በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 26

የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ

የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ

“የይሖዋ ቀን የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ [ነው]።”—1 ተሰ. 5:2

መዝሙር 143 ነቅተን በተስፋ እንጠብቃለን

ማስተዋወቂያ a

1. ከይሖዋ ቀን ለመትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የይሖዋ ቀን” የሚለው አገላለጽ ይሖዋ ጠላቶቹ ላይ የሚፈርድበትንና ለሕዝቦቹ መዳን የሚያመጣበትን ወቅት ያመለክታል። በጥንት ዘመን ይሖዋ የፍርድ እርምጃ የወሰደባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ኢሳ. 13:1, 6፤ ሕዝ. 13:5፤ ሶፎ. 1:8) በዘመናችን “የይሖዋ ቀን” የሚጀምረው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ በሚሰነዘረው ጥቃት ሲሆን የሚደመደመው ደግሞ በአርማጌዶን ጦርነት ነው። ከዚያ “ቀን” ለመትረፍ ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ ‘ለታላቁ መከራ’ እንድንዘጋጅ ብቻ ሳይሆን ‘ዝግጁ ሆነን እንድንጠብቅም’ አስተምሮናል።—ማቴ. 24:21፤ ሉቃስ 12:40

2. ከ1 ተሰሎንቄ ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ታላቁን የይሖዋን የፍርድ ቀን ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ለመርዳት በርካታ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ጳውሎስ የይሖዋ ቀን ወዲያውኑ እንደማይመጣ ያውቅ ነበር። (2 ተሰ. 2:1-3) ያም ቢሆን ወንድሞቹ የይሖዋ ቀን ነገ የሚመጣ ያህል ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ አበረታቷቸዋል። እኛም ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። ከሚከተሉት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሰጠውን ማብራሪያ እስቲ እንመልከት፦ (1) የይሖዋ ቀን የሚመጣው እንዴት ነው? (2) ከዚህ ቀን የማይተርፉት እነማን ናቸው? (3) ከዚህ ቀን ለመትረፍ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

የይሖዋ ቀን የሚመጣው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ 1 ተሰሎንቄን ሲጽፍ ጠቃሚ የሆኑ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)

3. የይሖዋ ቀን ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ የሚመጣው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 “ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ።” (1 ተሰ. 5:2) ስለ ይሖዋ ቀን አመጣጥ ከሚገልጹት ሦስት ዘይቤያዊ አገላለጾች የመጀመሪያው ይህ ነው። ብዙውን ጊዜ ሌቦች፣ ሰዎች በማይጠብቁበት ሰዓት ጨለማን ተገን አድርገው በፍጥነት ዝርፊያ ይፈጽማሉ። በተመሳሳይም የይሖዋ ቀን አብዛኞቹ ሰዎች በማይጠብቁት ሰዓት በድንገት ይመጣል። ሁኔታዎች የሚለወጡበት ፍጥነት እውነተኛ ክርስቲያኖችን እንኳ ሊያስደነግጥ ይችላል። ይሁንና እኛ እንደ ክፉዎች አንጠፋም።

4. የይሖዋ ቀን ከምጥ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

4 “ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት።” (1 ተሰ. 5:3) ነፍሰ ጡር ሴት ምጧ የሚጀምርበትን ትክክለኛ ጊዜ አታውቅም። ይሁንና ምጧ መምጣቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ነች። ምጡ ደግሞ ድንገተኛ፣ ሥቃይ የሚያስከትልና ማባሪያ የሌለው መሆኑ አይቀርም። በተመሳሳይም የይሖዋ ቀን የሚጀምርበትን ቀንና ሰዓት አናውቅም። ያም ቢሆን የይሖዋ ቀን እንደሚመጣና አምላክ በክፉዎች ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድ ድንገተኛና ማምለጫ የሌለው እንደሚሆን እርግጠኞች ነን።

5. ታላቁ መከራ እንደ ንጋት የሆነው በምን መንገድ ነው?

