የጥናት ርዕስ 28
ከአምላካዊ ፍርሃት ጥቅም ማግኘታችሁን ቀጥሉ
“አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው ይሖዋን ይፈራል።”—ምሳሌ 14:2
መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!
ማስተዋወቂያ a
1-2. ልክ እንደ ሎጥ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የትኛው ፈተና ያጋጥማቸዋል?
በዛሬው ጊዜ ዓለም የሚከተለውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ስናይ እንደ ጻድቁ ሎጥ ዓይነት ስሜት ይሰማናል። ሎጥ የሰማዩ አባታችን መጥፎ ምግባርን እንደሚጠላ ስለሚያውቅ “ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በማንአለብኝነት በሚፈጽሙት ድርጊት እጅግ እየተሳቀቀ” ይኖር ነበር። (2 ጴጥ. 2:7, 8) ሎጥ ለአምላክ ያለው ፍርሃትና ፍቅር በዙሪያው የሚኖሩት ሰዎች ከነበራቸው ያዘቀጠ ሥነ ምግባር እንዲርቅ ረድቶታል። እኛም ለይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ተከበናል። ያም ቢሆን ለአምላክ ፍቅርና ጤናማ ፍርሃት ካዳበርን የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ እንችላለን።—ምሳሌ 14:2
2 ይሖዋ በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ሲል በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ጠቃሚ ማበረታቻ አስፍሮልናል። ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ አረጋዊ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር መመርመራቸው ይጠቅማቸዋል።
ለአምላክ ያለን ፍርሃት ጥበቃ ያደርግልናል
3. በምሳሌ 17:3 መሠረት ልባችንን ለመጠበቅ የሚያነሳሳን አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
3 ምሳሌያዊ ልባችንን ለመጠበቅ የሚያነሳሳን አንዱ ወሳኝ ምክንያት ይሖዋ ልባችንን የሚመረምር መሆኑ ነው። ይህም ሲባል ሰዎች ከሚያዩት ገጽታችን ባሻገር እውነተኛ ውስጣዊ ማንነታችንን ይመለከታል ማለት ነው። (ምሳሌ 17:3ን አንብብ።) ሕይወት ሰጪ በሆነው ጥበቡ አእምሯችንን የምንሞላ ከሆነ ይወደናል። (ዮሐ. 4:14) እንዲህ ካደረግን ከሰይጣንና ከእሱ ዓለም የሚመጣውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መርዝ የምናስተናግድበት ቦታ አይኖረንም። (1 ዮሐ. 5:18, 19) ወደ ይሖዋ ይበልጥ በቀረብን መጠን ለእሱ ያለን ፍቅርና አክብሮት ይጨምራል። አባታችንን ማሳዘን ስለማንፈልግ ኃጢአት መፈጸምን ስናስበው እንኳ ይዘገንነናል። መጥፎ ነገር ለማድረግ ስንፈተን ‘ይህን ያህል ፍቅር ያሳየኝን አምላክ የሚያሳዝን ነገር እንዴት ሆን ብዬ እፈጽማለሁ?’ ብለን እናስባለን።—1 ዮሐ. 4:9, 10
4. አንዲት እህት ይሖዋን መፍራቷ ለፈተና እጅ እንዳትሰጥ የረዳት እንዴት ነው?
4 በክሮኤሺያ የምትኖር ማርታ የተባለች እህት የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም ተፈትና ነበር፤ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አጥርቼ ማሰብና ኃጢአት ከመፈጸም የሚገኘውን ቅጽበታዊ ደስታ ለማግኘት ያደረብኝን ፍላጎት መቋቋም ከብዶኝ ነበር። ሆኖም ለይሖዋ ያለኝ ፍርሃት ጥበቃ አድርጎልኛል።” b ማርታ ለአምላክ ያላት ፍርሃት ጥበቃ ያደረገላት እንዴት ነው? መጥፎ ውሳኔ ብታደርግ የሚከተለውን መዘዝ ቆም ብላ ማሰቧ እንደረዳት ተናግራለች። እኛም እንደዚያው ማድረግ እንችላለን። ኃጢአት መፈጸማችን የሚያስከትልብን ከሁሉ የከፋው መዘዝ ይሖዋን ማሳዘናችንና እሱን ለዘላለም ማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ ማጣታችን ነው።—ዘፍ. 6:5, 6
5. ከሊዮ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?
