በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 25

መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን

ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ

ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ

“ይሖዋ ሕያው ነው!”መዝ. 18:46

ዓላማ

የምናመልከው አምላክ ሕያው አምላክ መሆኑን ማስታወሳችን በእጅጉ ይጠቅመናል።

1. የይሖዋ ሕዝቦች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው እሱን ማምለካቸውን ለመቀጠል የሚረዳቸው ምንድን ነው?

 “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን”—መጽሐፍ ቅዱስ የምንኖርበትን ዘመን የሚገልጸው በዚህ መንገድ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) በዚህ ሥርዓት ውስጥ በሁሉም ሰው ላይ ከሚደርሱት ችግሮች በተጨማሪ የይሖዋ ሕዝቦች ተቃውሞንና ስደትን መቋቋም ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ችግሮች እያሉም ይሖዋን ማምለካችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል? ከሚረዱን ወሳኝ ነገሮች አንዱ፣ ይሖዋ “ሕያው አምላክ” መሆኑን ማስታወስ ነው።—ኤር. 10:10፤ 2 ጢሞ. 1:12

2. ይሖዋ ሕያው አምላክ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

2 ይሖዋ ፈተና ሲያጋጥመን የሚያበረታንና እኛን ለመደገፍ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን የሚፈልግ እውን የሆነ አምላክ ነው። (2 ዜና 16:9፤ መዝ. 23:4) እሱ ሕያው አምላክ መሆኑን ማስታወሳችን የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በተሳካ ሁኔታ ለመጋፈጥ ይረዳናል። ከንጉሥ ዳዊት ጋር በተያያዘ ይህ እውነት መሆኑ የታየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

3. ዳዊት “ይሖዋ ሕያው ነው” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

3 ዳዊት ይሖዋን ያውቀውና ይታመንበት ነበር። ንጉሥ ሳኦልን ጨምሮ ጠላቶቹ ሲያሳድዱት ዳዊት ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮአል። (መዝ. 18:6) አምላክ ጸሎቱን በመስማት ከታደገው በኋላ ዳዊት “ይሖዋ ሕያው ነው!” በማለት ስሜቱን ገልጿል። (መዝ. 18:46) ዳዊት ይህን ሲል አምላክ መኖሩን መናገሩ ብቻ አልነበረም። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ዳዊት ይህን ሲል ይሖዋ “ሕዝቦቹን ለመርዳት ሁልጊዜ እርምጃ የሚወስድ ሕያው አምላክ መሆኑን” በእርግጠኝነት እንደሚያምን መናገሩ ነው። አዎ፣ ዳዊት አምላኩ ሕያው መሆኑን በገዛ ሕይወቱ አይቷል፤ ይህ እምነቱ ደግሞ ይሖዋን ለማገልገልና ለማወደስ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል።—መዝ. 18:28, 29, 49

4. ይሖዋ ሕያው አምላክ መሆኑን ማመናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

4 ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነ ማመናችን እሱን በቅንዓት ለማገልገል ይረዳናል። ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና አምላክን በትጋት ማገልገላችንን ለመቀጠል የሚያስችል ተነሳሽነት ይኖረናል። ከዚህም ሌላ፣ ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።

ሕያው የሆነው አምላክ ያበረታሃል

5. ፈተናዎችን በልበ ሙሉነት ለመጋፈጥ የሚረዳን ምንድን ነው? (ፊልጵስዩስ 4:13)

5 ይሖዋ ሕያው እንደሆነና እኛን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆነ ካስታወስን ትንሽም ይሁን ትልቅ ማንኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንችላለን። ምክንያቱም የሚያጋጥመን ችግር ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ከአምላካችን አቅም በላይ አይደለም። እሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።) ስለዚህ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንችላለን። ትናንሽ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የይሖዋን እርዳታ ማየታችን ትላልቅ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንደሚረዳን እንድንተማመን ያደርገናል።

6. ዳዊት ልጅ ሳለ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ለማጠናከር የሚረዳ ምን ሁኔታ አጋጥሞታል?

6 ዳዊት በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ለማጠናከር የረዱትን ሁለት አጋጣሚዎች እስቲ እንመልከት። በልጅነቱ እረኛ ሳለ አንድ ድብና አንድ አንበሳ መጥተው የአባቱን በጎች ነጥቀው ወስደው ነበር። በሁለቱም ጊዜያት ዳዊት አውሬውን በማሳደድ በጎቹን ማስጣል ችሏል። ያም ቢሆን ይህን ማድረግ የቻለው በራሱ ኃይል እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንደረዳው ተገንዝቧል። (1 ሳሙ. 17:34-37) ዳዊት እነዚህን አጋጣሚዎች ፈጽሞ አልረሳቸውም። በእነዚህ አጋጣሚዎች ላይ ማሰላሰሉ ሕያው የሆነው አምላክ ወደፊትም እንደሚያበረታው እንዲተማመን ረድቶታል።

7. ዳዊት ትክክለኛውን እይታ መያዙ ጎልያድን እንዲገጥም የረዳው እንዴት ነው?

