በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶኛል

ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶኛል

የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ምሽት ቀና ብዬ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ስመለከት ትዝ ይለኛል። በዚህ ጊዜ ተንበርክኬ ለመጸለይ ተነሳሳሁ። በወቅቱ ስለ ይሖዋ ገና መማሬ ነበር፤ ሆኖም ልቤን አፍስሼ ወደ እሱ ጸለይኩ። “ጸሎት ሰሚ” ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትኩት የዕድሜ ልክ ወዳጅነት የጀመረው በዚህ መንገድ ነው። (መዝ. 65:2) ገና በቅርቡ ወዳወቅኩት አምላክ የጸለይኩት ለምን እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

ሕይወታችንን የቀየረ ክንውን

የተወለድኩት ታኅሣሥ 22, 1929 ኖቪል በምትባል ዘጠኝ የእርሻ መሬቶችን የያዘች አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው፤ ኖቪል የምትገኘው የቤልጅየሙ አርደን ክፍል በሆነችው የባስቶኝ ከተማ አቅራቢያ ነው። በእርሻችን ውስጥ ከወላጆቼ ጋር ያሳለፍኩት የልጅነት ሕይወቴ ደስ የሚል ትውስታ ጥሎብኝ አልፏል። እኔና ታናሽ ወንድሜ ሬመንድ በየቀኑ ላሞቻችንን እናልብ እንዲሁም ሰብል በመሰብሰቡ ሥራ እናግዝ ነበር። በመንደራችን ውስጥ ጠንካራ የትብብር መንፈስ ነበር፤ ሁሉም ሰው እርስ በርሱ ይረዳዳል።

ከቤተሰቦቼ ጋር በእርሻችን ውስጥ ስንሠራ

ወላጆቼ ኤሚል እና አሊስ አጥባቂ ካቶሊኮች ነበሩ። በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። ሆኖም በ1939 ገደማ በእንግሊዝ የሚኖሩ አቅኚዎች ወደ መንደራችን መጥተው አባቴ መጽናኛ የተባለውን መጽሔት (አሁን ንቁ! ይባላል) ኮንትራት እንዲገባ አበረታቱት። አባቴ እውነትን እንዳገኘ ወዲያውኑ ስለተገነዘበ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረ። አባቴ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ሲያቆም ወዳጆቹ የነበሩት ጎረቤቶቻችን አምርረው ይቃወሙት ጀመር። በካቶሊክነቱ እንዲቀጥል ጫና ያሳድሩበት ነበር። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የከረረ ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተዋል።

አባቴ ይህ ሁሉ ጫና ሲደርስበት ማየት በጣም ያሳዝነኝ ነበር። ይህም በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ወደ አምላክ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የእሱን እርዳታ እንድጠይቅ አነሳሳኝ። የጎረቤቶቻችን ተቃውሞ እየቀነሰ ሲመጣ ልቤ በደስታ ተሞላ። ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ።

በጦርነቱ ወቅት የነበረን ሕይወት

ናዚ ጀርመን ግንቦት 10, 1940 ቤልጅየምን ወረረ። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች አገሪቱን ለቀው ለመሰደድ ተገደዱ። የእኛ ቤተሰብም ወደ ደቡባዊ ፈረንሳይ ተሰደደ። መንገድ ላይ ሳለን በጀርመን ሠራዊትና በፈረንሳይ ሠራዊት መካከል በሚካሄዱ ብዙ አሰቃቂ ውጊያዎች መሃል አልፈናል።

ወደ እርሻችን ስንመለስ አብዛኞቹ ንብረቶቻችን ተዘርፈው ነበር። እዚያ የቀረው ውሻችን ቦቢ ብቻ ነበር። እነዚህን ሁኔታዎች ማየቴ ‘ጦርነትና መከራ የኖረው ለምንድን ነው?’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና ተጠናከረ

በዚያ ጊዜ አካባቢ ኤሚል ሽራንትዝ a የተባለ ታማኝ አቅኚ ሽማግሌ እየመጣ ይጠይቀን ነበር፤ ይህም በጣም ጠቅሞናል። በምድር ላይ መከራ የኖረው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በግልጽ አብራራልን። ስለ ሕይወት ያሉኝን ሌሎች ጥያቄዎችም መለሰልኝ። ከይሖዋ ጋር የነበረኝ ወዳጅነት ተጠናከረ፤ እንዲሁም እሱ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ።

