በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ አገልግሎት ያገኘኋቸው ያልተጠበቁ በረከቶችና ትምህርቶች

በይሖዋ አገልግሎት ያገኘኋቸው ያልተጠበቁ በረከቶችና ትምህርቶች

ልጅ ሳለሁ አውሮፕላን ሰማይ ላይ ሲበር ባየሁ ቁጥር ወደ ሌላ አገር ለመጓዝ እመኝ ነበር። እርግጥ ይህ ሕልሜ ሊሳካ ይችላል ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም።

ወላጆቼ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከኢስቶኒያ ወደ ጀርመን ተዛወሩ፤ እኔም የተወለድኩት እዚያው ነው። በዚያ ጊዜ አካባቢ ወደ ካናዳ ለመዛወር ዝግጅት እያደረጉ ነበር። ልክ ካናዳ እንደሄድን የምንኖረው በኦታዋ አቅራቢያ በሚገኝ የዶሮ እርባታ የሚካሄድበት አሮጌ ሕንፃ ውስጥ ነበር። በጣም ድሆች የነበርን ቢሆንም ቢያንስ ቁርሳችንን እንቁላል እንበላ ነበር።

አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ራእይ 21:3, 4⁠ን ለእናቴ አነበቡላት። በተማረችው ነገር ልቧ በጥልቅ ስለተነካ ማልቀስ ጀመረች። የእውነት ዘር ማደጉን ቀጠለ። ብዙም ሳይቆይ እናቴና አባቴ እድገት አድርገው ተጠመቁ።

ወላጆቼ የእንግሊዝኛ ችሎታቸው ውስን ቢሆንም ለእውነት ከፍተኛ ቅንዓት ነበራቸው። በየሳምንቱ ማለት ይቻላል አባቴ ሳድበሪ፣ ኦንታሪዮ ውስጥ በሚገኝ ኒኬል ማቅለጫ ፋብሪካ ውስጥ ሌሊቱን ሙሉ ከሠራ በኋላ ቅዳሜ እኔንና ታናሽ እህቴን ሲልቪያን ይዞን አገልግሎት ይወጣ ነበር። በተጨማሪም በየሳምንቱ በቤተሰብ ደረጃ መጠበቂያ ግንብ እናጠና ነበር። እማዬና አባዬ ለአምላክ ፍቅር እንዲያድርብኝ ረድተውኛል። ይህም በ1956 በአሥር ዓመቴ ራሴን ለይሖዋ ወስኜ እንድጠመቅ አነሳሳኝ። ለይሖዋ የነበራቸው ጥልቅ ፍቅር በመላው ሕይወቴ ብርታት ሆኖልኛል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ትኩረቴ መከፋፈል ጀመረ። አቅኚ ከሆንኩ በአውሮፕላን ዓለምን የመዞር ሕልሜን ለማሳካት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ላጠራቅም እንደማልችል ተሰማኝ። በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ዲጄ ሆኜ ተቀጠርኩ፤ ሥራዬን እወደው ነበር። ግን የምሠራው ማታ ማታ ስለነበር ከስብሰባዎች በተደጋጋሚ እቀራለሁ። በዚያ ላይ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው ለአምላክ ፍቅር ከሌላቸው ሰዎች ጋር ነው። በመጨረሻም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናዬ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ።

ወደ ኦሾዋ፣ ኦንታሪዮ ተዛወርኩ። በዚያም ከሬይ ኖርማንና ከእህቱ ከሌስሊ እንዲሁም ከሌሎች አቅኚዎች ጋር ተዋወቅኩ። ሁሉም ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ። ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ስመለከት ግቤን መለስ ብዬ ለማጤን ተነሳሳሁ። አቅኚነት እንድጀምር አበረታቱኝ። ስለዚህ መስከረም 1966 አቅኚ ሆንኩ። በሕይወቴ ደስተኛ ነበርኩ። ሆኖም ሕይወቴን የሚቀይሩ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች አጋጠሙኝ።

