በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም ናዝሬት ወደሚገኘው ቤታቸው ከመመለስ ይልቅ ቤተልሔም የቀሩት ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን አይነግረንም። ሆኖም ይህን ውሳኔ ያደረጉት ለምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችን ይዟል።

አንድ መልአክ ለማርያም እንደምትጸንስና ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። መልአኩ ይህን መልእክት ባደረሰበት ወቅት ማርያምና ዮሴፍ የሚኖሩት በገሊላ በምትገኘው በናዝሬት ነበር። (ሉቃስ 1:26-31፤ 2:4) በኋላ ላይ ከግብፅ ሲመለሱም እንደገና በናዝሬት መኖር ጀመሩ። ኢየሱስ በዚያ በማደጉ የናዝሬት ሰው ተብሏል። (ማቴ. 2:19-23) በመሆኑም የሦስቱም ማለትም የኢየሱስ፣ የዮሴፍና የማርያም ስም ሲነሳ ስለ ናዝሬት እናስባለን።

ማርያም በይሁዳ የምትኖር ኤልሳቤጥ የተባለች ዘመድ ነበረቻት። ኤልሳቤጥ የካህኑ የዘካርያስ ሚስት ስትሆን በኋላ ላይ መጥምቁ ዮሐንስን ወልዳለች። (ሉቃስ 1:5, 9, 13, 36) ማርያም ኤልሳቤጥን ልትጠይቃት ሄዳ ከእሷ ጋር ሦስት ወር በይሁዳ ቆይታለች። ከዚያም ማርያም ወደ ናዝሬት ተመለሰች። (ሉቃስ 1:39, 40, 56) በመሆኑም ማርያም የይሁዳን ክልል በተወሰነ መጠን ታውቀዋለች።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዮሴፍ በአዋጁ መሠረት ‘ለመመዝገብ’ ሄደ። በመሆኑም ዮሴፍ ከናዝሬት ተነስቶ ‘የዳዊት ከተማ’ ወደሆነችው ወደ ቤተልሔም ተጓዘ። በትንቢቱ መሠረት መሲሑም የሚወለደው በቤተልሔም ነው። (ሉቃስ 2:3, 4፤ 1 ሳሙ. 17:15፤ 20:6፤ ሚክ. 5:2) ዮሴፍ፣ ማርያም ኢየሱስን በቤተልሔም ከወለደች በኋላ አራስ ይዛ ወደ ናዝሬት ለመመለስ ረጅም ጉዞ እንድታደርግ አልፈለገም። ከኢየሩሳሌም ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በቤተልሔም ቆዩ። እንዲህ ማድረጋቸው ልጃቸውን ወደ ቤተ መቅደስ ይዘው ለመሄድና ሕጉ የሚጠይቀውን መሥዋዕት ለማቅረብ ያመቻቸዋል።—ዘሌ. 12:2, 6-8፤ ሉቃስ 2:22-24

ቀደም ሲል የአምላክ መልአክ ለማርያም፣ ልጇ “የዳዊትን ዙፋን” እንደሚወርስና ‘ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛ’ ነግሯታል። ታዲያ ዮሴፍና ማርያም፣ ኢየሱስ በዳዊት ከተማ መወለዱ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ተሰምቷቸው ይሆን? (ሉቃስ 1:32, 33፤ 2:11, 17) አምላክ ተጨማሪ መመሪያ እስኪሰጣቸው ድረስ እዚያው መቆየታቸው ተገቢ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል።

ኮከብ ቆጣሪዎቹ በመጡበት ወቅት ዮሴፍና ቤተሰቡ ቤተልሔም ከሄዱ ምን ያህል ጊዜ እንደሆናቸው አናውቅም። ሆኖም በወቅቱ ቤተሰቡ የሚኖሩበት ቤት ነበራቸው፤ ኢየሱስም ቢሆን አራስ ሳይሆን ‘ልጅ’ ነበር። (ማቴ. 2:11) ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው፣ ወደ ናዝሬት ከመመለስ ይልቅ በቤተልሔም ኑሯቸውን መሥርተዋል።

ሄሮድስ ‘በቤተልሔም የሚገኙ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ወንዶች ልጆች’ ሁሉ እንዲገደሉ አዘዘ። (ማቴ. 2:16) ይህን አዋጅ በተመለከተ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ስለነበር ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ይዘው ወደ ግብፅ ሸሹ፤ ሄሮድስ እስኪሞትም በዚያው ቆዩ። ከዚያ በኋላ ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ናዝሬት ሄደ። ይሁንና ወደ ቤተልሔም ያልተመለሱት ለምንድን ነው? ዮሴፍ የሄሮድስ ልጅ የሆነው አምባገነኑ አርኬላዎስ ይሁዳን እየገዛ እንደሆነ ስለሰማ እንዲሁም አምላክ ማስጠንቀቂያ ስለሰጠው ነው። ዮሴፍ በናዝሬት ኢየሱስን በሰላም ማሳደግ ይችላል።—ማቴ. 2:19-22፤ 13:55፤ ሉቃስ 2:39, 52

ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱበትን መንገድ ከመክፈቱ በፊት ነበር። በመሆኑም ዮሴፍ ትንሣኤ የሚያገኘው በምድር ላይ ነው። ያኔ ብዙዎች አግኝተውት እሱና ማርያም ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ በቤተልሔም የቆዩት ለምን እንደሆነ ሊጠይቁት ይችላሉ።