ጦርነቱ ከማብቃቱ በፊትም ቤተሰባችን ከወንድሞች ጋር አዘውትሮ ይገናኝ ነበር። ነሐሴ 1943 ወንድም ጆዜ-ኒኮላ ሚኔ ወደ ቤታችን መጥቶ ንግግር አቀረበ። ከዚያም “መጠመቅ የሚፈልግ ሰው አለ?” ብሎ ጠየቀ። በዚህ ጊዜ አባቴ እጁን አወጣ፤ እኔም እጄን አወጣሁ። ሁለታችንም በእርሻችን አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ትንሽ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅን።

ታኅሣሥ 1944 የጀርመን ሠራዊት በምዕራቡ ግንባር ለመጨረሻ ጊዜ ከባድ ጥቃት ሰነዘረ፤ ይህም የበልጅ ውጊያ ተብሎ ይጠራል። የምንኖረው ውጊያው በሚካሄበት ቦታ አቅራቢያ ስለነበር ለአንድ ወር ያህል በምድር ቤታችን ውስጥ ለመቆየት ተገደናል። አንድ ቀን ከብቶቻችንን ለመመገብ ስወጣ እርሻችን በፈንጂ ስለተደበደበ የበረቱ ጣሪያ ተበታተነ። በአቅራቢያዬ ባለ ጋጣ ውስጥ የነበረ አንድ የአሜሪካ ወታደር “መሬት ላይ ተኛ” ብሎ ጮኸ። እኔም ሮጬ ሄጄ ከእሱ አጠገብ መሬት ላይ ተኛሁ። እሱም ጉዳት እንዳይደርስብኝ የራስ ቁሩን ጭንቅላቴ ላይ አደረገልኝ።

መንፈሳዊ እድገት አደረግኩ

በሠርጋችን ቀን

ከጦርነቱ በኋላ እኛ ከምንኖርበት አካባቢ በስተ ሰሜን 90 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ከሚገኘው ከሊየዥ ጉባኤ ጋር አዘውትረን እንገናኝ ነበር። ውሎ አድሮ በባስቶኝ አነስተኛ የጥናት ቡድን ማቋቋም ቻልን። በወቅቱ ከግብር ጋር የተያያዘ ሥራ እሠራ ነበር፤ ሕግ የማጥናት አጋጣሚም አገኘሁ። ከጊዜ በኋላ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። በ1951 በባስቶኝ አነስተኛ የወረዳ ስብሰባ አካሄድን። በስብሰባው ላይ ወደ መቶ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተዋል። ከእነሱ መካከል ኤሊ ሮይተር የተባለች አንዲት ቀናተኛ አቅኚ ትገኝበታለች። ኤሊ በስብሰባው ላይ ለመገኘት በብስክሌት 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዛለች። ብዙም ሳይቆይ እኔና ኤሊ ተዋደድን፤ በኋላም ተጫጨን። በወቅቱ ኤሊ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድትካፈል ተጋብዛ ነበር። እሷም ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ደብዳቤ በመጻፍ ግብዣውን የማትቀበልበትን ምክንያት ተናገረች። በወቅቱ የይሖዋ ሕዝቦችን ሥራ ይመራ የነበረው ወንድም ኖር ‘አንድ ቀን ከባለቤትሽ ጋር በጊልያድ ትምህርት ቤት ትካፈሉ ይሆናል’ የሚል ደግነት የሚንጸባረቅበት መልስ ጻፈላት። የካቲት 1953 ተጋባን።