ይሖዋ አንድ ነገር እንድታደርጉ ከጋበዛችሁ ግብዣውን ተቀበሉ

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በቶሮንቶ፣ ካናዳ በሚገኘው ቤቴል ለማገልገል አመልክቼ ነበር። ከጊዜ በኋላ በአቅኚነት እያገለገልኩ ሳለሁ ለአራት ዓመታት በቤቴል እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ግን ሌስሊን በጣም ስለምወዳት ይህን ግብዣ ከተቀበልኩ ከእሷ ጋር ድጋሚ መገናኘት እንደማልችል ተሰማኝ። ለረጅም ሰዓት አጥብቄ ከጸለይኩ በኋላ ግብዣውን ለመቀበል ወሰንኩ። እያዘንኩ ከሌስሊ ጋር ተሰነባበትኩ።

ቤቴል ውስጥ በመጀመሪያ በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍል፣ በኋላም በጸሐፊነት ሠርቻለሁ። ሌስሊ ደግሞ ልዩ አቅኚ ሆና በጋተኖ፣ ኩዊቤክ ማገልገል ጀመረች። ስለ እሷ ብዙ ጊዜ አስብ ነበር፤ ‘በእርግጥ ውሳኔዬ ትክክል ነበር?’ የሚለው ጉዳይም ያሳስበኛል። ከዚያም ጨርሶ ያልጠበቅኩት ሁኔታ ተፈጠረ። የሌስሊ ወንድም የሆነው ሬይ በቤቴል እንዲያገለግል ተጋበዘ። ከእሱ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ መኖር ጀመርን። በዚህ መንገድ ከሌስሊ ጋር ድጋሚ መገናኘት ቻልኩ። የአራት ዓመት የቤቴል አገልግሎቴ በሚያበቃበት ቀን ማለትም የካቲት 27, 1971 ተጋባን።

በ1975 የወረዳ ሥራ በጀመርንበት ወቅት

እኔና ሌስሊ ኩዊቤክ ውስጥ በሚገኝ የፈረንሳይኛ ጉባኤ እንድናገለግል ተመደብን። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በ28 ዓመቴ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ስጋበዝ በጣም ተገረምኩ። ገና ወጣት ስለሆንኩ ብቃት እንደሌለኝ ተሰምቶኝ ነበር። ግን በኤርምያስ 1:7, 8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አበረታታኝ። ሆኖም ሌስሊ በተደጋጋሚ የመኪና አደጋ አጋጥሟት ያውቃል፤ እንቅልፍም ትቸገራለች። ‘ታዲያ በወረዳ ሥራ መካፈል የምንችለው እንዴት ነው?’ ብለን አሰብን። እሷ ግን “ይሖዋ አንድ ነገር እንድናደርግ ከጋበዘን ግብዣውን መቀበል አይኖርብንም?” አለችኝ። ስለዚህ ግብዣውን ተቀበልን። ለ17 ዓመታት በወረዳ ሥራ በደስታ አገልግለናል።

