በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 27

ይሖዋን መፍራት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ይሖዋን መፍራት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

“ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እሱን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው።”—መዝ. 25:14

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው

ማስተዋወቂያ a

1-2. በመዝሙር 25:14 መሠረት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

 ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት የትኞቹ ባሕርያት የሚያስፈልጉ ይመስልሃል? ‘ጥሩ ጓደኛሞች መዋደድና መደጋገፍ አለባቸው’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። ሆኖም ፍርሃት ለጥሩ ጓደኝነት አስፈላጊ ባሕርይ ነው ብለህ ላታስብ ትችላለህ። ያም ቢሆን የጭብጡ ጥቅስ እንደሚገልጸው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ‘እሱን ሊፈሩት’ ይገባል።—መዝሙር 25:14ን አንብብ።

2 ይሖዋን ስናገለግል የቆየነው ለምንም ያህል ጊዜ ቢሆን ሁላችንም ለእሱ ምንጊዜም ጤናማ ፍርሃት ሊኖረን ይገባል። ሆኖም አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? ለይሖዋ ፍርሃት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? አምላክን መፍራትን በተመለከተ የንጉሡ ቤት አዛዥ ከነበረው ከአብድዩ፣ ከሊቀ ካህናቱ ዮዳሄና ከንጉሥ ኢዮዓስ ምን እንማራለን?

አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?

3. ፍርሃት ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው? አብራራ።

3 የሆነ ዓይነት አደጋ ሊደርስብን እንደሚችል ከጠበቅን ፍርሃት ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ያለው ጤናማ ፍርሃት ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይችላል። እንዳንወድቅ ከፈራን ወደ ገደል አፋፍ ከመጠጋት እንቆጠባለን። ጉዳት እንዳይደርስብን ከፈራን ከአደገኛ ሁኔታ እንሸሻለን። ከምንወደው ሰው ጋር ያለን ዝምድና እንዳይበላሽ ከፈራን ደግነት የጎደለው ነገር ከመናገር ወይም ከማድረግ እንቆጠባለን።

4. ሰይጣን ለይሖዋ ምን ዓይነት ፍርሃት እንዲኖረን ይፈልጋል?

4 ሰይጣን፣ ሰዎች ለይሖዋ ጤናማ ያልሆነ ፍርሃት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ሰይጣን፣ ኤሊፋዝ እንደተናገረው ይሖዋ ቁጡ፣ ሰዎችን መቅጣት የሚወድና አገልጋዮቹ ምንም ቢያደርጉ የማይደሰት አምላክ እንደሆነ እንድናስብ ይፈልጋል። (ኢዮብ 4:18, 19) ሰይጣን፣ ይሖዋን ከመፍራታችን የተነሳ እሱን ማገልገላችንን እንድናቆም ይፈልጋል። በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ ለይሖዋ ተገቢ ፍርሃት ማዳበር ይኖርብናል።

5. አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?

5 ለአምላክ ተገቢ ፍርሃት ያለው ሰው እሱን ይወደዋል፤ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና የሚያበላሽ ምንም ነገር ማድረግ አይፈልግም። ኢየሱስ እንዲህ ያለ “አምላካዊ ፍርሃት” ነበረው። (ዕብ. 5:7) ይህ ሲባል በፍርሃት ይንቀጠቀጣል ማለት አይደለም። (ኢሳ. 11:2, 3) ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር የነበረው ከመሆኑም ሌላ እሱን መታዘዝ ይፈልግ ነበር። (ዮሐ. 14:21, 31) ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮትና አድናቆት አለን፤ ምክንያቱም እሱ አፍቃሪ፣ ጥበበኛ፣ ፍትሐዊና ኃያል ነው። በተጨማሪም ይሖዋ በጥልቅ እንደሚወደንና ለመመሪያዎቹ የምንሰጠው ምላሽ በእሱ ስሜት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ እናውቃለን። ይሖዋ ካልታዘዝነው እጅግ ያዝናል፤ ስንታዘዘው ደግሞ ልቡ ይደሰታል።—መዝ. 78:41፤ ምሳሌ 27:11

ለአምላክ ፍርሃት ማዳበር

6. ለአምላክ ፍርሃት ማዳበር የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (መዝሙር 34:11)

