የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ
እምነት አለህ?
ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን እምነት ሊኖረን ይገባል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “እምነት ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር አይደለም” ይላል። (2 ተሰ. 3:2) እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው እያሳደዱት ስላሉት ‘መጥፎና ክፉ ሰዎች’ ነው። ሆኖም ስለ እምነት የተናገረው ሐሳብ የሚሠራው ለእነዚህ ሰዎች ብቻ አይደለም። አንዳንዶች ሁሉንም ነገር የፈጠረ አምላክ መኖሩን የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ሆን ብለው ይክዳሉ። (ሮም 1:20) ሌሎች ደግሞ ከሰዎች የበለጠ ኃይል ያለው አካል መኖሩን እንደሚያምኑ ይናገሩ ይሆናል። ሆኖም ይህን ማመን ብቻውን ይሖዋን ለማስደሰት በቂ አይደለም።
ይሖዋ መኖሩንና ጠንካራ እምነት ላላቸው ሰዎች ወሮታ ከፋይ መሆኑን እርግጠኛ ልንሆን ይገባል። (ዕብ. 11:6) እምነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንድ ገጽታ ነው። አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ወደ ይሖዋ መጸለይ አለበት። (ሉቃስ 11:9, 10, 13) ይህን መንፈስ ለማግኘት የሚረዳን አንዱ ወሳኝ ነገር በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል ማንበብ ነው። ከዚያም ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰልና ያገኘነውን ትምህርት በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን የይሖዋ መንፈስ እሱን የሚያስደስት ዓይነት እምነት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ሕይወታችንን ለመምራት ይረዳናል።