የወረዳ የበላይ ተመልካች ሳለሁ ሥራ ስለሚበዛብኝ ለሌስሊ ብዙ ጊዜ መስጠት አልችልም ነበር። በዚያ ወቅት ሌላ ትምህርት አገኘሁ። አንድ ቀን፣ ሰኞ ጠዋት የቤታችን ደወል ጠራ። በሩ ላይ ማንም ሰው አልነበረም። ሆኖም አንድ ቅርጫት ተቀምጦ አገኘን። ቅርጫቱ ውስጥ የጠረጴዛ ጨርቅ፣ ፍራፍሬ፣ ቺዝ፣ ዳቦ፣ የወይን ጠጅና ብርጭቆ ነበር፤ ከዚያም ቅርጫቱ ውስጥ “ሚስትህን ሽርሽር ይዘሃት ሂድ” የሚል ወረቀት አገኘን። ፍክት ያለ ደስ የሚል ቀን ነበር። ሆኖም ንግግር መዘጋጀት ስላለብኝ ሽርሽር መሄድ እንደማልችል ለሌስሊ ነገርኳት። ያለሁበት ሁኔታ ቢገባትም ትንሽ አዝና ነበር። ተመልሼ ጠረጴዛው ጋ ከተቀመጥኩ በኋላ ሕሊናዬ ይከነክነኝ ጀመር። ኤፌሶን 5:25, 28⁠ን አስታወስኩ። ይሖዋ በዚህ ጥቅስ አማካኝነት የሚስቴን ስሜት ከግምት እንዳስገባ እየመከረኝ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ። ከጸለይኩ በኋላ ሌስሊን “እንሂድ” አልኳት፤ እሷም በጣም ተደሰተች። በአንድ ወንዝ ዳርቻ በሚገኝ የሚያምር ቦታ ሄደን ጨርቁን አነጠፍንና ጨርሶ የማንረሳው ቀን አሳለፍን። ንግግሬንም መዘጋጀት ችያለሁ።

ወረዳችን ከብሪትሽ ኮሎምቢያ እስከ ኒውፋውንድላንድ የሚገኙ በርካታ ጉባኤዎችን ያካትት ነበር። ሕይወታችን አስደሳች ነበር። ወደተለያዩ ቦታዎች የመጓዝ ሕልሜ ተሳካ። በጊልያድ ትምህርት ቤት ስለመማር አስቤ ባውቅም በውጭ አገር በሚስዮናዊነት የማገልገል ፍላጎት አልነበረኝም። ሚስዮናውያን ለየት ያሉ ሰዎች እንደሆኑና እኔ ብቃቱን ማሟላት እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። በዚያ ላይ በበሽታና በጦርነት በሚታመስ አንድ የአፍሪካ አገር እንዳልመደብ ፈርቼ ነበር። በካናዳ ባለው የአገልግሎት ምድቤ ደስተኛ ነበርኩ።

ያልተጠበቀ ምድብ—በኢስቶኒያና በባልቲክ አገራት ማገልገል

በባልቲክ አገራት ስንጓዝ

በ1992 የሶቪየት ኅብረት አባላት በነበሩ አንዳንድ አገራት ውስጥ በነፃነት መስበክ ተችሎ ነበር። በመሆኑም ወደ ኢስቶኒያ ተዛውረን በሚስዮናዊነት ለማገልገል ፈቃደኞች መሆናችንን ተጠየቅን። በጣም ደንግጠን ነበር። ሆኖም ስለ ጉዳዩ ጸለይን። አሁንም ‘ይሖዋ አንድ ነገር እንድናደርግ ከጋበዘን ግብዣውን መቀበል አይኖርብንም?’ ብለን አሰብን። ስለዚህ ግብዣውን ተቀበልን። ‘ቢያንስ የተመደብነው አፍሪካ አይደለም’ ብዬ አሰብኩ።

ወዲያውኑ ኢስቶኒያኛ መማር ጀመርን። በአገሪቱ ለተወሰኑ ወራት ካገለገልን በኋላ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጠየቅን። በሦስት የባልቲክ አገራት እንዲሁም በካሊኒንግራድ፣ ሩሲያ የሚገኙ 46 ጉባኤዎችንና ቡድኖችን መጎብኘት ነበረብን። በመሆኑም ላትቪያኛ፣ ሊቱዋንያኛና ሩሲያኛ ለመማር መሞከር ጀመርን። ከባድ ነበር፤ ሆኖም ወንድሞች ጥረታችንን ያደንቁ ነበር፤ ደግሞም በእጅጉ ረድተውናል። በ1999 በኢስቶኒያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ። እኔም ከቶማስ ኤዱር፣ ከሌምቢት ራይሌና ከቶሚ ካውኮ ጋር በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ።

