጌድዮን ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
4 ጌድዮን ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። b የይሖዋ መልአክ፣ እስራኤላውያንን ኃያል ከሆኑት ምድያማውያን እንዲታደግ እንደተመረጠ ለጌድዮን ሲነግረው ይህ ትሑት ሰው እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቷል፦ “የእኔ ጎሳ እንደሆነ ከምናሴ ነገድ የመጨረሻው ነው፤ እኔም ብሆን በአባቴ ቤት ውስጥ እዚህ ግባ የምባል አይደለሁም።” (መሳ. 6:15) ጌድዮን ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንደሆነ አልተሰማውም፤ የይሖዋ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነበር። በይሖዋ እርዳታ ጌድዮን የተሰጠውን ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ መወጣት ችሏል።
5. ሽማግሌዎች በትሕትናና ልክን በማወቅ ረገድ ፈተና ሊገጥማቸው የሚችለው እንዴት ነው?
5 ሽማግሌዎች በሁሉም ነገር ትሕትናና ልክን ማወቅ ለማንጸባረቅ ጥረት ያደርጋሉ። (ሚክ. 6:8፤ ሥራ 20:18, 19) ችሎታቸውንና ያገኙትን ስኬት በተመለከተ ጉራ አይነዙም፤ በአንጻሩ ደግሞ በድክመታቸው ወይም በስህተታቸው ምክንያት ተስፋ አይቆርጡም። ያም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች በትሕትናና ልክን በማወቅ ረገድ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። ለምሳሌ በርካታ ኃላፊነቶችን ከተቀበሉ በኋላ ኃላፊነቶቻቸውን በሙሉ መወጣት ሊከብዳቸው ይችላል። ወይም አንዱን ኃላፊነታቸውን በተወጡበት መንገድ የተነሳ ትችት ሊሰነዘርባቸው፣ ከሌላው ኃላፊነታቸው ጋር በተያያዘ ደግሞ ሊመሰገኑ ይችላሉ። ታዲያ ከጌድዮን ምሳሌ የሚያገኙት ትምህርት እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ለመወጣት የሚረዳቸው እንዴት ነው?
6. ሽማግሌዎች ልክን ማወቅን በተመለከተ ከጌድዮን ምን ትምህርት ያገኛሉ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 እርዳታ ጠይቁ። ልኩን የሚያውቅ ሰው የአቅም ገደብ እንዳለበት ይገነዘባል። ጌድዮን የሌሎችን እርዳታ በመጠየቅ ልኩን እንደሚያውቅ አሳይቷል። (መሳ. 6:27, 35፤ 7:24) ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቶኒ እንዲህ ብሏል፦ “በአስተዳደጌ የተነሳ ከምችለው በላይ ብዙ ሥራ የመቀበል ዝንባሌ ነበረኝ። በመሆኑም በቤተሰብ አምልኳችን ላይ ልክን ስለማወቅ እንድናጠና ዝግጅት አደረግኩ። ባለቤቴንም በዚህ ረገድ ሐሳብ እንድትሰጠኝ ጠየቅኳት። በተጨማሪም jw.org ላይ የሚገኘውን እንደ ኢየሱስ ሌሎችን አሠልጥኑ፣ ተማመኑባቸው እንዲሁም ኃላፊነት ስጧቸው የሚለውን ቪዲዮ ተመለከትኩ።” ቶኒ ሌሎች እንዲያግዙት መጠየቅ ጀመረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ቶኒ እንዲህ ብሏል፦ “የጉባኤው ሥራ በሚገባ እየተከናወነ ነው። እኔ ደግሞ መንፈሳዊነቴን ለመንከባከብ የሚያስችል ጊዜ አግኝቻለሁ።”
7. ሽማግሌዎች ትችት ሲሰነዘርባቸው የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ያዕቆብ 3:13)