5 ይሖዋን የምንፈራው ከሆነ መጥፎ ምግባር ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት አንመሠርትም። በኮንጎ የሚኖረው ሊዮ ይህን እውነታ ተምሯል። ከተጠመቀ ከአራት ዓመት በኋላ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጠመ። እሱ ራሱ መጥፎ ድርጊት እስካልፈጸመ ድረስ በይሖዋ ላይ ኃጢአት እየሠራ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ከመጥፎ ጓደኞች ጋር መግጠሙ የአልኮል ሱሰኛ ወደመሆንና የሥነ ምግባር ብልግና ወደመፈጸም መራው። ከዚያ በኋላ፣ ክርስቲያን ወላጆቹ ስላስተማሩት ነገር እንዲሁም ቀደም ሲል ስለነበረው ደስታ ማሰብ ጀመረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? አቋሙን አስተካከለ። በሽማግሌዎች እርዳታ ወደ ይሖዋ ተመለሰ። በአሁኑ ወቅት ሽማግሌና ልዩ አቅኚ ሆኖ በደስታ እያገለገለ ነው።
6. ከዚህ በመቀጠል ስለ የትኞቹ ሁለት ምሳሌያዊ ሴቶች እንመለከታለን?
6 ከዚህ በመቀጠል ምሳሌ ምዕራፍ 9ን እንመረምራለን። በዚህ ምዕራፍ ላይ ጥበብና ሞኝነት በሁለት ሴቶች ተመስለዋል። (ከሮም 5:14፤ ገላትያ 4:24 ጋር አወዳድር።) ይህን ምዕራፍ ስንመረምር፣ የሰይጣን ዓለም የሥነ ምግባር ብልግናና ፖርኖግራፊ እንደተጠናወተው በአእምሯችን እንያዝ። (ኤፌ. 4:19) በመሆኑም በቀጣይነት አምላካዊ ፍርሃትን ማዳበራችንና ከክፋት መራቃችን አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 16:6) ወንዶችም ሆንን ሴቶች በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከሚገኘው ምክር ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ሁለቱም ሴቶች ተሞክሮ ለሌላቸው ወይም “ማስተዋል ለጎደላቸው” ሰዎች ግብዣ እንደሚያቀርቡ ተደርጎ ተገልጿል። ሁለቱም በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ወደ ቤቴ መጥታችሁ ምግብ ብሉ’ የሚል ግብዣ ያቀርባሉ። (ምሳሌ 9:1, 5, 6, 13, 16, 17) ሆኖም ግብዣውን የሚቀበሉ ሰዎች የሚገጥማቸው ውጤት በእጅጉ የተለያየ ነው።
ከሞኝነት ጎዳና ራቁ
7. በምሳሌ 9:13-18 መሠረት አንደኛዋ ሴት የምታቀርበው ግብዣ ወደ ምን ይመራል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 በመጀመሪያ “ማስተዋል የጎደላት ሴት” የምታቀርበውን ግብዣ እንመልከት። (ምሳሌ 9:13-18ን አንብብ።) ይህች ኀፍረተ ቢስ ሴት ተሞክሮ የሌላቸውን ሰዎች ወደ እሷ መጥተው ምግብ እንዲበሉ ትጋብዛለች። ውጤቱስ ምንድን ነው? ጥቅሱ “በሞት የተረቱት በዚያ እንዳሉ” ይገልጻል። ምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ በሌላ ምዕራፍ ላይ ተመሳሳይ ዘይቤያዊ አገላለጽ እናገኛለን። ያ ምዕራፍ “ጋጠወጥ” እና “ባለጌ” ስለሆነች ሴት ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። “ቤቷ ሰውን ይዞ ወደ ሞት ይወርዳል” ይላል። (ምሳሌ 2:11-19) ምሳሌ 5:3-10 ደግሞ ስለ ሌላ “ጋጠወጥ ሴት” ይናገራል፤ እሷም ብትሆን “እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ።”
8. ምን ዓይነት ውሳኔ ሊደቀንብን ይችላል?
8 “ማስተዋል የጎደላት ሴት” የምታቀርበውን ግብዣ የሚሰሙ ሰዎች ግብዣዋን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰን ይኖርባቸዋል። እኛም እንዲህ ያለ ምርጫ ሊደቀንብን ይችላል። የፆታ ብልግና ለመፈጸም ስንፈተን አሊያም ደግሞ ሚዲያ ወይም ኢንተርኔት ላይ የፖርኖግራፊ ምስሎች ድንገት ሲመጡብን ምን ዓይነት ምርጫ እናደርጋለን?