በስተ ግራ በሊቱዌንያ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር ሳቀርብ

በስተ ቀኝ በ1999 የተቋቋመው የኢስቶኒያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ

ወደ ሳይቤሪያ ተግዘው ከነበሩ በርካታ ወንድሞች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አገኘን። በእስር ቤት እንግልት ቢደርስባቸውም እንዲሁም ከቤተሰባቸው ለመለየት ቢገደዱም በሁኔታው አልተመረሩም። ደስታቸውንና ለአገልግሎት ያላቸውን ቅንዓት ይዘው ቀጥለዋል። ይህም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመንም መጽናትና ደስታችንን መጠበቅ እንደምንችል እንድናስተውል ረድቶናል።

ለበርካታ ዓመታት ያለእረፍት ከሠራን በኋላ ሌስሊ ለየት ያለ ድካም ይሰማት ጀመር። የድካሟ መንስኤ ፋይብሮማያልጂያ የተባለው ሕመም እንደሆነ አላወቅንም ነበር። በዚህ ወቅት ወደ ካናዳ ስለመመለስ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርን። በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚካሄደው ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በተዘጋጀው ትምህርት ቤት እንድንካፈል ስንጋበዝ ግብዣውን መቀበል መቻላችንን ተጠራጥሬ ነበር። ሆኖም አጥብቀን ከጸለይን በኋላ ግብዣውን ተቀበልን። ይሖዋም ውሳኔያችንን ባርኮልናል። በትምህርት ቤቱ እየተካፈልን ሳለን ሌስሊ አስፈላጊውን ሕክምና አገኘች። በመሆኑም እንደ ቀድሞው በሙሉ ኃይል አገልግሎታችንን ማከናወን ቻልን።

ሌላ ያልተጠበቀ በረከት በሌላ አህጉር

በ2008 ኢስቶኒያ እያለን አንድ ምሽት ከዋናው መሥሪያ ቤት ስልክ ተደወለልኝ። በኮንጎ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናችንን ጠየቁኝ። በጣም ደነገጥኩ። በዚያ ላይ በማግስቱ መልስ መስጠት ነበረብኝ። መጀመሪያ ላይ ጉዳዩን ለሌስሊ አልነገርኳትም፤ ምክንያቱም ብነግራት በዚያ ምሽት እንቅልፍ እንደማይወስዳት እርግጠኛ ነበርኩ። እኔ ግን እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር አደረ። በአፍሪካ ከማገልገል ጋር በተያያዘ ያለብኝን ጭንቀት አስመልክቶ ስጸልይ አደርኩ።

በማግስቱ ለሌስሊ ስነግራት “ይሖዋ ወደ አፍሪካ እንድንሄድ እየጋበዘን ነው። ሄደን ካልሞከርነው ምድቡ አስደሳች መሆን አለመሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” ብለን አሰብን። ስለዚህ በኢስቶኒያ ለ16 ዓመታት ካገለገልን በኋላ ወደ ኪንሻሳ፣ ኮንጎ ሄድን። ቅርንጫፍ ቢሮው ውብ የአትክልት ስፍራ ነበረው፤ ቦታው ሰላም የሰፈነበት ነበር። ሌስሊ መጀመሪያ ላይ ክፍላችን ውስጥ ካስቀመጠቻቸው ነገሮች አንዱ ከካናዳ ከወጣንበት ጊዜ አንስቶ ያልተለያት አንድ ካርድ ነው፤ በካርዱ ላይ “በተተከላችሁበት ቦታ አብቡ” የሚል ጽሑፍ አለ። ከወንድሞች ጋር ከተገናኘን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ከቻልን እንዲሁም የሚስዮናዊነትን ሕይወት ከቀመስን በኋላ ምድባችንን በጣም ወደድነው። ከጊዜ በኋላ በ13 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የመጎብኘት መብት አግኝተናል። ይህም በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ያለውን አስደናቂ ልዩነትና ውበታቸውን ለማየት አስችሎናል። ቀደም ሲል የነበረኝ ፍርሃት በሙሉ ጠፋ። በአፍሪካ እንድናገለግል ስለላከን ይሖዋን አመሰገንነው።