6 ፈሪሃ አምላክ ይዘን አልተወለድንም፤ አምላካዊ ፍርሃት ልናዳብረው የሚገባ ነገር ነው። (መዝሙር 34:11ን አንብብ።) እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ፍጥረትን መመርመር ነው። የአምላክን ጥበብ፣ ኃይሉንና ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር “ከተሠሩት ነገሮች” ስናስተውል ለእሱ ያለን አክብሮትና ፍቅር እያደገ ይሄዳል። (ሮም 1:20) አድሪያን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በፍጥረት ላይ የተንጸባረቀው የይሖዋ ጥበብ በጣም ያስገርመኛል፤ እንዲሁም እሱ የሚበጀኝን ነገር እንደሚያውቅልኝ እንድተማመን ያደርገኛል።” በዚህ ላይ ማሰላሰሏ የሚከተለው መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ረድቷታል፦ “የሕይወቴ ምንጭ በሆነው በይሖዋና በእኔ መካከል ክፍተት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነገር የምፈጽምበት ምን ምክንያት አለ?” አንተስ በዚህ ሳምንት በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ለማሰላሰል የተወሰነ ጊዜ መመደብ ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህ ለይሖዋ ያለህን አክብሮትና ፍቅር ያሳድግልሃል።—መዝ. 111:2, 3

7. ጸሎት ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ለማዳበር የሚረዳን እንዴት ነው?

7 ለአምላካችን ፍርሃት ማዳበር የምንችልበት ሌላው መንገድ አዘውትረን መጸለይ ነው። ይበልጥ በጸለይን መጠን ይሖዋ ይበልጥ እውን ይሆንልናል። አንድን ፈተና ለመቋቋም ብርታት እንዲሰጠን በጠየቅነው ቁጥር ታላቅ ኃይል እንዳለው እናስታውሳለን። ልጁን ስለሰጠን ስናመሰግነው ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን እናስታውሳለን። ይሖዋ አንድን ችግር ለመወጣት እንዲረዳን ምልጃ ስናቀርብ ደግሞ ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ እናስታውሳለን። እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አክብሮት ያሳድጉልናል። በተጨማሪም ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያበላሽ ምንም ነገር ላለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክሩልናል።

8. ለአምላክ ያለንን ፍርሃት ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና በውስጡ ካሉት ጥሩም ሆነ መጥፎ ምሳሌዎች በመማር ለአምላክ ያለንን ፍርሃት ጠብቀን መኖር እንችላለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ ሁለት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የተዉትን ምሳሌ እንመለከታለን፤ እነሱም በንጉሥ አክዓብ ቤት ላይ አዛዥ የነበረው አብድዩና ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ናቸው። ቀጥሎ ደግሞ ጥሩ ጅማሬ ቢኖረውም በኋላ ላይ ከይሖዋ የራቀው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ ካደረገው ነገር ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።

ፈሪሃ አምላክ እንደነበረው እንደ አብድዩ ደፋር ሁኑ

9. አብድዩ ለይሖዋ ያለው ፍርሃት የረዳው እንዴት ነው? (1 ነገሥት 18:3, 12)

9 መጽሐፍ ቅዱስ አብድዩን b የሚያስተዋውቀን “አብድዩ ይሖዋን በጣም ይፈራ ነበር” በሚሉት ቃላት ነው። (1 ነገሥት 18:3, 12ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ጤናማ ፍርሃት አብድዩን የረዳው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት እንዲሆን ረድቶታል፤ በዚህም የተነሳ ንጉሡ በቤቱ ላይ ሾሞታል። (ከነህምያ 7:2 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም አብድዩ ፈሪሃ አምላክ የነበረው መሆኑ አስደናቂ ድፍረት እንዲኖረው ረድቶታል፤ ይህ ባሕርይ ደግሞ በእጅጉ ያስፈልገው ነበር። አብድዩ ይኖር የነበረው በክፉው ንጉሥ በአክዓብ ዘመን ነው። አክዓብ “ከእሱ በፊት የነበሩት [ነገሥታት] ሁሉ ከፈጸሙት የከፋ ድርጊት በይሖዋ ፊት” ፈጽሟል። (1 ነገ. 16:30) ከዚህም ሌላ፣ የባአል አምላኪ የነበረችው የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል ይሖዋን በጣም ከመጥላቷ የተነሳ ከሰሜናዊው መንግሥት ንጹሑን አምልኮ ለማስወገድ የተቻላትን ሁሉ ሞክራለች። እንዲያውም በርካታ የአምላክ ነቢያትን ገድላለች። (1 ነገ. 18:4) በእርግጥም አብድዩ ይሖዋን ያመልክ የነበረው በአስቸጋሪ ጊዜ ነው።

10. አብድዩ አስደናቂ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው?