9-10. ከፆታ ብልግና ለመራቅ የሚያነሳሱን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
9 ከፆታ ብልግና ለመራቅ የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። የምሳሌ መጽሐፍ፣ “ማስተዋል የጎደላት ሴት” “የተሰረቀ ውኃ ይጣፍጣል” እንደምትል ይናገራል። “የተሰረቀ ውኃ” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር አጋሮች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት አርኪ ከሆነ ውኃ ጋር ያመሳስለዋል። (ምሳሌ 5:15-18) ሕጋዊ ጋብቻ የፈጸሙ ባለትዳሮች በፆታ ግንኙነት መደሰት ይችላሉ። ‘ከተሰረቀ ውኃ’ ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው በእጅጉ የተለየ ነው። ይህ አገላለጽ ያልተፈቀደ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነትን ሊያመለክት ይችላል። ሌቦች ብዙውን ጊዜ የሚሰርቁት ተደብቀው እንደሆነ ሁሉ ብዙዎች እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን የሚፈጽሙት በድብቅ ነው። በተለይ ኃጢአት የሚፈጽሙት ሰዎች ድርጊታቸው ካልታወቀባቸው ደግሞ ‘የተሰረቀው ውኃ’ ይበልጥ ጣፋጭ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። በዚህ መልኩ መታለላቸው እንዴት ያሳዝናል! ይሖዋ ሁሉንም ነገር ይመለከታል። የእሱን ሞገስ ማጣት ከምንም በላይ መራራ ነው፤ ስለዚህ የእሱን ሞገስ የሚያሳጣ ነገር ፈጽሞ ‘ጣፋጭ’ ሊሆን አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ግን የፆታ ብልግና የሚያስከትለው መዘዝ ይህ ብቻ አይደለም።
10 የፆታ ብልግና ለኀፍረት፣ ለከንቱነት ስሜት፣ ላልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም ለቤተሰብ መፍረስ ሊዳርግ ይችላል። በእርግጥም፣ ማስተዋል ከጎደላት ሴት ‘ቤትም’ ሆነ ከምታቀርበው ምግብ መራቅ የጥበብ እርምጃ ነው። የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ብዙ ሰዎች ለመንፈሳዊ ሞት ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ ቃል በቃል ያለዕድሜያቸው እንዲቀጩ በሚያደርግ በሽታ ሊያዙ ይችላሉ። (ምሳሌ 7:23, 26) ምዕራፍ 9 ቁጥር 18 ላይ ‘እንግዶቿ በመቃብር ጥልቅ ውስጥ እንደሚገኙ’ ይናገራል። ታዲያ ብዙዎች ለዚህ ሁሉ መከራ የሚዳርገውን የዚህችን ሴት አታላይ ግብዣ የሚቀበሉት ለምንድን ነው?—ምሳሌ 9:13-18
11. ፖርኖግራፊ መመልከት በጣም ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ወደ ፆታ ብልግና የሚመራው አንዱ ነገር ፖርኖግራፊ ነው። አንዳንዶች ፖርኖግራፊ መመልከት ምንም ጉዳት እንደሌለው ይሰማቸዋል። ሆኖም ፖርኖግራፊ ጎጂ፣ የሚያዋርድና ሱስ የሚያስይዝ ነገር ነው። የብልግና ምስሎች በቀላሉ ከአእምሮ አይፋቁም። በተጨማሪም ፖርኖግራፊ መጥፎ ምኞቶችን ከመግደል ይልቅ ያቀጣጥላቸዋል። (ቆላ. 3:5፤ ያዕ. 1:14, 15) ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ብዙ ሰዎች የፆታ ብልግና መፈጸማቸው አይቀርም።
12. የፆታ ስሜት ከሚቀሰቅሱ ምስሎች መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
12 የፖርኖግራፊ ምስሎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያችን ላይ ድንገት ቢመጡብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ወዲያውኑ ምስሉን ማየታችንን ማቆም ይኖርብናል። ከሁሉ በላይ ትልቁ ሀብታችን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና መሆኑን ማስታወሳችን እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ ይረዳናል። እንዲያውም እንደ ፖርኖግራፊ የማይቆጠሩ አንዳንድ ምስሎችም እንኳ የፆታ ስሜትን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። እንዲህ ካሉ ምስሎች መራቅ ያለብን ለምንድን ነው? በልባችን ምንዝር ወደመፈጸም የሚመራ ትንሽ እርምጃ እንኳ መውሰድ ስለማንፈልግ ነው። (ማቴ. 5:28, 29) በታይላንድ የሚኖር ዴቪድ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “‘ምስሎቹ እንደ ፖርኖግራፊ የሚቆጠሩ ባይሆኑም እንኳ እነሱን ማየቴን ብቀጥል ይሖዋ ይደሰታል?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። እንዲህ ብዬ ማሰቤ የጥበብ እርምጃ ለመውሰድ ይረዳኛል።”
13. የጥበብ እርምጃ ለመውሰድ ምን ይረዳናል?