ኮንጎ እያለን እንደ ነፍሳት ያሉ የተለያዩ ምግቦች ቀርበውልን ነበር፤ መጀመሪያ ላይ እነዚህን ምግቦች ፈጽሞ ልንበላቸው የምንችል አልመሰለንም። ወንድሞቻችን ምግቦቹን በደስታ ሲመገቡ ስናይ ግን እኛም ለመሞከር ተነሳሳን። ደግሞም ምግቡን ወደድነው።

በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የታጠቁ ኃይሎች በመንደሮቹ ላይ ጥቃት ይሰነዝሩ እንዲሁም በሴቶችና በሕፃናት ላይ ግፍ ይፈጽሙ ነበር። በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞች መንፈሳዊና ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ችለናል። አብዛኞቹ ወንድሞች በጣም ድሆች ነበሩ። ሆኖም በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላቸው ጠንካራ እምነት፣ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲሁም ለድርጅቱ ያላቸው ታማኝነት ልባችንን ነክቶታል። ራሳችንን መለስ ብለን ለመገምገምና እምነታችንን ለማጠናከር አነሳሳን። አንዳንዶቹ ወንድሞች ቤታቸውንና ሰብላቸውን አጥተዋል። ይህም ቁሳዊ ነገሮች በፍጥነት ሊጠፉ እንደሚችሉና መንፈሳዊ ነገሮች ያላቸውን ዋጋማነት እንድገነዘብ ረድቶኛል። ወንድሞች ከባድ መከራ ቢያጋጥማቸውም አያጉረመርሙም። የሚያሳዩት መንፈስ የሚያጋጥሙንን ችግሮችና ያሉብንን የጤና እክሎች በልበ ሙሉነት እንድንጋፈጥ ብርታት ሰጥቶናል።

በስተ ግራ ለተወሰኑ ስደተኞች ንግግር ሳቀርብ

በስተ ቀኝ ሰብዓዊ እርዳታና የሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ ዱንጉ፣ ኮንጎ ስናደርስ

አዲስ ምድብ በእስያ

ከዚያም ሌላ ያልተጠበቀ ለውጥ አጋጠመን። ወደ ሆንግ ኮንግ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድንዛወር ተጠየቅን። በሩቅ ምሥራቅ እንኖራለን ብለን ፈጽሞ አስበን አናውቅም ነበር! ሆኖም በሌሎቹ ምድቦቻችን ሁሉ የይሖዋን ፍቅራዊ እጅ ስላየን አዲሱን ምድብ ተቀበልን። በ2013 ውድ ጓደኞቻችንንና ውቧን አፍሪካን ትተን ወደ አዲሱ ምድባችን ተጓዝን። ምን እንደሚጠብቀን አላወቅንም ነበር።

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች በሚኖሩባት በሆንግ ኮንግ መኖር ለእኛ ትልቅ ለውጥ ነበር። ቻይንኛ ቋንቋ መማርም ከብዶናል። ወንድሞች ግን ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን። ምግቡንም በጣም ወደድነው። ሥራው በፍጥነት ስለተስፋፋ ቅርንጫፍ ቢሮው ተጨማሪ የሥራ ቦታ ያስፈልገው ነበር። ሆኖም የመሬትና የቤት ዋጋ እጅግ አሻቀበ። በመሆኑም የበላይ አካሉ አንዳንዱ ሥራ በሌላ አገር እንዲሠራና የቅርንጫፍ ቢሮው ንብረት የሆኑት አብዛኞቹ ሕንፃዎች እንዲሸጡ ወሰነ። ብዙም ሳይቆይ በ2015 ወደ ደቡብ ኮሪያ ተዛወርን፤ አሁንም የምናገለግለው በዚያው ነው። እዚህም ሌላ ከባድ ቋንቋ መማር ይጠበቅብናል። ቋንቋው አሁንም ቢያታግለንም ወንድሞችና እህቶች ኮሪያኛችን እየተሻሻለ እንደሆነ ይነግሩናል።