5 እንደ ንጋት። ጳውሎስ በሦስተኛ ምሳሌው ላይ በሌሊት የሚሰርቁ ሌቦችን በድጋሚ ጠቅሷል። በዚህኛው ምሳሌ ላይ ግን ጳውሎስ የይሖዋን ቀን ያመሳሰለው ከንጋት ጋር ነው። (1 ተሰ. 5:4) በሌሊት የሚመጡ ሌቦች ትኩረታቸው ዝርፊያው ላይ ብቻ ስለሚሆን ሰዓቱ ሳይታወቃቸው ሊሄድ ይችላል። ድንገት ሊነጋባቸውና ሊጋለጡ ይችላሉ። በተመሳሳይም ታላቁ መከራ አምላክን የሚያሳዝኑ ሥራዎችን በመፈጸም እንደ ሌባ በጨለማ ውስጥ የሚመላለሱ ሰዎችን ያጋልጣቸዋል። እኛ ግን ይሖዋን ከሚያሳዝኑ ድርጊቶች በመራቅና “ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት፣ ጽድቅና እውነት” በመከታተል ለዚያ ቀን መዘጋጀት እንችላለን። (ኤፌ. 5:8-12) በመቀጠል ጳውሎስ ከዚያ ቀን የማይተርፉ ሰዎችን ለመግለጽ ሁለት ተያያዥ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል።

ከይሖዋ ቀን የማይተርፉት እነማን ናቸው?

6. ብዙዎች እያንቀላፉ ነው ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? (1 ተሰሎንቄ 5:6, 7)

6 “የሚያንቀላፉ ሰዎች።” (1 ተሰሎንቄ 5:6, 7ን አንብብ።) ጳውሎስ ከይሖዋ ቀን የማይተርፉ ሰዎችን ከሚያንቀላፉ ሰዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። በዙሪያቸው እየተከናወነ ያለውን ነገርም ሆነ የጊዜውን መሄድ አያስተውሉም። በመሆኑም ወሳኝ ክንውኖች ሲፈጸሙ ልብ ማለትም ሆነ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አይችሉም። በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በመንፈሳዊ አንቀላፍተዋል። (ሮም 11:8) የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ እንደሆነና ታላቁ መከራ በቅርቡ እንደሚመጣ የሚያሳየውን ማስረጃ ችላ ይላሉ። አንዳንዶች በዓለም ላይ የሚከሰቱ ትላልቅ ክንውኖችን ሲመለከቱ ከመንፈሳዊ እንቅልፋቸው ነቅተው ለመንግሥቱ መልእክታችን መጠነኛ ፍላጎት ሊያሳዩ ይችላሉ። ሆኖም ብዙዎቹ እንደነቁ ከመቆየት ይልቅ ተመልሰው ይተኛሉ። በፍርድ ቀን የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ያ ቀን በጣም ሩቅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) እኛ ግን፣ ንቁ እንድንሆን የተሰጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ቀን አልፎ ቀን ሲተካ አጣዳፊነቱ እየጨመረ እንደሚሄድ እንገነዘባለን።

7. የአምላክ ቁጣ ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ከሰካራሞች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

7 “የሚሰክሩ።” ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ቁጣ ሰለባ የሚሆኑ ሰዎችን ከሰካራሞች ጋር አመሳስሏቸዋል። በአልኮል ተጽዕኖ ሥር ያሉ ሰዎች በዙሪያቸው ለሚከናወኑ ነገሮች ምላሽ ለመስጠት ይዘገያሉ፤ እንዲሁም መጥፎ ውሳኔ ያደርጋሉ። በተመሳሳይም ክፉዎች ለአምላክ ማስጠንቀቂያዎች ምላሽ አይሰጡም። ወደ ጥፋት የሚያመራ አካሄድ ለመከተል ይመርጣሉ። ክርስቲያኖች ግን የማስተዋል ስሜታቸውን እንዲጠብቁ ተነግሯቸዋል። (1 ተሰ. 5:6) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት፣ የማስተዋል ስሜቱን የሚጠብቅ ሰው የተረጋጋ ነው፤ አጥርቶ ማሰብና ነገሮችን ማመዛዘን ስለሚችል ጥሩ ውሳኔዎችን ያደርጋል። ይሁንና መረጋጋትና ማመዛዘን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በዓለም ላይ ባሉት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዳንጠላለፍ ነው። የይሖዋ ቀን እየተቃረበ ሲመጣ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ አንዱን ወገን እንድንይዝ የሚደርስብን ጫና ይጨምራል። ሆኖም ‘እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ምላሽ እንሰጥ ይሆን’ የሚለውን በማሰብ መጨነቅ አይኖርብንም። የአምላክ መንፈስ መረጋጋትና ማመዛዘን እንድንችል እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ይረዳናል።—ሉቃስ 12:11, 12