10 አብድዩ አስደናቂ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው? ኤልዛቤል የአምላክን ነቢያት አሳድዳ መግደል በጀመረችበት ጊዜ አብድዩ መቶዎቹን ነቢያት ወስዶ ‘ሃምሳ ሃምሳ በማድረግ ዋሻ ውስጥ ደበቃቸው፤ እንዲሁም ምግብና ውኃ ይሰጣቸው ነበር።’ (1 ነገ. 18:13, 14) ደፋሩ አብድዩ ተይዞ ቢሆን ኖሮ ያለጥርጥር ይገደል ነበር። መቼም አብድዩ ሰው እንደመሆኑ መጠን እንዳይገደል ፈርቶ መሆን አለበት። ሆኖም አብድዩ ይሖዋንና እሱን የሚያገለግሉትን ሰዎች ከገዛ ሕይወቱ አስበልጦ ይወዳቸው ነበር።

በሥራችን ላይ እገዳ ቢጣልም አንድ ወንድም ለእምነት አጋሮቹ በድፍረት መንፈሳዊ ምግብ ሲያከፋፍል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) c

11. በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች የአብድዩን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 በዛሬው ጊዜ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች አሉ። እነዚህ ውድ ወንድሞችና እህቶች ለመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገባቸውን ክብር ይሰጣሉ፤ ሆኖም እንደ አብድዩ ይሖዋን ማምለካቸውን ለማቆም ፈቃደኞች አይደሉም። (ማቴ. 22:21) ከሰው ይልቅ አምላክን በመታዘዝ ፈሪሃ አምላክ እንዳላቸው ያሳያሉ። (ሥራ 5:29) እንዲህ የሚያደርጉት ምሥራቹን ማወጃቸውን በመቀጠልና በዘዴ ስብሰባዎችን በማድረግ ነው። (ማቴ. 10:16, 28) ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ሥራችን ለተወሰነ ጊዜ ታግዶ በነበረበት አንድ የአፍሪካ አገር የሚኖረውን የሄንሪን ምሳሌ እንመልከት። በእገዳው ወቅት ሄንሪ ለእምነት ባልንጀሮቹ መንፈሳዊ ምግብ ለማከፋፈል ራሱን አቅርቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በተፈጥሮዬ ዓይናፋር ነኝ። ስለዚህ የሚያስፈልገኝን ድፍረት የሰጠኝ ለይሖዋ ያለኝ ጥልቅ አክብሮት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።” አንተስ እንደ ሄንሪ ደፋር መሆን የምትችል ይመስልሃል? ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ካዳበርክ እንዲህ ያለ ድፍረት ማሳየት ትችላለህ።

ፈሪሃ አምላክ እንደነበረው እንደ ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ታማኝ ሁኑ

12. ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄና ሚስቱ ለይሖዋ አስደናቂ ታማኝነት ያሳዩት እንዴት ነው?

12 ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ይሖዋን ይፈራ ነበር፤ ይህ ፍርሃቱ ደግሞ ለይሖዋ ታማኝ እንዲሆንና ንጹሕ አምልኮን እንዲያራምድ አነሳስቶታል። የኤልዛቤል ልጅ ጎቶልያ በጉልበት ሥልጣን በያዘችበት ወቅት ዮዳሄ ታማኝነቱን አሳይቷል። ሕዝቡ ጎቶልያን የሚፈሩበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። እጅግ በጣም ጨካኝና የሥልጣን ጥመኛ ከመሆኗ የተነሳ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ በሙሉ ማለትም የገዛ የልጅ ልጆቿን ለመግደል ሞክራለች! (2 ዜና 22:10, 11) ከልጅ ልጆቿ አንዱ የሆነው ኢዮዓስ፣ የዮዳሄ ሚስት የሆነችው ዮሳቤት ስለደበቀችው ተረፈ። እሷና ባለቤቷ ልጁን ደብቀው አሳደጉት። በዚህ መንገድ ዮዳሄና ዮሳቤት የዳዊት ሥርወ መንግሥት እንዳይቋረጥ አድርገዋል። ዮዳሄ ለይሖዋ ታማኝ ነበር፤ እንዲሁም ጎቶልያን በመፍራት አልተሸበረም።—ምሳሌ 29:25

13. ኢዮዓስ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ዮዳሄ በድጋሚ ታማኝነቱን ያሳየው እንዴት ነው?