7 ትችት ከተሰነዘረባችሁ በገርነት ምላሽ ስጡ። ሽማግሌዎች ትችት በሚሰነዘርባቸው ጊዜም ትሕትናቸው ሊፈተን ይችላል። በዚህ ረገድም ቢሆን የጌድዮን ምሳሌ ሊረዳቸው ይችላል። ጌድዮን ፍጹም አለመሆኑን ስለሚያውቅ ኤፍሬማውያን ትችት በሰነዘሩበት ወቅት በገርነት ምላሽ ሰጥቷል። (መሳ. 8:1-3) መልስ የሰጠው በቁጣ አልነበረም። ስሜታቸውን ሲገልጹ በማዳመጥ ትሕትና አሳይቷል፤ እንዲሁም ውጥረት የሰፈነበትን ሁኔታ በዘዴ አርግቧል። ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎችም ትችት ሲሰነዘርባቸው በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም በገርነት ምላሽ በመስጠት የጌድዮንን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ያዕቆብ 3:13ን አንብብ።) በዚህ መንገድ ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
8. ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በሚመሰገኑበት ወቅት ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለባቸው? ምሳሌ ስጥ።
8 ይሖዋ እንዲወደስ አድርጉ። ጌድዮን ምድያማውያንን ድል በማድረጉ የተነሳ ክብር ሲሰጠው የሰዎቹ ትኩረት ወደ ይሖዋ እንዲዞር አድርጓል። (መሳ. 8:22, 23) ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ላከናወኑት ሥራ ይሖዋ እንዲመሰገን ማድረግ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 4:6, 7) ለምሳሌ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የማስተማር ችሎታውን በተመለከተ ቢመሰገን የሰዎቹን ትኩረት የትምህርቱ ምንጭ ወደሆነው ወደ አምላክ ቃል ወይም ከይሖዋ ድርጅት ወደምናገኘው ሥልጠና ማዞር ይችላል። ሽማግሌዎች ‘ወደ ራሴ አላስፈላጊ ትኩረት እየሳብኩ ነው?’ ብለው አልፎ አልፎ ራሳቸውን መመርመራቸው ጠቃሚ ነው። እስቲ የቲሞቲን ምሳሌ እንመልከት። ቲሞቲ ሽማግሌ ሆኖ በተሾመበት ወቅት የሕዝብ ንግግር ማቅረብ ይወድ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የተራቀቁ መግቢያዎችና ምሳሌዎች እጠቀም ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙዎች ያመሰግኑኛል። የሚያሳዝነው፣ የሰዎቹ ትኩረት የሚያርፈው በይሖዋ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን በእኔ ላይ ነበር።” ውሎ አድሮ ቲሞቲ ወደ ራሱ አላስፈላጊ ትኩረት ላለመሳብ ሲል የማስተማሪያ ዘዴውን መቀየር እንዳለበት ተገነዘበ። (ምሳሌ 27:21) ውጤቱስ ምን ሆነ? እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች ንግግሬ አንድን ችግር ለመወጣት፣ ያጋጠማቸውን ፈተና በጽናት ለመቋቋም ወይም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ እንደረዳቸው ይነግሩኛል። እነዚህን ሐሳቦች ስሰማ የሚሰማኝ ደስታ ከዓመታት በፊት ሰዎች ሲያወድሱኝ ይሰማኝ ከነበረው ደስታ በእጅጉ የላቀ ነው።”
በታዛዥነት ወይም በድፍረት ረገድ ፈተና ሲገጥማችሁ
9. የጌድዮን ታዛዥነትና ድፍረት የተፈተነው እንዴት ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
9 ጌድዮን መስፍን ሆኖ ከተሾመ በኋላ ታዛዥነቱና ድፍረቱ ተፈትኖ ነበር። የአባቱን የባአል መሠዊያ የማፈራረስ አደገኛ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። (መሳ. 6:25, 26) ሠራዊቱን ካሰባሰበ በኋላም የሠራዊቱን ቁጥር እንዲቀንስ ሁለት ጊዜ ታዟል። (መሳ. 7:2-7) በመጨረሻም፣ በውድቅት ሌሊት በጠላት ሰፈር ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ተነግሮታል።—መሳ. 7:9-11
10. ሽማግሌዎች ታዛዥነታቸው ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው?