ለይሖዋ ቀን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

ብዙ ሰዎች ግድየለሽ ቢሆኑም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር በመልበስ እንዲሁም ተስፋን እንደ ራስ ቁር በመድፋት የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን እንጠብቃለን (አንቀጽ 8, 12⁠ን ተመልከት)

8. አንደኛ ተሰሎንቄ 5:8 ንቁ ለመሆንና የማስተዋል ስሜታችንን ለመጠበቅ የሚረዱንን ባሕርያት የሚገልጻቸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 “ጥሩር እንልበስ፤ . . . ራስ ቁር እንድፋ።” ጳውሎስ ዝግጁ ከሆኑና የጦር ትጥቅ ከለበሱ ወታደሮች ጋር አመሳስሎናል። (1 ተሰሎንቄ 5:8ን አንብብ።) አንድ ወታደር በማንኛውም ጊዜ ለጦርነት ዝግጁ እንዲሆን ይጠበቅበታል። የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር በመልበስ እንዲሁም ተስፋን እንደ ራስ ቁር በመድፋት የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ እንችላለን። እነዚህ ባሕርያት በእጅጉ ይረዱናል።

9. እምነታችን የሚጠብቀን እንዴት ነው?

9 ጥሩር የአንድን ወታደር ልብ ከጉዳት ይጠብቅለታል። እምነትና ፍቅርም ምሳሌያዊ ልባችንን ይጠብቁልናል። አምላክን ማገልገላችንንና ኢየሱስን መከተላችንን እንድንቀጥል ይረዱናል። እምነት ካለን ይሖዋ እሱን በሙሉ ልባችን በመፈለጋችን ወሮታ እንደሚከፍለን እርግጠኞች እንሆናለን። (ዕብ. 11:6) እምነት፣ መከራ ቢደርስብንም እንኳ ለመሪያችን ለኢየሱስ ምንጊዜም ታማኝ እንድንሆን ያነሳሳናል። ስደት ወይም የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥማቸውም ንጹሕ አቋማቸውን ከጠበቁ በዘመናችን ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በመማር የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል እምነት መገንባት እንችላለን። በተጨማሪም መንግሥቱን ለማስቀደም ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ያደረጉ ክርስቲያኖችን ምሳሌ በመከተል ከፍቅረ ነዋይ ወጥመድ መራቅ እንችላለን። b

10. ለአምላክና ለባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ለመጽናት የሚረዳን እንዴት ነው?

10 ንቁ ለመሆንና የማስተዋል ስሜታችንን ለመጠበቅ ፍቅርም ያስፈልገናል። (ማቴ. 22:37-39) ለአምላክ ያለን ፍቅር፣ ችግር የሚያስከትልብን ቢሆንም እንኳ በጽናት እንድንሰብክ ይረዳናል። (2 ጢሞ. 1:7, 8) እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎችም ፍቅር ስላለን መስበካችንንና ክልላችንን መሸፈናችንን እንቀጥላለን፤ በስልክና በደብዳቤ ምሥክርነትም እንካፈላለን። በክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ተለውጠው ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንደሚጀምሩ ተስፋ እናደርጋለን።—ሕዝ. 18:27, 28

11. ለእምነት አጋሮቻችን ያለን ፍቅር የሚረዳን እንዴት ነው? (1 ተሰሎንቄ 5:11)