13 ይሖዋን ላለማሳዘን መፍራታችን የጥበብ እርምጃ ለመውሰድ ይረዳናል። አምላክን መፍራት “የጥበብ መጀመሪያ” ወይም መሠረት ነው። (ምሳሌ 9:10) በምሳሌ ምዕራፍ 9 የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ ስለዚህ ጉዳይ የሚያብራራ ዘይቤያዊ አገላለጽ እናገኛለን። ይህ ጥቅስ ስለ ሌላኛዋ ምሳሌያዊ ሴት ማለትም ስለ “እውነተኛ ጥበብ” ይናገራል።
“እውነተኛ ጥበብ” የምታቀርበውን ግብዣ ተቀበሉ
14. ምሳሌ 9:1-6 ስለ የትኛው ግብዣ ይናገራል?
14 ምሳሌ 9:1-6ን አንብብ። በዚህ ጥቅስ ላይ የእውነተኛ ጥበብ ምንጭና መሠረት ከሆነው ከፈጣሪያችን ከይሖዋ ስለሚመጣ አንድ ግብዣ እናነባለን። (ምሳሌ 2:6፤ ሮም 16:27) ይህ ጥቅስ ሰባት ምሰሶዎች ስላሉት ትልቅ ቤት ይናገራል። ይህ አገላለጽ፣ ይሖዋ ለጋስ እንደሆነና የእሱን ጥበብ በሕይወታቸው ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ሁሉ እንደሚቀበል ያሳያል።
15. አምላክ ምን እንድናደርግ ይጋብዘናል?
15 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር አትረፍርፎ የሚያቀርብ ለጋስ አምላክ ነው። በምሳሌ ምዕራፍ 9 ላይ በሴት በተመሰለችው “እውነተኛ ጥበብ” ላይ ይህ ባሕርይ ተንጸባርቋል። ዘገባው ይህች ምሳሌያዊ ሴት የወይን ጠጇን እንደደባለቀች፣ ሥጋዋን በሚገባ እንዳዘጋጀች እንዲሁም ገበታዋን እንዳሰናዳች ይናገራል። (ምሳሌ 9:2) በተጨማሪም በቁጥር 4 እና 5 መሠረት እውነተኛ ጥበብ “ማስተዋል ለጎደለው እንዲህ ትላለች፦ ‘ኑ፣ ያዘጋጀሁትን ምግብ ብሉ።’” ወደ እውነተኛ ጥበብ ቤት ሄደን የምታቀርብልንን ምግብ መመገብ ያለብን ለምንድን ነው? ይሖዋ ልጆቹ ጥበበኛ እንዲሆኑና ከጉዳት እንዲጠበቁ ይፈልጋል። ከመከራ እንድንማርና በጸጸት እንድንዋጥ አይፈልግም። “ለቅኖች ጥበብን እንደ ውድ ሀብት” የሚያከማቸው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 2:7) ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ካለን እሱን ማስደሰት እንፈልጋለን። ጥበብ የሚንጸባረቅበትን ምክሩን እንሰማለን፤ እንዲሁም በሥራ ላይ እናውላለን።—ያዕ. 1:25
16. አሌይን አምላካዊ ፍርሃት ማዳበሩ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የረዳው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
16 አሌይን አምላካዊ ፍርሃት ማዳበሩ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። መምህርና የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ይህ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎቹ የሥራ ባልደረቦቼ የፖርኖግራፊ ፊልሞችን እንደ ሥርዓተ ፆታ ትምህርት ይቆጥሯቸዋል።” አሌይን ግን በዚህ አልተታለለም። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክን ስለምፈራ እነዚህን ፊልሞች ለማየት ፈቃደኛ አልሆንኩም። ፊልሞቹን የማላይበትን ምክንያትም ለሥራ ባልደረቦቼ አስረዳኋቸው።” አሌይን፣ “እውነተኛ ጥበብ” “በማስተዋል መንገድ ወደ ፊት ሂዱ” በማለት የሰጠችውን ምክር ተግባራዊ አድርጓል። (ምሳሌ 9:6) አንዳንድ የሥራ ባልደረቦቹ አሌይን በወሰደው ቁርጥ አቋም ስለተደነቁ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል።