10 ሽማግሌዎች “ለመታዘዝ ዝግጁ” መሆን አለባቸው። (ያዕ. 3:17) ታዛዥ የሆነ ሽማግሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትንና ከይሖዋ ድርጅት የሚሰጡትን መመሪያዎች ቶሎ ብሎ በሥራ ላይ ያውላል። በዚህ መንገድ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ያም ቢሆን ታዛዥነቱ ሊፈተን ይችላል። ለምሳሌ የሚሰጡትን መመሪያዎች ተከታትሎ ተግባራዊ ማድረግ ሊከብደው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የተሰጠው መመሪያ ምክንያታዊ ወይም የሚያስኬድ መሆኑን ሊጠራጠር ይችላል። ወይም ነፃነቱን አደጋ ላይ የሚጥል ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል። ታዲያ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የጌድዮንን ታዛዥነት መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?
11. ሽማግሌዎች ታዛዥ እንዲሆኑ የሚረዳቸው ምንድን ነው?
11 የሚሰጣችሁን መመሪያ በጥሞና አዳምጡ፤ እንዲሁም በሥራ ላይ አውሉ። ጌድዮን የአባቱን መሠዊያ የሚያፈራርሰው እንዴት እንደሆነ፣ ለይሖዋ አዲስ መሠዊያ የሚገነባው የት እንደሆነ እንዲሁም የትኛውን እንስሳ መሥዋዕት ማድረግ እንዳለበት አምላክ ነግሮታል። ጌድዮን በተሰጠው መመሪያ ላይ ጥያቄ አላነሳም፤ ያለማንገራገር ታዟል። በዛሬው ጊዜ ሽማግሌዎች ከመንፈሳዊና ከአካላዊ ደህንነታችን ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ከይሖዋ ድርጅት በሚላኩ ደብዳቤዎችና ማስታወቂያዎች አማካኝነት ያገኛሉ። ሽማግሌዎች የሚሰጣቸውን ቲኦክራሲያዊ መመሪያ በታማኝነት ስለሚከተሉ እንወዳቸዋለን። እንዲህ በማድረጋቸው መላው ጉባኤ ይጠቀማል።—መዝ. 119:112
12. በቲኦክራሲያዊ አሠራሮች ላይ ለውጥ ሲደረግ ሽማግሌዎች ዕብራውያን 13:17ን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
12 ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ሁኑ። ጌድዮን የይሖዋን ትእዛዝ ተከትሎ ሠራዊቱን ከ99 በመቶ በላይ ለመቀነስ ፈቃደኛ እንደሆነ አስታውሱ። (መሳ. 7:8) ጌድዮን ‘ይሄ ለውጥ በእርግጥ አስፈላጊ ነው? ደግሞስ ያስኬዳል?’ በማለት አስቦ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጌድዮን ታዟል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም የይሖዋ ድርጅት በቲኦክራሲያዊ አሠራሮች ላይ ለውጥ ሲያደርግ ለውጡን ተግባራዊ በማድረግ የጌድዮንን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።) ለምሳሌ በ2014 የበላይ አካሉ የጉባኤና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች ወጪ ከሚሸፈንበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ አድርጓል። (2 ቆሮ. 8:12-14) ከዚያ በፊት ጉባኤዎች አዳራሽ ለመሥራት የሚሰጣቸውን ብድር መልሰው መክፈል ይጠበቅባቸው ነበር። አሁን ግን በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎች የሚያደርጉት መዋጮ ተሰባስቦ ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን በሚያስፈልጉበት ቦታ ሁሉ ለመገንባት ይውላል። አንድ ጉባኤ ገንዘቡን የመክፈል አቅም ባይኖረውም እንኳ አዳራሽ ይሠራለታል ማለት ነው። ሆዜ ይህ ለውጥ መደረጉን ሲሰማ ይህ አሠራር የሚያስኬድ መሆኑን ተጠራጥሮ ነበር። ‘በዚህ ዓይነትማ አንድም የስብሰባ አዳራሽ አይገነባም። በእኛ አገር ይህ የሚያዋጣ አካሄድ አይደለም’ ብሎ አሰበ። ታዲያ ሆዜ መመሪያውን እንዲደግፍ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በምሳሌ 3:5, 6 ላይ ያለው ሐሳብ በይሖዋ መታመን እንዳለብኝ አስታወሰኝ። ይህ አሠራር ያስገኘው ውጤትም በጣም አስደናቂ ነው። ከበፊቱ በበለጠ መጠን የስብሰባ አዳራሾችን እየገነባን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የአንዱ ትርፍ የሌላውን ጉድለት እንዲሸፍን በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተምረናል።”
13. (ሀ) ጌድዮን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር? (ለ) ሽማግሌዎች የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 በድፍረት የይሖዋን ፈቃድ አድርጉ። ጌድዮን ፍርሃት ቢሰማውም እንዲሁም የተሰጠው ኃላፊነት አደገኛ ቢሆንም ይሖዋን ታዟል። (መሳ. 9:17) ጌድዮን፣ ይሖዋ ዋስትና ከሰጠው በኋላ የአምላክን ሕዝቦች በሚታደግበት ወቅት እሱ እንደሚረዳው እርግጠኛ ሆነ። ሥራችን በታገደበት አካባቢ የሚኖሩ ሽማግሌዎች የጌድዮንን ምሳሌ ይከተላሉ። ሊታሰሩ፣ የወንጀል ምርመራ ሊደረግባቸው፣ ሥራቸውን ሊያጡ ወይም እንግልት ሊደርስባቸው እንደሚችል ቢያውቁም በስብሰባዎችና በአገልግሎት ላይ ግንባር ቀደም ሆነው በመካፈል ድፍረት ያሳያሉ። c በታላቁ መከራ ወቅት ሽማግሌዎች የሚሰጣቸው መመሪያ አደጋ ሊያስከትልባቸው የሚችል ቢሆንም እንኳ መመሪያውን ለመታዘዝ ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። መመሪያው በበረዶ ድንጋይ የተመሰለውን መልእክት ከማወጅ ወይም ከማጎጉ ጎግ ጥቃት መትረፍ ከሚቻልበት መንገድ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።—ሕዝ. 38:18፤ ራእይ 16:21
በጽናት ረገድ ፈተና ሲገጥማችሁ
14. የጌድዮን ጽናት የተፈተነው እንዴት ነው?
14 ጌድዮን መስፍን ሆኖ ባገለገለበት ወቅት በጣም አድካሚ የሆኑ ሥራዎችን አከናውኗል። በሌሊት ከተካሄደው ውጊያ በኋላ ምድያማውያን ሲሸሹ ጌድዮን ከኢይዝራኤል ሸለቆ አንስቶ እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ አሳደዳቸው፤ በወቅቱ ዮርዳኖስ ወንዝ በቁጥቋጦዎች የተሞላ ሳይሆን አይቀርም። (መሳ. 7:22) ታዲያ ጌድዮን ዮርዳኖስ ወንዝ ከደረሰ በኋላ ጠላቶቹን ማሳደዱን አቆመ? በፍጹም። እሱና 300ዎቹ ሰዎች ቢደክማቸውም እንኳ ዮርዳኖስን ተሻግረው ጠላቶቻቸውን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም ምድያማውያን ላይ ደረሱባቸውና ድል አደረጓቸው።—መሳ. 8:4-12
15. ሽማግሌዎች ጽናታቸው ሊፈተን የሚችለው መቼ ነው?
