በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 26

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው

ይሖዋን ዓለትህ አድርገው

ይሖዋን ዓለትህ አድርገው

“እንደ አምላካችን ያለ ዓለት የለም።”1 ሳሙ. 2:2

ዓላማ

ይሖዋን ከዓለት ጋር የሚያመሳስሉት ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም እነዚህን ባሕርያቱን መኮረጅ የምንችልበትን መንገድ እንማራለን።

1. በመዝሙር 18:46 ላይ ዳዊት ይሖዋን ከምን ጋር አመሳስሎታል?

 በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የሚከሰቱ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሕይወታችንን በከፍተኛ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ ሊቀይሩት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ ላይ ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነና በማንኛውም ጊዜ ሊረዳን ዝግጁ እንደሆነ ተመልክተን ነበር። የእሱን ድጋፍ በሕይወታችን ስናይ ‘ይሖዋ ሕያው እንደሆነ’ እርግጠኞች እንሆናለን። (መዝሙር 18:46ን አንብብ።) ነገር ግን ዳዊት ይህን ሐሳብ ከተናገረ በኋላ አምላክን “ዓለቴ” በማለት ጠርቶታል። ዳዊት ሕያው አምላክ የሆነውን ይሖዋን ግዑዝ ከሆነ ዓለት ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው?

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ ከዓለት ጋር የተመሳሰለው ለምን እንደሆነና ይህ ዘይቤያዊ አገላለጽ ስለ እሱ ምን እንደሚያስተምረን እንመለከታለን። እንዲሁም እሱን ዓለታችን አድርገን መመልከት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። በመጨረሻም ይሖዋን ከዓለት ጋር የሚያመሳስሉትን ባሕርያት እንዴት መኮረጅ እንደምንችል እንመለከታለን።

ይሖዋ ዓለት የተባለው ለምንድን ነው?

3. መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለት” የሚለውን ቃል በአብዛኛው የሚጠቀምበት እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)

3 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ያሉትን አንዳንድ ባሕርያት ለመግለጽ “ዓለት” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። ይህ ቃል በአብዛኛው የሚገኘው ይሖዋ አቻ የሌለው አምላክ መሆኑን በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ነው። ይሖዋ “ዓለት” ተብሎ የተጠራበት የመጀመሪያው ጥቅስ ዘዳግም 32:4 ነው። ሐና በጸሎቷ ላይ “እንደ አምላካችን ያለ ዓለት የለም” ብላለች። (1 ሳሙ. 2:2) ዕንባቆም ይሖዋን “ዓለቴ” ብሎ ጠርቶታል። (ዕን. 1:12) የመዝሙር 73 ጸሐፊ አምላክን “የልቤ ዓለት” በማለት ጠርቶታል። (መዝ. 73:26) ይሖዋም ቢሆን ራሱን ዓለት ብሎ የጠራበት ጊዜ አለ። (ኢሳ. 44:8) ከዚህ ቀጥሎ ይሖዋን ከዓለት ጋር የሚያመሳስሉትን ሦስት ባሕርያት እንመለከታለን። ከዚያም እሱን ‘የእኛ ዓለት’ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።—ዘዳ. 32:31

የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን እንደ አስተማማኝ ዓለት አድርገው ይመለከቱታል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)


4. ይሖዋ መጠጊያ የሆነው እንዴት ነው? (መዝሙር 94:22)

4 ይሖዋ መጠጊያ ነው። ግዙፍ የሆነ ዓለት አንድን ሰው ከአውሎ ነፋስ ሊከልለው እንደሚችል ሁሉ ይሖዋም አደገኛ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይጠብቀናል። (መዝሙር 94:22ን አንብብ።) ደህንነታችን የተጠበቀ እንዲሆንና ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስብን ይከላከልልናል። ወደፊት ደግሞ ከዚህም የበለጠ ነገር እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል፤ ሰላማችንንም ሆነ ደህንነታችንን አደጋ ላይ የሚጥልን ማንኛውንም ነገር ያስወግዳል።—ሕዝ. 34:25, 26

5. ይሖዋ እንደ ዓለት መጠጊያችን የሚሆነው እንዴት ነው?