17-18. “እውነተኛ ጥበብ” የምታቀርበውን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የትኞቹን በረከቶች እያገኙ ነው? ወደፊትስ ምን ይጠብቃቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ይሖዋ ስለ ሁለት ሴቶች የሚናገር ዘይቤያዊ አገላለጽ በመጠቀም አስደሳች የወደፊት ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ አሳይቶናል። “ማስተዋል የጎደላት” ጯኺ ሴት የምታቀርበውን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች በድብቅ ብልግና በመፈጸም ደስታ ለማግኘት ይፈልጋሉ። እነዚህን ሰዎች የሚያሳስባቸው የሚያገኙት ቅጽበታዊ ደስታ እንጂ የወደፊት ሕይወታቸው አይደለም። መጨረሻቸው ወደ “መቃብር ጥልቅ” መውረድ ነው።—ምሳሌ 9:13, 17, 18
18 “እውነተኛ ጥበብ” የምታቀርበውን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች ግን የሚያገኙት ውጤት ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው! በአሁኑ ጊዜ ማራኪ አቀራረብ ያላቸውና ገንቢ የሆኑ ምግቦችን ከያዘ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ድግስ ይቋደሳሉ። (ኢሳ. 65:13) ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤ ምርጥ ምግብ በመብላትም ሐሴት ታደርጋላችሁ።” (ኢሳ. 55:1, 2) ይሖዋ የሚወደውን ነገር እንድንወድና እሱ የሚጠላውን ነገር እንድንጠላ እንማራለን። (መዝ. 97:10) እንዲሁም ሌሎች ‘ከእውነተኛ ጥበብ’ ጥቅም እንዲያገኙ ግብዣ በማቅረብ እርካታ እናገኛለን። “ከከተማዋ በላይ ባሉ ከፍታ ቦታዎች ላይ [ሆነን] ‘ተሞክሮ የሌለው ሁሉ ወደዚህ ይምጣ’” ብለን የምንጣራ ያህል ነው። ግብዣችንን የሚቀበሉ ሰዎችም ሆኑ እኛ የምናገኘው ጥቅም በአሁኑ ጊዜ ብቻ የሚወሰን አይደለም። የምናገኘው በረከት ዘላቂ ነው፤ ‘በማስተዋል መንገድ ወደ ፊት እየሄድን’ ለዘላለም እንድንኖር ያስችለናል።—ምሳሌ 9:3, 4, 6
19. በመክብብ 12:13, 14 መሠረት ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? (“ አምላካዊ ፍርሃት ይጠቅመናል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
19 መክብብ 12:13, 14ን አንብብ። በእነዚህ ክፉ የመጨረሻ ቀናት አምላካዊ ፍርሃት ልባችንን ይጠብቅልናል፤ እንዲሁም ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ይረዳናል። እንዲህ ያለው ጤናማ ፍርሃት፣ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ‘እውነተኛ ጥበብን’ እንዲፈልጉና ከዚህ ጥቅም እንዲያገኙ ለመጋበዝ ያነሳሳናል።
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
a ክርስቲያኖች ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ማዳበር ይኖርባቸዋል። እንዲህ ያለው ፍርሃት ልባችንን ይጠብቅልናል፤ እንዲሁም ከፆታ ብልግና እና ከፖርኖግራፊ ወጥመድ ይጠብቀናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ምሳሌ ምዕራፍ 9ን እንመረምራለን፤ ይህ ምዕራፍ ሁለት ምሳሌያዊ ሴቶችን በመጠቀም በጥበብና በሞኝነት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያብራራል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኘውን ምክር መከተላችን ዘላቂ ጥቅም ያስገኝልናል።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።