11 ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንንም እንወዳቸዋለን። ‘እርስ በርስ በመበረታታት እንዲሁም እርስ በርስ በመተናነጽ’ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (1 ተሰሎንቄ 5:11ን አንብብ።) በአንድ ወገን ተሰልፈው እንደሚዋጉ ወታደሮች እርስ በርስ እንበረታታለን። እርግጥ ነው፣ አንድ ወታደር በጦርነት መሃል ሳያስበው ከጎኑ በተሰለፈው ወታደር ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ይሁን እንጂ በፍጹም ሆን ብሎ ጉዳት አያደርስበትም። እኛም ብንሆን ሆን ብለን በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ጉዳት እንደማናደርስ ወይም በክፉ ፋንታ ክፉ እንደማንመልስ የታወቀ ነው። (1 ተሰ. 5:13, 15) በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን በማክበር ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (1 ተሰ. 5:12) ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የተሰሎንቄ ጉባኤ ከተቋቋመ አንድ ዓመትም አልሞላውም ነበር። በመሆኑም በዚያ ጉባኤ የነበሩት የተሾሙ ወንዶች ተሞክሮ ስለሚጎድላቸው አንዳንድ ስህተቶችን ሠርተው ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። ታላቁ መከራ እየተቃረበ ሲመጣ ከዋናው መሥሪያ ቤትም ሆነ ከቅርንጫፍ ቢሮው መመሪያ ማግኘት አንችል ይሆናል፤ ስለዚህ በዚያ ወቅት ከአሁኑ ይበልጥ መመሪያ የምናገኝበት ዋነኛ መስመር ሽማግሌዎቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ከአሁኑ ለሽማግሌዎቻችን ፍቅርና አክብሮት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው። ምንም ነገር ቢመጣ የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ፤ በእነዚህ ታማኝ ወንድሞች አለፍጽምና ላይ ሳይሆን ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት እየመራቸው በመሆኑ ላይ ትኩረት እናድርግ።

12. ተስፋችን አስተሳሰባችንን የሚጠብቅልን እንዴት ነው?

12 የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት እንደሚጠብቅለት ሁሉ የመዳን ተስፋችንም አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል። ተስፋችን ጠንካራ ከሆነ ይህ ዓለም የሚያቀርብልን ማንኛውም ነገር ከንቱ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ፊልጵ. 3:8) ተስፋችን እንድንረጋጋና ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። አፍሪካ ውስጥ የሚያገለግሉት የዋለስና የሎሪንዳ ተሞክሮ ይህን ያሳያል። በሦስት ሳምንት ውስጥ የዋለስ አባትና የሎሪንዳ እናት ሞቱ። ዋለስና ሎሪንዳ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ወደ አገራቸው ተመልሰው ከቤተሰባቸው ጋር መሆን አልቻሉም። ዋለስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የትንሣኤ ተስፋ፣ ወላጆቻችን በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ባሳለፏቸው የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የነበሩበትን ሁኔታ ሳይሆን በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሚያሳልፏቸው የመጀመሪያ ቀናት ውስጥ የሚኖራቸውን ሁኔታ እንዳስብ ይረዳኛል። ሐዘኑ ሲበረታብኝ ይህ ተስፋ ያረጋጋኛል።”

13. መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 “የመንፈስን እሳት አታጥፉ።” (1 ተሰ. 5:19) ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስን በውስጣችን ካለ እሳት ጋር አመሳስሎታል። የአምላክ መንፈስ ካለን ትክክል ለሆነው ነገር የሚንበለበል ቅንዓት ይኖረናል፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማገልገል ከልባችን እንነሳሳለን። (ሮም 12:11) ታዲያ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን መጸለይ፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ማጥናት እንዲሁም በአምላክ መንፈስ ከሚመራው ድርጅቱ ጋር መተባበር እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን “የመንፈስ ፍሬ” እንድናፈራ ይረዳናል።—ገላ. 5:22, 23