13 ኢዮዓስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት በድጋሚ አሳየ። አንድ ዕቅድ አወጣ። ዕቅዱ ከተሳካ የዳዊት ሕጋዊ ወራሽ የሆነው ኢዮዓስ ንጉሥ ይሆናል። ካልተሳካለት ግን ዮዳሄ ሕይወቱን ማጣቱ አይቀርም። ይሖዋ ስለባረካቸው ዕቅዱ ተሳካ። ዮዳሄ ከአለቆቹና ከሌዋውያኑ ጋር በመተባበር ኢዮዓስን አነገሠው፤ ጎቶልያንም አስገደላት። (2 ዜና 23:1-5, 11, 12, 15፤ 24:1) “ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ ይሖዋ፣ ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ።” (2 ነገ. 11:17) “በተጨማሪም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ በር ጠባቂዎቹን በይሖዋ ቤት በሮች ላይ አቆመ።”—2 ዜና 23:19

14. ዮዳሄ ይሖዋን በማክበሩ የተከበረው እንዴት ነው?

14 ይሖዋ ቀደም ሲል “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” ብሎ ነበር። በእርግጥም ይሖዋ ዮዳሄን ክሶታል። (1 ሳሙ. 2:30) ለምሳሌ የዮዳሄ መልካም ሥራ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን በቃሉ ላይ እንዲሰፍር አድርጓል። (ሮም 15:4) በተጨማሪም ዮዳሄ በሞተበት ወቅት “ከእውነተኛው አምላክና ከአምላክ ቤት ጋር በተያያዘ በእስራኤል መልካም ነገር ስላደረገ በዳዊት ከተማ ከነገሥታት ጋር” የመቀበር ልዩ መብት አግኝቷል።—2 ዜና 24:15, 16

እንደ ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ በአምላካዊ ፍርሃት ተነሳስተን ወንድሞቻችንን በታማኝነት እንደግፍ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት) d

15. ስለ ዮዳሄ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 ስለ ዮዳሄ የሚናገረው ዘገባ ሁላችንም አምላካዊ ፍርሃት እንድናዳብር ሊረዳን ይችላል። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ምንጊዜም ንቁ ሆነው የአምላክን መንጋ በታማኝነት በመጠበቅ የዮዳሄን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ሥራ 20:28) አረጋውያን ይሖዋን እስከፈሩና ለእሱ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ዓላማውን ለመፈጸም ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ከዮዳሄ ምሳሌ መማር ይችላሉ። ይሖዋ ‘አታስፈልጉኝም’ አይላቸውም። ወጣቶች፣ ይሖዋ ዮዳሄን የያዘበትን መንገድ በመኮረጅ ታማኝ አረጋውያንን በአክብሮት ሊይዟቸው ይገባል፤ በተለይ ይሖዋን ለረጅም ጊዜ በታማኝነት ያገለገሉ አረጋውያንን ማክበራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 16:31) በመጨረሻም ዮዳሄን ከደገፉት አለቆችና ሌዋውያን ሁላችንም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ‘አመራር ለሚሰጡን’ በመታዘዝ በታማኝነት እንደግፋቸው።—ዕብ. 13:17

እንደ ንጉሥ ኢዮዓስ አትሁኑ

16. ንጉሥ ኢዮዓስ የአቋም ሰው እንዳልነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

16 የዮዳሄ መልካም ምሳሌነት ለንጉሥ ኢዮዓስ ጠቅሞታል። (2 ነገ. 12:2) በመሆኑም ወጣቱ ንጉሥ ይሖዋን ማስደሰት ይፈልግ ነበር። ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን ኢዮዓስ ከሃዲ የሆኑትን መኳንንት መስማት ጀመረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? እሱና ሕዝቡ “የማምለኪያ ግንዶችንና ጣዖቶችን ማገልገል ጀመሩ።” (2 ዜና 24:4, 17, 18) ይሖዋ በዚህ በጣም ስላዘነ “ወደ እሱ እንዲመልሷቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ . . . ሕዝቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም።” የዮዳሄን ልጅ ዘካርያስን እንኳ ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። ዘካርያስ የይሖዋ ነቢይና ካህን ብቻ ሳይሆን የኢዮዓስ የቅርብ ዘመድም ነበር። የሚያሳዝነው፣ ኢዮዓስ ያ ቤተሰብ ያደረገለትን ውለታ ከምንም ሳይቆጥር ዘካርያስን አስገደለው።—2 ዜና 22:11፤ 24:19-22

17. ኢዮዓስ ምን ደረሰበት?