7 ከጊዜ በኋላ ዳዊት ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ወደ እስራኤላውያን የጦር ሰፈር ሄደ። በዚያም ጎልያድ የተባለ ግዙፍ ፍልስጤማዊ ‘ለውጊያ በተሰለፈው የእስራኤል ሠራዊት ላይ በመሳለቁ’ የተነሳ ወታደሮቹ በፍርሃት እንደተሸበሩ አየ። (1 ሳሙ. 17:10, 11) ወታደሮቹ የተሸበሩት በሰውየው ግዝፈትና በተናገረው ግድድር ላይ በማተኮራቸው ነው። (1 ሳሙ. 17:24, 25) ዳዊት ግን ሁኔታውን የተመለከተው ከሌላ አቅጣጫ ነው። ሁኔታውን በእስራኤል ሠራዊት ላይ እንደተሰነዘረ ግድድር ብቻ ሳይሆን “ሕያው በሆነው አምላክ ሠራዊት ላይ” እንደተሰነዘረ ግድድር አድርጎ ቆጥሮታል። (1 ሳሙ. 17:26) ዳዊት በይሖዋ ላይ አተኩሯል። ዳዊት እረኛ ሳለ የረዳው አምላክ በዚህ ሁኔታ ውስጥም እንደሚረዳው ተማምኖ ነበር። አምላክ እንደሚረዳው በመተማመን ጎልያድን ገጠመው፤ ደግሞም አሸነፈው።—1 ሳሙ. 17:45-51

8. ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ እንደሚረዳን ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 እኛም ሕያው የሆነው አምላክ ሊረዳን ዝግጁ እንደሆነ ካስታወስን ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን። (መዝ. 118:6) ይሖዋ ቀደም ሲል ያደረጋቸውን ነገሮች መመርመራችን በዚህ እውነታ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ይሖዋ አገልጋዮቹን እንዴት እንዳዳናቸው የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን አንብብ። (ኢሳ. 37:17, 33-37) በተጨማሪም ይሖዋ በዘመናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶችን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ jw.org ላይ የወጡ ዘገባዎችን ተመልከት። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለአንተ ሲል እርምጃ የወሰደባቸውን ጊዜያት አስታውስ። እርግጥ ድብና አንበሳ እንደማሸነፍ ያለ አስደናቂ ተሞክሮ ማስታወስ አትችል ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ብዙ ነገሮችን እንዳደረገልህ የተረጋገጠ ነው። አንተን ወደ ራሱ በመሳብ ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት አድርጎሃል። (ዮሐ. 6:44) አሁንም ቢሆን እውነት ውስጥ መኖር የቻልከው እሱ ስለረዳህ ነው። ከዚህ በፊት ጸሎትህን የመለሰልህ፣ በትክክለኛው ጊዜ የሚያስፈልግህን እርዳታ የሰጠህ ወይም አንድን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳህ እንዴት እንደሆነ ለማስታወስ እንዲረዳህ ለምን አትጠይቀውም? እንዲህ ባሉ ተሞክሮዎች ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ አንተን መርዳቱን እንደሚቀጥል ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል።

ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች በስተ ጀርባ አንድ ወሳኝ ጉዳይ አለ (አንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)


9. ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ምሳሌ 27:11)

9 ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነ ማስታወሳችን ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። እንዴት? ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች በስተ ጀርባ በይሖዋና በሰይጣን መካከል የተነሳ ትልቅ ጉዳይ እንዳለ እናስታውሳለን። ዲያብሎስ ችግር ሲያጋጥመን ይሖዋን እንደምንተው ተናግሯል። (ኢዮብ 1:10, 11፤ ምሳሌ 27:11ን አንብብ።) ሆኖም ያጋጠሙንን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ ስንቋቋም ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እናሳያለን፤ ዲያብሎስ ውሸታም እንደሆነም እናረጋግጣለን። የባለሥልጣናት ተቃውሞ፣ የኢኮኖሚ ችግር ወይም በአገልግሎት ላይ የምታገኛቸው ሰዎች የሚሰጡት አሉታዊ ምላሽ ከባድ ፈተና ሆኖብሃል? ወይም ሌላ ዓይነት ፈተና እየተጋፈጥክ ነው? ከሆነ፣ ያጋጠመህ ሁኔታ የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት የሚያስችል አጋጣሚ እንደሚሰጥህ አስታውስ። በተጨማሪም እሱ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብህ እንደማይፈቅድ አትርሳ። (1 ቆሮ. 10:13) ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጥሃል።

ሕያው የሆነው አምላክ ወሮታህን ይከፍልሃል

10. ሕያው የሆነው አምላክ ለሚያመልኩት ሰዎች ምን ያደርጋል?