‘ምግባሬ የአምላክን መንፈስ በቀጣይነት ማግኘት እንደምፈልግ የሚያሳይ ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. የአምላክን መንፈስ ማግኘታችንን መቀጠል ከፈለግን ከምን መራቅ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ከሰጠን በኋላ ‘የመንፈስን እሳት እንዳናጠፋ’ መጠንቀቅ ይኖርብናል። አምላክ መንፈሱን የሚሰጠው ንጹሕ አስተሳሰብና ንጹሕ ምግባር ላላቸው ሰዎች ብቻ ነው። በርኩስ ሐሳቦች ላይ ካውጠነጠንን ወይም ርኩስ ምግባር ከፈጸምን አምላክ ለእኛ መንፈሱን መስጠቱን ያቆማል። (1 ተሰ. 4:7, 8) መንፈስ ቅዱስን ማግኘታችንን መቀጠል ከፈለግን ‘ትንቢቶችን ከመናቅ’ መቆጠብም ይኖርብናል። (1 ተሰ. 5:20) በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “ትንቢቶች” የሚለው ቃል በአምላክ መንፈስ የተነገሩ መልእክቶችን ያመለክታል። ይህም ከይሖዋ ቀንና ከጊዜው አጣዳፊነት ጋር የተያያዙ መልእክቶችን ይጨምራል። አርማጌዶን በእኛ የሕይወት ዘመን እንደማይመጣ በማሰብ ያንን ቀን አርቀን አንመለከትም። ከዚህ ይልቅ በየቀኑ ጥሩ ምግባር በማሳየትና ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮችን በመፈጸም’ ያንን ቀን በአእምሯችን አቅርበን እንመለከተዋለን።—2 ጴጥ. 3:11, 12

“ሁሉንም ነገር መርምሩ”

15. በተሳሳተ መረጃና በአጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳ እንዳንታለል ምን ማድረግ ይኖርብናል? (1 ተሰሎንቄ 5:21)

15 በቅርቡ የአምላክ ጠላቶች “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው በሆነ መንገድ ያውጃሉ። (1 ተሰ. 5:3) በአጋንንት መንፈስ የሚነገር ፕሮፓጋንዳ መላውን ምድር ይሞላል፤ ብዙዎችንም ያሳስታል። (ራእይ 16:13, 14) እኛ ግን ‘ሁሉንም ነገር የምንመረምር’ ወይም የምንፈትን ከሆነ አንታለልም። (1 ተሰሎንቄ 5:21ን አንብብ።) “መርምሩ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ውድ ማዕድናትን ከመፈተን ጋር በተያያዘ ይሠራበት ነበር። በመሆኑም የምንሰማው ወይም የምናነበው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መፈተን ይኖርብናል። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነበር። እኛ ደግሞ በተለይ ታላቁ መከራ እየተቃረበ ሲመጣ እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ሌሎች የሚናገሩትን ነገር ሁሉ በሞኝነት ከመቀበል ይልቅ የማመዛዘን ችሎታችንን በመጠቀም፣ የምናነበውን ወይም የምንሰማውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስና የይሖዋ ድርጅት ከሚናገሩት ነገር ጋር ማወዳደር ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን በአጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳ አንታለልም።—ምሳሌ 14:15፤ 1 ጢሞ. 4:1

16. ምን አስተማማኝ ተስፋ አለን? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምንድን ነው?

16 የአምላክ አገልጋዮች በቡድን ደረጃ ከታላቁ መከራ ይተርፋሉ። በግለሰብ ደረጃ ግን ነገ ምን እንደሚደርስብን አናውቅም። (ያዕ. 4:14) ያም ቢሆን ታላቁን መከራ በሕይወት ብናልፍም ሆነ ከዚያ በፊት ብንሞት ታማኝነታችንን እስከጠበቅን ድረስ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እናገኛለን። ቅቡዓን በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ይገዛሉ። ሌሎች በጎች ደግሞ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ይኖራሉ። እንግዲያው ሁላችንም አስደናቂ በሆነው ተስፋችን ላይ ትኩረት በማድረግ የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን እንጠብቅ!

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

a በ1 ተሰሎንቄ ምዕራፍ 5 ላይ ወደፊት ስለሚመጣው የይሖዋ ቀን የሚገልጹ የተለያዩ ምሳሌዎችና ዘይቤያዊ አገላለጾች እናገኛለን። ይህ ቀን ምንድን ነው? የሚመጣውስ እንዴት ነው? ከዚህ ቀን የሚተርፉት እነማን ናቸው? የማይተርፉትስ እነማን ናቸው? ለዚህ ቀን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ደብዳቤ በመመርመር የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

bራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል” በሚል ርዕስ የሚወጡትን ተሞክሮዎች ተመልከት።