17 ኢዮዓስ ለይሖዋ የነበረውን ጤናማ ፍርሃት ይዞ አልቀጠለም፤ ይህ ደግሞ በእጅጉ ጎድቶታል። ይሖዋ “የሚንቁኝ . . . ይናቃሉ” ብሎ ነበር። (1 ሳሙ. 2:30) አነስተኛ ቁጥር ያለው የሶርያ ሠራዊት “እጅግ ብዙ የሆነውን” የኢዮዓስን ሠራዊት ድል በማድረግ ኢዮዓስን ‘ክፉኛ አቆሰሉት።’ ሶርያውያኑ ከተመለሱ በኋላ ኢዮዓስ የገዛ አገልጋዮቹ የዘካርያስን ደም በማፍሰሱ ገደሉት። ይህ ክፉ ንጉሥ “በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ” የመቀበር መብት እንኳ አላገኘም።—2 ዜና 24:23-25፤ ማቴ. 23:35

18. በኤርምያስ 17:7, 8 መሠረት እንደ ኢዮዓስ እንዳንሆን ምን ይረዳናል?

18 ከኢዮዓስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢዮዓስ በእንጨት ተደግፎ እንደቆመና ሥር እንዳልሰደደ ዛፍ ነበር። እንደ እንጨት ደግፎ ያቆመው ዮዳሄ ከሞተና የክህደት ነፋስ መንፈስ ከጀመረ በኋላ ኢዮዓስ ተገንድሶ ወደቀ። ይህ ታሪክ እንደሚያሳየው ለአምላክ ያለን ፍርሃት የእምነት አጋሮቻችን ወይም ቤተሰቦቻችን በሚያሳድሩብን በጎ ተጽዕኖ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም። በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን መኖር ከፈለግን አዘውትረን በማጥናት፣ በማሰላሰልና በመጸለይ ለአምላክ ያለንን ፍቅርና ፍርሃት ልናጠናክረው ይገባል።—ኤርምያስ 17:7, 8ን አንብብ፤ ቆላ. 2:6, 7

19. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

19 ይሖዋ የሚጠብቅብን ነገር ከአቅማችን በላይ አይደለም። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር በመክብብ 12:13 ላይ ጠቅለል ተደርጎ ተቀምጧል፦ “እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው አጠቃላይ ግዴታ ነውና።” አምላክን የምንፈራ ከሆነ ወደፊት ምንም ይምጣ ምን እንደ አብድዩና እንደ ዮዳሄ ጸንተን መቆም እንችላለን። ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ምንም ነገር አያበላሽብንም።

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ፍርሃት” የሚለው ቃል በተለያየ መንገድ ተሠርቶበታል። እንደየአገባቡ ሽብርን፣ አድናቆትን ወይም አክብሮትን ሊያመለክት ይችላል። ይህ ርዕስ የሰማዩን አባታችንን በድፍረትና በታማኝነት እንድናገለግል የሚያነሳሳ ዓይነት ፍርሃት ለማዳበር ይረዳናል።

b ይሄኛው አብድዩ ከዘመናት በኋላ ከኖረውና በስሙ የተጠራ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ከጻፈው ከነቢዩ አብድዩ የተለየ ነው።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም በእገዳ ሥር ለወንድሞቹ መንፈሳዊ ምግብ ሲያከፋፍል የሚያሳይ ትወና።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት ወጣት እህት የስልክ ምሥክርነት ስለመስጠት ከአንዲት አረጋዊት እህት ስትማር፤ አንድ አረጋዊ ወንድም በድፍረት በአደባባይ ምሥክርነት ሲካፈል፤ ተሞክሮ ያለው አንድ ወንድም የስብሰባ አዳራሽ ጥገናን በተመለከተ ሥልጠና ሲሰጥ