10 ይሖዋ ለሚያመልኩት ሰዎች ምንጊዜም ወሮታ የሚከፍል አምላክ ነው። (ዕብ. 11:6) በአሁኑ ጊዜ ሰላምና እርካታ፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል። ይሖዋ ለእኛ ወሮታ ለመክፈል ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው በመተማመን ተስፋችንን በእሱ ላይ መጣል እንችላለን። ይህን ማመናችን በጥንት ዘመን እንደነበሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አገልግሎታችንን በትጋት ለማከናወን ያነሳሳናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ጢሞቴዎስ ይህን አድርጓል።—ዕብ. 6:10-12

11. ጢሞቴዎስ በጉባኤው ውስጥ ጠንክሮ እንዲሠራ ያነሳሳው ምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 4:10)

11 አንደኛ ጢሞቴዎስ 4:10ን አንብብ። ጢሞቴዎስ ሕያው በሆነው አምላክ ላይ ተስፋውን ጥሏል። ይህም ይሖዋንና ሌሎችን ለማገልገል ጠንክሮ እንዲሠራና ብርቱ ጥረት እንዲያደርግ አነሳስቶታል። ይህን ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የማስተማርና ንግግር የማቅረብ ችሎታውን እንዲያሳድግ አበረታቶታል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ወጣቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ለእምነት አጋሮቹ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅበት ነበር። አንዳንድ ከባድ ኃላፊነቶችም ተሰጥተውታል፤ ለምሳሌ ምክር ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጠንካራ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር መስጠት ነበረበት። (1 ጢሞ. 4:11-16፤ 2 ጢሞ. 4:1-5) ጢሞቴዎስ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚያከናውነውን ሥራ ላያስተውሉት ወይም ላያደንቁት ቢችሉም እንኳ ይሖዋ ወሮታውን እንደሚከፍለው እርግጠኛ መሆን ይችል ነበር።—ሮም 2:6, 7

12. ሽማግሌዎች ሥራቸውን በትጋት እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ይሖዋ የሚያከናውኑትን ሥራ እንደሚያስተውልና እንደሚያደንቅ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። እረኝነት ከማድረግ፣ ከማስተማርና ከመስበክ በተጨማሪ በርካታ ሽማግሌዎች በግንባታ ፕሮጀክቶችና በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ ይካፈላሉ። ሌሎች ደግሞ በሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ወይም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ ያገለግላሉ። እንዲህ ላሉት ሥራዎች ራሳቸውን የሚያቀርቡ ሽማግሌዎች ጉባኤው የሰው ሳይሆን የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ ይገነዘባሉ። በዚህም የተነሳ ሥራቸውን በሙሉ ልባቸው ያከናውናሉ፤ አምላክ ላከናወኑት ሥራ ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸውም ሙሉ በሙሉ ይተማመናሉ።—ቆላ. 3:23, 24

ጉባኤውን ለማገልገል ተግተህ ስትሠራ ሕያው የሆነው አምላክ ወሮታህን ይከፍልሃል (አንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)


13. ይሖዋ እሱን ለማገልገል በግለሰብ ደረጃ የምናደርገውን ጥረት ሲመለከት ምን ይሰማዋል?

13 እርግጥ ሽማግሌ ሆኖ ማገልገል የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም። ሆኖም ሁላችንም ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር አለን። አምላካችን እሱን ለማገልገል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይደሰታል። መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ለዓለም አቀፉ ሥራ የምናደርገውን መዋጮ ይመለከታል። ዓይናፋርነታችንን ለማሸነፍ ታግለን በስብሰባ ላይ ሐሳብ ለመስጠት እጃችንን ስናወጣ ይደሰታል፤ የደረሰብንን በደል ትተን ስናልፍና ይቅር ስንልም ልቡ ሐሴት ያደርጋል። የምትፈልገውን ያህል ማድረግ እንደማትችል ቢሰማህም እንኳ ይሖዋ የምታከናውነውን ሥራ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኛ ሁን። እሱን ለማገልገል ጥረት በማድረግህ ይወድሃል፤ ወሮታህንም ይከፍልሃል።—ሉቃስ 21:1-4