ኤሊ እና ልጃችን ሰርዥ

በዚያው ዓመት እኔና ኤሊ በኒው ዮርክ በሚገኘው ያንኪ ስታዲየም በተካሄደው “የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ” የተባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። እዚያ እያለን አንድ ወንድም ጥሩ ሥራ እንደሚሰጠኝ በመግለጽ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተዛውረን እንድንኖር ጋበዘን። ስለ ጉዳዩ ከጸለይን በኋላ እኔና ኤሊ ግብዣውን ከመቀበል ይልቅ ወደ ቤልጅየም ተመልሰን በባስቶኝ የሚገኘውን አሥር አስፋፊዎች ያሉትን ትንሽ ቡድናችንን ለመደገፍ ወሰንን። በቀጣዩ ዓመት ልጃችን ሰርዥ ሲወለድ በጣም ተደሰትን። የሚያሳዝነው ከሰባት ወር በኋላ ሰርዥ ታሞ ሞተ። የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለይሖዋ ነገርነው፤ አስተማማኝ የሆነው የትንሣኤ ተስፋም አበረታቶናል።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት

ጥቅምት 1961 በአቅኚነት ለማገልገል የሚያስችል ነፃነት የሚሰጥ ሥራ አገኘሁ። ይሁንና በዚያው ቀን በቤልጅየም የሚገኘው የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ ስልክ ደወለልኝ። እሱም የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኔን ጠየቀኝ። እኔም “ይህን ምድብ ከመቀበላችን በፊት አቅኚ ሆነን ማገልገል እንችል ይሆን?” ብዬ ጠየቅኩት። ጥያቄዬ ተቀባይነት አገኘ። ለስምንት ወር በአቅኚነት ካገለገልን በኋላ መስከረም 1962 የወረዳ ሥራ ጀመርን።

ለሁለት ዓመት ያህል በወረዳ ሥራ ከተካፈልን በኋላ በብራስልስ በሚገኘው ቤቴል እንድናገለግል ተጋበዝን። ጥቅምት 1964 እዚያ ማገልገል ጀመርን። ይህ አዲስ ምድብ ብዙ በረከት አስገኝቶልናል። ወንድም ኖር በ1965 ቤቴላችንን ከጎበኘ ብዙም ሳይቆይ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ፤ በዚህ ጊዜ በጣም ተገረምኩ። ከጊዜ በኋላ እኔና ኤሊ በጊልያድ ትምህርት ቤት 41ኛ ክፍል እንድንማር ተጋበዝን። ወንድም ኖር ከ13 ዓመት በፊት የተናገረው ሐሳብ ተፈጸመ! ከተመረቅን በኋላ ወደ ቤልጅየም ቤቴል ተመለስን።

ሕጋዊ መብታችንን ማስከበር

ባለፉት ዓመታት የሕግ እውቀቴን ተጠቅሜ በአውሮፓና በሌሎች አካባቢዎች ለአምልኮ መብታችን ጥብቅና የመቆም መብት አግኝቻለሁ። (ፊልጵ. 1:7) ይህ ኃላፊነት በሥራችን ላይ ገደብ ወይም እገዳ በተጣለባቸው ከ55 የሚበልጡ አገሮች ውስጥ ካሉ ባለሥልጣናት ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ፈጥሮልኛል። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስገናኝ ሕግ የተማርኩ ሰው መሆኔን ከመግለጽ ይልቅ ራሴን የማስተዋውቀው “የአምላክ ሰው ነኝ” ብዬ ነው። “የንጉሥ [ወይም የዳኛ] ልብ በይሖዋ እጅ እንዳለ ጅረት ነው። እሱ ደስ ወዳሰኘው አቅጣጫ ሁሉ ይመራዋል” የሚለው ሐሳብ እውነት መሆኑን ስለምገነዘብ ምንጊዜም በጸሎት የይሖዋን አመራር እጠይቃለሁ።—ምሳሌ 21:1

የአውሮፓ ፓርላማ አባል ከሆነ አንድ ባለሥልጣን ጋር በተገናኘሁበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ መቼም ቢሆን አልረሳውም። እሱን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ጥያቄ ካቀረብኩ በኋላ ሊያገኘኝ ፈቃደኛ ሆነ። እሱም “የምሰጥህ አምስት ደቂቃ ብቻ ነው፤ አንድ ደቂቃ እንኳ አልጨምርልህም” አለኝ። እኔም አጎንብሼ መጸለይ ጀመርኩ። ባለሥልጣኑ ግራ በመጋባት ምን እያደረግኩ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም ቀና ብዬ “አንተ አገልጋዩ በመሆንህ አምላክን እያመሰገንኩ ነው” አልኩት። እሱም “ምን ማለትህ ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ሮም 13:4⁠ን አሳየሁት። ባለሥልጣኑ ፕሮቴስታንት ስለነበር ጥቅሱ ትኩረቱን ሳበው። ውጤቱስ ምን ሆነ? ለግማሽ ሰዓት ያህል እንዳነጋግረው ፈቀደልኝ። በጣም ፍሬያማ የሆነ ውይይት አደረግን። እንዲያውም ለሥራችን ያለውን አክብሮት ገልጿል።

ባለፉት ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች አውሮፓ ውስጥ ከክርስቲያናዊ ገለልተኝነት፣ ልጅ ከማሳደግ መብት፣ ከግብር እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ብዙ ሕጋዊ ሙግቶችን አድርገዋል። ከእነዚህ መካከል በብዙዎቹ ውስጥ የመካፈል እንዲሁም ይሖዋ ስኬታማ ሲያደርገንና ድል ሲያጎናጽፈን የማየት መብት አግኝቻለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውስጥ ከ140 የሚበልጡ ክሶችን ረትተዋል!

በኩባ ተጨማሪ ነፃነት አገኘን

በ1990ዎቹ በሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባት በኩባ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የሃይማኖት ነፃነት እንዲያገኙ ለመርዳት በዋናው መሥሪያ ቤት ከሚያገለግለው ከወንድም ፊሊፕ ብረምሊ እና በጣሊያን ከሚኖረው ከወንድም ቫልተር ፋርኔቲ ጋር አብረን እንሠራ ነበር። በቤልጅየም ወደሚገኘው የኩባ ኤምባሲ ደብዳቤ ከጻፍኩ በኋላ ጥያቄያችንን እንዲያስተናግድ ከተመደበው ባለሥልጣን ጋር ተገናኘሁ። መጀመሪያ አካባቢ ከባለሥልጣኑ ጋር ያደረግናቸው ውይይቶች መንግሥት በሥራችን ላይ ገደብ እንዲጥል ያነሳሱትን የተሳሳቱ አመለካከቶች በመፍታት ረገድ እምብዛም ውጤት አላስገኙም ነበር።

ከፊሊፕ ብረምሊ እና ከቫልተር ፋርኔቲ ጋር በ1990ዎቹ ወደ ኩባ ከሄድንባቸው ጊዜያት በአንዱ

በጸሎት የይሖዋን አመራር ከጠየቅን በኋላ ወደ ኩባ 5,000 መጽሐፍ ቅዱሶችን ለመላክ ፈቃድ ጠየቅን፤ ጥያቄያችንም ተቀባይነት አገኘ። መጽሐፍ ቅዱሶቹ በሰላም ኩባ ደርሰው ለወንድሞች ተሰራጩ። በመሆኑም ይሖዋ ጥረታችንን እየባረከልን ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስን። ቀጥሎም 27,500 ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሶችን ለመላክ ፈቃድ ጠየቅን። አሁንም ጥያቄያችን ተቀባይነት አገኘ። በኩባ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ የግል ቅጂ እንዲያገኙ መርዳት መቻሌ በጣም አስደስቶኛል።

ሥራችን ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ለመርዳት ወደ ኩባ በተደጋጋሚ ተመላልሻለሁ። በዚህም የተነሳ ከበርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ችያለሁ።

በሩዋንዳ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን መርዳት

በ1994 ሩዋንዳ ውስጥ ባሉ ቱትሲዎች ላይ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከ1,000,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጨፍጭፈዋል። የሚያሳዝነው አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ተገድለዋል። ብዙም ሳይቆይ፣ የተወሰኑ ወንድሞች በሩዋንዳ ላሉ ክርስቲያኖች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቁ።