15 ሽማግሌዎች ጉባኤያቸውንና ቤተሰባቸውን በሚንከባከቡበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ በአካል፣ በአእምሮም ሆነ በስሜት ሊዝሉ ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
16-17. ጌድዮን እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? ሽማግሌዎችስ ስለ ምን ጉዳይ መተማመን ይችላሉ? (ኢሳይያስ 40:28-31) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 ይሖዋ ብርታት እንደሚሰጣችሁ ተማመኑ። ጌድዮን፣ ይሖዋ ብርታት እንደሚሰጠው ተማምኖ ነበር፤ ይሖዋም አላሳፈረውም። (መሳ. 6:14, 34) በአንድ ወቅት ጌድዮንና ወታደሮቹ ሁለት ምድያማውያን ነገሥታትን በእግራቸው ሲያሳድዱ ነበር፤ በወቅቱ ነገሥታቱ ግመል እየጋለቡ ሳይሆን አይቀርም። (መሳ. 8:12, 21) ሆኖም ቆራጦቹ እስራኤላውያን በአምላክ እርዳታ ማሸነፍ ችለዋል። ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ‘ፈጽሞ በማይደክመው ወይም በማይዝለው’ በይሖዋ መታመን ይችላሉ። እሱ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ብርታት ይሰጣቸዋል።—ኢሳይያስ 40:28-31ን አንብብ።
17 በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለውን የማቲውን ተሞክሮ እንመልከት። ማቲው እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “የፊልጵስዩስ 4:13ን እውነተኝነት በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። ብዙ ጊዜ ሲደክመኝና አቅሜ ሙሉ በሙሉ እንደተሟጠጠ ሲሰማኝ አምላክ ወንድሞቼን ለመደገፍ የሚያስችል አካላዊና አእምሯዊ ጥንካሬ እንዲሰጠኝ አጥብቄ እጸልያለሁ። በዚህ ወቅት የይሖዋ መንፈስ ብርታት ይሰጠኛል፤ እንዲሁም ለመጽናት ይረዳኛል።” ታታሪ የሆኑት ሽማግሌዎቻችን መንጋውን ለመንከባከብ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ ሲሠሩ ልክ እንደ ጌድዮን እንቅፋቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ በአካላዊም ሆነ በስሜታዊ ሁኔታ የአቅም ገደብ እንዳለባቸው መገንዘብና ከአቅማቸው በላይ ላለመሥራት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ያም ቢሆን ይሖዋ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ልመና እንደሚሰማና ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጣቸው መተማመን ይችላሉ።—መዝ. 116:1፤ ፊልጵ. 2:13
18. ሽማግሌዎች የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
18 ሽማግሌዎች ከጌድዮን ምሳሌ በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት ይችላሉ። ከሚቀበሉት የሥራ መጠን እንዲሁም ትችት ሲሰነዘርባቸው ወይም ምስጋና ሲቸራቸው ከሚሰጡት ምላሽ ጋር በተያያዘ ትሑት እንደሆኑና ልካቸውን እንደሚያውቁ ማሳየት ይኖርባቸዋል። በተለይ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረበ ሲመጣ ታዛዥነትና ድፍረት ማሳየት አለባቸው። በተጨማሪም ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥማቸው ይሖዋ ብርታት እንደሚሰጣቸው መተማመን ይኖርባቸዋል። በእርግጥም ታታሪ የሆኑትን እረኞቻችንን ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን፤ እንዲሁም ‘እንዲህ ያሉትን ሰዎች በአክብሮት እንይዛቸዋለን።’—ፊልጵ. 2:29
መዝሙር 120 እንደ ክርስቶስ ገር መሆን
a በእስራኤል ብሔር ታሪክ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በነበረው ዘመን ይሖዋ ለሕዝቦቹ እረኛ እንዲሆንና እንዲታደጋቸው ጌድዮንን ሾሞት ነበር። ጌድዮን ለ40 ዓመት ያህል ይህን ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል። ይሁንና በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው የጌድዮን ምሳሌ የሚረዳቸው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።