5 ይሖዋን እንደ ዓለት መጠጊያችን ልናደርገው የምንችልበት አንዱ መንገድ ወደ እሱ መጸለይ ነው። ስንጸልይ ይሖዋ ልባችንንና አእምሯችንን የሚጠብቅልንን “የአምላክ ሰላም” ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በእምነቱ ምክንያት ታስሮ የነበረውን የአርተምን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንድ ጨካኝ የወንጀል መርማሪ በተደጋጋሚ ጫና ሊያደርግበትና ሊያዋርደው ይሞክር ነበር። አርተም እንዲህ ብሏል፦ “መርማሪው ለምርመራ በጠራኝ ቁጥር እጨነቅ ነበር። . . . ሁሌም ለይሖዋ እጸልይ ነበር። ውስጤ እንዲረጋጋና ጥበብ እንዲሰጠኝ እጠይቀዋለሁ። . . . መርማሪው የተጠቀመባቸው መንገዶች ሁሉ እኔ ላይ አልሠሩለትም። . . . ይሖዋ ስለረዳኝ በግንብ አጥር የተከለልኩ ያህል ነበር።”

6. ሁልጊዜም በይሖዋ መታመን የምንችለው ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 26:3, 4)

6 ይሖዋ እምነት የሚጣልበት አምላክ ነው። ይሖዋ ልክ እንደማይነቃነቅ ዓለት ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ነው። “የዘላለም ዓለት” ስለሆነ ልንተማመንበት እንችላለን። (ኢሳይያስ 26:3, 4ን አንብብ።) እሱ ለዘላለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር የገባልንን ቃል ለመፈጸም፣ ጸሎታችንን ለመስማትና የሚያስፈልገንን ድጋፍ ለማድረግ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ስለሆነ እምነት ልንጥልበት እንችላለን። (2 ሳሙ. 22:26) ያከናወንነውን ሥራ ፈጽሞ አይረሳም፤ ምንጊዜም ወሮታችንን ይከፍለናል።—ዕብ. 6:10፤ 11:6

7. በይሖዋ መታመናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ዓለታችን እናደርገዋለን። በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ እሱን መታዘዝ ጥቅም እንደሚያስገኝልን እንተማመናለን። (ኢሳ. 48:17, 18) የእሱን ድጋፍ በሕይወታችን ባየን ቁጥር በእሱ ላይ ያለን እምነት ያድጋል። ከይሖዋ እርዳታ ውጭ ልንቋቋማቸው የማንችላቸውን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ይበልጥ ዝግጁ እንሆናለን። ማንም ሊደርስልን በማይችልባቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ይሖዋ እምነት የሚጣልበት አምላክ እንደሆነ ለመረዳት አጋጣሚ እናገኛለን። ቭላዲሚር እንዲህ ብሏል፦ “በማረፊያ ቤት ያሳለፍኩት ጊዜ ከአምላክ ጋር ያለኝ ዝምድና በጣም የተጠናከረበት ወቅት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ብቻዬን ስለነበርኩ እንዲሁም ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥሬ ውጭ ስለነበር በይሖዋ ይበልጥ መታመንን ተማርኩ።”

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመታመን እሱን ዓለታችን እናደርገዋለን (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


8. (ሀ) ይሖዋ የማይለወጥ አምላክ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክን ዓለታችን ማድረጋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (መዝሙር 62:6, 7)

8 ይሖዋ አይቀየርም። ልክ እንደ ግዙፍ ዓለት ይሖዋ የማይለወጥ አምላክ ነው። ይሖዋ ባሕርዩም ሆነ ዓላማው አይቀየርም። (ሚል. 3:6) በኤደን ዓመፅ በተነሳበት ጊዜ ይሖዋ ዓላማውን አልቀየረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ይሖዋ “ራሱን ሊክድ አይችልም።” (2 ጢሞ. 2:13) ይህም ማለት ምንም ነገር ቢፈጠር ወይም ሌሎች ምንም ነገር ቢያደርጉ ይሖዋ አምላክ ባሕርያቱን፣ ዓላማውን ወይም መሥፈርቶቹን አይቀይርም ማለት ነው። በማይለወጠው አምላካችን በመተማመን እንዲያድነንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን።—መዝሙር 62:6, 7ን አንብብ።

9. ከታትያና ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

9 በይሖዋ ባሕርያትና በዓላማዎቹ ላይ በማሰላሰል እሱን ዓለታችን ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን መከራን በምንጋፈጥበት ጊዜ ስሜታችን እንዲረጋጋ ይረዳናል። (መዝ. 16:8) በእምነቷ ምክንያት በቁም እስር ላይ የነበረችው የታትያና ተሞክሮ ይህን ያሳያል። ታትያና እንዲህ ብላለች፦ “ሙሉ በሙሉ ብቻዬን ነበርኩ። . . . መጀመሪያ ላይ ከባድ ነበር። ብዙ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይሰማኝ ነበር።” ነገር ግን የደረሰባት ፈተና ከይሖዋና ከዓላማው ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ማሰቧ ስሜቷ እንዲረጋጋና ፈተናውን በጽናት እንድትቋቋም ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ሁኔታ የደረሰብኝ ለምን እንደሆነ ሳስብ እዚህ ሁኔታ ውስጥ የገባሁት ለይሖዋ ባለኝ ፍቅር የተነሳ እንደሆነ አስታወስኩ። ይህም ስለ ራሴ ማሰቤን እንዳቆም ረድቶኛል።”

10. በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ዓለታችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 በቅርቡ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ መታመን የሚጠይቁ ፈተናዎችን መጋፈጣችን አይቀርም። ይሖዋ በታማኝነት ለመጽናት የሚያስፈልገንን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግልን ያለንን እምነት ለማጠናከር ጊዜው አሁን ነው። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንና በዘመናችን ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን ተሞክሮዎች በማንበብ ነው። አምላክ አገልጋዮቹን ለመደገፍ እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። በእነዚህ ታሪኮች ላይ በጥልቀት አሰላስል። ይህም ይሖዋን ዓለትህ ለማድረግ ይረዳሃል።

የይሖዋን እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያት ኮርጅ

11. የይሖዋን እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያት መኮረጅ የምንፈልገው ለምንድን ነው? (“ ወጣት ወንድሞች ሊያወጡት የሚችሉት ግብ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

11 ይሖዋ እንደ ዓለት የሆነው እንዴት እንደሆነ እስካሁን ተመልክተናል። አሁን ደግሞ እሱን ከዓለት ጋር የሚያመሳስሉትን ባሕርያት እንዴት መኮረጅ እንደምንችል እንመለከታለን። እንዲህ ባደረግን መጠን ጉባኤውን ለማነጽ ይበልጥ ብቁ እንሆናለን። ለምሳሌ ኢየሱስ ለስምዖን “ኬፋ” (ወይም “ጴጥሮስ”) የሚል ስም ሰጥቶታል፤ ይህ ስም “ትንሽ ዓለት” የሚል ትርጉም አለው። (ዮሐ. 1:42) ይህም ጴጥሮስ ለጉባኤው የመጽናኛና የብርታት ምንጭ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች “እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ” ተደርገው ተገልጸዋል። ይህም በጉባኤው ውስጥ ላሉት ከለላ እንደሚሆኑ የሚያሳይ ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው። (ኢሳ. 32:2) እርግጥ ነው፣ ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በመምሰል እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያትን ማንጸባረቅ ይችላሉ፤ ይህም ጉባኤውን ይጠቅማል።—ኤፌ. 5:1

12. ለሌሎች መጠጊያ መሆን የምንችልባቸውን መንገዶች ጥቀስ።

12 መጠጊያ ሁን። አንዳንድ ጊዜ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሕዝባዊ ዓመፅ ወይም ጦርነት ሲከሰት ለወንድሞቻችን ቃል በቃል መጠጊያ ልንሆን እንችላለን። በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ አንዳችን ሌላውን ለመርዳት የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎችን እንደምናገኝ ጥርጥር የለውም። (2 ጢሞ. 3:1) ከዚህም በተጨማሪ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ስሜታዊና መንፈሳዊ ከለላ ልንሆንላቸው እንችላለን። እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ወደ ስብሰባ ሲመጡ እነሱን ማነጋገርና ማጽናናት ነው። በዚህ መንገድ ጉባኤው ፍቅርና ሞቅ ያለ መንፈስ የሰፈነበት እንዲሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። የምንኖረው ፍቅር በጠፋበትና ውጥረት በነገሠበት ዓለም ውስጥ ነው። ስለዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስብሰባዎች ላይ ሲገኙ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው፣ መንፈሳቸው እንዲታደስና እንዲረጋጉ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን።

13. ሽማግሌዎች ለሌሎች መጠጊያ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 የጉባኤ ሽማግሌዎች ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ ማዕበል ላጋጠማቸው ወንድሞችና እህቶች መጠጊያ ሊሆኑ ይችላሉ። የተፈጥሮ አደጋና ድንገተኛ ሕመም በሚያጋጥምበት ጊዜ ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሆነው ተግባራዊ እርዳታ ይሰጣሉ። መንፈሳዊ እርዳታም ያበረክታሉ። አንድ ሽማግሌ ደግ፣ የሌሎችን ስሜት የሚረዳና ለመስማት ፈቃደኛ በመሆኑ የሚታወቅ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች እሱን ቀርበው ማነጋገር ቀላል ይሆንላቸዋል። አንድ ሽማግሌ እንዲህ ያሉ ባሕርያትን የሚያንጸባርቅ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች እንደሚያስብላቸው ስለሚሰማቸው እሱ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ቀላል ይሆንላቸዋል።—1 ተሰ. 2:7, 8, 11

ወንድሞችና እህቶች ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ ማዕበል ሲያጋጥማቸው ሽማግሌዎች መጠጊያ ይሆኑላቸዋል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት) a


14. እምነት የሚጣልብን ሰዎች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 እምነት የሚጣልብህ ሁን። ሌሎች በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜ እምነት እንዲጥሉብን እንፈልጋለን። (ምሳሌ 17:17) ‘እምነት የሚጣልበት ሰው ነው’ የሚል ስም ማትረፍ የምንችለው እንዴት ነው? ሁልጊዜ አምላካዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ጥረት በማድረግ ነው፤ ለምሳሌ ቃላችንን ለመጠበቅና ሰዓት አክባሪ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ልናደርግ ይገባል። (ማቴ. 5:37) በተጨማሪም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተግባራዊ እርዳታ ማበርከት እንችላለን። ከዚህም ሌላ፣ ኃላፊነቶቻችንን በተሰጠን መመሪያ መሠረት ማከናወን ይኖርብናል።

15. ሽማግሌዎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸው ጉባኤውን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

15 እምነት የሚጣልባቸው ሽማግሌዎች ለጉባኤው በረከት ናቸው። እንዴት? አስፋፊዎች የጉባኤ ሽማግሌዎችን፣ ለምሳሌ የቡድን የበላይ ተመልካቻቸውን በማንኛውም ጊዜ ማግኘት እንደሚችሉ ሲያውቁ ይረጋጋሉ። እንዲሁም የጉባኤ ሽማግሌዎች ሊረዷቸው ፈቃደኛ እንደሆኑ ሲገነዘቡ እንደሚወደዱ ይሰማቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክር በራሳቸው አመለካከት ላይ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስና ታማኙ ባሪያ በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ከሆነ የእምነት አጋሮቻቸው እምነት ይጥሉባቸዋል። አንድ ሽማግሌ የአስፋፊዎችን ሚስጥር የሚጠብቅና ቃሉን የሚያከብር ከሆነ ወንድሞችና እህቶች በእሱ ላይ ያላቸው እምነት ይጨምራል።

16. የማይለዋወጥ አቋም ያለን መሆኑ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

16 የማይለዋወጥ አቋም ይኑርህ። ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆራጥ ከሆንንና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን የምናደርግ ከሆነ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ እናሳድራለን። በእምነትና በትክክለኛ እውቀት እያደግን ስንሄድ በእውነት ውስጥ ሥር እንሰዳለን። ወላዋይ፣ ጽኑ አቋም የሌለን ወይም በሐሰት ትምህርቶችና በዓለም አስተሳሰብ እየተገፋን በቀላሉ ወዲያና ወዲህ የምንዋልል ሰዎች አይደለንም። (ኤፌ. 4:14፤ ያዕ. 1:6-8) አስደንጋጭ ሁኔታ ሲያጋጥመን በይሖዋና እሱ በገባው ቃል ላይ ያለን እምነት ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። (መዝ. 112:7, 8) መከራ ያጋጠማቸውን ሰዎች መርዳትም እንችላለን።—1 ተሰ. 3:2, 3

17. ሽማግሌዎች ሌሎች ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ሽማግሌዎች በልማዶቻቸው ልከኛ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ሥርዓታማና ምክንያታዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ወንዶች ሌሎች ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው ይረዳሉ፤ እንዲሁም ‘የታመነውን ቃል በጥብቅ በመከተል’ ጉባኤውን ያጠናክራሉ። (ቲቶ 1:9፤ 1 ጢሞ. 3:1-3) ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ በመሆንና እረኝነት በማድረግ አስፋፊዎች አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ፣ በአገልግሎት እንዲካፈሉ እንዲሁም የግል ጥናት እንዲያደርጉ ይረዳሉ። ሽማግሌዎች፣ ወንድሞችና እህቶች አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በይሖዋና በዓላማዎቹ ላይ እንዲያተኩሩ በማበረታታት ሊረዷቸው ይችላሉ።

18. ይሖዋን ማወደስና ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ የምንፈልገው ለምንድን ነው? (“ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚረዳ መንገድ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

18 ስለ ይሖዋ ግሩም ባሕርያት ስናስብ ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት “ዓለቴ የሆነው ይሖዋ ይወደስ” ለማለት እንነሳሳለን። (መዝ. 144:1) በይሖዋ ላይ እምነት ከጣልን እሱ መቼም ቢሆን አያሳፍረንም። ይሖዋ ምንጊዜም በመንፈሳዊ እንድናብብ እንደሚረዳን በመተማመን በዕድሜያችን ሁሉ፣ በእርጅናችን ዘመንም ጭምር “እሱ ዓለቴ ነው” ማለት እንችላለን።—መዝ. 92:14, 15

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

a የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሁለት ሽማግሌዎችን በነፃነት ቀርባ ስታነጋግር።