በስተ ግራ ሆንግ ኮንግ እንደሄድን

በስተ ግራ የኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ

ያገኘናቸው ትምህርቶች

አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ሆኖም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ከሰዎች ጋር ቶሎ ለመቀራረብ እንደሚረዳ ተመልክተናል። በወንድሞቻችን መካከል ካለው ልዩነት ይልቅ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች እንደሚበዙ አስተውለናል። በተጨማሪም ይሖዋ የፈጠረን ልባችንን ወለል አድርገን ከፍተን ብዙ ጓደኞችን ማፍራት እንድንችል አድርጎ እንደሆነ ተገንዝበናል።—2 ቆሮ. 6:11

ለሰዎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ፍቅርና አመራር ለማስተዋል ጥረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተምረናል። ሲከፋን ወይም ወንድሞችና እህቶች የሚወዱን መሆኑን ስንጠራጠር ጓደኞቻችን የሰጡንን አበረታች ካርዶች ወይም ደብዳቤዎች መለስ ብለን እናነባለን። ይሖዋ ማጽናኛና ብርታት በመስጠት ጸሎታችንን ሲመልስልን በግልጽ አይተናል።

ባለፉት ዓመታት እኔና ሌስሊ ምንም ያህል ሥራ ቢበዛብን አንዳችን ለሌላው ጊዜ መስጠት እንዳለብን ተምረናል። በተጨማሪም በተለይ አዲስ ቋንቋ በምንማርበት ጊዜ በራሳችን ላይ መሳቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበናል። በእያንዳንዱ ምሽት በዕለቱ ያጋጠመንን አስደሳች ነገር በማስታወስ ይሖዋን ለማመስገን ጥረት እናደርጋለን።

እውነቱን ለመናገር፣ ሚስዮናዊ መሆን ወይም በሌላ አገር መኖር እንደምችል አይሰማኝም ነበር። ያም ቢሆን በይሖዋ እርዳታ ሁሉም ነገር እንደሚቻል በመመልከቴ ደስተኛ ነኝ። ነቢዩ ኤርምያስ “ይሖዋ ሆይ፣ አሞኘኸኝ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ እጋራለሁ። (ኤር. 20:7) አዎ፣ ይሖዋ ያልጠበቅናቸውን ስጦታዎችና ጨርሶ አስበን የማናውቃቸውን በረከቶች ሰጥቶናል። ሌላው ቀርቶ በአውሮፕላን የመጓዝ ሕልሜን አሳክቶልኛል። ልጅ እያለሁ በሕልሜም ሆነ በእውኔ ልገምት ከምችለው በላይ ወደ ብዙ አገሮች ተጉዣለሁ። በአምስት አህጉሮች ውስጥ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ጎብኝቻለሁ። በተሰጡን የአገልግሎት ምድቦች ሁሉ ሌስሊ ያደረገችልኝን ድጋፍና ያሳየችውን የፈቃደኝነት መንፈስ በጣም አደንቃለሁ።

የምናገለግለው ማንን እንደሆነ እንዲሁም እነዚህን መሥዋዕቶች የምንከፍለው ለምን እንደሆነ ሁልጊዜ ለማስታወስ እንሞክራለን። በአሁኑ ጊዜ ያገኘናቸው በረከቶች ወደፊት ይሖዋ ‘እጁን ዘርግቶ የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት ለሚያሟላበት’ ጊዜ የቅምሻ ያህል ብቻ ናቸው።—መዝ. 145:16