ቡድናችን ወደ መዲናዋ ወደ ኪጋሊ ሲደርስ እዚያ ያለው የትርጉም ቢሮና የጽሑፍ ማከማቻ በጥይት ተበሳስቶ ነበር። በገጀራ ስለተገደሉ ወንድሞችና እህቶች የሚገልጹ በርካታ አሳዛኝ ታሪኮችን ሰማን። ሆኖም ወንድሞችና እህቶች ስላሳዩት ክርስቲያናዊ ፍቅር የሚገልጹ በርካታ ተሞክሮዎችም ሰምተናል። ለምሳሌ በአንድ የሁቱ ቤተሰብ ግቢ ውስጥ ባለ ጉድጓድ ውስጥ ለ28 ቀናት ተደብቆ የቆየ አንድ ቱትሲ ወንድም አግኝተናል። በኪጋሊ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ከ900 ለሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ ማበረታቻ ሰጥተናል።

በስተ ግራ፦ በትርጉም ቢሯችን ውስጥ በጥይት የተመታ መጽሐፍ

በስተ ቀኝ፦ እርዳታ በማድረሱ ሥራ ስካፈል

ቀጥሎም ድንበር ተሻግረን ወደ ዛየር (አሁን ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ይባላል) ሄድን። ወደዚያ የሄድነው በጎማ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኙ የስደተኛ ካምፖች የሸሹ በርካታ የሩዋንዳ ወንድሞችና እህቶችን ማግኘት ስለፈለግን ነው። ሆኖም ልናገኛቸው አልቻልንም። ስለዚህ ወደ እነሱ እንዲመራን ይሖዋን በጸሎት ጠየቅነው። ከዚያም አንድ ሰው ወደ እኛ አቅጣጫ ሲመጣ አየን። እኛም የይሖዋ ምሥክሮችን ያውቅ እንደሆነ ጠየቅነው። እሱም “አዎ፣ እኔም የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ሲል መለሰልን። ከዚያም “ወደ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ልወስዳችሁ እችላለሁ” አለን። ከእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ጋር የሚያንጽ ስብሰባ ካደረግን በኋላ 1,600 ገደማ ከሚሆኑ ስደተኞች ጋር ተሰብስበን መንፈሳዊ ማበረታቻና ማጽናኛ ሰጠናቸው። ከበላይ አካሉ የተላከውን ደብዳቤም አነበብንላቸው። ወንድሞችና እህቶች የሚከተለውን ማበረታቻ ሲሰሙ ልባቸው በጥልቅ ተነካ፦ “ሁልጊዜ እንጸልይላችኋለን። ይሖዋ እንደማይተዋችሁ እርግጠኞች ነን።” የበላይ አካሉ የጻፈው ይህ ሐሳብ እውነት መሆኑ ታይቷል። በዛሬው ጊዜ ሩዋንዳ ውስጥ ከ30,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋን በደስታ እያገለገሉ ይገኛሉ።

ታማኝነቴን ለመጠበቅ ቆርጫለሁ

ለ58 ዓመታት ያህል በትዳር ከቆየን በኋላ በ2011 ውዷን ባለቤቴን ኤሊን በሞት አጣሁ። የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት፤ እሱም አጽናንቶኛል። ለሌሎች የመንግሥቱን ምሥራች ማካፈሌም እንድጽናና ረድቶኛል።

አሁን የምገኘው በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ቢሆንም በየሳምንቱ በክርስቲያናዊ አገልግሎት እካፈላለሁ። እዚህ በቤልጅየም ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኘውን የሕግ ክፍል መደገፍ፣ ተሞክሮዬን ለሌሎች ማካፈል እንዲሁም በቤቴል ቤተሰብ ውስጥ ላሉ ወጣቶች እረኝነት ማድረግ መቻሌም ያስደስተኛል።

በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሖዋ የጸለይኩት ከ84 ዓመታት ገደማ በፊት ነው። ከዚያ ዕለት አንስቶ ከይሖዋ ጋር በመጓዝ አስደሳች ሕይወት አሳልፌያለሁ፤ ወደ እሱም ይበልጥ ቀርቤያለሁ። ይሖዋ በሕይወት ዘመኔ በሙሉ ጸሎቴን ስለሰማኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።—መዝ. 66:19 b

a የወንድም ሽራንትዝ የሕይወት ታሪክ በመስከረም 15, 1973 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 570-574 ላይ ወጥቷል።

b ይህ ርዕስ በመዘጋጀት ላይ ሳለ የካቲት 4, 2023 ወንድም ማርሴል ጂሌት በሞት አንቀላፍቷል።