ሕያው ከሆነው አምላክ ጋር ተቀራርበህ ኑር

14. ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን መኖራችን ለእሱ ያለንን ታማኝነት ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ይሖዋ እውን ከሆነልን ለእሱ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ቀላል ይሆንልናል። ከዮሴፍ ጋር በተያያዘ ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። ዮሴፍ የሥነ ምግባር ብልግና ላለመፈጸም ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። አምላክ ለእሱ እውን ነበር፤ እሱን ማሳዘንም አልፈለገም። (ዘፍ. 39:9) ይሖዋ እውን እንዲሆንልን ከፈለግን ጊዜ መድበን ወደ እሱ መጸለይና ቃሉን ማጥናት ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል። እንደ ዮሴፍ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ካለን እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም።—ያዕ. 4:8

ሕያው ወደሆነው አምላክ መቅረብህ ታማኝነትህን ለመጠበቅ ይረዳሃል (አንቀጽ 14-15⁠ን ተመልከት)


15. እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ካጋጠማቸው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ዕብራውያን 3:12)

15 ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነ የሚረሱ ሰዎች በቀላሉ ከእሱ ሊርቁ ይችላሉ። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። ይሖዋ መኖሩን ያውቁ ነበር፤ ሆኖም እሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላላቸው መሆኑን መጠራጠር ጀመሩ። እንዲያውም “ለመሆኑ ይሖዋ በመካከላችን አለ ወይስ የለም?” ብለው ጠይቀዋል። (ዘፀ. 17:2, 7) ከዚያ በኋላ በአምላክ ላይ ዓመፁ። የእነሱ ታሪክ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል፤ እነሱ የተከሉትን የዓመፀኝነት ጎዳና መከተል እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው።—ዕብራውያን 3:12ን አንብብ።

16. እምነታችንን ምን ሊፈትነው ይችላል?

16 የምንኖርበት ዓለም ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ መኖር ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋል። ብዙዎች አምላክ መኖሩን አያምኑም። የአምላክን መሥፈርቶች የማያከብሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ የተሳካላቸው ይመስል ይሆናል። እንዲህ ያለውን ሁኔታ ስናይ እምነታችን ሊፈተን ይችላል። አምላክ መኖሩን ባንክድም እንኳ እኛን የሚረዳን መሆኑን መጠራጠር ልንጀምር እንችላለን። የመዝሙር 73 ጸሐፊ እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ አድሮበት ነበር። በዙሪያው ያሉት ሰዎች የአምላክን ሕጎች ባያከብሩም እንኳ አስደሳች ሕይወት ሲመሩ ተመልክቷል። በዚህም የተነሳ አምላክን ማገልገል የሚክስ መሆኑን መጠራጠር ጀመረ።—መዝ. 73:11-13

17. ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ምን ይረዳናል?

17 መዝሙራዊው አመለካከቱን እንዲያስተካክል የረዳው ምንድን ነው? ይሖዋን የሚረሱ ሰዎች ስለሚደርስባቸው መዘዝ አሰላሰለ። (መዝ. 73:18, 19, 27) አምላክን ማገልገል ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞችም ማሰብ ጀመረ። (መዝ. 73:24) እኛም ይሖዋ ስለሰጠን በረከቶች ማሰላሰል እንችላለን። በተጨማሪም ይሖዋን ባናገለግል ኖሮ ሕይወታችን ምን ይመስል እንደነበር ማሰብ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ እንዲሁም እንደ መዝሙራዊው “እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል” የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል።—መዝ. 73:28

18. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጋፈጥ የምንችለው ለምንድን ነው?

18 “ሕያው የሆነውንና እውነተኛውን አምላክ” ስለምናገለግል በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና መጋፈጥ እንችላለን። (1 ተሰ. 1:9) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ሲል እርምጃ የሚወስድ እውን የሆነ አምላክ ነው። በጥንት ዘመን ከአገልጋዮቹ ጋር እንደነበር አስመሥክሯል፤ በአሁኑ ጊዜም ከእኛ ጋር ነው። በቅርቡ፣ በምድር ላይ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ መከራ ይጠብቀናል። ሆኖም ታላቁን መከራ የምንጋፈጠው ብቻችንን አይደለም። (ኢሳ. 41:10) እንግዲያው ሁላችንም “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንበል።—ዕብ. 13:5, 6

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን